የሱማሌ ፖለቲካ ትናንት፣ ዛሬና ነገ!

0
774

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረ ወዲህ ያለውን የሶማሌ ክልል የፖለቲካ ታሪክ የሚዳስሱት ይነገር ጌታቸው፣ የ12ቱን የክልሉን ርዕሳነ ብሔራት የሥልጣን ጉዞም አካትተዋል። በተለይም የመሪዎች መጨረሻ ከሌሎች ክልሎች በተለየ እስር የሆነበትን ምክንያት ከማዕከላዊው መንግሥት ጣልቃ ገብነት አንጻር እንዲሁም በክልል ካሉ የድንበር ግጭቶች ጋር በማያያዝ ይህንን መጣጥፍ አሰናድተዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ሥር ያልተለመዱ ኹነቶች የየዕለት ዜና ከሆኑ ውለው አድረዋል። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ከፊሎቹ ትናንት ያልነበሩና የሰርክ ሕይወታችንን የሚፈታተኑ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የትናንት ታሪካችን አካል ሆነው የመርሳት ደለል ተጭኗቸው የኖሩ ናቸው።

ከሕዝብ መልክ ይልቅ በአራት ኪሎ አምሳል የተጠፈጠፈው የሱማሌ ክልል ፖለቲካን በተለይም ጎዴና ጅግጅጋን የተንተራሰው ሽኩቻ አሁንም ቢሆን ከሰፌድ ላይ ሩጫው ፈቀቅ አለማለቱን ማንሳት ይቻላል። ይህንንም ትችት መሰረት የሚያስይዙ ኹለት መከራከሪያዎችን አንስቶ ማብራራቱ አግባብ ይሆናል።

የምኒልክ ቤተ መንግሥት ቡራኬ!
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በፖለቲካ ሕይወታቸው ሁሌም የሚገርማቸው ጉዳይ የሱማሌ ፖለቲከኞች በነሐሴው የሕገ መንግሥት ጉባዔ ላይ መሳተፍ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ ግርምት ከኹለት ነገሮች የሚቀዳ ነው። የመጀመሪያው የሱማሌ ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ በመንፈስ ከራቁ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩና ለኦጋዴን ነጻነት ሲፋለሙ የኖሩ ከመሆናቸው ጋር ይተሳሰራል።

ኹለተኛው የአግራሞታቸው ምንጭ በሱዳን አደራዳሪነት የሱማሌ ፖለቲካ ኀይሎች በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሲጠየቁ ያሳዩት እምቢተኝነት ነበር። የወቅቱ የኦብነግ ሊቀመንበር ሼክ ኢብራሂም አብዱላሂ ማኽ የሽግግር ቻርተሩን እንዲቀበሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ቻርተሩ ለኢትዮጵያውያን እንጂ ለኦጋዴን ሕዝብ ምኑ ነው?” ማለታቸው ከላይ ላነሳነው መደመም ጉልበት እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም።

ይህ አጋጣሚም ኢሕአዴግ ገና ከጅምሩ በሱማሌ ክልል ላይ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሔድን እንዲከተል በር ከፍቷል። በቆዳ ስፋትም የሃገሪቱን አንድ ሦስተኛ ከመገንጠል ለማዳን በሚል ስሌት ለአራት ኪሎ ታማኝ የሆነን ሰው ወደ ሥልጣን ማምጣት ተለምዷዊ ሆኗል።

በዚህ መነሻም በአቶ መለስ ፊታውራሪነት በሱማሌ ሕዝብ አነስተኛ ቅቡልነት ያለውን የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር ሥያሜውን ወደ የምዕራብ ሶማሊያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ምሶዴፓ) በመቀየር በሽግግሩ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል። ምሶዴፓ በነሐሴው ኮንፈረስ ላይ ኹለት ወንበር ያገኘ ሲሆን የኢሳና የጉረጉኸ ፖለቲካ ድርጅቶችም ክልሉን በመወከል ተጨማሪ ወንበር ተችረዋል።

