“አገር ውስጥ ላለው ለውጥ ኢሳት እና ኦ ኤም ኤን ያበረከቱት አስተዋጽዖ ከማንም በላይ ዋጋ ሊሰጠው የሚችል ነው።”

0
910

 በፈቃዱ ሞረዳ  የብዙ ዓመታት ተመክሮ ያላቸው ጋዜጠኛ ናቸው። በ50ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት በፍቃዱ፣ “ለእግራቸው መጫሚያ፣ ለራሳቸው ባርኔጣ” ከሌላቸው ደሃ ገበሬ ቤተሰብ በአሁኑ አጠራር በኦሮሚያ ክልል ኢሊባቦር ዞን መወለዳቸውንና እስከ 11ኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተላቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውንም በእርሻ ሥራ ማገዛቸውን ይናገራሉ።

በወቅቱ የነኢሕአፓ/መኢሶን ዘመን በመሆኑ የውይይት ክበብ ውስጥ በንቃት ይሳተፉ እንደነበር የሚናገሩት በፈቃዱ፥ ከዚሁ ክበብ ጋር በተያያዘ የውጪ ዕድል አግኝተው በመጠባበቅ ላይ በነበሩበት ወቅት የአየር ወለድ ማስታወቂያ በመውጣቱ ከጓደኞቻቸው ጋር በመመካከር ወታደራዊ ሕይወትን ጀመሩ። ከወታደራዊው ሥልጠና በኋላ የጦር ኀይሎች የሬዲዮ መርሃ ግብር ላይ በጋዜጠኝነት ተመድበው በማገልገል መቶ አለቃ ማዕረግ ድረስ ደርሰዋል። አብረዋቸው ከሠሩት ታዋቂ ጋዜጠኞች መካከል አክለሊ ዘለቀ፣ ሲሳይ ታደሰ፣ ደረጄ ኀይሌ፣ አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት መኩሪያ መካሻ (ዶ/ር) እንዲሁም ወደ መጨረሻ አካባቢ አብረው የሠሩት የባሕር ኀይል ባልደረባ የነበረው ታዋቂ ደራሲ ዘነበ ወላ መጥቀስ ይቻላል።

የ1983ቱን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ለጥቂት ወራት በተሐድሶ ሆለታ ያሳለፉት በፈቃዱ፣ በአዲሱ መንግሥት የጦር ኀይሎች የሬዲዮ መርሃ ግብር እንዲያዘጋጁ ቢጋበዙም ከወቅቱ አመራሮች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ስላልቻሉ ወደ ተሐድሶ ተመልሰው እንዲገቡ ተደርጓል።

ከአጭር ሬዲዮ ሥርጭት በስተቀር መጻሕፍት እንኳን እንደልብ ማግኘት በማይቻልበት ትውልድ ሥፍራቸው፤ ግጥም ይገጥሙና ጽሑፍ ይጽፉ እንደጀመሩ የሚናገሩት በፈቃዱ፣ እሳቸው “ተሰጥዖ” የሚሉት ለጋዜጠኝነት ሕይወታቸው በር መክፈቱን ይናገራሉ። አዲስ አበባ ላይ የጨረሱት የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኮተቤ መምህራን ኮሌጅን እንዲቀላቀሉ በማስቻሉ በቋንቋ መምህርነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

የአገራችን የነፃ ፕሬስ ማቆጥቆጥ በጀመረባቸው 1980ዎቹ አጋማሽ፣ በግል ለሚታተሙ ኅብር እና አሌፍ’ የሚባሉ መጽሔቶች ላይ መሥራት የጀመሩት በፈቃዱ ከጓደኞቻቸው እገዛ ጋር ‘ጦማር’ የሚባል ጋዜጣ በማቋቋም በጋዜጣኝነትና በባለቤትነት ከ12 ዓመታት በላይ ዘርፉን አገልግለዋል

የጋዜጠኛ እስር እና እንግልት እንደ ብርቅ በማይታይበት ከ1985 አገር ለቀው እስከተሰደዱበት 1997 ድረስ፥ በፍቃዱ ከአንድ ሳምንት እሰከ ስድስት ሳምንታት በዘለቀ የእስር ቤት ቆይታ ቢያንስ ለዘጠኝ ጊዜያት መታሰራቸውን ያስታውሳሉ። በፈቃዱን ከእስራቱ፣ ወከባውና ክሶቹ ባሻገር ለስደት የዳረጋቸው ዋናው ገፊ ምክንያት የ1997 ምርጫን ተከትሎ መንግሥት 23 የኅትመት ውጤቶች እንዳይታተሙ ለማተሚያ ቤቶች የሰጠው ትዕዛዛ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ዐሥር ወራት በኬኒያ የተቀረውን ከ14 ዓመታት በላይ በሰሜን አሜሪካ በስደት ያሳለፉት በፈቃዱ፣ የኹለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ቤተሰብ ለመምራት ከሚሠሩት ሥራ ጎን ለጎን በዳያስፖራ በሚገኙት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ለዘጠኝ ወራት እንዲሁም በኢሳት ላይ ከ4 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሔደው 33ኛው የኦሮሞ ጥናት ማኅበር የተሳተፉት በፈቃዱ፣  ከዚህ ቀደም “የትውልዴ መዝሙር” የተሰኘ የግጥም መድብል በ1994 ለተደራሲያን ጀባ ያሉ ሲሆን አሁን ደግሞ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ የኅትመት ብርሃን ለማግኘት ማተሚያ ቤት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ በሙያዊ ሕይወታቸው እና በወቅታዊ የአገር ጉዳይ ዙሪያ ከበፈቃዱ ሞረዳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አገራቸውን ማገልገል ለሚፈልጉ ግን ተገድደው ለወጡ ሰዎች የስደት ሕይወት ምን ይመስላል?
ከዚህ የወጣሁት በኬንያ በኩል ነው። በዛም 10 ወር ያህል ነው የቆየሁት። ከአገሬ ስወጣ ምንም ገንዘብ አልነበረኝም፤ አንድ መቶ ዶላር ይዤ ነው ኬንያ የገባሁት። ቤተሰቤ [እንዲሁ ምንም] የገቢ ምንጭ አልነበራቸውም።

