የቋንቋ ጉዳይ በ“ጠርዝ ላይ”

0
594

ከጥቂት ወራት በፊት “ጠርዝ ላይ” በሚል ርዕስ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) በቋንቋ እና ጋዜጠኝነት ዙሪያ ያሳተሙትን መጽሐፍ ማንበብ ይገባል የሚሉት መላኩ አዳል፣ በተለይ በመጽሐፉ ውስጥ ቋንቋ በተመለከተ የተነሱ ነጥቦች ላይ በማጠንጠን መጽሐፉ ሊመልሳቸው ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል።

መንደርደሪያ – ስለቋንቋ
ቋንቋ የባሕል አካል ከሆኑት እሴቶች፣ ትዕምርቶች፣ ወግና ልምድ እና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተጨማሪ አንዱና በሰዎች ዘንድ የተደረጉ ድርጊቶችን ለመመዝገብና ወደሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚጠቅም አንዱ መሣሪያ ነው። በመቀጠልም ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ በመሆን ማገልገል ጀመረ። በሒደትም፣ ሰዎች ሐሳባቸውን የሚወክልላቸው ምልክት ወይም ፊደል፤ ብሎም ጽሑፍን ፈጠሩ። ይህም የቋንቋንና የሐሳብን ግንኙነት ፈጠረ። ለምሳሌ የቆንጆ ሴት ምስልና ሴት የሚለው ቃል በተፈጥሯቸው ባይገናኙም፤ የቋንቋና የአንጎል ግንኙነት ግን ሴት የሚለውን ቃልና እውኑን የሴትን ምስል ግንኙነት እንዲኖር አድርጓል።

ከዚህ ተያያዥ ስለሆነው የቋንቋ አጠቃቀምና ትምህርት ስርዓት፤ እንዲሁም ቋንቋ አጠቃቀምና የቋንቋ ፖሊሲ ትንሽ ማለት ወሳኝ ነጥብ ነው። ትምህርት፣ እውቀት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበትና ማኅበራዊ ትችቶችም የሚዳብሩበት መንገድ ነው። የትምህርት ዓላማ እውቀትን፣ ክህሎትንና አመለካከትን በማስተካከልና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ዜጎች ለአገርና ለራሳቸው ጠቃሚዎች ማድረግ ነው። መደበኛ ትምህርት የአንድን አገር ወጣት ትውልድ ባሕል በሚፈለገው መንገድ መቅረጽና በምክንያት የሚኖር ኅብረተስብ ለመፍጠር የሚዘየድ ስርዓት ነው። እናም የትምህርት ስርዓት የአገርን ጠቅላላ የወደፊት አቅጣጫ መሰረት ያደረገ፣ ወጥና አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመቅረጽ በሚያስችል መልክ መቀረጽ ይኖርበታል። ይህን ለማሳካት ደግሞ መሰረታዊ የሆነ ሌላ ጉዳይ አለ። እሱም የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ ነው። ይህ ጉዳይ ወጥ የትምህርት ስርዓት እንዲኖረን ብቻ አይደለም የሚጠቅመን፤ የቃላት መዋስንና አጠቃቀምን ስርዓት በማስያዝ ጭምር እንጂ። ይህም የትምህርት ሒደትን፣ የመግባባት አቅምን በማሳለጥ እውቀትን ይጨምራል፣ የአገርን አንድነትንና ዕድገትን ያፋጥናል።

የቋንቋን አጠቃቀምና አመራር በተመለከተ ያለው የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ለራሳችን እንዲመች አድርጎ መጠቀምም ጥሩ አማራጭ ነው። ከላይ እንደተባለው፣ ለመማር ምስለት በጣም ወሳኝ ነው። የምንማረውን ነገር በአዕምሯችን መሳል ካልቻልን መማር አዳጋች ይሆናል። ለዚህም ነው የመርጃ መሣሪያዎች አስፈላጊ የሆኑት።

ቪዲዮዎች፣ የፕላዝምና ፖውር ፖይንት መርጃዎች፣ የቤተ ሙከራና የወርክሾፕ የክህሎት ሥልጠናዎች የሚያስፈልጉትም ለዚህ ነው። እናም የምንጠቀምባቻው ቃላት ቢቻል በእውን፣ ካልተቻለ የምናብ ምስል ሊወክሉ ይገባል። ይህ ማለት ደግሞ የምንጠቀምባቸው ቃላት (ከውጭም ይምጡ ወይም ነባር) በሕግ የሚመሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከተው ተቋም ማቋቋምና በብቁ የሰው ኀይል ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህም ቋንቋዎች የታለመላቸውን ዓላማ እንዲመቱ፣ የኅብረተሰብ ዕድገት ምንጭ እንጂ መሰናክል እንዳይሆኑ ያደርጋል።

