በግጭቱ 19 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ
በሞያሌ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለፀ። ግጭቱ በመሬት ይገባኛል ቅራኔ መነሳቱ የታወቀ ሲሆን፤ የሠላም ሚንስቴር የሟቾች ቁጥር አለመታወቁን ጠቅሶ የፌደራል ጸጥታ ኃይል ጣልቃ መግባቱን አሳውቋል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ባወጣው መግለጫ የኦሮሚያ ታጣቂዎች በንጹሃን የሱማሌ ብሔር ተወላጆች ላይ ተኩስ ስለመክፈታቸው፣ በዚህም 13 ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል። ቢቢሲ የሞያሌ ወረዳ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ቦሮ ሆቃን ጠቅሶ እንደዘገበው በኦሮሚያ ወገን ስድስት ሰዎች ሲሞቱ 72 ደግሞ ቆስለዋል። በሱማሌ ክልል የደኅንነት አማካሪው ሸኑ ጎደኖ በበኩላቸው ከሱማሌ ወገን 13 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እና 30 መቁሰላቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
የሞያሌ ወረዳ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊው አሊ ጠቼ ግጭቱ በሱማሌ በኩል የመሬት መስፋፋት ፍላጎት በመኖሩ እንደተነሳ ሲገልፁ አቶ ሸኑ ደግሞ የግጭቱ መንስዔ በኦሮሞዎች በኩል የመሬት መስፋፋት ፍላጎት በመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ሁለቱ ሕዝቦች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች የኦሮሞ ተወላጆች ባንዲራ በመትከላቸው ‹‹በባንዲራ ንቀሉ አንነቅልም›› ሙግት ግጭቱ መነሳቱንም ጨምረው ገልጸዋል። በግጭቱ የአንድ ትምህርት ቤት ሁለት ክፍሎች እና የጤና ኬላ መቃጠሉም ተናግሯል።
ኦብነግ በበኩሉ የፌደራል መንግሥቱና የሱማሌ ክልል በአስቸኳይ ጣልቃ ገብተው እየደረሰ ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃት እንዲያስቆሙም በመግለጫው አሳስቧል።
አዲስ ማለዳ ከሠላም ሚንስቴር ታማኝ ምንጭ እንዳጣራችው የሰሞኑ ግጭት መነሻ በገብራ ሱማሌና ገብራ ቦረና ተወላጅ ሁለት ግለሰቦች ፀብ የተነሳ ሲሆን መልኩን ቀይሮ ወደ ጎሳ ግጭት መቀየሩ ታውቋል። ላለፉት አምስት ቀናት በነበረው ግጭት ግን የደረሰውን የሞትና አካል ጉዳት መረጃ ሚንስትሩ እንዳልደረሰው የተናገሩት ምንጫችን የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ እንዲገቡ ከረቡዕ ጀምሮ ትዕዛዘ መሰጠቱን ገልፀዋል።
በሞያሌ ተመሳሳይ ግጭት ሲቀሰቀስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በተለያየ ጊዜያት እያገረሸ ለሕይወት መጥፋት፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው የሞያሌ ችግር መነሻ ምንድን ነው ብለልን የጠየቅናቸው ምንጫችን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ምንጫችን በቀድሞው የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚንስቴር ሲሰሩ ጉዳዩን በቅርበት ይከታተሉት እንደነበር በመጥቀስ ያለፌደራል መንግሥቱ ዕውቅናና ይሁንታ በሞያሌ የሚገኙ የኦሮሚያና ሱማሌ ብሔሮች ‹ከአስፓልት ወዲያ የሱማሌ ከአስፓልት ወዲህ የኦሮሞ› የሚል የቦታ መካለል ውስጥ ስለመግባታቸውም አስረድተዋል። ይህ የነዋሪዎች ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ የፌደራል መንግሥቱ ከሚለው በጋራ የመኖር መርህ የሚጣረስ መሆኑንም አንስተዋል። አሁን ላይ ‹‹አንድ ሰው አስፓልት ሲያቋርጥ ሊገደል ይችላል›› ያሉት ምንጫችን በአካባቢው ስርዓት አልበኝንት እየነገሰ መምጣቱን አመልክተዋል።
‹‹ሱማሌዎች ቦታ እያስፋፉ ነው የሚል ዕምነት ያላቸው የኦሮሚያ ተወላጆች ሱማሌ በሞያሌ ዳዋ ዞንን ለመመስረት ማቀዳቸው ተገቢ አይደለም በሚል ኦሮሞዎች ሞያሌ የኦሮሚያ እንጂ የሱማሌ አይደለም›› በሚል መሠረታዊ ቅራኔ መኖሩንም ምንጫችን አክለዋል።
ላለፉት ወራት መንገድ በመዝጋት በኦሮሚያ በኩል ወደሱማሌ የሚሄዱ ዕርዳታዎች እንዳያልፉ እየተደረገ መሆኑን የነገሩን ታማኝ ምንጫችን በአንድ የበጎ አድረጎት ድርጅት ወደ ሱማሌ ሲጓጓዝ የነበረ የመድኃኒት ድጋፍ ኦሮሚያ ውስጥ በግዴታ እንዲራገፍ ተደርጎ ወደመጋዘን እንዲገባ መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ስለጉዳዩ መብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠቱ የቢሯቸው ኃላፊነት እንዳልሆነ በመጥቀስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ከኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም።
አብነግ ባወጣው መግለጫ ሁሉን አካታች የሆነ የእርቅ ሂደት እንዲጀመር እና ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ወደ ሠላማዊ ግንኙነት እንዲመለሱ ጠይቋል።
ከዚህ ቀደም መሠረታዊ ችግሮቹን ለመለየትና እርቅ ለማውረድ የፌደራል መንግሥቱ አልሰራም ወይ ያልናቸው የሠላም ሚንስቴር ምንጫችን እንዳሉት ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ማወያየት ሲጀመር የግጭት አነሳሽነትን ተግባር አንዳቸው ባንዳቸው እያሳበቡ መስማማት ላይ ሊደርሱ እንዳልቻሉ ነግረውናል። በሠላም ሚንስቴር ስለታቀደው መፍትሔ የጠቅናቸው ምንጫችን ተቋሙ ገና በመደራጀት ላይ መሆኑን በመጥቀስ አሁን ላይ ሚንስቴሩ በስሩ ለሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ግጭቶችን ፈጥኖ እንዲያስቆምና አጥፊዎችን ሕግ ፊት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ስለመሰጠቱ አረጋግጠዋል።