ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኑሮ ውድነት የዜጎችን ሕይወት ክፉኛ አመሰቃቅሎታል አሉ

0
938

ባለፈው ረቡዕ፣ ነሐሴ 1/2011 “የኢትዮጵያን የፖለቲካ አጀንዳ አድማስ ማስፋት” በሚል መሪ ቃል የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ባዘጋጀው መድረክ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር፣ የኑሮ ውድነት ጫና ልጓም ያጣ ነው ሲል አስታውቋል።

ላለፉት ዐሥርተ ዓመታት ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሲመራ ነበረው የአገራችን የኢኮኖሚ ስርዓት በአንድ በኩል በዓለም ተወዳዳሪ ቢሊየነሮችን ሲፈጥር፣ በሌላ በኩል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የድሃ ድሃዎችን ፈጥሯል ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የአገራችን ክፍሎች፣ ከሁሉም ብሔር እና ሃይማኖት ባሕር ማዶ ይሰደዳሉ፣ ይሞታሉ ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ሆኖም ችግራቸው አገራዊ አጀንዳ ሆኖ ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችል ሥራ ሲሠራ እምብዛም አይታይም ብለዋል። በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት የሚኖሩና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ዋና ችግራቸው ሥራ አጥነት ሲሆን፣ ወጣቶቹን ላልተፈለገ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ከመዳረግ ባሻገር የህልውና ጉዳይ ለመሆን መብቃቱንም ተናግረዋል።

በዕለቱ “በኢትዮጵያ ትኩረት የተነፈጋቸው አርብቶ አደሮች” በሚል ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ኮንቴ ሙሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በጠረፋማ እና ቆላማው የአገራችን ክፍል የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ካሉበት እጅግ አስከፊ የኑሮ ውጣ ውረድ የሚታደጋቸው የፖሊሲ አማራጮችን በአፋጣኝ የሚሹ ቢሆንም፣ ጉዳዮቸው በአገራችን ፖለቲከኞች ለአፍታም ሲወሳ አይሰማም ብለዋል። በኮንቴ ሐሳብ የሚስማሙት አብዱል ቃድር በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 60 ከመቶ የሚሆነው የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ የሚኖሩባቸው አካባቢዎች መሆኑን ልብ ይሏል ሲሉ አስታውቀዋል። የአካባቢ ጥበቃ፣ የደን መመናመን፣ በረሃማነትና የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፋዊ አጀንዳዎች በአገራችን ፖለቲካ ብዙም ትኩረት ሲያገኙ አይስተዋልም ሲሉም ያክላሉ።

ኮንቴ የአርብቶ አደር ፖሊሲ የሌላት ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ናት ይላሉ። የከተሞች መስፋፋት ለአርብቶ አደሩ ሥጋት ሆኗል ያሉት ኮንቴ፣ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ለመሥራት የተወሰደው ቦታ ለአርብቶ አደሩ የመኖር ዋስትና የነበሩ ቦታዎች ቢሆኑም፣ ሕዝቡን ይቀይራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና አርብቶ አደሩ ሲጠብቀው የነበረው በቢሊዮኖች ገንዘብ የወጣበት ፋብሪካ ውጤታማ ባለመሆኑ አርብቶ አደሩን ጎድቶታል ሲሉ ተናግረዋል።

አብዱልቃድር በተለያየ ደረጃ ብሔር ተኮር ፖለቲካ ከሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ኀይሎች በተቃራኒ የቆሙ እና “የኅብረ ብሔር” ወይም “የዜግነት” ፖለቲካን እናራምዳለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሙሉ አቅማቸውን የብሔር ፖለቲካን በመቃወም፣ አለፍ ሲልም የብሔር ፖለቲካን አምርረው በማውገዝና እውቅና በመንፈግ በሌላ ጽንፍ ላይ ቆመው “የኅብረ ብሔር” ፖለቲካን እንደሚያራምዱ አውስተዋል። የብሔር እና ኅብረ ብሔር ፖለቲካ አንዱ ለሌላው በሥጋትነት እየቀረበ እና ኹለቱም የፖለቲካ ጎራዎች ራሳቸውን ለማጠናከር የሌላውን ችግር በማብራራት፣ የአገራችን ፖለቲካ ከብሔር ጉዳይ ፈቅ እንዳይል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አድርገዋል ሲሉም በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ሒደት ገልጸዋል።

