የተማሪዎች የደንብ ልብስ ልገሳ እና የአምራቾቹ ቅሬታ

0
1646

ያለንበት 2011 አሮጌ ብለን አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዋዜማው ላይ እንደመገኘታችን መጠን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን የምንሰማቸው የደብተርና የስክርቢቶ እንዲሁም የሌሎች ተዛማጅ የትምህርት ግብዓት ማስታወቂያዎች የወቅቱ ድምቀቶች እና ለተማሪዎች ደግሞ የዕረፍት ወራታቸው መገባደዱን ማብሰሪያ ደውሎች ናቸው። በመዲናችን አዲስ አበባ ደግሞ ከዚህ ባለፈ የተማሪዎች የደንብ ልብስ ገበያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚደራበት በዚህ ወቅት ላይ ነው። በርካታ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅፋ የያዘችው አዲስ አበባ ከሌሎች የክልል ከተሞች ይልቅ የደንብ ልብሶችን በስፋት በመጠቀም የሚስተካከላት የለም።

ይህንም ተከትሎ በርካታ የደንብ ልብስ አምራቾች ከሾላ ገበያ እስከ ኻያ ኹለት፤ ከመርካቶ እስከ ኮልፌ የመመገቢያና የእንቅልፍ ጊዜያቸውን ሳይቀር ሰውተው ቀን ከሌት በመሥራት ጊዜያዊ የሆነውን የገበያ ሲሳይ እንዳያመልጣቸው ይተጋሉ። ይህ ሁሉ ርብርብ ግን ታዲያ ተረት የሆነ ይመስላል። አምራቾችም ትናንትን በትዝታ ብቻ እየኖሩ የዘንድሮ የደንብ ልብስ ገበያን እጃቸውን አጣጥፈው በሐዘን ተውጠው እየሸኙት ይገኛሉ።

ሰለሞን አማን የተዘጋጁ የደንብ ልብሶችን ለተማሪዎችና ለሆቴል ቤት አስተናጋጆች በመሸጥ እንዲሁም በትዕዛዝ በማዘጋጀት ሥራ ላይ ከተሰማራ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል። እንደ ሰለሞን ገለጻ፥ ለወትሮው የትምህርት መጀመሪያ ቅድመ ወራት ላይ የሚኖረው የተማሪዎች የደንብ ልብስ ገበያ ፋታ የሚነሳ እንደነበርና ከገቢም አንጻር ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚገኝበት ወቅት እንደሆነ ይናገራል። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ 680 ሺሕ ተማሪዎች ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ነፃ የደንብ ልብስ እንዲከፋፈል በመወሰን ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል።

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገበያው ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፤ ይባስ ብሎ ደግሞ ዋና ገበያችን ተዘጋብን” ይላል ሰለሞን አዲስ ማለዳ በሚሠራበት ስፍራ ተገኝታ ባነጋገረችው ወቅት። ጉዳዩ እንዲህ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነጻ ሊያከፋፍል ላሰበው የተማሪዎች ደንብ ልብስ የማምረቱን ዕድል የሰጠው ለጥቂት እና ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ድርጅቶች ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሰለሞን ላሉ የልብስ ስፌት ድርጅቶች ትልቅ ኪሳራ ነው። ሰለሞን በአማካኝ አንድ የደንብ ልብስ ከስድስት መቶ ብር እስከ ዘጠኝ መቶ ብር እንደሚሸጥና በቀን እስከ 7 ሺሕ ብር ሽያጭም እንደነበረው ተናግሮ በዚህ ዓመት እንዲህ መሆኑን ግን አምኖ መቀበል አልቻለም።

“እኛ ከተማ አስተዳደሩ የጀመረው እንቅስቃሴን በሙሉ ልባችን እንደግፋለን ነገር ግን ይህን ያህል ብዛት ያለው ዩኒፎርምን ለኹላችንም በማከፋፈል እንድንሠራ ቢያደርገን መልካም ነበር” የሚለው ሰለሞን የደንብ ልብሱን እንዲያመርቱ ድርጅቶች ሲመረጡ ግልፅ እና አካታች ጨረታ እንዳልተደረገና የተመረጡት ብቻ ዕድሉን እንዳገኙ ተናግሯል። በሥሩ 6 ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ሰለሞን ጠብቆት የነበረው የደንብ ልብስ ገበያ በመቀዛቀዙ ሠራተኞችን ነገ ዛሬ ሳይል ለመቀነስ እንደሚገደድ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

አዲስ ማለዳ አሁንም ቅኝቷን እንደቀጠለች ነው። ከኻያ ኹለት ማዞሪያ ወደ ቴሌ መድኀኒያለም በሚወስደው መንገድ ላይ ወቅቱን ተከትሎ ይታይ የነበረው የደንብ ልብስ ገበያ ግብዓተ መሬቱ እንዳይፈፀም የሚንገታገት ይመስላል። በዚሁ አካባቢ ሃምሳ ሠራተኞችን በቋሚነትና ተጨማሪ ዐሥር ሠራተኞችን በጊዜያዊነት ቀጥራ የምታስተዳድረው ኤልሳቤጥ ጌታቸው ስለ ጉዳዩ ቅሬታዋን ታሰማለች።