ይህ ተሳትፎ ግን 13 ያህል ጎሳዎች ላሉት የሱማሌ ክልል በቂ የሚባል አልነበረም። ይሁን እንጂ የሱማሌ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄው ዕውን ሆኖ በ1985 የወሰን ማካለል ሥራ ሲጀመር ኦብነግ አገር ውስጥ ገብቶ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው አሳወቀ። በወቅቱ የድርጅቱ ቃል አቀባይ የነበረው አብዱላሂ ሞሐመድ ሰዒድ ወደ አዲስ አበባ መምጣትም በኢሕአዴግና በሱማሌ ፖለቲካ ልኂቃን መካከል ያለውን ልዩነት ለማርገብ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል። ኦብነግ በፌደራሊዝሙ ሐሳብ ላይ እንደሚስማማና በተግባር አይቶት ከመዘነ በኋላ ከኢሕአዴግ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑን መግለጹም አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ነው ተባለ። በኢሕአዴግ ሰፊ ድጋፍም በጥር 1985 ጋርቦ ላይ ብሔራዊ ኮንፈርስ አካሒዶ በይፋ ሥራ ጀመረ።

ከኮንፈረሱ በኋላም ኦብነግ አገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም የድርጅቱ መሪ የነበረው ሼክ ኢብራሂም ግን ከኢሕአዴግ ሰዎች ጋር መገናኘት አልፈልግም ማለቱ የሚያስገርም ነበር። እንዲህ ያለ ተቃርኖ ያሳሰበው የሽግግር መንግሥቱም ኦብነግን በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለ ጉዞውን ቀጠለ። መንግሥት አልባ በሆነችው ሶማሊያ በኩል መውጫ መግቢያውን ያደረገው የሪያድ ዩንቨርሲቲ መምህሩ ሼክ ኢብራሂምም በጊዜ ሒደት ዓላማው ግልጽ እየሆነ መጣ
የሽግግር መንግሥቱን አለሁ እያለ ለነገ ትግሉ የሚረዳውን ወታደራዊ ኀይል ማደራጀት ጀመረ። በኹለት ቢላዋ የሚበላው የኦብነግ አመራር በ1987 በተካሔደው ምርጫ ተሳትፎ በማድረግ ከፍተኛ ድምጽን አገኘ። ኦጋዴን በሚል የሚጠራውን አካባቢም ሱማሌ ክልል ብሎ ለመጥራት መወሰኑን አስታወቀ።

የሽግግሩ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔ በድሉ ማግስት ወደ ድሬዳዋ አቅንተውም ከዚህ በኋላ ሱማሌ ኢትዮጵያዊ ዜግነት አግኝቷል ሲሉ ተደመጡ። የክልል መንግሥት ምሥረታ ውስጥ የገባው ኦብነግ ድሬዳዋን ዋና መቀመጫ አድርጎ ቢመርጣትም ድሬዳዋ ላይ የኦሮሚያ ይገባኛል ጥያቄ በመነሳቱ ለጊዜው ወደ ጎዴ እንዲዛወር ተደረገ። ለአፍታ በከፍታ ላይ የነበረው የኢሕአዴግና የኦብነግ ወዳጅነት ዳግም የረገበውም በዚህ ሰሞን ነበር።

የምስረታ ሂደቱ ላይ ተቃውሞ ያነሱት ሼክ ኢብራሂም ክልሉን ከመምራት በማፈግፈጋቸው አብዱላሂ መሐመድ ሰዒድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ተመረጡ። ይህንንም እንደመልካም አጋጣሚ የወሰዱት አቶ መለስም አብዱላሂን ወደ አዲስ አበባ አስጠርተው ከጎናቸው እንደሚሆኑ ነገር ግን የኦብነግ የነፃ አውጪነት ስያሜ ወደ ፓርቲነት እንዲቀየር አሳሰቡ።

ክልሉ ከኦጋዴን በተጨማሪ ሌሎች ጎሳዎች እንዳሉበት በማሳሰብም የሥሙ መቀየር ላይ ድርድር እንደሌለ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ። ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳደር የስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ወታደራዊ ኀይሉ በእጃቸው ያለው እና ፍላጎታቸው በቅጡ በማይታወቀው በጠቅላዩ ትእዛዝ ስር መሆኑ፥ ከሼክ ኢብራሂም ረጅም እጅ ጋር ተዳምሮ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸው ነበር።