በሔዱኩበት ይረዱኝ የነበሩት እነ ሲፒጄ ነበሩ። በእነርሱ እርዳታ ወደ አሜሪካ የመሔድ አጋጣሚ ተፈጠረ።
ቤተሰቤን ይዤ በመሔዴ መጀመሪያ የቤተሰብ ኀላፊነትን መወጣት ትልቅ ግዴታ ነበር። በማታውቀው አገር ውስጥ የባሕል ተፅዕኖ አለ፤ ቋንቋውን መለማመድ፤ ኑሮን የማመቻትና የሥራ ጉዳይም አለ። መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ የሚችለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው።

እኔ በአሜሪካን ወለል ከማጽዳት ሥራ ነው የጀመርኩት። ከቤተሰቤ ጋር የራሳችን ሬስቶራንት እስከማቋቋም ደርሰን ነበር፤ ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ብናቆመውም።

አሜሪካ ስንገባ መጀመሪያ ያረፍው ቺካጎ ነበር፤ ከዛም መዳረሻችን ሂውስተን የሚባል ቦታ ለመሔድ ኤርፖርት ስንጠብቅ ለልጃችን ውሃ መግዛት የሚያስችል ሳንቲም አልነበረንም። በጥቅሉ [ሕይወትን] ከዜሮ ነው የጀመርነው [ለማለት] ነው።

በዛም መካከል ግን አላረፍኩም፤ ከሥነ ጽሑፍ አልራቅኩም። እዛው አገር ባሉ አንዳንድ መጽሔቶች ላይ እጽፍ ነበር። የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሲቋቋሙ መጀመሪያ በኦ ኤም ኤን (በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ) ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩ። የምችለውን ለማበርከት ሞከርኩኝ። በዛም ለአንድ 9 ወር ሠራሁ።

ኦ ኤም ኤን በተቋቋመበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ችግሮችና ያለመግባባቶች ነበሩ፤ የለቀቁት ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው?
እነዚህ ልዩነቶች የትም አገር ያሉ ተፈጥሮአዊ ናቸው፤ እንጂ በኦ ኤም ኤን ብቻ የተከሰተ ተዓምር አይደለም። የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የሚሻኮቱበት ቦታ ነው፤ ስለዚህ አለመግባባቶች ነበሩ። ኦ ኤም ኤን ለብቻው የሚሠራው በኦሮምኛ ቋንቋ ነው። የሚያነሳውም የኦሮሞን ጉዳይ ነው። እኔም ከዛ ማኅበረሰብ በመወለዴ የተነሳ ያንን ማኅበረሰብ ማገልገል፤ ለእናት ለአባቴ፤ ለእህት ለወንድሞቼ፤ ለዛ ማኅበረሰብ ድምጽ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ስላመንኩበት ነው እዛ ውስጥ የገባሁት።

በምን መንገድ ብንሔድ ይሻላል በሚለው ላይ በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ልዮነቶች ነበሩ። ፈረሱ ኮርቻ ላይ በግራ በኩል እንውጣ ወይስ በቀኝ በኩል እንውጣ በሚለው ላይ አከራካሪ ነገሮች ነበሩ። ይህም ነገር በኦ ኤም ኤን [ውስጥ] ነበር። እኔ ደግሞ ባለኝ የተፈጥሮ ባሕሪ እንደዚህ ዓይነት ልዩነት ባለበት ቦታ አንዱን ጎራ ይዤ ሌላው ላይ ድንጋይ መወርወር አለብኝ የሚል አቋም የለኝም። ልዩነቶችን አቻችሎ አብሮ መሥራትን እመርጣለሁ፤ የሚያግባቡ ጉዳዮችን እያጎለበቱ መሥራትን እመርጣለሁ። በማይግባቡበት ጉዳይ ደግሞ ተከባብሮ መሥራትን እመርጣለሁ። ያ በማይቻልበት ሁኔታ መራቅ እንደሚገባኝ አምናለሁ። በዛ ምክንያት ነው ከኦ ኤም ኤን የወጣሁት።

ከዛ ቀጥታ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳትን) ተቀላቀሉ?
አይደለም! ለአንድ ዓመት ያህል ቤተሰቦቼ ጋር ተመልሼ ሌላ ሥራ መሥራት ጀመርኩ። ከዛም አገር ውስጥ ያለው ትግል እየጠነከረ መጣ። ኢሳት ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ በሌሎች ቋንቋዎች የመሥራት ግልጽ ፖሊሲ አልነበረውም፤ የሚሠራበት ቋንቋ አማርኛ ነው ይልና ‘’እንደአስፈላጊነቱ በሌሎች ቋንቋዎች’’ ይላል። በዚህ ለረጅም ጊዜ ቆየና አገር ውስጥ ያለው ትግል እየሰፋና በተለይ በኦሮምያ ያለው እንቅስቃሴ ተደማጭነቱ ሲሰፋ በአፋን ኦሮሞን ለመክፈት ፍላጎት አሳዩ፤ ጠየቁኝ። እኔም እሺ ብዬ የኦሮምኛ ዝግጅት ክፍልን ከፈትን፤ ሌሎች ሰዎችን ቀጥረን መሥራት ጀመርን።

