የተቀዛቀዘው ቡሄ እና የቡሄ ጨዋታ

0
1235

አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ በማለት የሚከበረው የቡሄ በዓልና ጨዋታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በከተሞች መቀዛቀዙ በርትቶበታል፤ የዘንድሮውም ከአምናና ካቻምናው እምብዛም የተለየ እንደማይሆን አዲስ ማለዳ ካሰባሰበችው ዳሰሳና አስተያየት መገንዘብ ተችሏል።

“ሃሌ ሉያ አንተ ሰው ሆይ
ቡሄ መድረሱን ሰምተሃል ወይ…
መስማቱንማ ሰምቼ ነበር
ከሱ ቢያደርሰኝ ልዑል እግዚአብሔር” ይላሉ፤ እንዲህ ከቡሄ መዳረሻ ቀናት ላይ የተገኙ ቡሄን የናፈቁ ቀደምት ልጆችና ወጣቶች። በአርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን እምነትና አስተምሕሮ ላይ መሠረቱን አድርጎ መቆያውን በማኅበረሰብ እሴት ላይ ያኖረው የቡሄ በዓል ከአንድ ቀን በኋላ ይከበራል።

“ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፤ ከዓመቱ ዝናባማ ወቅት የመለያያው ዋዜማ ቡሄ በተቀዛቀዘ ስሜት ቢሆንም እየተጠበቀ ነው።
ቡሄ የሚለው ቃል ትርጓሜ “ገላጣ፣ መላጣ” ነው ሲሉ መዛግብት ያስረዳሉ። በዓሉን ለማክበር መነሻ ምክንያት የሆነው በሃይማኖቱ አስተምሕሮ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረታቦር አምላክነቱን መግለጡ ነው። ለዚህም ነው በዓሉ ደብረታቦር እየተባለ የሚጠራው። ደብረ ታቦር የግዕዙ አጠራር ሲሆን በአማርኛ የታቦር ተራራ እንደማለት ነው። የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው አገር ሲሆን ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ የወጣበት፤ ሙሴና ኤልያስም በተገኙበት ብርሃነ መለኮቱ የገለጠበት ተራራ ነው።

ከመንፈሳዊ የበዓሉ አከባበር ጎን ለጎን ባሕላዊ ክንዋኔዎች ደግሞ አሉ። እናቶች ሙልሙል መጋገራቸውና በዓሉን አስመለክተው ሙገሳ ለሚያሰሙ እንዲሁም ለሚጨፍሩ ልጆች መስጠታቸው፣ የጅራፍ ጩኸት፣ ምሽት ላይ የሚደረገው የችቦ ማብራት ሥነ ስርዓትም ከበዓሉ አከባበር የሚጠቀሱ ክዋኔዎቸ ናቸው። እነዚህም ተግባራት ለብቻቸው ተገንጥለው የሚገኙ ሳይሆን በምሳሌና በማስታወሻነት ከመሰረታቸው ጋር የተሳሰሩ ናቸው። የችቦውንና የሙልሙሉን ነገር ታድያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሊቃውንት ሲያስረዱ ተከታዩን ይላሉ፡-

“ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር። የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል። ‘ቡሄ’ ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው። ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል። ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ። የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት ምሳሌ ሲኾን፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡም ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል።”

ይህን ተከትሎ የቡሄ በዓል በከተማ እንዲሁም በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ደምቆ ይከበራል። በተለይም በተለምዶ የቆሎ ተማሪዎች የሚባሉ ወይም የአብነት ተማሪዎች “ስለ ደብረ ታቦር” እያሉ እህል በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት የሚበላውንና የሚጠጣውን አዘጋጅተው፤ ቅኔ እየዘረፉና እየተቀባበሉ፤ በዕለቱ ሊያስቀድሱ ወደ ቤተክርስትያን ከሔዱ ምዕመናን ጋር ያከብሩታል።

ከአንድ ዓመት በፊት የቡሄ በዓል በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባሕል ማዕከል ሲከበር፤ የቴአትር ምሩቅ የሆኑት ወንድሜነህ ላዕከማርያም የበዓሉን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት በተመለከተ ጥናታዊ ወረቀት አቅርበው ነበር። በዚህም የቡሄ በዓል በተለይ ለማኅበረሰቡ የጨመረውን እሴት ጠቅሰዋል። አያይዘውም ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው ክብረ በዓላት መኖራቸውን በማስታወስ፤ ወደ ማኅበረሰቡ የሚገቡበትና አግልግሎት የሚሰጡበት የየራሳቸው መንገድ አላቸው ብለዋል።

የደብረታቦር ወይም የቡሄ በዓልም በዛ መሠረት በልጆችና በማኅበረሰቡ መካከል የሚያስተሳስርና የሚያጋራ ባሕል በመሆን እያገለገለ ነው። ቡሄ ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆን አልፎ የማኅበረሰቡ፤ ከዛም ተሻግሮ አከባበሩም ባሕል ከመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል። ያም ብቻ አይደለም፤ ለሥነ ቃል ያበረከተውንም አስተዋጽዖ ወንድሜነህ በጥናታቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም። እዚህ ላይ ታድያ የቡሄ በዓል ላይ ወጣቶች የሚያቀርቧቸው ግጥሞች ይዘትና ዓይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ መሆኑን አንስተዋል።

