“አፋር ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ ማንነት የለውም።”

0
898

ዶ/ር ኮንቴ ሞሳ የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው። የተወለዱት በአፋር ክልል ዱለቻ ወረዳ ሲሆን አብዛኛውን የልጅነት ዕድሜያቸውን በአርብቶ አደርነት በተለይም ከግመል ጋር ማሳለፋቸውን የሚናገሩት ኮንቴ፥ የ1966ቱን ድርቅ ተከትሎ በመካከለኛው አዋሽ እርሻ ልማት አሁን ከሰም ቀበና ስኳር ፋብሪካ ቋሚ ሕይወት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ኮንቴ ከቤተሰባቸው መካከል ብቸኛ የትምህርት ዕድል ያገኙ ይኹኑ እንጂ፥ ትምህርት የጀመሩት ዘግይተው በዐሥራ አንድ ዓመታቸው ነው፤ ከጉብዝናቸው የተነሳ ግን 6ኛ ክፍልን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት ብቻ ነው የፈጀባቸው። የ6ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በጥሩ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ እስከ 12ኛ ክፍል ወደተማሩባት እንዲሁም “በይበልጥ እኔነቴን አገኘሁባት” ወደሚሏትን ድሬዳዋ አመሩ።

በ1970ዎቹ ይካሔዱ በነበሩት የውይይት ክበባት ንቁ ተሳታፊ እንደሆኑ የሚናገሩት ኮንቴ፥ ደደር በምትባል የገጠር ከተማም የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ተሳታፊ ነበሩ። በ1977 አካባቢ የነበረውን የብሔራዊ ውትድርና በማምለጥ በጅቡቲ በኩል ፈረንሳይ፣ እንዲሁም ከ10 ወራት ቆይታ በኋላ ኑሮና ሕይወቴን አቀናሁባት ወደሚሏት ስዊድን በማምራት ለሰላሳ ዓመታት ኖረዋል።

የ51 ዓመቱ ኮንቴ በስዊድን ቆይታቸው ከመጀመሪያ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ከመማር ባሻገር ትዳር መስርተው የሦስት ወንድ ልጆች አባት ለመሆን በቅተዋል። የዶክትሬት ዲግሪያቸው በሉላዊ ጤና አጠባበቅና በማኅበረሰብ ሕክምና (Global Health and Social Medicine) ላይ ሲሆን የሥራ ልምዳቸውን በተመለከተም በዓለም ባንክ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም የስዊድን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካሪም ሆነው አገልግለዋል፤ ወደ ኢትዮጵያ እስኪመጡ ድረስ በስዊድን አገር በሚገኘው ሉንድ ዩኒቨርስቲ በመምህርነትና ተመራማሪነት ከዕውቀታቸው አጋርተዋል።

ኮንቴ ከአፋር አገኘሁት ከሚሉት ግልጽነትና ሌሎች ጥሩ እሴቶች ጋር የድሬዳዋ ማኅበረሰብ አቃፊነት “ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርበት ስብዕና እንድይዝ አድርጎኛል” ይላሉ። ስለድሬዳዋ ተናግረው የማይጠግቡት ኮንቴ፥ ድሬዳዋን “የአብሮነት እና የአንድነት ገበያ ነች” በማለት ይገልጿታል።

የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ኮንቴ ሙሳን (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ስለአፋር ሕዝብና ፓርቲያቸው እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በማናገር የአንደበት እንግዳ አድርጓቸዋል።

አዲስ ማለዳ፡ ሁሉን አካታች ከሆነ ከአፍር ማኅበረሰብ ውስጥ ወጥተው እንዴት የአፍር ሕዝቦች ፓርቲን መሰረቱ?
ኮንቴ ሙሳ (ዶ/ር)፡ ይህንን እንቅስቃሴ ስንጀምር የፖለቲካ ፓርቲ እንሆናለን ብለን አልነበረም። ማኅበራዊ ፍትሕን በሚመለከት አርብቶ አደሩ ከቀዬው በትላልቅ የእርሻ ፕሮጀክቶች ምክንያት የማፈናቀሉ፤ በተለይ በክልሉ የነበረው የአስተዳደር ብልሹነትን በተመለከተ ነበር የተነሳነው። መነሻው ብዙ ጊዜ የአፋር ማኅበረሰብ ማኅበራዊ ፍትሕ ጥያቄ እንጂ የፖለቲከ ጥያቄ አይደለም። ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገን የመገንጠል ጥያቄ ይዘን አልተነሳንም። በዛም ላይ ይሔ ምድር የአፋር ብቻ ነው፤ ሌላው አይኑረበት የሚል ነገርም የለንም። እናም የእኛ ዋና መነሻ የሆነን የማኅበራዊ ፍትሕ፣ ትምህርት፣ ጤና እና ኑሮን ማሻሻል ነው። በተለይ አርብቶ አደሩ በጣም የተገፋ ስለሆነ ነው።

የኢትጵያን የፖለቲካ ታሪክ ስናይ ብዙ ጊዜ የመሐል አገር ችግር ነው የሚነሳው፤ መሬት ላራሹ እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል። አፋርን ከፖለቲካው ያገለለ ነው። አሁንም ቢሆን በራሱ ሳይሆን በሞግዚት ነው የሚተዳደረው። እንደሚታወቀው አጋር፣ ኋላ ቀርና አናሳ ክልል ተብሎ የፖለቲካ ሥም ከወጣላቸው ብሔሮች አንዱ መሆኑ ነው [ለመደራጀት] የመጀመሪያ ምክንያታችን።