ኦ ኤም ኤን ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው የተቀላቀልኩት። ኢሳትን ደግሞ በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2015 ላይ ነው። ያኔ የኦ ኤም ኤን ዋና አዘጋጅ የነበሩት ዶክተር ብርሃኑ አውስትራልያ ነበሩ፤ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር ደግሞ ሜሪላንድ ሲሆን፤ ቢሮው ደግሞ ሚኒሶታ ነበር። ፕሮግራም ከማዘጋጀት ጎን ስቱዲዮ መምራት አለብህ ተብዬ እኔም ወደ ሚኒሶታ ነበር የሄድኩት። ሃሳቡንም ያቀረበልኝ መጀመሪያ መረራ ጉዲና ነበር። በዛም በአብዛኛው የማኔጅመንት ሥራ ነበር ስሠራ የነበረው።

ኢሳት ላይ አፋን ኦሮሞ ዝግጅት ጀመርን። እኔ መኖሪያዬ ቴክሳስ ነው፤ የኢሳት ቢሮ ደግሞ ዲሲ ነው። እናም ቤቴ ውስጥ አንድ ክፍል ስቱዱያ ገንብቼ ነው በኢሳት ለ4 ዓመት የሠራሁት።

የኹለቱን ጣቢያዎች የሥራ ሁኔታ በንጽጽር እንዴት ያዩታል?
ኹለቱም “ሬዚስታንት” (የትግል) ሚዲያዎች የሚባሉና ለትግል ወይም ለለውጥ ማኅበረሰብ ማንቃት፣ ለትግል ማብቃት፤ እንዲሁም መረጃ መስጠት ግብ ያደረጉ ናቸው። በአገሪቱ የሚደረጉ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ማሳየት፤ በምሥራቅ የሚደረገውን ለምዕራብ ማሳወቅና ሰው እንዲናበብ ለማድረግ የተቋቋሙ ናቸው።

በፖሊሲ ደረጃ የተለያዩ ናቸው። ኦ ኤም ኤን በብዛት የሚያተኩረው በኦሮሚያ ወይም በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዙሪያ ነው። ኢሳት ደግሞ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ፤ ሁሉንም በኢትዮያዊነት ማዕቀፍ ማየት አለብን ብሎ፤ ፖሊሲ ቀርጾ የሚሠራ የሚድያ ተቋም ነው። ሁለቱም በኢትዮጵያ መሠረታዊ የሆነ የዲሞክራሲ ለውጥ መምጣት አለብት በሚለው ላይ ይስማሉ።

የትኩረት አቅጣጫችን የት መሆን አለበት በሚለው ላይ፤ ኦ ኤም ኤን በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው የሚያተኩረው ወይም የጋምቤላ፣ የአፋር፣ በአማራና ደቡብ የሚካሔዱትን ጉዳዮች አያስተናግድም ማለት አይደለም። ኢሳትም በክልሎች የሚነሱ ጉዳዮችን አያስናግድም ማለት አይደለም። ዞሮ ዞሮ እነዚህን ጉዳዮች በምን ማዕቀፍ ነው የሚያስተናግዱት በሚለው ላይ ልዩነት አላቸው።

ከተቋማቱ ጋር አብረው የሚነሱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አሉ፤ ከኦ ኤም ኤን ጃዋር መሐመድ፤ ከኢሳት ጋር አበበ ገላው። እነዚህን ኹለት አለቆች በንጽጽር እንዴት ይገልጿቸዋል?
በኦ ኤም ኤን እያለሁ ከጃዋር ጋር በቅርብ እንገናኛለን፤ እኔ በነበርኩ ጊዜ እርሱ ኮሎምቢ ዩኒቨርስቲ ይማር ነበር። እኔ ከለቀቅኩ በኋላ ነው የኦ ኤም ኤን ዳይሬክተር ሆኖ የተሾመው። በሥራ እንገናኛለን፤ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ እንዲሁም ቦርድ ውስጥ ነበር። ትልቅ ሚና ነበረው፤ ኦ ኤም ኤን ውስጥ የማይታይ ጠንካራ እጅ ነበረው ማለት ይቻላል።

ልጁ ጥሩ ችሎታና ተሰጥዖ አለው፤ በተለይ የማስተባበር ችሎታውን በጣም ነው የማደንቅለት። ታች ካለው ማኅበረሰብ ጀምሮ እስከ ፕሮፌሰሮች ድረስ አስተባብሮ በቦርድ አባልነት፣ በሥራ አስፈጻሚነት፣ ገንዘብ በማሰባሰብ በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ለብቻው ነው የሠራው ማለት አይደለም፤ አገር ውስጥ ያለው ችግር አስተዋፅዖ አድርጎለታል።

ይሁንና ኦ ኤም ኤንን በመመሥረትና እዚህ ደረጃ በማድረስ በኩል ጃዋር መሐመድ የተጫወተውን ሚና ማናናቅ አይቻልም። ሰዎች እንደፍላጎታቸው የተለያየ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል። እኔ ብዙውን ጊዜ የማምንበትና ለሰውም የምናገረው ሰዎች፣ ግለሰቦችም ተቋማትም የየራሳቸው ችግር ይኖርባቸዋል። ነገር ግን አዎንታዊ ነገሮችን አውጥቶ ማጎልበት መቻል ጥሩ ነገር ነው፤ እኔም በዛ ላይ አተኩራለሁ። የሰዎችን መልካም የሆነ ነገር ማጎልበት ጥሩ ይመስኛል፤ ሁል ጊዜ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን ከማንሳት ማለቴ ነው። እኔ ማድረግ የማልችለውን ማድረግ የሚችሉ ሰዎች ለእኔ የተሸሉ ሰዎች ስለሆኑ አከብራቸዋለሁ።

