በ3.7 ቢሊዮን ብር አዲስ የአየር ትራንስፖርት ሊመሰረት ነው

0
621
  • የአክስዮን ድርሻው በመጪው ሶስት ወር ውስጥ መሸጥ ይጀመራል

አሜሪካን አገር በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመቀሌ ከተማ መቀመጫውን ያደረገ አዲስ የአየር ትራንስፖርት በ 134 ሚሊዮን ዶላር ለማቋቋም ማሰባቸውን ባሳለፍነው ሳምንት በፕላኔት ሆቴል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ኖርዝ ስታር የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የአየር ትራንስፖርት ኩባንያ መቀመጫውን በመቀሌ ከተማ ያደረገው በአዲስ አበባ ያለውን የአየር መጨናነቅ በመሸሽ እንደሆነ እና ባህር ዳር እና ድሬዳዋ ከተማ መቀመጫ ለማድረግ ታስቦ እንደነበርም የድርጅቱ መስራች መኮንን አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

‹‹በኢትዮጲያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ የንግድ መአከል ልትሆን እንደምትችል በመገመት መቀሌን መርጠናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መቀመጫውን ከአዲስ አበባ ውጪ ያደረገ የመጀመሪያው አየር መንገድ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹የአፍሪካ ነፃ የአየር ቀጠና በመከፈቱ የአቬሽን ኢንዱስትሪው መነቃቃቱ አይቀርም፣ ይንንም እንደመልካም አጋጣሚ እንጠቀምበታለን›› ሲሉ መኮንን ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ከሶስት አመት በኋላ መንገደኞችን ወደ ማጓጓዝ ስራ ይገባል የተባለው አክሲዮን ማህበሩ በቀጣይም በተለያዩ ደረጃዎች የእቃ ማመላለሻ፣ የባለሞያዎች ማሰልጠኛ እና የጥገና ክፍል ይኖረዋልም ተባሏል፡፡

የአየር ትራንስፖርት ማጓጓዣው ሊቋቋም የታሰበው በመጀመርያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻ ካደረጋቸው አገራቶች ውጪ ለመስራት እንደሆነም መኮንን ተናግረዋል፡፡ ይህም ለህብረተሰቡ ተጨማሪ የመዳረሻ አማረጭ ሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከአርትስ ቲቪ መስራቾች መሃል አንዱ የሆኑት መኮንን የአክሲዮን ድርሻው በመጪው ሶስት ወር ውስጥ መሸጥ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ስድስት የአየር ትራንስፖርት ማጓጓዣ አገልግሎቶች ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ አበርዲን ፣አቢሲኒያ ፣ ኢስት አፍሪካ ፣ ናሽናል እና ትራንስ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ትልቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን ከአንድ መቶ በላይ አውሮፕላኖች ባለቤት እና በቢሊዮን ዶላሮች የሚያተርፍ የመንግስት ልማት ድርጅት ነው፡፡

መጪው ሶስት ዓመታት ውስጥ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው ኖርዝ ስታር ሰባተኛው የአየር ትራንስፖርት ማጓጓዣ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here