የኩላሊት ህመምተኞች ማኅበር ለዘጠና ሦስት የኩላሊት ህሙማን የነፃ የኩላሊት እጥበት እንዲያገኙ ዕድል ማመቻቸቱን አስታወቀ። ማኅበሩ ‹‹ከራስ ቆርሶ ለራስ ማዋጣት›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ባንኮች የሒሳብ አካውንት በመክፈት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ በርካታ የግል ባንኮች ሰራተኞች ከደሞዛቸው በማዋጣት ማኅበሩን እያገዙ ይገኛሉ።
ማኅበሩ ከኩላሊት ሕመም ጋር በተያያዘ በየጎዳናው ላይ የሚደረገውን የገቢ ማሰባሰቢያ ለማስቀረት ከበርካታ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እያሰባሰበ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም መሰረት ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ መድኅን ድርጅት እና የአዲስ አበባ ከተማ አንበሳ አውቶብስ ድርጅት የማኅበሩ ዋነኛ ደጋፊዎች እንደሆኑም ታውቋል።
ነፃ የኩላሊት እጥበት ሕክምናው በዳግማዊ ሚኒልክ እና በዘውዲቱ ሆስፒታል የሚከናወን ሲሆን በአንዳንድ የግል ሆስፒታሎችም እንደሚከናወን ማኅበሩ ይፋ አድርጓል። ባሳለፍነው ረቡዕ ነሐሴ 8/2011 የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዘውዲቱ ሆስፒታል ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ኹሉም የአቅሙን በመደገፍ የማኅበሩን ህልም ለማሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል
ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011