የኢሳት ምስረታን በተመለከተ አከራካሪ ጉዳዮች አሉ፤ ሰፊም ናቸው። አበበ ገላው ግን ከአገር ቤት ጀምሮ በነጻ ፕሬሱ አካባቢ ያለውን አስተዋጽዖ አውቀዋለሁ። ወደ ኢሳት የመጣው እኔ ኢሳት ከጀመርኩ በኋላ ነው። አበበ በጣም ጥሩና አብረህ ልትሠራው የምትችለው ነው። ሙያውን ያውቃል፤ ጥሩ የሥራ ፍላጎት አለው፤ አገሩን ይወዳል፤ እልኸኛ ነው፤ በተቻለ መጠን ሥሜታዊ አይደለም፤ ሚዛናዊ ነው።

ኹለቱም የራሳቸው የሆነ ስብዕና ያላቸው ሰዎች ናቸው። ኹለቱም ወደ ሚድያ ከማቅናታቸው በፊት ጓደኛሞች የነበሩና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲመካከሩ የነበሩ እንደነበሩ ነው የሚናገሩት። ኹለቱም የየራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው አውቃለሁ።

ኢሳት እና ኦ ኤም ኤን ተልዕኳቸውን መትተዋል ማለት ይቻላል?
ትግሉ አልቆመም፤ አይቆምም ይቀጥላል፤ የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለውም። አሁን አገር ውስጥ እያየን ካለነው ሁኔታ አንጻር እነዚህ የሚድያ ተቋማት ያደረጉት አስተዋጽዖ ቀላል አይደለም፤ ማንም ሊክደውም አይችልም። ኅብረተሰቡን ከማነሳሳት አንጻር፣ መብቱን እንዲያውቅ ከማድረግና በተለያዩ አቅጣጫዎች ትግሉን እየደረጉ ያሉት ኀይሎች እንዲናበቡ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ብዬ አምናለሁ። አሁን አገር ውስጥ ላለው ለውጥም እነዚህ ሚድያዎች ያበረከቱት አስተዋጽዖ ከማንም በላይ ዋጋ ሊሰጠው የሚችል ነው። ይሕን መመዝገብ የሚችለው ኅብረሰተቡ ነው፤ ታሪክ ነው። ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ የእነዚህ ኹለት መገናኛ ብዙኀን አስተዋጽዖ ትልቅ ነው።

ከለውጥ በኋላ ኹለቱም አዲስ አበባ ላይ ቢሮ ከፍተዋል። ኢሳት ከግማሽ በላይ አባላቱን ሸኝቷል። የዚህ ትርምስና በውስጥ ያለው ተቃርኖ መሠረታዊ መንስዔ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
በግለሰቦች ጉዳይ ውስጥ አለመግባትን እመርጣለሁ። የተከሰቱት ነገሮች ግን ተፈጥሯዊ ናቸው። አንድ ተቋም የራሱ ሕይወት አለው፤ ይንቀሳቀሳል፤ ያድጋል፤ ይሰፋል፤ ይወድቃል። ሁል ጊዜም በትግልና በፍጭት ውስጥ ነው ያለው። እነዚህ ተቋማት ውስጥ የተሰባሰቡት ብዙዎቹ ለጥቅም ብለው አይደለም። በእርግጥ በስደት እየተኖረ ለሕይወትና ለኑሮ የሚበቃውን ማግኘት መቻል ያስፈልጋል። አብዛኛው ሰው ግን በዚህች አገር እንዲመጣ በሚፈለገው ለውጥ ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ማበርከት አለብኝ ብሎ የገባ ነው። እንደዛ ሲሆን ግን የሐሳብ ልዩነቶች የሉም ማለት አይደለም።

ካነሳኸው ጉዳይ ጋር በተያያዘ በዛም በሚሠሩት ሰዎች መካከል የሐሳብ ልዩነቶች ተፈጥረዋል። በዛም ምክንያት መለያየት መጥቷል። በተለይ ኢሳት የሚደገፈው በግለሰቦች መዋጮ ነው፤ ውጪ አገር ባሉ ሰዎች ማለት ነው። አገር ውስጥ ያለው ለውጥ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ነካክቷል። ውጪ አገር ያሉ ተቃዋሚዎች አገር ውስጥ የመግባታቸው ሁኔታ፤ በአገር ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳር መስፋቱና ዳያስፖራው ውጪ አገር ያለው ትግል አብቅቶለታል ብሎ የማመኑ ጉዳይ፤ በዛም ላይ አገሩ ውስጥ የተፈጠረው ነገር የዳያስፖራውን ስሜት ለኹለት የከፈለ ነበር። “ለውጥ አለ፤ ለውጡን መደገፍ አለብን” በሚለው እና “ለውጥ የለም፤ ሥማዊና ማስመሰል ነው፤ ትግሉን መቀጠል አለብን” በሚለው መካከል ሰፊ ልዩነት ፈጥሯል። ይህም ልዩነት ኢሳት ውስጥም ተከስቷል።

የሰዉ ለኹለት መከፈል የፋይናንስ አቅሙ ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። ኢሳት ሰፊ ነው፤ ከኻያ በላይ ሰዎችን ቀጥሮ ነው የሚያሠራው፤ የተለያየ ስቱድዮዎች ያሉት ድርጅት ነው። የፋይናንስ ችግር ሲፈጠር ሁሉን ሠራተኛ ይዞ መሔድ አይቻልም። ይህ የታወቀ ነው፤ በየትኛውም ዓለም ትላልቅ ድርጅቶችም የሠራተኛ ቅነሳ ያደርጋሉ። አንዳንድ ሠራተኞችን ለጊዜው ለመቀነስ አመራሩ እርምጃ ለመውሰድ ሞክሮ ነበር። የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ “መቀነስ የለበትም፤ ችግር ያለው አመራሩ ላይ ነው” ብለው፤ “የተቀነሱ ሰዎች ካልተመለሱ እኛም ለቅቀን እንወጣለን” በማለት ለቅቀዋል። የራሳቸውን ተቋም ያቋቋሙ ሰዎችም አሉ።

