ረቂቅ አዋጁና የፓርቲዎች እሰጣ ገባ

0
986

የሰሞኑን መነጋገሪያ ባስ ሲልም መጨቃጨቂያ ከሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች መካከል አንዱ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ነው። በተለይ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ጉልህ የሚባል የልዩነት ድምፆች ተሰምተዋል፤ ሮሮዎችና ውግዘቶችም እንዲሁ።

የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ከረቂቅ ሕጉ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ እና የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ምርጫ ውድድር በሚገቡበት ወቅት በጊዜያዊነት ከመንግሥት ሥራቸው መልቀቅ አለባቸው የሚሉት ኹለት አንቀፆችን በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምላሽ፣ የምሁራንን አስተያየቶች እንዲሁም የአገራትን ተመክሮ አካቶ በሐተታ ዘማለዳ አጠናቅሯል።

የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለኹለት ከፍሎ በሐሳብ እያፋጨ ይገኛል። ሐምሌ 18/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱም በረቂቅ ሕጉ መሻሻልና መካተት አለባቸው በተባሉ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች መክረዋል። በዕለቱ አበል ሳይከፈለን አንሰበሰብም የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጨምሮ ስብሰባውን ረግጠው የወጡም ነበሩ።

በውይይቱ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በእጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ፣ የምርጫ ሒደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደሞዝና ጥቅማ ጥቅማቸውም እንደማይከበር በሚዘረዝረው ረቂቅ ሕግ አንቀጽ 33 ላይ፣ እንዲሁም አገር ዐቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 10 ሺሕ፣ የክልል ደግሞ 4000 መመስረቻ ፊርማ ያስፈልጋል በሚለው ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።

ሰላሳ ሦስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅርቡ በተቋቋመው የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተዘጋጅቶ የቀረበው የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ይዘቱ የዜጎችን የመደራጀት፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የሚገድብ በመሆኑ ከመጽደቁ በፊት ተመልሶ ለውይይት መቅረብ አለበት ሲሉ በሰጡት መግለጫ ላይ ረቂቅ ሕጉን ተቃውመዋል። ከቀናት በኋላም ሌሎች 27 ፓርቲዎች ተመሳሳይ መግለጫ አውጥተዋል።

ፓርቲዎቹ ረቡዕ፣ ሐምሌ 24/2011 በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ቢሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ ሕጉ ላይ ውይይት አድርገንበት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን የቀረበው ግን ከተወያየንበት ውጭ የሆነና የማናውቀው ሕግ በመሆኑ በምርጫ ቦርድ ክህደት ተፈጽሞብናል ብለዋል።

ፓርቲዎቹ እንዳሉት፣ የተዘጋጀው ሕግ ነባር የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያከስም፤ አዳዲሶችም እንዳይታሰቡ የሚያደርግ አፋኝ ሕግ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ የሚወዳደሩ ከሆነ የ6 ወር ደሞዛቸው ሳይከፈላቸው መደረግ ይኖርበታል የተባለውም ተገቢ ያልሆነ ነው በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ተግባራዊ ይሁን ከተባለ ግን መጀመር ያለበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሆኑን መንግሥት ሊያረጋግጥ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል። መንግሥት አጠቃላይ የምርጫ ስርዓቱን አሻሽላለሁ በሚል ቃል የገባውን ነገርም ከመተግበር መቆጠቡን ያሳሰቡት ፓርቲዎቹ፣ ይህ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለሥልጣናት በበኩላቸው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ካደን” በማለት ያሰሙትን ወቀሳ አጣጥለውታል። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ በአዲስ መልክ የተደራጀው ቦርዳቸው የማንም “አሽከር” መሆን አይችልም።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ እንዳሉት፣ ቦርዱ ተቃዋሚዎችን፣ ገዢውን ፓርቲንም ሆነ አገርና ሕዝብን በገለልተኝነት የሚያገለግል ተቋም ነው። ተቃዋሚዎች በረቂቅ ሕጉ ተካትቷል ያሉትን ያልተስማሙበትን ሐሳብ በዝርዝር እንዲያቀርቡም ምክትል ሰብሳቢው አሳስበዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ረቂቅ ሕጉን ሲቃወሙ በኹለት መልኩ እንደሆነ ሲነገር ይደመጣል። ተቃውሞውን ከሚያሰሙት መካከል አብዛኞቹ፣ የፓርቲያቸው ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የተገነዘቡት ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች በአንድ ግለሰብ የሚመሩ የቤተሰብ ፓርቲዎች መሆናቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጭምር ይነገራል። ከቤተሰቦቻቸው ውጪ አባል ስለሌላቸው የተባለውን መስፈርት ማሟላት ለእነሱ ከባድ ነው። ሌሎቹ ደግሞ መስፈርቱን ጠብቀው የተደራጁ ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች አንቀጹን በኹለት መንገድ ሲቃወሙ ይደመጣል። አንደኛው እነሱ የሚወዳደሩበት ክልል ውስጥ የሚገኘው ገዢ ፓርቲ፣ አባላት ለመመልመል አይደለም በክልሉ ገብተው በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ፈተና ስለሆነባቸው የደኅንነት ሥጋት አለብን የሚለው ነው። ኹለተኛው፣ ረቂቅ ሕጉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከተስማሙበት ውጪ የቀረበ በመሆኑ፣ ከቦርዱ ጋር እንደገና መምከር አለብን የሚል ነው። የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልምድ፣ አቅም፣ ባሕልና ጥንካሬ የኋላ ታሪክ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ስለመሆኑ በርካታ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

