የመጀመሪያው የሒሳብ አያያዝ ሶፍትዌር በ50 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ተግባራዊ ሊሆን ነው

0
354

በኢትዮጵያ በአምስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 50 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የታሰበው እና ለመጀመሪያ ጊዜ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሒሳብ አያያዝ እውን ለማድረግ ሥራ ተጀመረ። የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፤ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በትግራይ እና በቤንሻንጉል ብሔራዊ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 50 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ የሒሳብ አያያዛቸውን ለማዘመን በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ ሶፍትዌር በመሥራት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አያልሰው ወርቅነህ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው እንደገለፁት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከዚህ በፊት ይታይባቸው የነበረውን የተጋነነ የገንዘብ ብክነት ለማስቀረት፣ የሒሳብ አያያዙ ከዘመናዊነቱ ባለፈም ተጠያቂነትም እንዲሰፍን ለማድረግ የታሰበ ሲሆን የረጅም ጊዜ ዕቅድ ቢሆንም የማኅበራቱ አባላት ገንዘባቸውን በፈለጉበት ጊዜ የሚያንቀሳቅሱበት የአውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ መሳሪያ (ኤ.ቲ.ኤም) እንዲኖራቸው እንደ ግብ መያዙን ተናግረዋል። በግልፅ ጨረታ ወጥቶ የሶፍትዌር ሥራውንም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ እየሠራው እንደሚገኝ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሶፍትዌሩን ሠርቶ በማስረከብ በቀጣዩ ዓመት አዲሱን ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ስርዓቱን በተመረጡት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ተግበራዊ እንደሚደረግ ታውቋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ሃምሳ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ውጤታቸው ከታየ በኋላ በቀጣይ ደግሞ በቀሪ ክልሎች በሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ እንደሚተገበር ለማወቅ ተችሏል። የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባሕላዊና ሌሎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለሟሟላት እና በተናጥል ሊፈቱ ያልቻሏቸውን ችግሮች በጋራ ለማቃለል የሚል ሐሳብ በመሰነቅ ወደ የተመሰረተ መንግሥታዊ ድርጅት ነው።

አሁን በደረሰበት ደረጃ ከኻያ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ኤጀንሲው። 20 ሚሊዩን አባላትንም በውስጡ አቅፎ ይዟል። ከ85 ሺሕ በላይ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 388 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖችና 3 የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ተደራጅተው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረጉም ይገኛሉ ። የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ከተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች መካከልም ለአብነት ለመጥቀስ በግብርና ምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎች እና ግብዓቶች አቅርቦትና ስርጭት፤ በግብርና ምርት ግብይትና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር (በአግሮ ፕሮሰሲንግ)፤ በገንዘብ ቁጠባና ብድር እና በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይገኛሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘም የኅብረት ሥራ መኅበራቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በቋሚነትና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here