እነዚህ የወጡ ሰዎች “ከሙያው ሥነ ምግባር አንጻር የሚሠሯቸው ሥራዎች እንዴት ሊታዩ ይችላሉ? በፊት በኢሳት ሲያንጸባርቁት ከነበራውና አሁን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምን ይመስላሉ?” ብሎ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። እሱ አሁንም አጠያያቂ ነው።

ሙያዊ ሥነ ምግባር በእነዚህ ሬሲስታንት (የትግል) በተባሉ ተቋማት አይከበርም ማለት ነው? መጠበቅ አለበት ካሉስ እነዚህ ኹለት ተቋማት ምን ያህል አክብረው ሠርዋል?
እኔ መጠበቅ አለበት እላለሁ። ወደኋላ ስመለስ፤ በአገር ውስጥ የፕሬስ ሥራን በምንሠራበት ጊዜ መረጃዎችን የማግኘት ችግር ነበር። አንዱ በተለይ ሙያው ከሚጠይቀው መካከል ሚዛናዊ ማድረግ እና ስሜታዊ አለማድረግ ነው። ማለትም ባለሙያው ከግራና ከቀኝ መረጃዎችን አሰባስቦ፤ ለሰው ደረቁን እውነት ሰጥቶ ፍርዱን ለሰዉ ትቶ ማውጣት ነው።

በኢትዮጵያ ከበፊትም ጀምሮ እንዲህ ዓይነት ዕድሎችን ማግኘት አይቻልም ነበር። መንግሥትም በሩን ዘግቶ ነበር። ለነጻው ፕሬስ የሚሰጠው ምንም መረጃ ስላልነበር፤ የአንድ ወገንን መረጃ ተይዞ ሲወጣ ነው የነበረው። በእነዚህ ኹለት ሚድያዎችም አካባቢ ከርቀት ይሠራም ስለነበር እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ነበሩ፤ ያን ማሟላት አልተቻለም።

ከዛም ባለፈ ሆነ ተብሎ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤ ኹለቱም የአክቲቪስት ሚድያ ነበሩ። በዛ ባህሪ መሠረት አንዳንዴ ማጋነን እና ሚዛናዊ ያልሆኑ መረጃዎችን መስጠት፣ በሚሰጡ አስተያየቶችም ላይ ሚዛናዊ ያለመሆን ጉዳዮች ይታዩ እንደነበር አምናለሁ።

አሁን በተቻለ መጠን፤ እኔ እንደማስበው፤ በተለይ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ፤ መረጃዎችን በቅርብ የማግኘትና ባለሥልጣናትንም ጠይቆ ሚዛናዊ የማድረግ ዕድሎች ስላሉ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ አያለሁ፤ በቂ ነው ለማለት አይደለም። የአቅም ጉዳይ ሊኖር ይችላል፣ ዘጋቢዎችን ልኮ የማሥራት፣ የዘጋቢዎች አቅም እና የሥልጠና ጉዳዮችም አብረው ሊነሱ ይችላሉ።

ብዙ ሚድያ ላይ የምናያቸው ሰዎች “በሙያው ምን ያህል ልምድ አላቸው? ምን ያህል ሥልጠና ወስደዋል?” ብለን ካሰብን እውነት ለመናገር ደረታችንን ነፍተን አፋችንን ሞልተን የምንናገራቸው ነገሮች አይደሉም። የምናያቸው ጅምሮች ግን አሉ፤ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች በኩል ቢሆን፤ መረጃዎችን ሚዛናዊ ለማድረግ የሚሰጠውን ስንመለከት የሚታዩ አዎንታዊ የሆኑ ነገሮች ይታያሉ። ወደ ተሻለ ነገር እየሄደ ነው የሚል ተስፋ አለኝ።

በጋዜጠኝነትና አክቲቪዝም መካከል መቀላቀል ይታይል። በእርሶ አመለካከት ጋዜጠኝነትና አክቲቪዝም ምንና ምን ናቸው? አብረው ሊሔዱስ ይችላሉ ወይ?
አብረው መሔድ ይችላሉ፤ ጋዜጠኝነት በራሱ አክቲቪዝም ነው ብዬ አምናለሁ። ጋዜጠኛ ሁል ጊዜ ለሐሳብ ነጻነት መሟገት ነው። ሕዝብ መረጃ እንዳያገኝ የሚያደርጉት እንቅፋቶችን፣ ፖሊሲዎችንና ስርዓትን መቃወምና ማጋለጥ መቻል አለብህ፤ እንደጋዜጠኛ። አደባባይ ወጥተህ ባንዲራ ወይም መፈክር ይዘህ ባይሆንም፤ እነዚህን ተፈጥሯዊ የሆኑ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች ሊከለክሉና ሊያደናቅፉ የሚችሉ ፖሊሲዎች፤ አፈጻጸሞች ሲፈጠሩ ማጋለጥና የምርመራ ሥራዎችን መሥራት መቻል በራሱ አክቲቪዝም ነው።

አንዳንዴ ተነጥለው ሊታዩ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም። ዋናው ነገር ከፕሮፓጋንዳና ሚዛናዊ ካልሆነ ነገር ወጥቶ፤ ሚዛናዊ የሆነ ነገር ማቅረብ መቻል ነው። አክቲቪዝም ብዙ ጊዜ ፍላጎትን መሠረት አድርጎ ነው፤ አንድ ግብም አለው። በአብዛኛው ግቡ ፖለቲካዊ ነው። ነገር ግን አክቲቪዝም በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል፤ በአካባቢ ጉዳይ፣ በፖለቲካ፣ በጋዜጠኝነት፣ በሴቶች ጉዳይ፤ በወጣቶች ጉዳይ ይሠራል። ግብ አድርጎና ዓላማዬ ብሎ የሚሠራው ነገር አለ።