ኹለተኛው ምክንያት አገር ዐቀፍ ሆኖ የሁሉንም ችግር የሚያይ የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖሩ ነው። ኢሕአዴግም የአራት ፓርቲዎች ስብስብ ነው፤ ይሔ በአፋር ብቻ ሳይሆን ኦጋዴንም ቢታይ፤ ጋምቤላም ችግር ሲፈጠር መቼ ነው እንደ ሕዝብና እንደ አገር ሰላማዊ ሰልፍ የወጣነው? መጀመሪያ ከምታውቀው ቀዬ ይጀመር ብለን ነው ይህን ፓርቲ የጀመርነው።

በዚህ ብቻ ሳንወሰን ቀጠልን፤ የመገንጠል ዓላማ ካላቸው ድርጅቶች በስተቀር ከተለያዩ መድረኮችና ድርጅቶች ጋር ኅብረት መፍጠር ጀመርን። ከአርበኞች ግንቦት ሰባት፤ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና የሲዳማ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅት ጋር ሆነን፤ በውጪ አገር ሳለን የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የሚባል ድርጅት መሥርተን ነበር።

በአጠቃላይ እኛ ከኢትዮጵያዊነት የሚያወጣን ሥራ አልሠራም። ድርጅቱ የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ ይባል እንጂ ከዜግነት ፖለቲካ ውጪ ለመሆን ሳይሆን አርብቶ አደርን የሚወክል ፓርቲ በአገራችን ባለመኖሩ ነው።

አንዳንዴ ትንሽ ግብዝነት አለብን፤ ምክንያቱም አፋር ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ ማንነት የለውም፤ ተጋጭቶበትም አያውቅም። የአፋር ታሪክ ብዙ አልተዘገበም እንጂ ያልተዘመረለት ሕዝብ ነው። ቱርክ ወደ ኢትዮጵያ እንዳትገባ፤ በግብጽና በሌሎች ብዙ ወረራዎች ከቀይ ባሕር ጠላት ወደ ውስጥ አገር እንዳይገባ የተከላከለ ሕዝብም ነው። መግቢያውም በዛ ነበርና እነርሱም [ሕዝቡ] የበረሃው ማስተር ስለሆኑ ጠላትን፤ ጣልያንን ጨምሮ በማሸነፍ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ያ አቃፊነት ግን አሁንም [በአፋር] አለ። በአፋር ክልል ባላጋንን የሕዝብ መፈናቀል ያልደረሰበት ነው። ለምሳሌ በአፋር የሚኖር በንግድም ቢባል፤ በመንግሥት ሥራና በእርሻ እንዲሁም በሌላ ሥራ ምክንያት የሌለ የኢትዮጵያ ብሔር ያለ አይመስለኝም። ግን አንድም ቀን በብሔር የተነሳ ውጣ የተባለ ሰው የለም።

እንደጠቀሱት በሌሎች ክልሎች እንደምናየውና እንደምንሰማው ያለ መፈናቀል አፋር ክልል የለም። ምን ዓይነት አኗኗርና ማኅበራዊ እሴት ቢኖር ነው ወይስ የክልሉ መንግሥት ያደረገው ነገር አለ?
እንደማስታውሰው ከዚህ በፊት ጅቡቲ መንገድ በአፋር ወጣቶች ሲዘጋ፤ እኛ እዛ ነበርን። በመስመሩ የመጨረሻው መኪና ጅቡቲ የመጀመሪያው አዋሽ ደርሶ ነበር፤ ብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች በመኪና ተጨናንቆ ነበር ማለት ነው። እኛም ያደረግነው “እሺ ወጣቶች መንገድ ዘግታችኋል፤ ግን አገራዊ ኀላፊነት ስላለብን፤ ሕይወት ማዳን አለብን” በማለት ተነጋገርን፤ ምግብና ውሃ ለሹፌሮች ማሰራጨት ጀመርን። ሥጋት የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ የመንገድ ላይ ፌስቲቫል መሰለ። አንድ ንብረትና መኪና ሳይቃጠል የወጣቶቹ ጥያቄ ተመልሶ መንገዱ ተከፈተ። ይህ አንድ ምሳሌ ነው።

ሌላው አፋር “ግብዝ” ነው። ያለእኛ ኢትዮጵያ የለችም፤ እኛም ያለኢትዮጵያ የለንም ይላል። ስለዚህም እኛ ጋር የሚኖረው ሕዝብ ወገናችን ነው ብሎ ያምናል። በአፋር ባሕል ውስጥ እሴቶች አሉ። ለምሳሌ በአፋር ነፍሰ ገዳይ አይገደልም፣ እስር ቤትም የለም። ምክንያቱም “ነፍስ ከሁሉ በላይ ክቡር ናት፤ ከፈጣሪ በቀር ነፍስ የማጥፋት መብት ያለው ሰው የለም” ብለው ያምናሉ። ይህ ለአፋር ሕዝብ መሠረታዊ ፍልስፍና ነው። አብሮ የመኖሩ ነገር ለየት ያለው ከዚህ የተነሳ ነው።

በተጨማሪም የአፋር ሕዝብ አብሮ እንጂ እንደ ግለሰብ መኖር የሚችል አይደለም። አካባቢው አደገኛ ነው፤ በረሃ ነው፤ ሀብትንም መጋራት አለ። ሕዝቡ እንጂ ክልሉ ለየት ያለ ስርዓትና አስተዳደር ኖሮት አይደለም።

የብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ አፋር እምብዛም አይታይም። ይሔስ መሠረቱ ምንድን ነው?
አፋር ራሱን እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ የለችም ብሎ ያምናል። ኹለተኛ በሙዚቃችንም “አገር ብርሃን የላትም፤ ምድር ብርሃን የላትም፤ ብርሃኗ ሕዝቧ ነው” የሚሉት ነገር አለ። ይህ ከትውልድ ትውልድ ሕጻናት ሲዘምሩት የሚያድጉት ነው።

ሌላው ለኢትዮጵያ ብዙ የተከፈለ መስዋዕትነት አለ። ቱርክ፣ ግብጽን፣ ፖርቱጋልና አረቦችንም ከመመለስ ታሪክ አንጻር ብዙ ያልተዘመረላቸው ናቸው። ለእኛ ኢትጵያዊነትን የሚሰጥ ሰው የለም ይላሉ። አንድ ግመል እየነዳ የሚሔድ ሰው የኢትዮጵያን ባንዲራ አድርጎ በረሃ ሲያቋርጥ፤ አንዳንድ ሰዎች እንዴት ክብር ያለውን ባንዲራ አንገቱ ላይ እንደጨርቅ አንጠልጥሎ ይሔዳል ይሉታል። አፋሮች የሚሉት “አገራችን እኛን መስላ የምትኖር ናት” ነው። እኛ ተንቀሳቃሽ ነን፤ አንድ ቦታ የሚኖር ሰው ይኖራል፤ እኛ ግን ስለምንሔድና ተጓዥ ስለሆንን በሔድንበት አብራን ታድራለች የሚል እሴት አላቸው።

ሲመስለኝ ከኑሮውና ፍልስፍናው እንዲሁም ከተከፈለው መስዋዕትነት አንጻር ሲታይ ስብዕናውም ኢትጵያዊነት ነው። እስከ አሁን ድረስ እንገነጠላለን ያለ አንድም የአፋር ድርጅት የለም። ምክንያቱም አፋሮች “ከየት ነው፤ ከማን ነው ነጻ የምንወጣው?” ይላሉ።
በአንድ ወቅት ሡልጣን ዓሊ ሚራህ “ጨርቅ ለእኛ ምንም አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነት እናስተምራችኋለን” ሲባሉ ነው፤ “እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቃሉ” ብለው የተናገሩት። እናንተ አገር ለመገንጠል ተደራጅታችሁ በፖሊሲ ስትሔዱ፤ እኛ ደግሞ አገርን አንድ ለማድረግ የመጣን ነንና አትሞክሩ ብለዋቸዋል። ነጻ አውጪ ብቻ ናችሁ፤ እኛን ስለኢትዮጵያዊነት ልታስተምሩ አትችሉም ብለውም ነበር።

በቅርቡ በተካሔደ ውይይት ላይ “በኢትዮጵያ ትኩረት የተነፈጋቸው አርብቶ አደሮች” የሚል ጥናት አቅርበው ነበር። በኢትዮጵያ የአርብቶ አደር ፖሊሲ አለመኖሩ ምን አሳጣን?
ፖሊሲው አለመኖሩ አቃፊነትን አሳጥቶናል፤ ባይተዋርነትን ፈጥሯል። በኢኮኖሚ በኩል ትልቅ ጉዳት ነው። አርሶ አደሩ ላይ ማሻሻያ እንደታሰበ ሁሉ አርብቶ አደሩም ላይ ያስፈልጋል። በኢኮኖሚ ደረጃ ያለውን አስተዋጽዖ አጉልቶ ማሳየት፣ በአካባቢው ያለው የመሬት ጉዳት ለአየር ጸባይ መቀየር ድረሻ አለው፤ ብዙ ይመጋገባልና ያንን አለማካተታችን ለሌሎች ችግሮች ይዳርጋል። ፖለሲው አለመኖሩ ለብዙ ዘርፎች ችግር ያመጣል፤ ለአካባቢ፣ ለንግድ፣ ለጤና እና ማኅበረሰቡ። ፖሊሲ ያለው ሴክተር ኑሮን ለማሻሻል በብዙ መንገድ ያግዛል። ብዙ አገራትም አላቸው፤ በእኛም አገር ወጥ የሆነ የአርብቶ አደር ፖሊሲ መኖር አለበት የሚል ዕይታ ነው ያለኝ።

በእናንተ በኩል ይህ የአርብቶ አደር ፖሊሲ እንዲኖር ምን እየሠራችሁ ነው?
በፓርቲ ደረጃ ገና መግባታችን ነው። የፓርቲያችን ፕሮግራም ግን ራሱ አርብቶ አደር ተኮር ነው። ጤና፣ ትምህርትና ንግዱንም ስታየው በዛ አካባቢ ያለውን ሀብትና እውቀት ማውጣት ነው። በመሆኑም በአገር ደረጃ ፖሊሲውን በመቅረጽ የራሳችን ተጽዕኖ ማድረግ እንፈልጋለን። በአፋር ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 61.3 የሚሆን ቦታ በአርብቶ አደር የተያዘ ነው። እንደተፎከካካሪ ፓርቲ በመንግሥት ደረጃ እውቅና እና ትኩረት እንዲያገኝ እየጎተጎትን ነው።