የማንነት ፖለቲካ ለአንዳንዶቻችን ለኢትዮጵያችን ሰላም፣ እኩልነት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሆኖ ሲቀርብ፣ ሌሎቻችን በማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አደረጃጀት የውድቀት፣ የግጭትና የመበተን አደጋ ምንጭ ሆኖ ይታያል ሲል ፓርቲው አስታውቋል። ኹለቱን የፖለቲካ አስተሳሰቦች ሊያስታርቅ የሚችል ሦስተኛ ወይም መካከለኛ መስመር በብዙዎች ሲቀነቀን አይስተዋልም። የብሔር እና የማንነት ጥያቄ ባለፉት 60 ዓመታት የአገራችን ፖለቲካ ምሰሶና ማገር፣ ጣራና ግድግዳ ሆኖ የቆየ ሲሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የብሔር ጥያቄ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ሆነዋል ብሏል።

የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢ የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግሥቴ በበኩላቸው፣ ዜጋ ተኮር ፖለቲካችን እየተገፋ፣ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም በሰፊው መቀንቀኑን አውስተው፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የዚህ አካል በመሆን ችግሩን ሲያባብሱት ይስተዋላል ብለዋል። በተቃዋሚዎች መካከል ያለው መተፋፈን ፖለቲካው እንዳያድግ ማነቆ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መላኩ ተገኝ (ዶ/ር)፣ ይህቺን አገር እያመሱ ያሉ የተወሰኑ ፖለቲካዊ አመለካከቶች መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ሁሉም ነገር የተማሪ ንቅናቄ እንደሆነ አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎች መሳሳታቸውን ያስታወቁት መላኩ፣ የብሔር ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ መነሳት የጀመረው ከተማሪዎች ንቅናቄ ቀደም ብሎ ጣሊያን ከወጣ ከኹለት ዓመት በኋላ መሆኑን ይናገራሉ። አክለውም የብሔር ጥያቄ የተማሪው ሳይሆን በተማሪው የሚያላክኩት ልኂቃን መሆኑን ያስረዳሉ።

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ድኅነትን ማስቀረት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እና በአገር ደኅንነት ዙሪያ ጥናት አድርጎ ያቀረበ አላየሁም ይላሉ መላኩ። በእነዚህ ጉዳዮችም ላይ መድረኮች ተዘጋጅተው ማየት የተለመደ አለመሆኑንም በማስረዳት። ከዚህ ይልቅ የምሁራን መግነን በፓርቲዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይገልጻሉ።
እንደ መላኩ ገለጻ፣ ፓርቲዎች አመራሮቻቸውን የሚቆጣጠሩበት ሕግ የላቸውም። አመራሮቹም ዲሞክራት አይደሉም። ለአገር ሰላም፣ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና ደኅንነት ከመሥራት ይልቅ የራሳቸው ሥልጣንና ጥቅም ጎልቶ ይታያቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው ጥቅም ውጪ የሚታያቸው ባለመሆናቸው ለአገርም ለሕዝብም የሚጠቅሙ አይደሉም።

ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ መንግሥታት ሕገ መንግሥትን እንደ ቅዱስ ቃል የማይሻርና የማይለወጥ አድርጎ የማየት ነገር አለ የሚሉት መላኩ፣ በአንዳንድ የሰለጠኑ አገራት በሃያ ዓመት ውስጥ ከዐሥር ጊዜ በላይ ሕገ መንግሥት መሻሻሉን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ሕዝብ ሳያምንባቸው በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ማናቸውም ጉዳዮች መሻሻል እንዳለባቸውም መላኩ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here