የፖለቲካው አክቲቪዝም ጋር ጋዜጠኝነት መደበላለቅ በእኛ አገር ይታያል። በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ጋዜጠኛና አክቲቪስት ወይም የሰብኣዊ መብት ተሟጋችና አክቲቪስት እገሌ ተብሎ ሲጻፍ አያለሁ፤ ግን አይስማማኝ። እንዲህ ያሉ መደበላለቆች አሁንም አሉ፤ ይህን ሹመት ማን እንደሚሰጥ ግን አላውቅም፤ ኅብረተሰቡ ይሁን ወይ ራሱ ግለሰቡ ለራሱ እየሰጠ ይሁን አላውቅም፤ ግን አሁንም መደበላለቅ አለ።

አክቲቪዝም በተለያየ ዘርፍ አንድ ነገርን አንስቶ ለዛ ነገር መሟገት፤ ሰውን ማነሳሳትና ግንባር ቀደም ሆኖ መሳተፍ ማለት ነው። እሱን በተለይ የሐሳብና የሚድያ ነጻነትን አይተህ፤ እነዚህ ነጻነቶች በታፈኑበት አገር ለዛ የምትቀሰቅስ ከሆነ የሚድያ አክቲቪዝም ሥራን መሥራት ትችላለህ፤ ጋዜጠኛ ሆነህ ያንን የሚያግድህ የለም ማለት ነው።
አሁን የምናያቸው አንዳንድ ነገሮች ግን ጋዜጠኝትንና የሚድያ አክቲቪስትነትን ሥራ ሳይሆን የፖለቲካ አክቲቪስትነቱን እና ሚድያውን ነው፤ ፖለቲካ ደግሞ ከጀርባው ያለው ጥያቄ የሥልጣን ጉዳይ ነው። ጋዜጠኛ ከሥልጣን ጋር ትግል ውስጥ መግባት የለበትም። እነዚህን ከሚመለከቱ ጉዳዮች ጋር ፍልሚያ ውስጥ መግባት የለበትም።

የሥልጣንና የፖለቲካ ጉዳይን እና ጋዜጠንነትን የማደበላለቁ ነገር ይታያል ማለት ነው። እነዚህ ነገሮችን መራቅ ያስፈልጋል፤ አይኑሩ ማለት አይደለም። በፖለቲካ ጉዳይ የሚሠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለይተው በዛው መንገድ ይቀጥሉ፤ ሚድያውን ይጠቀሙ። ሚድያው ላይ የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ሚድያው እንዲሸከሙ የሚያስገድደው መስቀል አለ፤ ያንን መሸከም መቻል ያስፈልጋል። ዓለማቀፍ የሥነ ምግባር መርህ አለ፤ ያንን ተከትሎ መሥራት መቻል ነው። ሥራውን ለእነርሱ መተውና የፖለቲካ ሥራውን የሚሠራ ከሆነ በዛው መቀጠል፤ ጋዜጠኛውን በሚያስፈለግ ቦታ መጠቀም። እዚህ ጋዜጠኛ ነኝ እያሉ በዚህ በፖለቲካ ሽኩቻ እገባለሁ እያሉ ነው። በአንድ ወቅት አስፈላጊ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል፤ አሁን ግን ከእንደዚህ ዓይነት ነገሮች እየተላቀቅን መሔድ አለብን። የሚድያውን ድባብ አንረብሽ። ሰዎችም ለሚድያ ያላቸውን ግንዛቤ አናበላሸው።

በአገር ውስጥ የተደረገው ለውጥ የዳያስፖራው ፖለቲካ ላይ ምን ለውጣ አመጣ ማለት ይቻላል?
የነዶክተር ዐቢይ አሕመድ ቡድን ወይም ቲም ለማ ለእኔ በኢሕአዴግ ውስጥ የተደረገ ሪፎርም ነው። እነዶክተር ዐቢይ ሲመጡ ሌላ ድብቅ ዓላማ ይዘው ወይም ኢሕአዴግን እናፈርሳለን ብለው አልመጡም። ኢሕአዴግን ሪፎርም እናደርጋለን፤ ከዚህ ቀደም የሔድንበት መንገዶች ሁሉ አያዋጡም፤ ወደ ጥፋት እየወሰዱን ነው። አገሪቱንም ወደ ማጥፋት እየሔደ ስለሆነ የቀደመውን አሠራራችንን ማየት አለብን ብሎ ከኢሕአዴግ ውስጥ የወጣ ኀይል ነው። አዲስ ሐሳብ ይዞ የመጣ ነው።

ያ ሐሳብ ደግሞ እኛም ቀደም ብለን ስንጽፍበት፤ ስንታሰርበትና ስንሰደድበት የነበረ ነው። ብዙ የፖለቲካ ፓርዎችም ቀድመው ያነሱት ሐሳብ ነው። ያ ሐሳብ እነ መረራ ጉዲና የታሰሩለት፤ እነ ብርሃኑ ነጋ የተሰደዱለት ነው። ከሞላ ጎደል ጥያቄውን ከኢሕአዴግ ውስጥ፤ አዲስ የለውጥ ሐሳብ አለን ብለው የተነሱ ሰዎች ያመጡት ጉዳይ ነው።