ይህንን ምክንያት በማድረግም ክልሉን ለመገንጠል ሲንቀሳቀሱ ነበር በሚል ለእስር ተዳረጉ። ክልሉም ዳግም ከኢሕአዴግ እጅ መውጣት ጀመረ። ይህ ያስደነገጣቸው የምኒልክ ቤተ መንግሥት ሰዎች የዚያድ ባሬ ጦር ኀይል አብራሪ የነበሩትን ሀሰን ጀር ኸለንን በረጅም ገመድ አስረው ሊሾሟቸው ፈለጉ። ነገር ግን የሀሰን የሥልጣን ዘመን ከቀደመውም የከፋ ሆነ፣ ኦብነግ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠኝን የመገንጠል መብት የመጠቀም መብት አለኝ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄን ለኢሕአዴግ ማሰማት ቀጠለ።

ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ከሦስት ወራት በኋላም ጅግጅጋ ላይ በክልሉ ምክር ቤት በኩል የመገንጠል ጥያቄን በይፋ አጽድቆ ለፌዴራል መንግሥቱ ላከ። በወቅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የኦብነግን የመገንጠል ሐሳብ የደገፉ ሰልፎች የተካሔዱ ሲሆን በዋርዴሩ ሰልፍ ላይ የተገኙት የኦብነጉ መሪም በመከላከያ ኀይሉ ቁጥጥር ሥር ዋሉ። ሼኽ ሀሰን ለቀናት ማረሚያ ቢቆዩም ደም አፋሳሽ በሆነ የተኩስ ልውውጥ ከማረሚያ ሊያመልጡ ቻሉ። ይህ የታሪክ ወቅት ኦብነግ ከኢሕአዴግ ጋር በሰላማዊ መንገድ መታገል ርባና ቢስ መሆኑን የተረዳበት ጊዜ ይመስላል። በዚህ ምክንያትም ዋናው የኦብነግ አመራር የትግል ስልቱን ወደ ትጥቅ እንደቀየረ አስታወቀ።

የቀረው አንጃ በአንጻሩ ተስፋ ሳይቆርጥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ለመተግበር ደፋ ቀና ማለትን ምርጫው አደረገ። የምኒልክ ቤተ መንግሥት ሰዎች በሱማሌ ክልል የፖለቲካ ልኂቃን ተስፋ ቢቆርጡም አዲስ ርዕሰ መስተዳደር ለመሾም ግን ወደ ኋላ ሳይሉ በኹለት ዓመት ውስጥ ሦስተኛው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አብዱራሕማን ኡጋስ ሞሐመድ ተሾሙ። በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሐረር በማምራት ለክልሉ ፖለቲከኞች ‹‹ሕገ መንግሥቱ ለሕዝቡ እንጅ ለእናንተ ለፖለቲካ ነጋዴዎች አይደለም የመገንጠልን መብት የፈቀደው›› የሚል ማሳሰቢያን አስተላለፉ። በዚህ ሳያበቁም የክልሉን የፖለቲካ ችግር ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ከኦብነግ የተነጠለውን አንጃ ከምዕራብ ሱማሌ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጋር እንዲዋሐድና ለክልሉ መረጋጋት እንዲሠራ ምክር አቀረቡ።

ይህን ባሉ በማግስቱም የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ (ኢሶዴሊ) ሁርሶ ላይ ተመሰረተ። አሕመድ ማካሂል ሀሰን አዲሱ ሊቀመንበር ተደርገው መሰየማቸውን ተከትሎም ክልሉን ማስተዳደር ጀመሩ።

ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ከግለሰባዊ ለውጥ ይልቅ የፓርቲውን አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ነው ብለው በማመናቸው ኢሶዴሊ ከሌላ ፓርቲ ጋር ተዋወቀ። የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) የትናንት ታሪክን ሊያሽር አሀዱ ብሎ ጉዞ ጀመረ። ከሀዲር ሙዓለምም የድርጅቱ መሪ ሆኖ ብቅ አለ። ጎሳ ተኮሩ የሱማሌ ፖለቲካ ግን ለዚህ ሰውም የሚበጅ አልሆነም። እናም የምኒልክ ቤተ መንግሥት ሰዎች የሚያምኑትን እስኪያገኙ አሰሳቸውን ቀጥለዋል። የክልሉ መሪዎችም ከቤተ መንግሥት ወደ ማረሚያ ቤት ማምራታቸውን ቀጠሉ።