ፓርቲና ምርጫ በኢትዮጵያ
በ1983 በነበረው የሽግግር ወቅት ውዥንብር የበዛበት ስለነበር የነበሩት ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው ሥልጣን ቢከፋፈሉም ቅሉ ከፓርቲ ብዛትና የተለያየ ሐሳብ ካላቸው ቡድኖች ተሳትፎ አኳያ ግን፣ እንደ ሽግግር መንግሥቱ ያለ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ተፈጥሮ አያውቅም ማለት ይቻላል የሚሉ አሉ። በእርግጥ እነኢሠፓ፣ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ባለመወከላቸው እንዲሁም፣ እነ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጥለው በመውጣታቸው፣ እነ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) በመገለላቸው ጎደሎ ነበር።

በቀጣይ በተደረጉት አምስት ምርጫዎችም፤ በንጽጽር ከ1997ቱ ምርጫ በስተቀር፤ ተስፋ አስቆራጭ፤ የሕዝቡን ፍላጎትና ምርጫ ግምት ውስጥ ያልከተቱ ምርጫዎች ከመካሔዳቸውም ባለፈ፣ ሕዝቡ ተስፋ የሚያደርግባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጭጨውና ጠፍተው ለዓመታት መዝለቃቸውን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ።

ዳዊት ዓለሙ በጀርመን የ“University of Passau Governance and Public Policy” ድኅረ ምረቃ ተማሪ ናቸው። ዳዊት፣ የፖለቲካ ፓርቲ እሳቤና ተሞክሮ የአገራችን የፖለቲካ ባሕል ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ የተመሰረቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ሊያስብል በሚችል መልኩ የመደራደር አቅማቸው በጉልበት ላይ፣ ወይም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው። ይህም በመሆኑ በአገራችን ደካማ ወይም ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የራቀው ፖለቲካዊ ባሕል እንዲሰራፋ ሆኗል ሲሉ መጋቢት 12/2008 በታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በጻፉት መጣጥፍ ላይ አትተዋል።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው የሰው ኀይል አቅም በጣም ትንሽ መሆኑን የሚያስረዱት ዳዊት፣ አንደኛ፣ ተምሯል ከሚባለው አጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አንጻር ሲታይ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ሰው እጅግ በጣም አናሳ ነው። ኹለተኛ፣ ከፍተኛ አመራሮች መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ፓርቲዎች ሲሰነጠቁ ከፖለቲካ ትግሉ የሚርቀው ከኹለቱም ወገን ከቀረው የሰው ኀይል አንጻር በጣም ከፍተኛው ነው። ይህም የሚታየው ፓርቲዎች ከተሰነጠቁ በኋላ እንደቀድሟቸው ለመሆን አለመቻላቸው ላይ ነው። ሦስተኛ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአብዛኛው አቅምና እውቀት ላይ ሳይሆን በጥቅመኝነት (Patronage) ላይ የተመሰረቱ ስለሆነ መካከለኛ አመራሮቹ ደካማ አቅም ያላቸው ይሆናሉ። በአባላት ደረጃም ቢሆን የሚታየው እውነታ የሰው ኀይል ልማት ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸው አነስተኛ አቅም ነው።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት
መሰንበት አለሙ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ናቸው። ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀትና አሠራር በጣም ደካማ ነው ብለው ያምናሉ። በአብዛኛው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ግልጽነት የጎደለውና የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን ከማሳካት ይልቅ የከፍተኛ አመራሮችን ተክለ ስብዕና በሚያጎላ መልኩ የሚቀረጽ ነው የሚሉት መሰንበት፣ ለዚህም የአብዛኛዎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥምና ፖለቲካዊ ፕሮግራም ጎልቶ ከመውጣት ይልቅ፣ የመሪዎች ሥም በስፋት መታወቁን እንደማሳያ ያቀርባሉ። ይህም በመሆኑ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣም ምስጢረኛነት የበዛው አሠራር፣ የገነነ ማዕከላዊነትና ጥብቅ ከላይ ወደ ታች አደረጃጀት እንዲሁም፣ ግልጽነት የሚጎላቸው የውስጥ አሠራር ድንጋጌዎች ያሏቸው በመሆናቸው ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ባሕል የጎደላቸው መሆናቸውን ያብራራሉ። በዚህም የተነሳ ተራ አባሎቻቸውንና ዜጎችን በተለምዷዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሥራዎች በሚባሉት ውስጥ የማያሳትፉና በማኅበራዊ መሰረቶቻቸው ከሞላ ጎደል አየር ላይ የተንሳፈፉ ናቸው ሲሉ ያክላሉ።