የዳያስፖራው ፖለቲካ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖለቲካ ነው። ዳያስፖራው መንግሥትን የሚደግፍ አለ፤ ተቃዋሚንም ይደግፋል። ዳያስፖራው በአገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰፊና ለሁሉም ሜዳው ምቹ ሆኖ ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር የሚደረግበት ስርዓት ቢፈጠር ይፈልጋል።

በአገር የታሰሩ ሲፈቱ፤ በስደት ላይ የነበሩና ትጥቅ ትግል ሲያካሒዱ የነበሩት ወደ አገር እንዲገቡ በሩ ሲከፈትላቸው፤ ውጪ የነበረው ኀይል በደስታ ተቀብሎታል። [ይሁንና አንዳንድ] ሰዎች የእኔን ፍላጎት ብቻ ለማስፈጸም የመጡ ናቸው ብሎ የሚያስብ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ እነርሱ በፈለጉት መንገድ ነገሮች ሳይሔዱ ሲቀሩ፤ ወደ ኋላ [ያፈገፈጉ] ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

በአጠቃላይ አገር ውስጥ የተፈጠረው ለውጥ ከአገር ውጪ የነበረውን የተቃውሞ እንቅስቀሴ በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለኹለት ከፍሎታል። በዚህም የነበረውን ጥንካሬ አላልቶታል፤ ከፋፍሎታል። በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው ጥንካሬም በተመሳሳይ ላልቷል። አሁን ባለው ሁኔታ በዳስፖራውም በተቃዋሚውም ሆነ በገዢው ፓርቲ በኩል ጠንካራ ያልሆኑ ኀይሎች አንድ ላይ መጥተው ጠንካራ ለመሆን እየጣሩ ነው፤ አንድም አንዱ ጠንካራ ሆኖ ደካማውን አጥፍቶ የተሻለ ጠንካራ ለመሆን እየሠራ ነው የሚመስለኝ።

ለውጡን ብዙዎች በተስፋና በሥጋት ነው የተቀበሉት። ከለውጡ በኋላ መፈናቀልና መሰደድ፤ ግድያና አለመረጋጋት ተፈጥሯል። ለእርሶ ሥጋቱ ነው ተስፋው የሚያይለው? አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
እኔ ምን ጊዜም የተስፋ ደጋፊ ነኝ፤ ሁሌም ተስፋ ነው የሚታየኝ። መፈናቀልና መሰል የሚባሉ ነገሮች ለውጡ ያስከተላቸው ናቸው ብሎ የሚነገረውን ነገር ማመን ይቸግረኛል። ለለውጡ ምክንያት የሆኑ ናቸው። ለውጡ በአንዴ በተዓምር በአንድ ሌሊት የሆነ አይደለም። ለዓመታት የተከማቹ ችግሮች ናቸው እንጂ ይሄ ለውጥ የፈጠረው አይደለም። ይሔ ለውጥ ለእነዚህ ነገሮች ፈንድቶ መውጣት ያደረገው ነገር በአደባባይ እንዲወጡና እንዲነገሩ አደረገ።

አንዳንዴ ማኅበረሰባችንንም ባንረሳው ጥሩ ነው። በእውቀትና ግንዛቤ ደረጃ ለውጥን የመቀበል ፍላጎታችን አንዳንዴም ለውጥ ሲመጣ ጥቅም ማጣትም አለና፤ በእነዚህ ሁኔታዎች መካከል መናጥ ይመጣል። የዛ መናጥ አካል ነው እንጂ እስካሁን የተፈጠሩት መሰደድና መፈናቀሎችን ለውጡ የፈጠራቸው ነው ብዬ አላስብም። ለመኮነንም ይከብዳል ብዬ አስባለሁ። እንዲያውም ወደ ተሻለ ነገር እየሔድን ያለን ይመስለኛል። አሁን እየተከፈለ ያለው ዋጋ፥ ለዛ የተሻለ ተስፋ የሚከፈል ዋጋ ነው ብዬ ነው የማምነው።

እኔ ከሥጋት ይልቅም ተስፋ ነው የሚታየኝ፤ ተስፋው ግን ቁጭ ተብሎ እግር ተጣምሮ የሚጠበቅ አይደለም። ሊሠራበትና ዋጋ ሊከፈልበት የሚገባ በርካታ ነገር አለ።

ለውጡን የተሳካ ለማድረግና ተስፋውም እንዲቀጥል መገናኛ ብዙኀን ምን ሚና መጫወት አለባቸው?
ስለሚድያ ስናነሳ ስለጋዜጠኝነት ነው የምናነሳው። ጋዜጠኝነት ከምንም በላይ ኀላፊነት ነው፤ ማኅበራዊ ኀላፊነትን መሸከም የማይችል ጋዜጠኛ አደጋው ያን ያህል ነው። የአገራትን ልምድ ስናይ፤ እዚሁ በቅርባችን ያለውን የሩዋንዳን ታሪክ ማንሳት እንችላለን። በሩዋንዳ ለተፈጠረው እልቂት ሚድያ የነበረው ድርሻ ቀላል አይደለም። በዛው ረገድ በተለያዩ አገራት ደግሞ ኅብረተሰብን በማረጋጋትና በማስተማር ሚድያው የተጫወተው ሚና፤ በተለይ ጋዜጠኛው ቀላል አይደለም።

ለሙያቸው የቆሙ ጋዜጠኞች የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም፤ ደግሞም ወደ ኋላ እንዳይመለስ በተቻለ መጠን በኀላፊነት ስሜት፤ በተለይ ግጭት በሚፈጠርበት አካባቢ ላይ፤ ግጭት እንዴት ነው የሚዘገበው የሚለው ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። ገበያን አስበን የምንሠራ ከሆነ ችግር ውስጥ እንገባለን። ለገበያ ብቻ ብሎ ከመሥራት መራቅ ያስፈልጋል። አደጋን ሊያስከትል፤ የሰው ሕይወት ሊያጠፋና ዜጋን ለችግር ሊዳርግ የሚችል ሥራን ሠርተን ጥቅም ከምናገኝ ቢቀር ይሻላል።