የመጨረሻው መጀመሪያ
በሶማሌ ክልል ውስጥም ሆነ ከሌላ ክልል ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶች መነሻና መድረሻቸው በጎሳ የተቀነበበ ነው። ከውሃ ችግሩም ባለፈ የአካባቢው አርብቶ አደር ለዘመናት የተጠቀመባቸው የግጦሽ መሬቶች ለከብቶች መኖ መንፈግ ጀምረዋል። የግጦሽ መሬት ፍለጋ የጎሳን ድንበር ጥሶ ከሌላ መንደር መሄዱ ግዴታ መሆኑ እና ይህም ለግጭት በር መክፈቱ አልቀረም።

እነዚህ ግጭቶች ታዲያ ማንነት ላይ ያተኮረ ፌዴራላዊ ስርዓት መተግበሩን ተከትሎ ከጎሳ አልፈው ክልላዊ አንድምታን እየተላበሱ መጥተዋል። በአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችም በቦረና እና በኢሳ ጎሳ መካከል መባላቸው ቀረና በኦሮሚያና በሱማሌ መከካል ይባሉ ጀመር። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባርን የመሰሉ በሶማሌ በክልል ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም የታሪካዊ የግዛት ጥያቄን ዓላማቸው አድረገው የተለያዩ ቦታዎችን ወደ ሱማሌ ክልል እንዲዋሰኑ የወተወቱትም በዚህ ገፊ ምክንያት ነው።

የኢትዮ ሱማሌ ክልል ከአፋርና ኦሮሚያ ጋር እንደመጎራበቱ መጠን ዛሬም ያልተፈቱ የድንበር ጥያቄዎች እንዳሉበት እሙን ነው። ከድሬዳዋ በባቢሌ እስከ ሞያሌ የተዘረጋው የድንበር ጥያቄ ግን የግጦሽ መሬትን ብቻ ማዕከል ያደረገ አይደለም።

ከድሬዳዋ ብንጀምር የሱማሌ፣ ኦሮሚያና አፋር ታሪካዊ ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት ከተማ ናት። ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ሲቆጣጠር ኦሕዴድ ቀድሞ በአካባቢው የተገኘ የፖለቲካ ድርጀት እንደመሆኑ መጠን የድሬዳዋ ጉዳይ ወደ ኦሮሚያ ያደላ ቢመስልም የሱማሌ ክልልም ዋና መቀመጫውን በዚህች መዲና ለማድረግ መወሰኑ መልኩን አስቀይሮታል። አፋሮች በሱማሌ የኢሳ ጎሳ አባላት ግጭት ተማርረው ከአካባቢው ቢርቁም የታሪካዊ ባለቤትነት ጥያቄያቸው ግን በፌዴራላዊ ስርዓቱ ይፈታል የሚል ዕምነት ነበራቸው። ይህ እምነታቸው ግን የሱማሌና ኦሮሚያ ፖለቲከኞች በድሬዳዋ ይገባኛል ላይ ዙሩን ሲያከሩት እየረገበ የሔደ ይመስላል።

በሽግግር መንግሥቱ ማግስት ድሬዳዋ አምሰት ግለሰቦችን በያዘው የጋራ ምክር ቤት እንድትመራ በፌዴራሉ መንግሥት ሲወሰን አፋሮች አንድም መቀመጫ ለማግኘት አልታደሉም። ኹለት ከሶማሌ፣ ኹለት ከኦሮሚያ እንዲሁም አንድ አማራን ያካተተው የድሬደዋ የጋራ አስተዳደር በጊዜ ሒደት ከተማዋን ወደ ፌዴራል ከተማነት እንድትሸጋገር አድርጓል። ይህ መፍትሔ ግን ፍጹም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ የድሬዳዋ ችግር የአደጋ ጊዜ መውጫ እንዳይኖረው አድርጓል።