እንደመሰንበት ገለጻ፣ ፓርቲዎቹ እርስ በራሳቸው ያላቸው ድርጅታዊ ግንኙነት ሻካራና በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ በአብዛኛው ከገዢው ፓርቲ ጋር ባላቸው የመገዳደር ሒደቶች ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም። ይህም የሚያመላክተው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ አጀንዳ ቀርጸው ሕዝቡን በማስተባበር ገዢውን ፓርቲ የማስገደድ አቅማቸውን መገንባት አለመቻላቸውን ነው።

“ነጋዴ ተቃዋሚዎች”
የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ፣ የአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር የተባሉ ሰዎች በቂ ክፍያ ካልተከፈላቸው ሦስትና አራት ፓርቲ እስከ መቀያየር የደረሱ፤ ስድስትና ሰባት ፓርቲ ውሰጥ ገብተው መታወቂያ ያላቸው ናቸው። ከምርጫ ቦርድ በሚወስዱት ገንዘብ የተለያዩ ሰዎችን ከተለያየ ቦታ በገንዘብ ይገዙና ለዛው ሰሞን ሥራ ብቻ ምርጫው እስኪያልቅ ያሰማሩዋቸዋል፤ የቀን አበል ወጪ እየከፈሉ።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው፣ እነዚህ “ነጋዴ ግለሰቦች” ወደ ፓርቲው የሚመጡት ለምርጫው ሰሞን ሥራ ብቻ እየተከፈላቸው ነው። ሙሉጌታ እንደሚገልጹት፣ ግለሰቦቹ በየመሸታ ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ነን በሚል ዲስኩር ሲያሰሙ ሰክረው የሚያመሹም ሆድ ይፍጀው እንደሚባለው ብዙ ናቸው። አይደለም ሕዝብን ወክለው አገር ለመምራት የተገለገሉበትን ሒሳብ የማይከፍሉ፤ ራሳቸውንም በሥነ ምግባር መምራትና ማስተዳደር የተሳናቸው ናቸው።

ኢሕአዴግ በተቃዋሚነት ሥም የሰጣቸውን ቢሮ ያከራዩ፤ በሕዝብ ሥም የሚነግዱ “ጩሉሌዎች”ም አሉ ይላሉ ሙሉጌታ። በእዚህ ጨዋ ሕዝብ ሥም ሊቀልዱበት አይገባም። ሕዝቡ እያንዳንዳቸውን ፈልፍሎና አጣርቶ ያውቃቸዋል ሲሉም ያክላሉ።