እርሶ የሚመሩት የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው። በተግባር እያደረጋችሁት ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ከውጭ ከመጡ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅድሚያ እውቅና ያገኘነውና ከምርጫ ቦርድ የምስክር ወረቀት የተሰጠን እኛ ነን። ከገባንም 8 ወር ቢሆነን ነው፤ ሒደቱ ትንሽ ዘግይቶ ነበር። እውቅና የማግኘት ጉዳይ ለእኛ ወሳኝ ነበር፤ ምክንያቱም በክልሉ የሚነሱ ሕጋዊነት የሌላቸው ናቸው በሚል በነጻነት እንዳንንቀሳቀስ የሚደረጉ ነገሮች ነበሩ።

በተወሰነ ጊዜ ሚድያ ላይ ብቻ ነበር የምንታየው፤ አሁን እውቅናው ከተገኘ በኋላ ግን በየቦታው ሔደን ሕዝብን የማደራጀት ሥራ እየሠራን፣ ቢሮ እየከፈትንና አባላት እየመለመልን፤ የተቻለንን እያደረግን ነው። ሕዝቡም ከምንጠብቀው በላይ ድጋፍ እየሰጠን ይገኛል። በክልሉ ለጊዜው ወደ 10 የሆኑ ቢሮዎች በተለያዩ ዞኖች አሉን። ቢሮዎቹን በበጎ አድራጎት ሰው ቤቱን እየሰጠን፤ ባለሀብቶችም እየረዱን እንጂ የሀብት ችግር አለብን።

በቀጣይ የፖለቲካ መርሃ ግብራችንን ለሕዝቡ ማስተዋወቅ ነው። አካታች፣ አሳታፊ፣ በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ከዛም ባለፈ በአገር ደረጃ ሰላም እንዲሰፍን በተለያዩ መድረኮች እየተሳተፍን የራሳችንን እንቅስቃሴና ተሳትፎ እያደረግን ነው። በተጨማሪም በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመርጠን 108 ፓርቲዎችን እየመራን እንገኛለን። ይህም ለአገር የሚበቃ ርዕይ እንዳለን ማሳያ ነው።

ምርጫ ቦርድ አካባቢ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የማሰባሰብ፣ ወደ አንድ የማምጣትና አሁን ካለንበት ሰብሰብ ብሎ የመሔዱን ሁኔታ እያቀናጀን ነው። በአፋር ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ደረጃ የሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችንም ፎርም ማድረግ ላይ የራሳችንን ተሳትፎ እያደረግን ነው። 108 ሆኖ አገር መምራት አይቻልም።

ለውጡ በንጽጽር ሲታይ በአፋር ክልል ዘግይቷል፤ በአፋር ያለው ለውጥ አሁን ላይ ምን ይመስላል?
አሁን በንጽጽር እኛ ስንመጣ ከነበረው የፖለቲካው አየር ተቀይሯል። ያኔ በጠላትነት የመታየትና “ክልል አይፈልጉም፤ አንድ ኢትዮጵያን መመለስ የሚፈልጉ ናቸው፤ በፌዴራሊዝ አያምኑም፤ የግንቦት ሰባት ተላላኪ ናቸው፤ አገርና ስርዓቱን ለማፍረስ የሚጥሩ ናቸው” የሚል ብዙ ውዥንብር ሕዝቡ ውስጥ ተዘርቶ ነበር። አሁን ግን ከአዲሱ አመራር ጋር የመቀራረብ ሁኔታ አለ።

ማሻሻያው ግን ከአመራር አልፎ ወደ ታች አልወረደም፤ በዞንና ወረዳ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የቀድሞ ስርዓት ቅሪቶች አሁንም አሉ፤ ይሔ ብዙ ችግር ይፈጥራል ብለን እናምናለን። ሌላው መሪው የአፋር ፓርቲም በራሱ የውስጥ ችግር ተጠምዶ ይገኛል። ያም በአፋር ክልል ያለው ሁኔታ አንዳንዴ የኢሕአዴግ ነጸብራቅ ይመስላል። ኢሕአዴግ ውስጣዊ አንድነቱ እየተናጋ እንደመጣው ሁሉ፤ አፋር ውስጥ ያለው ፓርቲ ውስጥም በጎሳ ተከፋፍለው ክልሉን የማስተዳደር ብቃታቸው ራሱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ማሻሻያው በፕሬዝዳንት ደረጃ ያለው ሁኔታ ጥሩ ሲሆን ከዛ በተረፈ ግን ወረድ ተብሎ ቀበሌና ወረዳዎች ላይ ችግሮች እንዳሉ ነው። እንደውም ችግሩ እየተባባሰ፤ በአፋርና አፋር መካከል ግጭቶች እየተፈጠሩ ነው። በመሆኑም ማሻሻያው ወደ ታች አልወረደም።

በየክልሉ የተለያዩ የወጣቶች ስብስብ እንቅሰቃሴ ይደረግ ነበር። በለውጡ የዱኮ ሂና (የአፋር ወጣቶች) ሚና እና ተሳትፎ ምን ይመስላል?
የአፋር ወጣቶች ለውጡ በሰላማዊ መልክ እንዲመጣ ያደረጉት ትግል ከፍተኛ ነው። ሕዝብን አስተባብረዋል፤ የሕዝቡን አንድነት ለማስጠበቅም ብዙ ታግለዋል። አሁን አዲስ አመራር ከመጣ በኋላ ግን ያደርጉ የነበሩት እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ይመስላል። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አብዛኛው ወጣት ሥራ አጥ ነው። በመሆኑም ወጣቱን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ በጥቅማ ጥቅሞች መያዝ አለ፤ በአዲሱ አመራር ሥልጣን የተሰጣቸው ልጆችም አሉ።