በጠቅላላው ቋንቋ ከሰዎች ለሰዎች እውቅት ማግኛ፣ ማስተላለፊያና ሰንዶ ማስቀመጫ አንዱ መሣሪያ ነው። የጋራ እሴትን መሰረት ያደረገና ወጥ የሆነ ትምህርት መስጠት የማትችል አገር የነገ ኅልውናዋ አደጋ ውስጥ ነው። የኢትዮጵያም ችግር ይኸው ነው። ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በራስ ቋንቋ መማር ጥሩ ሆኖ እያለ፣ የጋራ የሚያደርግ የጋራ ቋንቋ በተለይም አማርኛ በትምህርት ቤቶች፤ ልጆች በደንብ እንዲማሩ አለመበረታታቱ ለአገር አንድነትና ዕድገት እንቅፋት እየሆነ ነው። ስለዚህም ማንም ቋንቋ የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ ከመወሰኑ በፊት የትምህርት ስርዓታችን በምን ቋንቋና ለምን በዚያ ቋንቋ መሰጠት እንዳለበት፣ የግብዓት አቅርቦትን፣ የፖሊሲ ውሳኔዎችን፣ የቋንቋዎች ድርሻንና ትግበራን መሰረት ያደረገ ጥናት አድርጎ ስምምነት መደረስ አለበት። ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን ከፖለቲካችን ትርምስ ሌላ መጨመር እንዳይሆን እሰጋለሁ።

“ጠርዝ ላይ” የቋንቋ ጉዳይ ሲዳሰስ
ከዚህም በመነሳት በድሉ ዋቅጀራ (ዶ/ር) ጠርዝ ላይ በሚል ያሳተመውን መጽሐፍ በተለይም የቋንቋ ጉዳይ የሚመለከተውን ምዕራፍ በጋራ እናያለን።
ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ የኦነግን የኦሮምኛ ጽሑፍ በግዕዝ ፊደላት ሳይሆን በላቲን ፊደላት ይሁን የሚል ጥያቄ የራሱ በማድረግ እንዲፈፀም አድርጓል። በዚህም የብዙ ኦሮሞ ወገኖቻችን የሥራና የቦታ ምርጫ ተወስኗል። አሁን ደግሞ ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን እየተጠየቀ ነው። ሌሎችንም ቋንቋዎች ባካተተ መልኩ ሕገ መንግሥት ተሻሽሎ መሆን ይችላል። የቋንቋ ወጥነትን መጠበቅና ብዙ ቋንቋዎችን መቻል ወጥ የሆነ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠርም እንደሚያግዝ አምናለሁ፤ በደንብ ታስቦበትና ጥናትን መሰረት አድርጎ እስከተሰራ ድረስ።

የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል ፍኖተ ካርታ መሠራቱንና ውይይት እየተደረገበት መሆኑን እናውቃለን። አሁን ደግሞ የአዲስ አበባ ልጆች ኦሮምኛ እንዲማሩ መወሰኑን እየሰማን ነው። ይህ የቋንቋ ተማሩ ውሳኔ የትምህርት ስርዓት ለውጡን የሚያውክ ነው። በተጨማሪም የእኔ ጥያቄ ይህ የቋንቋ ዜና ዓላማው ምንድን ነው? ልጆቻችን ኦሮምኛ የሚማሩትና የፌዴራል ቋንቋ የሚሆነው የላቲን ጽሑፋን ይዞ ወይስ የኢትዮጲክ ፊደላትን ሲጠቀም? ምንም የፖሊሲ ስምምነት በሌለበት ቋንቋ ተማሩ ብሎ ማወጅ ሕገ ወጥ ነው። አሁን ደግሞ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ተመሳሳይ ሐሳብ ትንሽ ለዘብ አድርጎ “ጠርዝ ላይ” በሚባለው መጽሐፉ ይዞ ብቅ ብሏል።

1) በጠቅላላው ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ነገር ግን እንደ መጽሐፉ ሥም የኦሮሞ የሆነ አዎንታዊውንና ጥቅሙን ብቻ እየጠቀሰ፣ አሉታዊውን ሳይነካ ጠርዝ ጠርዙን ሲሔድ ነው የተመለከትኩት። ይህም የፖለቲካ ውግንናው የት እንደሆነ ያመላክታል፤ አማርኛ በፌዴራል ያለው ቦታ የተዋጠለት አይመስልም። በተቻለ መጠን አማርኛ ተናጋሪው፣ ከአፋን ኦሮሞ ተናጋሪው በቁጥር ያነሰ መሆኑን ለማሳመን ይጥራል፣ የምሁር አቅሉ እየቆነጠጠው መሆኑን በሚያሳብቅ መንገድ። እንዲያውም ከአማርኛ ማስተማር ወደ አፋን ኦሮሞ ማስተማር የሚቀየርበት ክልል እንደሚኖር ጠቁሟል። አማርኛ በካሪኩለሙ ቢኖርም ትምህርቱ በአግባቡ እንደማይሰጥ ምንም አላለም።