እንደ ሙላቱ ገለጻ፣ ትላልቆቹ ሰዎች ለምርጫው ሥራ ተብሎ በወሰዱት ገንዘብ 90 በመቶ የሚሆነውን ለራሳቸው የግል ጥቅም ያውሉታል። ንግድ ይከፍታሉ፤ መኪና ይለውጣሉ፤ የሌላቸውም መኪና ይገዛሉ፤ ሌሎችም መኪና ይነግዳሉ። ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ቢሠሩ ለመንግሥትም ለሕዝብም ይጠቅሙ ነበር። ተቃዋሚ የመሆን ብቃቱና ምክንያታዊነቱም የላቸውም።

የፖለቲካ አመራሮቹ እንደሚሉት፣ ጥቂት ጠንካራዎች መኖራቸው ይታወቃል። አይደለም አገርና ሕዝብ ለመምራትና ለመወከል የራሳቸውን ድርጅት ፕሮግራም አጥርተው የማያውቁም አሉ። አስረድተው ለመከራከር የማይችሉ፣ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ብቁ ያልሆኑ፣ ፖለቲካ ምን እንደሆነ በቅጡ ለይተው የማያውቁና በተቃዋሚ ፖለቲከኛነት ሥም ያሉ እንደ ንግድ ሥራ ቢዝነስ ያደረጉት ብዙ ናቸው። በዛው ልክ ብስሎችና አስተዋዮችም አሉ። ሰክነው የሚያዩ በስክነት የሚከራከሩ።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴት) ለአዲስ ማለዳ በላከው ጽሑፍ፣ በአገራችን ካሉት “የተመዘገቡ ድርጅቶች” ውስጥ ብዙዎቹ ቀደም ሲል ኢሕአዴግን አጅበውት እንዲጓዙ የፈለፈላቸው ስለሆኑ እነርሱን ማስወገድ ከፈለገ ኢሕአዴግ አሁንም በአንድ ቀን ሊያደርገው የሚችለው ቀላል ተግባር ነው ብሏል።

የረቂቅ ሕጉ አከራካሪ አንቀጾች
የፓርቲ መመስረቻ ጉዳይ
ሐምሌ 18/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሕግ፣ የፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ጋር በተደረገው ውይይቶች ላይ አለመግባባቶች ተከስተው ነበር።

አገር ዐቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 10 ሺሕ መመስረቻ ፊርማ ያስፈልጋል የሚለውን አንዳንድ ፓርቲዎች በተጠቀሰው ቁጥር ልክ አባላትና ደጋፊ ፊርማ ማሰባሰብ ያስቸግረናል በማለት ተቃመውታል። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው፣ አንድ መንግሥት ለመመስረት የሚወዳደር አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ የተጠቀሰውን ቁጥር ደጋፊዎች ማሰባሰብ መቻሉ አስፈላጊና ጫና የማያሳድር፤ ነገር ግን ፓለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ማኅበረሰባዊ መሰረት ለማስፋት የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል። ከ100 ሚልዮን በላይ ዜጎች ባለበት አገር፣ አገር ዐቀፍ ፓርቲ ለመሆን 10 ሺሕ የደጋፊ ፊርማ ማሰባሰብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫ ቦርድን ሐሳብ የሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አልጠፉም። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አንዷለም አራጌ ለፋና ቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት ፓርቲ ለመመስረት የቀረበው ቁጥር የተጋነነ አለመሆኑን ያምናሉ። የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ደጋፊንና ሕዝብን ይዞ እንደመሆኑ መጠን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላለበት አገር ይህን ያህል ተከታይ ማቅረብ የሚከብድ አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ ትዴት፣ በአንዷለም አሳብ አይስማማም። አሁን የተረቀቀው “ማሻሻያ“ አዳዲስ ድርጅቶች በያዙት ሐሳብ ዙርያ፣ ከትንሽ የአባላትና ደጋፊዎች ቁጥር ተነስተው እንዲያድጉ የሚያበረታታ ምኅዳር የሚፈጥር ሳይሆን፣ ገና ከጅምሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ከፊታቸው እንዲደቀን ያደርጋል ሲሉ ይሞግታሉ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ በላኩት ጽሁፍ፣ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ በሕጉ ውስጥ የተጠቀሰው 10 ሺሕ መሥራች አባላት ቅድመ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠር አባል አለኝ ከሚል ገዢ ፓርቲ ጋር ትርጉም ያለው ፉክክር አድርገው ሥልጣን ለመያዝና ተቋማዊ ሥራ ለመሥራት የሚፈልጉ ፓርቲዎችን የሚያሳስብ ነው ብለን አናምንም ብለዋል፡፡