ሆኖም ግን በእኔ ዕይታ የወጣቱ እንቅስቃሴ ከስሟል ማለት አልፈልግም። አሁን አካሔድና እርምጃውን እየተከታተለ ነው። ጠያቂ ወጣት ተፈጥሯል፤ በትምህርት ደረጃም የተሻሉ አሉ። እኔ በአፋር ወጣቶች ላይ ተስፋ አልቆርጥም። አሁን ወጣቱ ሚዛናዊ ለሆነ አካሔድ እያኮበኮበ እንጂ ዱኮ ሂና ጠፍቷል እንደሚባለው፥ በዛ ደረጃ አይደለም።

የእናንተ ፓርቲ ከወጣቱ ጋር ምን እየሠራ ነው?
ውጪ ብዙ ቆይተን ነው የመጣነው፤ በዕድሜም ገፋ ያልን ነን። የእኛ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ፖለቲካችን የተበላሸው ወጣቶችና ሴቶችን አለማሳተፋችንና ማግለላችን ነው ብለን ኀላፊነቱን ወስደናል። በእኛም ፓርቲ በሥራ አስፈጻሚውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ያሉት በ20ዎቹ ዕድሜ ያሉ ናቸው። ይህን ነገር ወጣቱ እንዲሸከመው ነው። ምክንያቱም ቀጣይ ትውልድ እነርሱ ናቸው፤ እኛ ከእነርሱ ተውሰን ነው ያለነው።

ስለዚህ ወጣቱን ማቀፍ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ነው። ርዕያችን ከትውልድ ትውልድ መተላለፍ አለበት፤ ያም በተለይ ወጣቶችና ሴቶችን አሳታፊ መሆን አለበት። ፓርቲያችን በአባላት ደረጃ 90 በመቶው ወጣት በመሆኑና ዘመን አሻጋሪ የፖለቲካ ፕሮግራም ስለያዝን ከአፋር ሕዝብና ወጣት ባሻገር አገር ማስተዳደር የሚችል ርዕይ አለን ብለን እናምናለን።

የተመዘገቡ ምን ያህል አባላት አሏችሁ?
እስከአሁን ባደረግናቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አባላት በስፋት እየተመዘገቡ ነው። ትላንት [እሁድ፣ ነሐሴ 6] በደረሰኝ ሪፖርት በዚህ አንድ ወር 15 ሺሕ አባላት ተመዝግበዋል። እርግጠኛ የሆነ ቁጥር የለንም፤ ግን በሔድንበት ከተማ የሚደረግልንን አቀባበል እናያለን። የአባላት ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም።

በአፋር ከሶማሌ እና ከኦሮሚያ አጎራባች ጋር የሚነሱ ግጭቶች አሉ። የአፋርን እንዲሁም የአገርን ሰላም ከመጠበቅ አንጻር እንዴት መያዝ አለበት?
እኛ እንደምናውቀው አፋር ከጎረቤቱ ጋር በሰላም መኖር የሚፈልግ ሕዝብ ነው። ሆኖም በአፋርና በኢሳ መካከል የተነሳው ቅራኔ ሚድያ የሚዘግብበት ሁኔታ አለ። በአፋርና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ተብሎ ነው የሚዘገበው። ይህ ትክክል አይደለም። ሦስቱ የኮንትሮባንድ ከተሞች [አዳይቱ ኡንዳፎኦ እና ጋዳማይቱ] ከመነሻቸውም ጀምሮ ከጅቡቲና ሶማሌ ላንድ የሚመጣውን ኮንትሮባንድ ለማሰራጨት የተሠሩ ናቸው። የሚገኙትም በአስፋልት ዳር ነው፤ የአፋር ክልል ድንበር ደግሞ ያንን ብዙ አልፎ ነው።

አንደኛው ሰዉ ማወቅ ያለበት ይህ የድንበር ግጭት አይደለም። ግጭቱን የሚያነሳሱት ደግሞ የተለየ ጥቅም ያላቸው ናቸው። እነዚህም በኹለት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ፤ አንደኛ በለውጡ ምክንያት የተገፉ፤ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ኀይሎች አሉ። ኹለተኛ በዛ በኩል የሚገባው ኮንትሮባንድም ጥቅምና የስርጭቱ መስመር ሲዘጋ፤ እስከ ታይዋን የሚደርስ የተያያዘ መስመር በመሆኑ በጥቅም ላይ የተመሠረተ ግጭት ነው።

የአፋርና የኢሳ አርብቶ አደር መካከል ግጭቶች በፊትም ነበሩ። ነገር ግን በዚህ ደረጃ በመሣሪያ የታገዘ አልነበረም። ይህኛው ግጭት የአርብቶ አደሩ አይደለም፤ በዚህም የፖለቲካ ንግድ ነው የተያዘው።