“ባሕል ይፈጠራል፤ ያድጋል እንዲሁም ይሞታል›› ያሉት ወንድሜነህ፤ ይሁንና እንዲህ ያሉ በዓላት ማኅበረሰባዊ መሠረታቸው እንዳለ ሆኖ ሃማኖታዊም ሆነ ታሪካዊ መሠረታቸውን ሊለቁ እንደማይገባ አሳስበዋል። በአንጻሩ ግን አሁን ላይ የቡሄ በዓል በተለይም ለሥነ ቃል ከሚኖረው ፋይዳ አንጻር በብዛት ከመሠረቱ ተፋትቶ ይታያል። ነባሩ ትውፊት በገጠራማዋ ኢትዮጵያ ነው የቀረው፤ ብዙ ልጆች በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ስለሚሽቀዳደሙ የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያውቁት ብዙዎቸ ናቸው የሚሉ ንግግሮች ይደመጣል።

ለዚህም አንዱ መገለጫ እንደተባለው ለቡሄ ልጆች የሚያሰሟቸው የጭፈራ ግጥሞች ተጠቃሽ ናቸው። በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ በላይ ኃይለማርያም ደብረታቦር/ቡሄ በደብረታቦር ከተማ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ከነሐሴ 13 ቀን ጀምሮ “ቡሄ ጊዮርጊስ” ተብሎ እስከሚጠራው ነሐሴ 23 ድረስ ለቀናት፤ ልጆችም በየቤቱ እየዞሩ በመጨፈር ሲያከበብሩት ይቆያሉ።

“በየቤቱ ለሚጨፍሩ ልጆች ድሮ ድሮ የሚሰጠው ሽልማት ሙልሙል ዳቦ ነበር፤ በኋላ ግን ወደ ገንዘብ ተለወጠ” የሚሉት ባለሙያው፤ እሱ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ “እዛ ማዶ አንድ ጀሪካን….የኔማ እገሌ ሊሔድ ነው አሜሪካን” ዓይነት የቡሄ በዓል የልጆች ጭፈራ ግጥሞች ፋይዳ የሌላቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ይህንንም ለማስተካከልና የቀደመውን ለመመለስ ካለፈው ኹለት ዓመት ወዲህ፤ በተለይም ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በዓሉ ትውፊታዊ ይዘቱ እንዲመለስ እንዲሁም ያለውን ጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ በኩል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

“መጣና በዓመቱ…… ኧረ እንደምን ሰነበቱ
የጌታዬ ሰቀላ…… ተሸልሟል በአለላ
የእመቤቴ አዳራሽ…… ተሸልሟል በሻሽ
ክፈት በለው በሩን…… የጌታዬን
ክፈት በለው ተነሳ…… ያንን አንበሳ” የሚሉ የጭፈራና ዝማሬ መግቢያዎች እንዲሁም ነባሮቹን ግጥሞች የጠቃቀሱት በላይ፤ “እነዚህ ማሞገሻዎቹ ራሳቸው ሞገስ አላቸው” ብለዋል። እነዚህ ግጥሞች ባሕሉን የሚያስታውሱ፣ መሠረቱን የሚያነሱ ሐሳቦች ናቸው ሲሉም አክለዋል።

ይህን ለማስተካከልና ወደ ቀደመ ነገሩ ለመመለስ መፍትሔው ከተቋማት የሚገኝ ብቻ አይደለም። በተለይ በየአካባቢው ያሉ በዕድሜ የገፉ ትላልቅ ሰዎች ለልጆቹ ሥነቃሉን ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል ያሉት በላይ ናቸው። ግድፈቱና ስህተቱ ከልጆቹ አለማወቅና አለመነገር የሚመነጭ በመሆኑና፤ ልጆችም ከአባቶቻቸው ያልተቀበሉትን ሊሰጡ ስለማይችሉ ለብዙኅን ተደራሽ የሆነ ድምጽ ያላቸው ጸሐፍትም የቀደመውን እንዲያሳውቁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህም ባለፈ ሙዚቀኞችም ከቡሄ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ለአድማጭ ሲያደርሱ እነዚህን ሥነ ቃሎች መጠቀማቸው፤ ትውፊታዊውን የበዓሉን አከባበር ወደ ነበረበት ይመልሳል ሲሉ ጠቅሰዋል። በባሕልና ቱሪዘም በኩል ግን የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች ቢኖሩም ቡሄን በተመለከተ ስንኞችን በመበተን እየተሠራ ነው ብለዋል። እስከአሁን ግን ባሕልና ቱሪዘም ቢሮዎችን ጨምሮ በዚህ ላይ ኀላፊነቱን የተወጣ እንደሌለ ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ያነሱት።

የዘንድሮን የቡሄን በዓል አከባበር በተመለከተ የሚኖረውን ክዋኔም አያይዘው የገለጹት በላይ፤ ከቀደመው ዓመት ጀምሮ “ደብረታቦርን በደብረታቦር” በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሔድ የነበረው አከባበር ይቀጥላል ብለዋል። ከሃይማኖቱ ተቋሙ ጋር በመሆን እንዲሁም መገናኛ ብዙኀንን በመያዝ ይህን አጠናክሮ መቀጠልንም እቅድ አድርገዋል። “መገናኛ ብዙኅን መስኮቶች ናቸው፤ አንዳንዴም ራሳቸውም ቢሆኑ በር አንኳክተው ማየት አለባቸው” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም ቸል የተባሉና ያልተነኩ ባሕላዊ እሴቶችን በማውጣት የመገናኛ ብዙኀን ሚና ላቅ እንደሚል አስታውሰዋል። ቡሄን በተመለከተ ግን በተለይ ለሙዚቃ ባለሙያዎች የቀደመውንና መሠረቱን ሳይረሱ እንዲሠሩ በማለት ጥብቅ አደራቸውን በአዲስ ማለዳ በኩል አስተላልፈዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here