የትዴትን ሐሳብ የማይቀበሉት ሙሉጌታ፣ አንድ ፓርቲ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ፣ ዐሥር ሺሕ አባል ከሌለው ፓርቲ ለመባል እንደሚያስቸግር በማውሳት፣ በተለይ ኹለትና ከዛ በላይ ዓመታትን ያስቆጠሩ ፓርቲዎች ይህንን እንደ አጀንዳ ማቅረብ እንደሌለባቸውና በቆይታቸው ይህንን ያህል ተከታይ ማፍራት አለመቻላቸው ድክመታቸውን የሚያሳይ መሆኑን ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር)፣ በየትኛውም ዓለም በፖለቲካ ውስጥ ልዩነት አለ ይላሉ። በኢትዮጵያ እኛ ያልነው ካልሆነ የሚለው ብሂል ተደጋግሞ ይሰማል የሚሉት መምህሩ፣ ከሌላ አገር ተሞክሮ ተወስዶበት፣ ራሳቸው ፓርቲዎቹ መክረውበት የተወሰነውን ውሳኔ አልቀበልም ብሎ ማለት ውሃ የማያነሳ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ማንኛውም ሕግ ሲወጣ ሁሉንም ሊያስደስት እንደማይችል ያወሱት ዮናስ፣ አብላጫውን ካስማማ ተግባራዊ ይሆናል ሲሉ አክለዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀመንበር አብዱል ቃድር አደም (ዶ/ር) አስታራቂ ሐሳብ ያቀርባሉ። አንድ ፓርቲ ለመመስረት የቀረበው ቁጥር የተጋነነ አይደለም የሚሉት አብዱልቃድር፣ ነገር ግን ከፓርቲዎቹ የሚቀርቡት ጥያቄዎችና ሐሳቦችን አድምጦ ምርጫ ቦርድ ለውይይት በቂ ጊዜ መያዝ እንዳለበት ያስረዳሉ። ከፓርቲዎቹ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች አሸናፊ ሐሳቦች ጎልተው ስለሚወጡ፣ ያኔ አሸናፊውን ሐሳብ ይዞ መውጣት አያስቸግርም ሲሉ ይመከራሉ።
በተለያዩ የደኅንነት ሥጋት ችግሮች ሳቢያ፣ የተባለውን ቁጥር ማሟላት የማይችሉ ፓርቲዎችም ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የመንግሥት ሠራተኞችን ደሞዝ የሚከለክለው አንቀጽ
የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ምርጫ ውድድር በሚገቡበት ወቅት በጊዜያዊነት ከመንግሥት ሥራቸው መልቀቅ አለባቸው የሚለው የሕጉ ክፍልም ከፍተኛ ውይይትና ክርክር ተደርጎበታል። ፓርቲዎች የመንግሥት ሠራተኞችን የምርጫ ፓለቲካ ተሳትፎ ይጎዳል በሚል የተቃወሙት ሲሆን የምርጫ ቦርድ ኀላፊዎችና የሕግ አርቃቂ ቡድኑ በበኩላቸው የመንግሥት ሥራ በፓለቲካ የተነሳ እንዳይጎዳ እንዲሁም በፓርቲና በመንግሥት መቀላቀል የተነሳ ይቀርብ የነበረውን የሀብት አጠቃቀም ችግር እና አቤቱታ ያስቀረዋል በሚል የሕጉ አካል መደረጉን ገልጸዋል።

የመንግሥት ሀብት ለምርጫ ሥራ እንዳይውል ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በመንግሥት ሥራ ሥም ለምርጫ ቅስቀሳ እና የፓርቲ ፖለቲካ ሀብት እንዳይውል በሚል የተዘጋጀ መሆኑን ማብራሪያ ሰጥተውበታል። የሲቪል ሰርቪስ አዋጁም በተመሳሳይ እገዳ እንደሚያስቀምጥም ተጠቁሟል።
የውድድሩን ፍትሃዊነት ከማረጋገጥ አንጻር መታየት የሚገባው ነው ያሉት ናትናኤል፣ በዕጩዎች መካከል የሚደረገው ፉክክር ውስጥ የመንግሥትን ንብረት እና ሥልጣን በመጠቀም ውጤቱ ላይ ሊኖር የሚችለውን ተጽዕኖ መገደብ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