ይሕ ግጭት የሚያወሳስበው በሶማሌ ክልል አሁን የተነሳው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ነው። ይህን ለማርገብ በፌዴራል ደረጃ በ2007 የተደረገ ጥናትና የተወሰነ ውሳኔ አለ። በኹለቱ ክልሎች መካከል ሰላም መስፈን አለበት። በቅርቡ በአፋርና ኦሮሞ መካከልም አዋሽ አርባ አካባቢ የተነሳ ግጭት ነበር። እሱም በተወሰነ ደረጃ አሁን ተይዟል፤ መሰራጨትም የለበትም። ስለዚህ ሰላም ሲባል ለአፋር ብቻ ሳይሆን ሰላም ሁላችንም ስለሚያገባን፤ ከግጭት ወደ ሰላምና አብሮ መኖር መመጣት አለበት፤ ይህቺ አገር ለሁላችን ትበቃናለች። ነገር ግን አንዱ በሌላው ህልውና ላይ መረማመድ የትም አያደርስም። ለዚህ ነው የአፋር ማኅበረሰብ ግዛት ማስፋፋትን በከፍተኛ ደረጃ እየተቃወመ ያለው።

ግዛት ማስፋፋት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
እንደሚታወቀው የግዛት ማስፋፋት ጥያቄ በሶማሌ ክልል በኩል አለ። በሶማሌ ክልል በኩል በቅርቡ የወጣ መግለጫም አለ። እነዛ ነገሮች ሰብሰብ ሲሉ ሌላ ፍላጎት እንዳለ ያስታውቃል። ነገር ግን እኛ የምንለው በአፋርና ሶማሌ ክልል መካከል በባሕላዊ መንገድ፤ በሕዝቦች ይህ ነገር እልባት ማግኘት አለበት። በፌዴራልም በኩል “ድንበር የት ነው?” የሚለው ነገር መጠናት አለበት።

ከኢሳ ጋር በተያያዘ “ክልሉ መሬቱን እንጂ ሕዝቡን አይፈልግም” የሚለው ላይ ምን ይላሉ?
እስከማውቀው ይህ የተለመደ አባባል ነው። አፋሮችም የኢትዮጵያ ሕዝብ መሬታችንን እንጂ እኛን አይፈልገንም ይላሉ። ለግጭቱ መንስኤ ብዙ ታሪክ ቢኖርም ይህንን ግጭት ያቀጣጠለው፤ የአፋርን ባንዲራ አውርደውና አቃጥለው የሶማሌ ባንዲራ መሰቀሉ እና ያንን ለማስከበር የሔዱ ልዩ ኀይሎች ደግሞ መገደላቸው ነው።
እኔ እስከማውቀው የአፋር ክልል ለእነዚህ ቀበሌዎች በጀት ይሰጣል። ክልሉ ለራሱ ደሃ ነው፤ “እኛ የሌለንን አንቡላንስ ሰጥተናል፤ እነርሱን ለማቀፍ ያለንን እያካፈልን ነው” የሚል ነገር ይሰማል። ስለዚህ መሬቱን እንጂ ሕዝብን አይፈልጉም የሚባለው ነገር እውነት አይመስለኝም፤ ይሔ የአክቲቪስት ቋንቋ ነው።

የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥትን የሰላም አያያዝ እንዴት ይገመግሙታል?
እስከአሁን ባየሁት ብዙ ኮንፈረንስ ነበር፤ የአፋርና የኢሳ የሰላም ኮንፈረንስ። ልዩነቱን የማየው፤ አንደኛ ድርድሩ ራሱ መመጣጠን የጎደለው ነው፤ የፌዴራል መንግሥትም ያላየው ነው የምለው፤ አፋርና ኢሳ ቢባልም፤ በስርዓት ደረጃ ግን በዚህ የአፋር ክልል በዚህ የኢሳ ጎሳ አለ። ክልልና ጎሳ ሲደራደር ምን ዓይነት ውሳኔ መወሰን ይችላል የሚለው መታየት አለበት። በእኔ ዕይታ ከዚህ አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎ በኹለቱ ክልሎች መካከል የግጭቱ መንስኤ ምንድን ነው? እንዴት ይፈታ? ምን የጋራ ፕሮጀክች አሉ? በሚል በመንግሥት ደረጃ መታየት አለበት።

አፋር ካለው የተፈጥሮ አቀማመጥ አንጻር የቱሪዝም መስህብ መሆን የሚችል ነው። እንደዛም ሆኖ በቱሪስም ፍሰት ብዙ ይቀረዋል። በተፈጥሮ የታደለውን እምቅ አቅም ያክል በልማት ያልቀደመበት ምክንያት ምንድን ነው?
ክልሉ ያለው እምቅ ሀብት ሲታይ እና ያለበት የዕድገት ደረጃና ሥራ አጥነት ተመጣጣኝ አይደለም። ስለዚህ አሳታፊ በሆነ መንገድ ቢሠራ አፋር በፍጥነት መልማት ከሚችሉ የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱ ነው። ጨው፣ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርትና መሰል፤ እንዲሁም የሶላር ኢነርጂና የጂዮ ተርማል ዘርፍ አለ።