በተለይም ከአብዮቱ በኋላ አርብቶ አደሩ ህብረተሰብ መንግሥት በተከተለው የመሬት ላራሹ መርህ ከአካባቢያቸው እየተገፉ ለመሬታቸው ባይተዋር መሆናቸውን ይገልጻሉ። አካባቢያችንን ጥለን ወደ ሌላ ስፍራ ግጦሽ ፍለጋ ባመራንበት ወቅት ለኦሮሞ አርሶ አደር መሬታችን ተከፋፈለብን የሚሉት የሱማሌ አዛውንቶች፤ የፌዴራል ስርዓቱ ይህን ታሪካዊ ግፍ ተረድቶ መፍትሔ እንዲሰጥ ሲጠይቁ ይሰማሉ።

ግጭቶች የማይጠፉባት ባቢሌም ኢሕአዴግ አገር ማስተዳደር በጀመረ ማግስት በኦሕዴድ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ የገባች ብትሆንም ኦብነግ ግን ይህን ፈጽሞ እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ አሳውቋል። በሱማሌ ክልል ይንቀሳቀስ የነበረው አሊ-ታህድ አል-እስላሚያም ባቢሌን ከኦሕዴድ አስተዳደር ለመንጠቅ ተደጋጋሚ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽሟል። በአካባቢው የሚገኘው የሱማሌ ሀዌ ጎሳ ታጣቂዎችም ባቢሌን ለመንጠቅ የሚቦዝኑ አልሆኑም።

የኹለቱ ክልሎች የድንበር ይገባኛል ጥያቄ መኢሶም ላይ ቀጠለ። የኢሳ እና ሀዌ ጎሳ አባላት የሚበረክቱበት ይህ አካባቢ መሬቱ የእርሻ መሬትም በመሆኑ ውዝግቡ የግጦሽ ቦታ ለማግኘት ብቻ አልሆነም። ኢሳዎች በ1978 በኦሮሞና በደርግ ወታደሮች የተፈጠረባቸውን ግፍ ለመበቀል በመኢሶና አካባቢው የኦሮሚያ አከባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸም ጀመሩ።

ኢሕአዴግ የድንበር ይገባኛል ጥያቄውን በጊዜያዊ መፍትሄ ሲፈታ ቢቆይም በ1997 ግን በሕዝበ ውሳኔ ወሰን የመለየት ሥራ የጀመረ ሲሆን ከቅራኔዎች የጠራ ግን አልነበረም።

የአካባቢው የፖለቲካ ልኂቃን እንደሚሉት የአርብቶ አደሩ አካባቢ በሆነው የሶማሌ ክልል ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ መሬቱን ከመሸለም ያልተናነሰ ተግባር ነበር። ሕዝበ ውሳኔ ከተካሔደባቸው 424 ቀበሌዎች ውስጥ 350 የኦሮሚያ ክልልን ለመቀላቀል ሲወስኑ የቀሩት ወደ ሶማሌ ክልል ተጠቃለሉ።

ሞያሌ ላይ ያለው ውዝግብ ግን በህዝበ ውሳኔ ብቻ የሚቋጭ አልነበረም። ሞያሌን ለሁለት ከፍሎ የኦሮሚያ እና የሶማሌ በሚል እንድትጠራ አደረጋት። በ1998 የሶማሊያ ታጣቂዎች መኢሶ ላይ ጥቃት ፈጽመው የበርካቶችን ሕይወት ነጠቁ። በህዝበ ውሳኔው ወደ ሶማሌ ክልል የተጠቃለሉ የሀዌ ጎሳ አባላት ላይ ከኦሮሞ ጎሳዎች ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሙ ቀጠለ።

የመከላከያ ኃይሉ በአንድ በኩል የሱማሌ ክልልን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ግዛት የማስቀጠል ኃላፊነት ተሰጥቶት ከኦብነግና አሊ-ታህድ አል-ስላምያ ጋር በየጉራንጉሩ ይፋለማል። ወዲህ ደግሞ ጎሳ ተኮር የሆነው ፀብ የክልል ፖለቲካን ተላብሶ ውሉ የጠፋ ቋጠሮ ሆኗል። በእነዚህ አጣብቂኞች መሀል የፌዴራል መንግሥቱ እንደተለመደው አዲስ ሰውን ለማንገሥ እየባተ ነው።