2) ስህተት የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ የሆኑ
ሀ) አሁን ባለው ሁኔታ፣ በአማርኛ አፋቸውን የፈቱ በአፋን ኦሮሞ አፋቸውን ከፈቱ ያንሳሉ?
ለ) የሲዳማ ቁጥር ከአሁን በፊት ከ5 በመቶ በታች ቢሆንም አሁን ግን ከዚያ በላይ ይሆናል? የሚሉ ሐሳቦች አስፍሯል። ኹለቱም የፖለቲካ ጥቅም ካልሆነ፣ በሎጂክ አሳማኝ ሆነው አላገኘኋቸውም።

3) የቋንቋ ፌዴራሉን ተከትሎ የተቀረጸው የትምህርት ስርዓት የአፈፃፀምና የአገር አንድነት ችግሮች መፍጠሩን ገልፆ መቀጠል እንዳለበት ግን ይነግረናል፤ የችግሩ መፍቻ መፍትሔ አልተብራራም። እንዲያውም ቋንቋዎች የፌዴራል መሆንና መፎካከር አለባቸው ይለናል። በእሱ ቦታ ላሉ ሰዎች የትምህርት ስርዓት ማስተካከል እና ስምምነት ሳይደረግ፣ የቋንቋ ተግባቦት ሳይጠና፣ የውጭ ጉዳይ ሳይታሰብበት አፋን ኦሮሞ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን ማለት ትልቅ ስህተት ነው።

4) የፌዴራል ቋንቋ የሚሆኑት ከ5 በመቶ በላይ ሕዝብ የሚናገራቸው ናቸው። እነዚህ ቋንቋዎች ፌዴራል ባለው ማንኛውም ጉዳይ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይደረጋል ይልና ትንሽ ቆይቶ ቅድሚያ ለኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋ የመሆን ዕድልን ይሰጣል። ለምን ኦሮምኛ ከሌሎች እንደሚቀድም፣ በውድድሩ የሚመጣው ትርምስ የሚመራበትንና የሚፈታበትን መንገድ አልጠቆመም። ይህን ለማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻል አስፈላጊነትን አይጠቅስም።

5) በላቲን የመጻፍ ሒደትን አዋጭ አለመሆንና የአገርን አንድነት ከመሸርሸር አንጻር ያለውንና የሚኖረውን አስተዋጽዖ ቢገልፅም፣ በላቲን መጻፍ የተወሰነበትን ምክንያት በኢትዮፒክስ መጻፍ ስለማይቻል ሳይሆን የኦነግ/ኦሕዴድ/ሕወሓት አማራንና አማርኛን ማዳከም የፖለቲካ ሴራ መሆኑን ከመጻፍ ታቅቧል። አፋን ኦሮሞ ወይም ሌሎች የፌዴራል የሚሆኑት በኢትዮፒክ ሲጽፉ ወይስ በላቲን እየፃፉ የሚለው አልተብራራም።

6) በመጀመሪያ ኹለት ቋንቋ መጠቀምን (bilingualism) ከብዙ ቋንቋ መጠቀም (multilingualism) ለምን መረጠው ብዬ አስቤ ነበር በመጨረሻ፣ አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ ጋር ከሌሎችን ቀድሞ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን ሲል ዓላማው ግልፅ ሆኖልኛል።

7) በጠቅላላው የትምህርት ስርዓቱ መሻሻልና የቋንቋ ስምምነት፣ ለሁሉም ወሳኝ መሆኑ በበቂ ሁኔታ አልተዳሰሰም። እንዲያውም የበለጠ ከአገር ውድቀት ጠርዝ ላይ መሆናችንን አስገንዝቦኛል።

8) በድሉ ዋቅጅራ በመጽሐፉ ቀዳማዊና ዳግማዊ ኢሕአዴግ የሚሉ ሐረጋትን ተጠቅሟል፤ የሕወሓትና የኦሕዴድ/ኦነግ መንግሥት ለማለት አለመድፈሩ ግን ገርሞኛል፤ እውነቱ ይኸው ነውና።

9) ልሳነ ብዙነት (multilingualism) የሰዎች ብዙ ቋንቋ መናገር እንጂ፣ በአንድ አገር ውስጥ ብዙ ቋንቋ መነገር አልመሰለኝም፤ እናም ጸሐፊው ይህንን ጉዳይ እንዴት እንዳዩት ግልጽ ቢያደርጉት።
እነዚህን ከላይ ያነሳኋቸው ጉዳዮችን በትኩረትና በማስረጃ በማስደገፍ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋለሁ እላለሁ።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here