ክልሉ እንደተባለው የጂዪ ፖለቲካል አቀማመጡ ራሱ ገንዘብ ነው፤ መጠቀም ከተቻለ። አገልግሎት ሲጪ ዘርፉ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ቢመቻች ትልቅ ነገር ነው። እኛም ‘ኢኮ ቱሪዝም’ን ማካሔድ እንፈልጋለን፤ ይህም የአካባቢውን ነገር ሳይለውጥ ያለው ሁኔታ ተጠብቆ እሳተ ጎመራውን ኤርታሌን ማሳየትን ጨምሮ ብዙ መታየት ያለባቸው ድንቅ ሀብቶች አሉ። ነገር ግን አልተሠራባቸውም። ከአፋር ክልል አልፎ ለአገር የሚበቃ ብዙ ነገር አለ፤ እዛ ላይ መዋዕለ ነዋይ እንዲፈስ አልተደረገም።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ትልቁ ችግራችን ኀይል ነው። በትንሹ ለአፍሪካ የሚበቃ ኀይል በአፋር አለ። እዛ ላይ ትንሽ ኢንቨስት ቢደረግ ጥሩ ይሆናል። ሌላው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች አሉ፤ ሸንኮራ ተዘርቶበት ምንም ምርት ያልሰጠ አለ፥ እንደ ተንዳሆ ዓይነት። ምናልባት ቦታው እህል ተዘርቶበት ሰው በልቶ ጠግቦ፤ ከዛ በኋላ መሐል አገር ያለውን የኑሮ ውድነትም ዝቅ ሊያደርግ የሚችል ሁኔታ ስላለ፤ በአፋር ትልቁ ነገር የፖሊሲ አቀራረጽ ችግር ነው።

የምርጫ ረቂቅ ሕግ ብዙ ውዝግብ አስነስቷል። የእናንተ ምላሽ ወይም አቋም ምንድን ነው?
እኛ ጋር ኹለት ዕይታ ነው ያለን፤ የፓርቲዎች ሰብሳቢ ነን። ረቂቅ ሕጉ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንፈልጋለን። እንደፓርቲ 10 ሺሕም መሥራቾች ለማስፈረም ሥጋት የለንም። አንዳንድ ፓርቲዎች ግን ችግር ሊፈጥርባቸው እንደሚችል እንረዳለን።

ዞሮ ዞሮ ወደ አገራዊ ስዕል መቀየር አለበት። እንደፓርቲ [ረቂቅ ሕጉ] ልክ ነው እንላለን። ሁሉም በየጎጆ ቁጭ ቁጭ ከሆነ ለአገር ምንም ዋጋ የለውም። የኔ ሐሳብ የኔ ርዕይ በአፋር ተከልሎ ብቻ እንዲቆይ ሳይሆን ከአፋር ውጪ ወጣ ብሎ የሚሔድ ነው። ገዢው ሐሳቡ መሆን ለአለበት። በአገር ደረጃ ፓርቲዎችን የመምራት ኀላፊነት ስለተሰጠን ሁሉንም ማጣጣም ይጠበቅብናል።

አፋር ሕዝቦች ፓርቲ ከኢዜማ ጋር ድርድር ላይ ናቸው የሚባል ነገር አለ፤ እውነት ነው?
በአገር ደረጃ በሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ማኅበራዊ ፍትሕን በሚመለከት ከኢዜማ ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለየት ያለ አቋም የለንም። ማኅበራዊ ፍትሕ ካለ አሁን የተነሱ የዜግነትም ሆነ ብሔር ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ። ስለአገር ነው የምናወራው፤ ስለ ግለሰብ አይደለም።

በኢዜማ ውስጥ ያሉ አመራሮች ጋር በውጪ አገር ስንሠራ ነበር፤ በተለይ ማኅበራዊ ፍትሕን በማስፈን ረገድ ኢትዮጵያውያኖች ሁሉ ራሳቸውን የሚያዩባት አገር መገንባት ላይ ልዩነት የለንም።

ከኢዜማ ጋር ልዩነታችን እኛ የክልል ፓርቲ ነን፤ ከምርጫ ቦርድ በዛ እውቅና አግኝተናል። ኢዜማ ደግሞ አገር ዐቀፍ ነው። ስለዚህ ሰው ያጋንነዋል እንጂ አገር ዐቀፍ መሆኑ ለሁሉም ይበጃል። ተስፋ አደርጋለሁ፤ በአገር ደረጃ ከኢዜማ ጋር አብረን እንደምንሠራ። የራሳችን ደግሞ ይዘን የተነሳነው ጥያቄ አለ፤ በአገር ደረጃ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን ማግለል አንፈልግም፤ ማግለልም ሞኝነት ነው።

አፋር የሚኖረው ኢትዮጵያ ስትኖር ነው። ለአፋር ብቻ የሚመጣ ሰላምና ፍትሕ የለም፤ የተያያዘና ተመጋጋቢ ነው። እኛ ከማንም ጋር በወንድማማችነት፣ በአገር ልጅነትና በፍቅር ለመሥራት፤ ከኢዜማ ወንድሞቻችንም ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን። እንደተባለው በተለያየ የፖለቲካ መድረክ ነው የተመዘገብነው፤ ነገር ግን አገርን በተመለከተ የሚያለያየን ነገር የለም።

በአገራችን በታየው ለውጥ በመጀመሪያ የነበረው ትልቅ ተስፋ ነበር። ከዓመት ጉዞ በኋላ ግን ብዙ አስቸጋሪና አጠራጣሪ ሁኔታዎች እያየን ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ተስፋውን እንደያዘ ወደታለመለት ይጓዛል ብለው ያስባሉ?
እኛ እንደ ፖለቲከኞች ትልቁ ምግባችን ተስፋ ነው። የመቀየር እና ለውጥ የማምጣት ፍላጎት ከሌለ ፖለቲከኛ መሆን የለም። በዛ መንገድ ላይ ግን ወጣ ገባ የሆኑ ችግሮች አሉ።

አንደኛው በአራት ድርጅቶች የተመሰረተው ኢሕአዴግ ነው። በእነዚህ ድርጅቶች መካከል ራሱ ብዝኀነት የለም። በመካከላቸው መለያየት እንዳለ እናያለን። ከዛ አልፎ በእያንዳንዱ ድርጅት ውስጥ የራሱ የሆነ የመከፋፈል ሁኔታ አለ።

