እነሆ አዲስ ማለዳ!

0
625

የዓለማችን የመጀመሪያዎቹ ጋዜጦች መታተም የጀመሩት በ17ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በጀርመን አገር ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ የህትመት የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ የተደማጭነት ማማ ላይ ይገኛል፡፡ ዘርፉ የሰው ልጅ አዕምሮን ለመቅረፅ መረጃ ከማቀበል፣ ግንዛቤ ከመፍጠርና ማዝናናት ባሻገር ዜጎች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሯዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፤ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ምሶሶ የሆነው የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚያበረክተው አስተዋፅዖውም ወደር የለውም፡፡
ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሠረት ነው፡፡ የሕትመት ብዙኃን መገናኛዎች ደግሞ ይህንን ዕሴት ዕውን ለማድረግ እና ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ አማራጭ መድረክ ናቸው፡፡ በመረጃ ያልበለፀገ ማኅበረሰብ መንግስትን ተጠያቂ የማድረግ አቅሙ ውስን ነው፡፡ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ሊዳብር የሚችለውም የሐሳብ ሙግትና ምክንያታዊነት እየጎለበተና ባህል እየሆነ ሲመጣ ነው፡፡ እነዚህን ዐቢይ ተልዕኮዎች ለማሳካት ከግለሰብ፣ ቡድንና መንግሥት ተፅዕኖ የተላቀቁና በስርዓት የተደራጁ የብዙኋን መገናኛ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ከአንድ ክፍለ ዘመን ጥቂት ዓመታት የዘለለ ዕድሜ ቢኖረውም የሙያው ዕድገትም ሆነ ያሳረፈው በጎ ተፅዕኖ የሚያኮራ አይደለም። በተለያዩ አጋጣሚዎች ብልጭ እያለ ብዙም ሳይቆይ ድርግም የሚለው የመገናኛ ብዟኃን ህልውና የፖለቲካችን አንድ አካል ሆኗል። በ1960ዎቹ የፈነዳው ሕዝባዊ አብዮት፣ በ1980ዎቹ መጀመሪያና አጋማሽ የመጣው መንግሥታዊ ለውጥ እናምርጫ 1997 ለመገናኛ ብዙኃን መነቃቃት የፈነጠቁት ተስፋ የፖለቲካችን ሐዲድ መሳትን ተከትሎ ተስተጓጉሏል፡፡
ባለፉት ሰባት ወራት ኢትዮጵያ የምትገኝበት የፖለቲካ ሒደት ከዚህ ቀደም ከተገኙ መልካም አጋጣሚዎች ውስጥ ይመደባል። አዲስ ማለዳም ይህ መልካም አጋጣሚን በመጠቀም ኢትዮጵያችን ያገኘችው የለውጥ ተስፋ እንዳይቀለበስ የበኩሏን አዎንታዊ አስተዋፅዖ ለማድረግ ትሰራለች፡፡ ይህች የሁላችን የሆነች ጋዜጣ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም የመሆን ዓላማዋን ሰንቃ እነሆ የበኩር እትሟን ዛሬ ይዛላችሁ ቀርባለች፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። አንዳንዶች እንዲያውም ዘርፉ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ከጀርባ አጥንትነት ሚና ጋር ያመሳስሉታል።
አዲስ ማለዳ ዜጎች ማወቅ የሚገባቸውን ወቅታዊ መረጃዎች ታደርሳለች፤ ትምህርት አዘል ሥልጡን የውይይት መድረክ በመፍጠር የሠለጠነ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ተዋስዖ እንዲዳብር ትሠራለች። በተጨማሪም የምርመራ ጋዜጠኝነትን በመተግበር የአገር ሐብት እንዳይባክን፣ የተደራጀ ወንጀል እንዳይስፋፋና በሥልጣን መባለግና ያለአግባብ መጠቀምን በማጋለጥ ዲሞክራሲያዊነት እንዲያብብ፣ የመብት ጠያቂነት እንዲጎለብት ብሎም ኃላፊነትና ተጠያቂነት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በመንግሥት ደረጃ እንዲዳብር የበኩሏን ሚና ለመወጣት ትሰራለች፡፡
የአዲስ ማለዳ አሳታሚ ‹ቻምፒዮን ኮሚዩኒኬሽንስ› በሕትመት ብዙኃን መገናኛው ዘርፍ በንግድና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› ወርሐዊ የአንግሊዝኛ መጽሔትን በማሳተም የሰባት ዓመት ልምድ አለው። አዲስ ማለዳም ከዚሁ ልምድ ተቋዳሽ በመሆኗ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን በፅናት አንባቢዎቿን ለማገልገል ተዘጋጅታለች፡፡
ጋዜጣችን ለመገናኛ ብዙኃን እድገት መልካም አበርክቶ እንዲኖራት በማሰብ፣ የጋዜጠኝነትን ሙያ እና አንባቢዎችን በማክበር እንድትዘጋጅ፣ እንዲሁም ዘላቂ፣ አሳታፊ እና ተዳራሽ ተክለ-ቁመና እንዲኖራት የሚያስችሏትን እሴቶች አንግባለች፡፡
የአዲስ ማለዳ እሴቶች