የመጨረሻው መጨረሻ
ከ11 ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ 12ኛውን ሰው ተስፋ ያደረጉት አቶ መለስ የክልሉ የፍትህና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ላይ ዐይናቸው ያረፈ ይመስላል። የኢትዮጵያ ሶማሊያ ዴሞክራሲያዊ ሊግና የኦብነግ ህጋዊው አንጃ ተዳቅለው ኢሶህዴፓን ሲመሰርቱም እዛው ነበር። ህጋዊ እንቅስቃሴን ከሚያደርገው ኦብነግ ጋር በመሆን ሲታገል የኖረው ይህ ሰው የሼኽ ኢብራሂሙን የኦብነግ አንጃ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው የሚያጠራጥር አይደለም።

ይህ ብቻም አይደለም በዛይድ ባሬ ስርኣት ውስጥ የነበሩትን የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች ወዳጅ ማድረጉም የቀጠናውን ፖለቲካ ከማንም በላይ እንዲረዳ አስችሎታል። አብዲ መሃመድ ዑመር ከሱ በፊት ያሉት የክልል ርዕስ መስተዳደሮች መጨረሻቸው ማረሚያ ቤት መሆኑን ቢያውቅም ወደኋላ ግን አላለም። ኦብነግ የኦጋዴን ህዘብ የራሱ ዕድል በራሱ መወሰን አለበት በሚለው አቋሙ አሁንም እንደፀና ነው።

የአዲሱን ርዕሰ መስተዳደር ሹመትም በክልሉ ለውጥ የማያመጣ በማለት አወገዘ። የተለመዱ ጥቃቶችንም በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች መፈጸሙን አጠናከረ። በነዳጅ ፍለጋ ላይ የነበሩ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን ላይ በወሰደው ጥቃትም ዓለማቀፋዊ መነጋገሪያ ለመሆን በቃ።

ገና ከጅምሩ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የአብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳደር በጊዜ ሂደት ግን በሁለት እግሩ መቆም ጀመረ። በእነዚህ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች መሃል የተገኘው አዲሱ አመራር በመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ እና በአቶ መለስ ምክር ወደ መረጋጋት ማምራት ጀመረ። አብዲ መሀመድ ዑመርም በበርካቶች መደነቅ ጀመሩ።
የርዕሰ መስተዳደሩ ከዲያስፖራው ጋር ያለው ግንኙነት መሻሻል ሁለት ፖለቲካዊ ጥቅሞች የነበሩት ይመስላል። የመጀመሪያው ጅግጅጋን ከሌሎች ታዳጊ ክልሎች ርዕሰ መዲናዎች በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትገኝ ረድቷታል። ከዚህ በተጨማሪም የኦብነግ የጀርባ እጥንት የሆነውን የዲያስፖራ ድጋፍ እንዲቀንስ አድርጎታል። ሁለት ድሎችን ያስመዘገበው የአቶ አብዲ አመራር በመከላከያ ሰራዊት እጅ አዙር አገዛዝ ስር የነበረውን ክልል ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር ጀመረ። ይህ ዓይነቱ ውጤት ግን ሙሉ ተስፋን ያነገበ አልነበረም። አብዲ መሀመድ ዑመር በአንድ በኩል ጎሳ ተኮሩ የሶማሌ ፖለቲካ ስልጣኑን ሊነጥቀው እየተንደረደረ ነው። በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ጋር ያለው ታሪካዊ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከቁጥጥር መውጣት ጀመረ።

የኮንትሮባንድ ንግዱ ተጠቃሚ ያደረጋቸው አካላት የሱማሌ ክልልን ትልቁ የፖለቲካ ገበያ አደረጉት። ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት የታደለው አብዲ መሃመድ ዑመር በአንድ ነገር እርግጠኛ የሆነ ይመስላል፤ ከእሱ በፊት ከነበሩ 11 ርዕሰ መስተዳድሮች የተሻለና ክልሉን የማረጋጋት ቁልፉ በእጁ አንዳለ። ከምኒልክ ቤተ-መንግሥት ስልጣን ቀብተው የላኩት ሰዎችም የአብዲ መሀመድን ጥቅም ተረድተዋል። የታላቋ የሱማሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብበት የኖረውን ክልል ኢትዮጵያዊ አድርጓልና።