የመኢአድ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሙሉጌታ፣ አዋጁ የመንግሥት ሠራተኛ በዕጩነት ለምርጫ ውድድር ሲቀርብ በጊዜያዊነት ከሥራ ገበታው መልቀቅ አለበት የሚለው አንቀጽ መሰረዝ እንዳለበት ተናግረዋል። አንቀጹ የተማረውን የኅብረተሰብ ክፍል ደሞዜን አጣለሁ በሚል ስሜት ከፖለቲካ ተሳትፎ ሊገድበው ይችላል ባይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተወካይ ደጀኔ ጣፋ፣ እንደተናገሩትም የመንግሥት ሠራተኛ በዕጩነት ሲቀርብ ደሞዝ አይከፈለው የሚለው አንቀጽ የተማረው ክፍል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቦታ እንዳይኖረው የሚያደርግ አካሔድ ነው።ይህም ወደ ምክር ቤቱ በሚመጣው ተመራጭ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን አክለዋል።

ብርቱካን በበኩላቸው፣ በግብር ከፋዩ የሚበጀተው በጀት ለምርጫ ቅስቀሳና ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል በዕጩነት የሚቀርብ የመንግሥት ሠራተኛ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ‘ደሞዝ አይከፈለውም’ ብለዋል። ይህም በሕዝብ ሀብት፣ ገንዘብና በተቋማት አደረጃጀት ላይ የተዛባ አስተሳሰብ እንዳይመጣ ከማገዙ ባለፈ የመንግሥት ተቋማት ተዓማኒና ለተቋቋሙለት ዓላማ ብቻ እንዲሠሩ በማድረግ መንግሥትና ፖለቲካን ለመለያየት ያስችላል ነው ያሉት።

የአገራት ተሞክሮ
ትዴት ለአዲስ ማለዳ በላከው የጽሑፍ ምላሽ አገሮች ፖለቲካ ድረጅቶች በሕጋዊነት ለመመዝገበብና ለመንቀሳቀስ የሚያስቀምጡት የአባላት መመስረቻ ፊርማ ወይም የደጋፊዎች ቁጥር አሁን አገራችን ውስጥ የተረቀቀው ሕግ ከሚጠየቀው እጅግ ያነሰ መሆኑን ያስረዳል። ትዴት፣ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት ሕንድ፣ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት የሚያስፈልገው የ100 ሰው ፊርማ መሆኑን፣ ፖላንድ አንድ ሺሕ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ኔፓል ዝቅተኛ ቁጥር የለም፣ ስዊድን 1 ሺሕ 500፣ ካናዳ 250፣ ጋና 210፣ ደቡብ አፍሪካ 500፣ ቤልጅየም 3050፣ ናይጀሪያ 500፣ ሱዳን 500 እንደሚጠየቅ አስረድተዋል ።
ከተጠቀሱት ሌላ የፓርቲዎችን ሕጋዊነት ለመስጠት እጅግ የተጋነነ ያባላት ቁጥር የሚጠይቁ አንድ ኹለት አገሮች
መኖራቸውን ጠቅሰዋል፤ ከእነርሱም ውስጥ አንዷ ኬንያ መቶ ሺሕ እንደሚጠየቅም በጽሑፉ ውስጥ ተካቷል።

ፍኖተ ነጻነት መጽሄት በሃምሌ 24/2004 ዕትሙ “ጋናዊ መሆን አማረኝ” በሚል ርእስ ባቀረበው ጽሁፉ እንዳስነበበው፣ ጋና በ2000 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ ቁጥር 574ን አወጀች። የዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 ቁጥር 1 ሀ፤ በዘር፣ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢና በሙያ ዘርፍ ተደራጅቶ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል። በዚህ የተነሳ በታኅሣሥ 1991 በተደረገው የመጀመሪያ የመድብለ ፓርቲ ብሔራዊ የምርጫ ውድድር ለመካፈል፣ በአወዳዳሪው የጋና ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የቀረቡት 23 የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