ሚድያው በተቻለ መጠን፤ አገሪቱ ሊያሠሩ የሚችሉ ሕጎች አሏትና፤ በሚያሠራው ሕግና በሙያ ሥነ ምግባር መካከል ሆኖ መጫወት ይቻላል። ስለዚህ ጋዜጠኛው በተለይ ለሙያው ሥነ ምግባር ራሱን የሰጠ ጋዜጠኛ በዚህ አገር ኀላፊነቱን መወጣት መቻል አለበት።

በእርግጥ ለውጥ የለም ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። እኔ እዛ ውስጥ አይደለሁም፤ የማያቸው ነገሮች አሉ። የእኔ እዚህ አገር መገኘትና እዚህ ቁጭ ብዬ መናገር መቻል በራሱ ለእኔ ለውጥ ነው። ትላንት እስር ቤት ውስጥ ታጉረው የነበሩና ይፈቱ እያልን የጮህንላቸው ጓደኞቻችንን እዚህ አገር ውስጥ በሰላም ማግኘታችን ለውጥ ነው፤ በስደት የቆዩና ጫካ ገብተው የነበሩ ሰዎችን እዚህ መጥተን ማየታችን ለውጥ ነው። ልንንቀው አይገባም፤ ትን ነገር ይዘን ማስፋት መቻል አለብን። የተገኘው ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስ፤ የሚመለሰውም በለውጡ ጠላት ነው ተብሎ የተፈረጀ ከሆነም፤ ሚድያው ኀላፊነት በተሞላው ሁኔታ መንግሥትንም መቆጣጠር መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ።

ከሚድያው ባሻገር ሕዝባዊ መሠረት እንዲይዝ ምን መደረግ አለበት?
እኔ የተለየ ሕዝባዊ መሠረት መያዝ አለበት ብዬ አላስብም። ከመነሻውም ለውጡ የመጣው ከሕዝብ ነው። ከላይ የወረደ አይደለም። ብሶት ነው ያመጣው፤ ከወጣቱና ከገበሬው፤ ከተገፋው ሕዝብ የመጣ ለውጥ ነው። የሕዝብ ለውጥ ነው። ይህ የሕዝብ ለውጥ ከሕዝብ እጅ እንዳይወጣ ምን መደረግ አለበት የሚለው ነው እንጂ መልሶ የሕዝብ ለውጥ መደረግ አለበት የሚለው ጉዳይ ችግር አይመስለኝም።

እንዴት ወደ አገር ቤት መጡ?
ከአገር ከወጣሁ ቤተሰቤን አላየሁም። እናት፤ እህት ወንድሞች፤ ጓደኞች አሉኝ ይናፍቁኛል፤ አገሬ ይናፍቀኛል። እሱን ብዬ መጣሁ። በአጋጣሚ ስመጣ ደግሞ የኦሮሞ ጥናት ጉባኤ ከ33 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ ተካሔደ። በዚያ ስብሰባ ላይ ተሳትፌ ነበር። አልፎም ባለፉት 15 ዓመታት የያዝኩት የአጫጭር ልብለወዶች ስብስብ መጽሐፍ ነበረኝ። ይህን አገሬ መጥቼ ለማሳተም ህልም ነበረኝ። በውጪ አገር እያለሁ የማሳተም ዕድል ነበረኝ፤ የተሻለ ጥቅምም አገኝ ነበር። ግን ለራሴ የገባሁት ቃል ነበር፤ አገሬ ገብቼ አሳትማለሁ ብዬ ነበር። ባልተጠበቀ ሁኔታ ደግሞ ይህ ለውጥ ሲመጣ፤ ቃሌን አገሬ መጥቼ ማስፈጸም ስላለብኝ ነው አንድም የመጣሁት።

ሲፒጄ ባወጣው ሪፖረት ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ ፕሬስ የሚፈጠር ከሆነ አገሬ ተመልሼ ሕዝቤን አገለግላለው ብለው ነበር። ጊዜው ደርሶ ይሆን?
ያ ጊዜ መቼ እንደሆነ አላውቅምም፤ አውቃለሁም። የማውቀው እንዲህ ከጋዜጠኞች ጋር በመገናኘቴ ነው። የእኔ በዘጋቢነት፣ ጋዜጣ አዘጋጅነት ወይም ሪፖርተርነት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ የሚድያ ዓለም ውስጥ የራስን ሐሳብ በነጻነት መስጠትም በራሱ አንድ ተሳትፎ ነው። እንደበፊቱ አዘጋጅና አሳታሚ ሆኖ መሥራት ላይ ፍላጎቱ አለኝ። ግን መቼ እና የት ቦታ ላይ ነው የሚለው ላይ ብዙ የሚያሳስቡኝ ጉዳዮች አሉ።

የአገሪቱ ሁኔታ ሳይሆን በግል የቤተሰብ በርቀት መገኘት አንዱ ነው። ጠቅልሎ ወደ አገር ቤት መምጣትን በተመለከተ ውሳኔ ላይ አልደረስኩም። “በምን መልኩ፤ እንዴትና ስለ ምንድን ነው የምሠራው?” የሚለውም ውሳኔ የሚፈልግ ነው። እንደ አንድ የሚድያ ሰው ማበርከት የሚገባኝን ለማበርከት እሠራለሁ፤ አሁን እዚህ ያለኝ አጭር ጊዜ ነው፤ እዛም ሆኜ ለመሥራት ሐሳብ አለኝ። ግን አገሬ ውስጥ እሳተፋለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here