አቶ አብዲ ኦብነግና ሌሎች የሚፈንጩበትን ክልል በልምድ ታጅቦ የግል ርስቱ አደረገው። ኢህአዴግ ኦብነግ ከሚፈነጭበት የኢሶህዴፓው ሰው ቢፈነጭበት የሚያጣው ብዙ አልነበረምና ሊከለክለው ባለመፈለጉ ከምኒልክ ቤተ-መንግሥት በረጅም የታሰረበትን ገመድ በጥሶ ያሻውን ሲያደርግ ተው የሚለው አልተገኘም። የመሀል ሀገሩ ፖለቲካ ይህን ላለማድረጉ አንዱ በአቶ መለስ ይሁንታ የተሾሙትን ሰው ለመንካት ድፍረቱን ያገኘ አለመኖሩ ሲሆን፥ ሌላው እሳቸውን መነካካትም ክልሉን ወደለየልት ቀውስ እንደሚወስደው መገመቱ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመሀል ሀገር ተቃውሞ መናጥ መጀመሩም አቶ አብዲ ላይ ያለው የኢህአዴግ ዓይን እንዲነቀል የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህ መሃል ግን የኢትዮ ሱማሌና የኦሮሚያ ድንበር ግጭት ዳግም አገረሸ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሀገር ውስጥ ፍልሰትም ተመዘገበ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከተሾሙ በኋላ ወደ ጅግጅጋ አምርተው የሁለቱን ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ቢያወያዩም ነገሩ የመዳፈን እንጂ የመጥፋት ምልክት አላሳየም።
አብዲን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው አንድም አሁን ያለው የምኒልክ ቤተ-መንግሥት ሰው የሾመው ያለመሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል የጎሳ ፖለቲከኞች አጋጣሚውን ተጠቅመው ከስልጣን እንዲወርድ መወትወታቸውን ቀጥለዋል። ዐቢይም በፊናቸው ሌላ ፈተና እየጠበቃቸው ነበር። የመጀመሪያው የኦሮሞ ፖለቲካ ትግል ለስልጣን ያበቃቸው ሰው ናቸውና የኦሮሚያን ህዝብ ጥያቄ የመስማት ኃላፊነት አለባቸው። አብዲ ኢሌ በሚል ስሙ የሚነሳው ሰው በኦሮሞ ህዘብ የሚወደድ አይደለም።
በዚህ መሃል ዐቢይ ምቹ አጋጣሚን ያገኙ ይመስላል። የመሀል ሀገር ፖለቲካው ንረት መቀዛቀዝ ሲጀምር ዐይናቸውን ዳግም ወደ ሱማሌ ክልል ላኩ። በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ጥያቄ መነሳት የለበትም ለሚለው አብዲ የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግርና ተግባር የሚዋጥለት አይሆንም።

የመደመር ፖለቲካን ከአንገት በላይ ተቀብሎ ሰልፍ ቢወጣም ፌርማታው ግን ለሱም ሆነ ለሱማሌ ህዝብ የሚሆን አልመሰለውም። እናም ሁለቱም ወቅት መጠበቅን ምርጫቸው አደረጉ።

የመሀል ሀገሩ ሰው ዕውቅና የሰጡትና ይሁንታን የቸሩት ውይይት በድሬዳዋ ስለአብዲ ሊመክር ተቀመጠ። ለአቶ አብዲ ይህ ስብሰባ በመደመር ስም ስልጣን ለመንጠቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። እናም ስብሰባው ህገ-ወጥ ነው፤ መካሄድ የለበትም የሚል አስተያየትን ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ላከ፤ የሚሰማው ግን አልተገኘም።

የሱማሌን ፖለቲካ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሰው የመጫወቻ ካርታው ተማጽኖ ብቻ አይደለም። ሌላኛውን ካርደ መዘዘው። የራስን ዕድል በራስ መወሰን እሰከ መገንጠል ይላል። እሱን በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ለመምዘዝ ሲንደረደር የመከላከያ ኃይሉ ጣልቃ ገባ። አቶ አብዲ ካርዱን ወደ ሸሚዙ ቢከተውም የሱማሌ ወጣቶች ግን ከዘመናት በኋላ ዳግም በጅግጅጋ ጎዳናዎች ላይ ስለ ሱማሊያ እየዘመሩ የታላቋን ሱማሊያን ሰንደቅ ዓላማም አውለበለቡ።