ከእነዚህ 23 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በሒደት በጋና የፖለቲካ መድረክ ላይ ጎልተው የወጡትና የጋናን የምርጫ ፖለቲካ መቆጣጠር የቻሉት ግን የሊበራል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ነው የሚባለው ኒው ፓትሪዮቲክ ፓርቲ (NPP) እና የግራ መሀል (center – left) ርዕዮተ ዓለም የሚያራምደው የብሔራዊ ዲሞክራቲክ ኮንግረስ (ኤን ዲ ሲ) ናቸው። ከ1992 ጀምሮ በጋና የተካሔዱትን ብሔራዊ ምርጫዎች በማሸነፍ የሥልጣን ወንበሩን የተፈራረቁበት እነዚህ ኹለት ፓርቲዎች ናቸው።

እነዚህ ኹለት ፓርቲዎች ለዚህ የበቁት የሥልጣን መንበሩን ሲቆጣጠሩ ተፎካካሪያቸውን በማዋከብ እያዳከሙ፤ ወይም መሪዎቻቸውን በሰበብ አስባቡ እስር ቤት በማጎር እያፈረሱ ከቶውንም አይደለም። ይህን ለማድረግ ቢፈልጉም እንኳን በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው የጋና የፍትሕ ስርዓትና የዲሞክራሲ ተቋማት ዕድልም ቀዳዳም የሚሰጡ አይደሉም። እነዚህ ኹለት ፓርቲዎች በጋና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ይህን የመሰለ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉት የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ ከፍተኛ የማደራጀትና የማንቀሳቀስ ችሎታ ያለው ንቁ አመራር ባለቤቶች በመሆናቸው ነው። ጋናውያን ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ አባል በሆኑበት ወይም በሚደግፉት የፖለቲካ ፓርቲ የተነሳ አንዳች ዓይነት ችግር ይገጥመኛል ብለው መጨነቅ አቁመዋል።

የጋና የፖለቲካ ፓርቲዎችም የቢሮና የስብሰባ አዳራሽ ኪራይ ጉዳይ ጨርሶ የሚጨነቁበትና እንደ ቁም ነገር የሚያዩት ጉዳይ አይደለም። ይህ ሁኔታ መላ ጋናውያን በአገራቸው የፖለቲካ መድረክ በነፃነትና በሙሉ ፍላጎት ተካፋይ እንዲሆኑ ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል።

በኢኮኖሚያቸው ባደጉና በበለጸጉ ታላላቅ አገራት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣሊያ፣ ካናዳ፣ እስራኤል ወዘተ በቁጥር አነስተኛ ፓርቲዎች ነው ያሉዋቸው። በተለይም በአሜሪካን ኹለቱ ዋነኛና ግዙፍ ፓርቲዎች፤ ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት መካከል የሚደረገው ፉክክር ሁል ጊዜም ከአገራቸው አልፎ የዓለም ትኩረትን እንዳገኘ ነው

እንደመፍትሔ
አብዱልቃድር እንደሚሉት፣ የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ምርጫ ነው። የምርጫ ሥርዓቱንና የአመራረጥ ሁኔታውም ቢሆን እነዚህን መብቶች ለመተግበርና በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ የራሳቸው ተፅዕኖ ሊኖራቸው መቻሉ አያጠራጥርም። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 እንደተገለጸው ሥልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ ነው። የምርጫ መርሆችን በተመለከተ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 38 ላይ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ሁሉን ዐቀፍ፣ ሚስጥራዊ መሆን፣ በየጊዜው መካሔድ እንዳለበት አስቀምጧል። የምርጫ ሥርዓቱን ደግሞ አንደኛ-አላፊ የሚባለውን ሥርዓት (First-Past-The-Post) እንዲከተል በሕገ መንግሥት ተወስኗል።

አንዷለም ለፍና ቴሌቪዥን በሰጡት ምላሽ በበኩላቸው፣ የምርጫ ሥርዓቱ ፓርቲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን የዜጎች መብትን ሊያቀጭጭ የሚችልበት ሁኔታ ስላለ፣ የዜጎችን የፖለቲካ መብት የሚያሰፋና የሚያስጠብቅ የምርጫ ሥርዓትን ማስፈን ግድ ነው ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የፖለቲካ ስርዓት መመስረት ግድ መሆኑን ያሳስባሉ።
በኢትዮጵያ ባለቤት አጥቶ በግለሰቦች ዘፈቀዳዊ አሠራር ሲመራ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የራሱ የመንግሥት የፓርቲ ስርዓትም ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ መሰንበት ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here