ባለ ኹለት መልኩ የጭነት ተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሕግ

0
1026

ለይትባረክ ደርቤ ክረምት ማለት በሙቀት ለነደደው አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል መቀዝቀዣ ወይም አሮጌውን ዓመት በአዲሱ ለመተካት የሚታለፍበት ቀዝቃዛ መተላለፊያ አይደለም ። በራሱ በይትባረክ አገላለፅ ክረምት ማለት ‹‹የሞት ሸለቆ ›› ነው። ምክንያቱ ደግሞ የስራ እንቅስቃሴ የሚቀዛቀዝበት ወቅት በመሆኑ።

ይትባረክ ደርቤ የከባድ መኪና ባለቤት ነው። ክረምት በአብዛኛው የከባድ መኪና ሥራዎች ስለሚቀዛቀዙ በዘርፉ ለተሰማሩ ግለሰቦች ክረምት ደስታን ይዞላቸው አይመጣም። ይትባረክ በሃምሳ በመቶ ክፍያ ከባንክ ጋር በመነጋገር መኪናውን ከገዛ አንድ ዓመት አልፎታል። ነገር ግን በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት እንደልቡ ለተቀጣሪ ሹፌር መኪናውን በመስጠት ገንዘብ መስራት አልቻለም ምክንያቱ ደግሞ ንብረቴ ላይ ጉዳት ይደርስብኛል በሚል ፍራቻ ነው። ‹‹ብጥብጥና ግጭቱን በመፍራት መኪናውን ከአዲስ አበባ አስወጥቼው አላውቅም እዚሁ ተባራሪ ስራዎችን እንዲሰራ ነው ማደርገው›› የሚለው ይትባረክ በአመዛኙ ክረምት ደግሞ ሥራ የሚታጣበት በርካታ ግንባታዎች በአዲስ አበባም ሆነ በተቀሩት የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚቋረጡበት በመሆኑ በርካታ ችግሮችን በከባድ መኪና ባለቤቶችና በተቀጣሪ አሽከርካሪዎች ላይ ማስከተላቸው አልቀረም።

ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን ይትባረክን ትልቅ ጭንቅ ውስጥ የከተተው በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የወጣው እና ከባድ መኪናዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱበት የሰዓት ገደብ ነው። ሰኔ 30/2011 ጀም ተግበራዊ የሆነው ይህ ሕግ ከባድ መኪኖች ከምሽቱ ኹለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ብቻ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ የሚያስገድድ ሲሆን ሕጉን በማያከብሩ አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ ቅጣት የሚጣል ይሆናል። ይትባረክ ሕጉን በሚመለከት ከፍተኛ ተቃውሞ አለው። ‹‹ቀኑን ሙሉ ሰርተን ዕዳችንን ለመክፈል እያዳገተን ባለበት ሁኔታ ይባስ ብሎ ውስን ሰዓት ሰርተን ጭራሽ ለዕለት ጉርስም ለማግኘት የምንችል አይመስለኝም ›› ሲል ምሬቱን ይገልፃል። ‹‹በጣም የሚገርመው ነገር ሕጉ የወጣው በመጀመሪያ ደረጃ ክረምቱ የሚገባበትና የከባድ መኪና ሥራ የሚቀዘቅዝበት ጊዜ ላይ ነው። ታዲያ ተሯሩጠን እንዳንሰራ ደግሞ በቀን መንቀሳቀስ እንዳንችል ተደረግን፤ አንዳንድ ጊዜ ሳስበው መንግስት ከወሰነ በኋላ የሚያስብ እየመሰለኝ ነው›› ሲል ይናገራል ይትባረክ። ሕጉ በዚሁ ከቀጠለ ይትባረክ ኪሳራ ውስጥ እንደሚገባና ንብረቱንም ባንክ እንደሚወስድበት ጥርጣሬ የለውም። ምክንያቱ ደግሞ በየጊዜው የሚጨምረው የባንኩ ወለድ ይትባረክ እየከፈለ ካለበት መጠን ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ነው ።

አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ ግራና ቀኝ እንዲሁም የመንገድ አካፋዮች ላይ በብዛት ተሰድረው የሚታዩት ከባድ የጭነት መኪኖች በተለይ ደግሞ የክረምቱን ወራት መግባት ተከትሎ ስራ ስለማይኖር እና ከከተማ ወጥተው ለመስራትም በጭቃ ስለሚያዙ ቁጥራቸው ከፍ ይላል። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በታዘበችው ከሰሚት አደባባይ በፍሊንት ሰቶን ቤቶች ወደ ጎሮ አደባባይ በሚዘልቀው መንገድ ላይ የመንገዱን አካፋይ ብቻ ሳይሆን የአንድ መኪና ማሳለፊያ ብቻ በማስቀረት ዋና መንገድ ግራና ቀኝ ላይ በርካታ ገልባጭ የጭነት መኪኖች በተለምዶ ‹‹ሲኖ ትራክ ›› የሚባሉ ተሸርካሪዎች ያለ ስራ ቆመዋል።