  • ሙያተኝነት
  • ሐቀኝነት
  • ምክንያታዊነት
  • ዴሞክራሲያዊነት
  • ብዝኃነት
  • ሥልጡንነት
  • ጨዋነት
  • አሳታፊነት

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ገለልተኛና ነፃ መድረክ ነች፡፡ ታማኝነታችን እና ወገንተኝነታችን ለሙያችን፣ ለእሴቶቻችን እና ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎቻችን ነው። እሴቶቻችንን ለሚያከብሩ የየትኛውም የፖለቲካም ይሁን ሌላ አመለካከት የሚያራምዱ ወገኖች ሐሳባቸውን የማንሸራሸሪያ መድረክነቷ ያለአድሎ ክፍት ይሆናል፡፡
አምደኞቻችን በድፍረት ሳይሆን በኑሮ አጋጣሚ፣ በትምህርት፣ እና በሥራ ጉዳይ በጥልቀት ስለሚያውቁት ጉዳይ የሚጽፉ እንዲሆኑ የማያቋርጥ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ› እንዲሉ አንድም ምሁራን እና ባለሙያዎች ባደባባይ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ እናበረታታለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንባቢዎች በሒደቱ የተረጋገጠ መረጃ እንዲያገኙ እናግዛለን። ይህም ዴሞክራሲ የሚሻውን የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ይረዳል፡፡
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ለዴሞክራሲያዊነት የቆመች እንደመሆኗ፣ ዴሞከራሲን ለማበረታታት ከሲቪክ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች ጋር ተያያዣነት ያላቸውን ሥራዎች በልዩ ትኩረት ትዘግባለች፣ መድረክ ትሰጣለች፣ ተሳትፎም ታደርጋለች፡፡ ይህንን ልዩ ትኩረት ለማድረግ የወሰንበት ምክንያት ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት በሌሉበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ መጠበቅ የዋህነት ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም ዲሞክራሲን ሊያጎለብትና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ስር እንዲሰድ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶችን በቋሚነት ትተገብራለች፡፡
ውድ አንባቢዎቻችን፣
ይህ ሕዝባዊ ዓላማችን ግቡን እንዲመታ ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ አንብቡን፤ አስተያየታችሁን ላኩልን ፤ የንግድ ድርጅቶችም ምርትና አግልግሎታችሁን በጋዜጣችን አስተዋውቁ፡፡
በመጨረሻም አዲስ ማለዳ እዚህ እንድትደርስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ የለፋችሁ ምክትል መራሔ አሰናጁ በፍቃዱ ኃይሉ፤ ዋና አዘጋጁ ታምራት አስታጥቄ እና መላው የዝግጅት ክፍሉ ባልደረቦችን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ አሳታሚው ላወጣው የአምደኝነት ጥሪ በጎ መላሻችሁን የሰጣችሁ ምሁራኖቻችንም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተሳትፎ እንጂ በምኞት አይገነባም!

አማንይሁን ረዳ
መራሔ አሰናጅ/Executive Editor

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here