ዐቢይ ከጀርባቸው ያለውን ታላቅ ሸክም ተገላግለዋል። አብዲ ኢሌ የሚባልን ሰው ከስልጣን በማውረድም የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ መልሰዋል። ስልጣን የሚሹት የሶማሌ ጎሳዎች የኦጋዴኑ ሰው ከመንበሩ መነሳቱ አስደስቷቸዋል። የትናንት ወኔው ተዳክሞ በአብዲ መሐመድ ዑመር ዘመን የህልውና ስጋት ውስጥ የቆየው ኦብነግ ወደ ሀገር ውስጥ መመለሱም የስሜት መደበላለቅ ፈጥሯል።

የሶማሌ ፖለቲካ ድርሰት ግን 12 ፣13 እያለ ፌርማታ አልባው ፖለቲካ ቀጥሏል። በቀድሞው ጊዜ በማኅበራዊ ድረ ገፅ የሱማሌ ብሔረተኛ ሆኖ የምናውቀው ሙስጠፋ መሀመድም የጅግጅጋውን ቤተ መንግሥት ተቆናጧል። ተቃርኖዋዊ በሆነ መልኩ የትናንት መገለጫውን በአዲስ ተክቶም ለዜግነት ፖለቲካ ማበብ የሚሠራ ሰው መሆኑን በንግግሮቹ አሳይቷል።

በክልሉ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የታላቋ ሱማሊያ ዳግም እንመሰርታለን ሀሳብ የያዘ ኮከብ ጨምሮ ስለኢትዮጵያዊነት መስበክ ግራ ያጋባል። ተረኛው ከአራት ኪሎ ተቀብተው ለሹመት የበቁት ሙስጠፋ ተቃርኗዊ መንገድ ግን በዚህ ብቻ የታጠረ ሳይሆን ኹለት አስርት ዓመታትን የተሻገሩት የሱማሌ ህዝብ ፍላጎቶች አሁንም አልተነኩም፤ የሚነኩም አይመስሉም። በርግጥም እነሱን ማንሳትም አራት ኪሎን ማስከፋት ነው። በመሆኑም ምርጫው ሁለት ነው። ወደ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት እያንጋጠጡ በትናንቱ መንገድ መጓዝ? አልያም በቆዳ ስፋቱ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ የሆነውን ክልል የሚመጥን የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ብቅ ማለት? የመጀመሪያውን መንገድ ከትናንት እስከዛሬ ተጉዘንበታል።

የሱማሌን ህዝብ ዘንግቶ ለአራት ኪሎ መታመኑን አይተነዋል። በርካታ መሪዎችንም አንግሷል አውርዷል። ለሱማሌ ህዝብ ሳይሆን ለአቶ መለስ፣ ለአቶ ኃይለማርያም እንዲሁም ለዐቢይ መታመን አሹሟል። መሪዎች ፊት ሲያዞሩም ወደ ማረሚያ መወርወር ተለምዷል።

በእኔ ግምት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምም ሆነ ዴሞክራሲ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ለመሆኑ ዝቅተኛ ማሳያው የሱማሌ ክልል ፖለቲካ ነው። ኢህአዴግ ክልሎችን የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት አድርጌያለሁ ካለበት ጊዜ አንስቶ ለአፍታም ቢሆን የጅግጅጋን ፖለቲካ በነፃነት እንዲራመድ ፈቅዶ አያውቅም። ህዝቡም የወደደውን ለመሾምም ሆነ ለመሻር ተግባር ሳይሆን ተስፋ አልተቸረውም።

በኢትዮጵያ አይደለም በዓለም ታሪክ ውስጥ በተከታታይ የመጡ 12 የክልል ፕሬዝዳንቶች የታሰሩበት ህዝብ ሱማሌ ብቻ ይመስለኛል። ይህ እውነት የትናንት ብቻ ሳይሆን የነገም ላለመሆኑ ማንም እርግጠኛ አይመስለኝም። ከዚህ አንፃር የሱማሌን ፖለቲካ ከተጋነነው የአራት ኪሎ ምርኮኝነት አላቆ ህዝባዊነትን እንዲላበስ ማድረግ ያሻል። ለዚህ ቀጣዩ ምርጫ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቢሆንም የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር ጊዜያዊ መንገድ ግን ትልቅ ዋጋ ያለው ነው።

ይነገር ጌታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻው mar.getachew@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here