ለወትሮው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ያለ መከልከል ሲምዘገዘጉ የሚውሉት ሲኖ ትራክ መኪኖች አዲሱን ሕግ ተከትሎ እግራቸው ተይዟል። ለረጅም ሰዓት በዛው ቦታ ላይ ለመቆማቸውም እስከ ጎማቸው አጋማሽ ድረስ በጭቃ መዋጣቸው ምስክር ነው። ከላይ በጠቀስነው አካባቢ አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው አሽርካሪ ደግሞ የተለየ አስተያየት ሰጥቷል። ስሙ ቹየ አበራ ሲል የተዋወቀኝ አሽከርካሪ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ ወይም ራቅ ካለም ከዝዋይ አሸዋ በማመላለስ ነው ኑሮውን የሚገፋው ። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ መስተዳደር ያወጣው አዲሱ ሕግ ግን ኑሮውን ፈታኝ እንዲሆን እና ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። ‹‹እኔ የሚከፈለኝ ጭነት በተገኘ ጊዜ እንጂ ወርሃዊ ደሞዝተኛ አይደለሁም›› ሲል የሚጀምረው ቹየ፤ አሸዋ ለማመላለስ በሚያደርገው ጉዞ ሕጉ እያሰራው እንዳልሆነም ይናገራል። ‹‹በቢያጆ የምንሰራበት ጊዜ ስለሚኖር ቶሎ አሸዋውን ቶሎ አድርሰን ለተጨማሪ ዙር እንመላለስ ነበር ነገር ግን አሁን ምንም ያህል በጊዜ ብንደርስ ከምሽቱ ኹለት ሰዓት በፊት አዲስ አበባ መግባት ስለማንችል ጭነት ጭነን አዲስ አበባ ዳር ላይ መቆም ግዴታ ሆኖብናል›› ሲል ያብራራል። ቹየ በአንድ ሌሊት አንድ ጊዜ ብቻ ነው አሸዋ የሚያመጣው ይህ ደግሞ የገቢ መጠኑን በእጅጉ ጎድቶታል። ‹‹ከዚህ በፊት በቀን የማገኘው የነበረው ገቢ እና አሁን የማገኘው ገቢ በጣም የተራራቀ ነው ። አሁን በጣም ትንሽ ብር ነው የማገኘው። ቀደም ሲል ዕቁብ እጥል ነበር አሁን ግን ከመሰረታዊ ፍላጎቶቼ ተርፎ እቁብ መጣል አልቻልኩም።›› ሲል ተናግሯል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በምሽት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በርካታ የፀጥታ ችግር እንደሚያጋጥማቸውም ቹየ አልሸሸገም። ‹‹የተጫነውን ጭነት ይዘን በምሽት ወደ ምናራግፍበት ቦታ ስንሔድ ተገቢ ጥበቃ ስለማይኖርና ጭነቱ የሚራገፍበት ከዋና መንገድ ገባ ስለሚል ዝርፊያዎችና ድብደባዎች ይደርሰብናል›› ሲልም ተናግሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ፕረስ ሴክረታሪ ፌበን ተሾመ ስለ ጉዳዩ ሲመልሱ ‹‹የተሻለ ጥቅም ሲመጣ የሚጎዳ አካል ቢኖርም ዞሮ ዞሮ ግን ጥቅሙ ይበልጣል›› ሲሉ ይጀምራሉ። የከባድ ተሸከርካሪዎች መንቀሳቀሻ ሕግ ከዚህ በፊትም በአርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ዘመንም ተግባራዊ ሆኖ እንደነበር ፌበን ያወሳሉ። ‹‹በዋናነት ከተማዋ ላይ የሚታየው የትራፊክ መጨናነቅን ለማስቀረት፣ ከባባድ የመኪና አደጋዎችን በአዲስ አበባ ለመቀነስ እንዲሁም ከተማዋ ነቅታ እንድታድር ወይም እንዳትተኛ ስለሚፈለግ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ። ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን አብረው መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሁንም ድረስ ጉድለት መኖሩን የሚያምኑት ፕረስ ሴክረታሪዋ በቅርቡ የፀጥታውንም ጉዳይ ዕልባት እንደሚያገኝ አስታውቀዋል። አዲሱ ሕግ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ስለተገኘው ለውጥ ፌበን ሲመልሱ ‹‹የትራፊክ ፍሰቱ በጣም ተሻሽሏል፣ አደጋዎችም ቁጥራቸው እንደቀነሰ ነው የሚሰማኝ ›› ሲሉ ተናግረው የከተማ አስተዳደሩ የሕጉን ውጤታማነት በየጊዜው እንደሚገመግምና አበረታች እንደሆነም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ሰኔ 30/2011 ወደ ተግባር የገባው አዲሱ ሕግ ሞተር ሳይክልንም በከተማ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ዕገዳ የሚጥል ነበር ። የኹለቱንም ሕጎች ጠቅለል አድርገው ፌበን ሲናገሩ አዲስ አበባን ለመኖሪያ ምቹ፣ ነዋሪዎቿ ተመችቷቸው እንጂ ተሳቀው የማይኖሩባት ለማድረግ የወጡ ሕግጋት እንደሆኑ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በሞተር ሳይክል እየታገዙ የሚፈፀሙ ዝርፊያዎችን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቆጣጠር እንደተቻለም አያይዘው ገልፀዋል። በከተማዋ አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና ቁጥሩ እያሻቀበ የመጣው ከባድ መኪኖች የሚያደርሱት አደጋ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ አሁንም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ጠንክሮ እንደሚሰራ አዲስ ማለዳ የገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ከሞተር ሳይክል ዕገዳ ጋር በተያያዘ ከተማ አስተዳደሩ ተደራጅተው በመምጣት ፈቃድ አግኝተው የሞተር ትንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም የመልዕክት ማድረስ ስራዎችን መስራት እንደሚችሉ ማስታወቁ የሚታወስ ነው ።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here