ከዚህም በተጨማሪ አጋር ፓርቲ ብለው በሪሞት የሚያሠሯቸውን ፓርቲዎች እንዴት ነው ለማካተት የሚሞክሩት የሚለውም አንዱና ሌላው ችግር ነው። መሪው ድርጅትና ከእሱ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች አሉ።

ሌላው የተቃዋሚ ድርጅቶች ነን። ጠንከር ብሎ የመውጣት ሥራ ካልተሠራ አሁን ባለንት ከ100 በላይ ድርጅቶች አገር መምራት የማይችሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሔን የፖለቲካ ማኅበረሰብ ሰብሰብ ማድረጉ ትልቁ ሥራ ይመስለኛል፤ በኢሕአዴግም በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርዎችም በኩል ያለው ትልቁ የቤት ሥራ ይሔ ይመስለኛል። ሰብሰብ ብሎ ለሕዝብ እና ትውልድ ተሸጋሪ የሆነ ርዕይ ማምጣት የሚችለው የትኛው ነው የሚለው መታየት አለበት።

አፋሮች የሰው ልጅ የመጨረሻው ወዳጁ ተስፋ ነው ይላሉ። ለፖለቲከኞች ትልቁ ነገር ተስፋ ነው። ስንነሳ የሰውን ሕይወት በመለወጥና የራስንም ግብ በማሳካት ተስፋ ስለሆነ፤ ተስፋ አለ።

ስለዚህ ለውጡ የታሰበለትን ግብ ይመታል ብለው ያስባሉ?
ለውጡን ለውጥ የምናደርገው እኛ ነን፤ ከሌላ የሚመጣ ነገር የለም። ለውጡ ግብ እንዲመታ ማድረግ ያለበት ሕዝቡም ነው፤ ለውጥ በአንድ ሰው ብቻ የሚመራ አይደለም። ለውጡ እዚህ ደረጃ የደረሰውም በሕዝብ ግፊት ስለሆነ አሁንም ማሻገርና ማስቀጠልም የሚችለው ሕዝብ ነው፤ ስለዚህ ሕዝብ እስካለ ድረስ ለውጥ ይኖራል። የሚጠበቁ ለውጦች ምናልባት መጠናቸው፣ ተጽዕኗቸው እና ደረጃቸው ለየት ቢልም ለውጥ መጥቷል፤ ይሔ ለውጥ ደግሞ ለራሳችን ብለን ነው ልናስቀጥለው የምንችለው። ሕዝቡም እንደዛ ነው ማየት ያለበት።

የለውጥ ሒደቱ በመጣበት ፍጥነት ለምን ለመሔድ አልቻለም?
ይህን በኹለት መንገድ ነው የማየው። አንደኛው መሪው ድርጅት ለውጥ መጣ እንጂ ለውጡን በቀጣይነትና ጠንክሮ እንዲወጣ የነበረው አካሔድ ጥንካሬው ይህን ያህል አልነበረም። ለውጡ ሲመጣ ኢሕአዴግ ራሱ ተከፋፍሎ የመጣ ለውጥ ስለሆነ የሁሉንም ይሁንታ ያገኘ አልነበረም።

ኹለተኛው በሕዝብ ደረጃ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በአክቲቪስቶች ይህን ለውጥ ለማስቀጠል የተሠሩ መሠረታዊ ሥራዎች እምብዛም ነበሩ። አክቲቪስት ሕዝብን የማነቃቃት ሥራ ካልሆነ በተለይ ለውጡን ተቋማዊ ማድረግ ላይ ድጋፍ አልነበረም። ተቋማት ጠንካራ አልነበሩም፤ የፍትሕ ተቋም ቢባል፤ የሕግ የበላይነትን የሚያስጠብቁ ተቋማት ጠንካራ አልነበሩም። እነዛ ተቋማት ብዙ ዝግጅት ስላልነበራቸው በየቦታው እንደምናየው ባንክ ይዘረፋል፣ ሰው ይሰቀላል፣ ሰው ይገደላል። ይህ ማለት የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩ አካላት ረግበው ነበር ማለት ነው። ስለዚህ ነው ወደምንፈልገው ደረጃ መሔድ ያላስቻለን እሱ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው።

ኢሕአዴግ በዚህ መፍረክረክ ውስጥ ሆኖ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ እሔዳለሁ ብሏል። ምርጫም ተቃርቧል፤ ኢሕአዴግ የሚሳካለት ይመስልዎታል?
ኢሕአዴግ እስካሁን ድረስ በሚገርም ሁኔታ እንደ ግንባር ነው ራሱን የሚያየው። አሁን ሥማቸውን ያልቀየሩም አሉ፤ ለምሳሌ ሕወሓት አንዱ ነው። አሁንም ነጻ አውጪ ነው፤ መሠረታዊ ለውጥ የለም። ግማሹ ነጻ አውጪ ነው፤ ግማሹ ፓርቲ ነው። በጠቅላላው ደግሞ ግንባር ነው። በዚህ ሁኔታ የውህደቱ ነገር እንዴት ነው አጣጥሞ ማስኬድ የሚቻለው። ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ ለመምጣት በቅድሚያ መቀረፍ ያለባቸው ነገሮች አሉ። ስለዚህ የኢሕአዴግ ውሕደት በቅርብ የሚሳካ አይመስለኛም።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here