“በእናቴ ልጠራ!”

0
885

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የቃቄ ውርድወት ወይም ውርድወት በጊዜዋ አድርጋቸው ከነበሩ ትግሎችና አቅርባቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል “በእናት ሥም እንጠራ” የሚለው አንዱ ነው። በጊዜው እርሷን የተከተላት ብዙ ሰው ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ፤ ነገር ግን በዓለማችን ይህን ጥያቄ ያነሱ ሌሎች ሰዎች ስለመኖራቸው ባናውቅም ውርድወት ግን በተገለጠልን የታሪክ መረጃ መሰረት ብቸኛዋ ናት።

ይህን መሠረት አድርጎ በጫንያለው በቀለች ወልደጊዮርጊስ የተደረሰው “የቃቄ ውርድወት” ትውፊታዊ ቴአትር ላይ፤ ደራሲውን ጨምሮ አዘጋጁ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ፤ እንዳነበባችሁት ከሥማቸውና ከአባታቸው ሥም መካከል ላይ የእናታቸውን ሥም አካትተው ነበር። ቴአትሩ ከመድረክ ከወረደም በኋላ በዚሁ ሥም መጠራታቸውን ቀጥለዋል።

እንደምናውቀው ዘርና ትውልድ በአባት ነው የሚቆጠረው፤ ይህ ለዘመናት ዓለማችን የተመራችበት ስርዓትና አሠራር ነው። የሰው ልጅ ደግሞ ተፈጥሮ አስለምዳው ሥምን እንዲሁም ዘመናት ተሻግሮ መኖርን አብዝቶ ይወዳል፤ ሁሉም በአቅሙ በቁጥር የተወሰነውን የዕድሜ ገደብ በሥም ተሻግሮ ሊቃኝ ይፈልጋል። ይህ ተዳምሮ ነው ወንድ ልጅ ሲወለድ እልል ተብሎ ሴት የተወለደች እንደሆነ ደስታው እንዲቀንስ ያደረገው።

በአንጻሩ ሴት ደግሞ ይህን አትጠይቅም። ለብቻዋ ንጉሥ ያሳደገች ብትሆን እንኳን፤ ንጉሡ አንድም በአባቱ አንድም በሥራው ይጠራ ይሆናል እንጂ፤ በእርሷ ሲጠራ አይታይም። አንዳንዴማ ከዚህም አልፎ እናት ራሷ በልጇ ስትጠራ እንሰማለን፤ “የእገሌ እናት!” ይባል የለ?

ምናልባት ተፈጥሮን የተረዳው የቀደመው ማኅበረሰብ፤ ሴት ልጅ የእናትነት ጸጋን ስለታደለች፤ ለማመጣጠን ሲል፤ ለወንዱ ደግሞ ሥም እንዲቆይለት ብሎ ይሆን? ብቻ ግን ሁሌም የእናት ሥም ገላጭ ከሚፈልገው ከዝርዝር የታሪኩ መዝገብ ነው የሚገኘው።

እኔ የምላችሁ ግን፤ የውርድወት ትግል ዛሬ ላይ ቢመጣስ? አባቶች አትቀየሙንና በእናታችን እንጠራ ብለን “ሆ!” ብንልስ? ነገሩ የሴቶች ጥያቄ ብቻ መስሏችኋል? አይደለም። ሁላችን በእናታችን ሥም ብንጠራ ታሪክ ሲቀየር በዓይናችን እናያለን። ዛሬ ዘርና ብሔር ቆጥሮ፤ የአባቱንና የአባቶቹን ሥም እየጠቀሰ የሚናከስ ሁሉ ጸጥ ይል ነበር።

ብዙዎች አንዱን ብሔር ተገንና “ጥላ” አድርገው ሌላው ላይ ድንጋይ የሚወረውሩ፤ በእርግጠኝነት ቦታ ቀይረው መገኘታቸው አይቀርም። ወይም ሁላችን ራሳችንን እንጠይቅ፤ በእናታችን ሥም ብንጠራ ኖሮ “ብሔር” የሚለው መጠይቅ ይቀየርለታል የተባለው አሁን የያዝነው መታወቂያ ላይ ያለው የብሔር ሥም ምን ይሆን ነበር? እሱን ነው ያልኩት! በእናት ሥም መጠራት የአገራችንንም ታሪክ ሊቀይር ይችላል።

ሊድያ ተስፋዬ
liduabe21@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here