“አስቀድሞ ሳይነገረን ከዚህ ቀደም እንደምናደርገው በርካታ ደንብ ልብሶችን አምርተን ከጨረስን በኋላ ከተማ አስተዳደሩ እንዲህ ዓይነት መልካም የሚመስል ግን እኛን የሚገድል ሐሳብ ይዞ በመምጣት ከጨዋታ ውጪ አድርጎናል” ስትል ትናገራለች። ኤልሳቤጥ በዚህ ሥራ ላይ ስድስት ዓመታን አሳልፋለች፣ በርካታ ውጣ ውረዶችንም አሳልፋለች ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ከመንግሥት በኩል የተቃጣ የኪሳራ አደጋ ግን ገጥሟት አያውቅም። “ዓመቱን ሙሉ የምሠራው እኮ በዚህ ወራት እንደምሰራው የደንብ ልብስ ገበያ አይሆንም” የምትለው ኤልሳቤጥ ከባድ ኪሳራ እንደተጋረጠባት ትናገራለች። “እሺ አሁን ያዘጋጀኋቸውን ልብሶች ምን ላደርጋቸው ነው” ስትልም ግራ በተጋባ እና ሐዘን ባጠላበት ስሜት ራሷን መልሳ ትጠይቃለች። ለወትሮው ኤልሳቤጥ ከነሐሴ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ መስከረም ግማሽ እና መጨረሻ ድረስ ከተማሪዎች የደንብ ልብስ ጋር በተያያዘ በቀን እስከ 20 ሺሕ ብር ሽያጭ እንደሚኖራት ለአዲስ ማለዳ አልሸሸገችም። ይሁን እንጂ እነዛ አቅልን አስቶ የሚያከንፈው የደንብ ልብስ ገበያ አሁን ሙሉ በሙሉ ባይባልም አክትሟል። “ዋናው ገበያችን ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች በኩል እንጂ አሁንም የግል ትምህርት ቤቶችም ከእኛ ይገዛሉ ነገር ግን የለመድነው እንደዚህ አይደለም” ስትል ትናገራለች።

በቅርቡ ከተማ አስተዳደሩ የማምረት ሥራውን ለግዙፎቹ “ቢግ ኤም”፣ “አይካ አዲስ” እንዲሁም “ብራስ ጋርመንት” መስጠቱን ተከትሎ ከላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸውን ጨምሮ ከኻያ የሚበልጡ የደንብ ልብስ አምራቾች ተሰባስበው አቤት ለማለት ወደ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አምርተው ነበር። ነገር ግን ያገኙት ምላሽ “ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጣ ትዕዛዝ ነው፣ ጉዳዩ አስቸኳይ ስለሆነ በአንድ ጊዜ በርካታ የደንብ ልብሶችን ማምረት የሚችሉት ብቻ ናቸው የተመረጡት እና በመጨረሻም እባካችሁ ጽሕፈት ቤቱን ለቃችሁ ውጡ” የሚሉ ሦስት ምላሾችን እንዳገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት መንግሥት በዝቅተኛ አቅም ያላቸውን ድርጅቶች አጎለብታለሁ እያለ ባለበት ሰዓት እንዴት ግዙፎቹ እንዲውጡን ያደርጋል ሲሉም ተደምጠዋል። መጪው የግብር መክፈያ ወራት እንደመሆኑ መጠንም የሚጣልባቸውን ግብር ለመክፈል የሚያስችላቸው አቅም ላይ ለመገኘታቸውም እርግጠኞች መሆን አልቻሉም።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው የልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤት ጌታቸው ዓለሙ፤ ጉዳዩ በቀጥታ ባይጎዳውም የጎረቤቶቹ መጎዳት እንደሚያመው እና በተዘዋዋሪ ዳፋው ለእሱም እንደሚተርፍ ግን ግን አልሸሸገም። “እኔ ዋነኛ ደንበኞቼ የግል ትምህርት ቤቶች ናቸው ነገር ግን የመንግሥት ትምህርት ቤት ደንበኞች ያሏቸው ድርጅቶች ደንበኞቻቸው ሲነጥፉ የእኔን ደንበኞች መጋራታቸው የማይቀር ነው” ሲልም ጉዳቱን ያያይዘዋል። ቀጥሎም ይኸኛው ዓመት በዚህ ዓይነት መልኩ ቢጠናቀቅም ለቀጣዩ ዓመት ከዚህ የተለየ ይሆናል ብሎ እንደማይጠብቅና በዚሁ ከቀጠለ የልብስ ስፌት ኢንዱስትሪው በከፍተኛ መጠን እንደሚጎዳም አስተያየቱን አስቀምጧል።

ጉዳዩን በሚመለከት አዲስ ማለዳ አዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን አነጋግራ ነበር። የጽሕፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክረታሪ ፌቨን ተሾመ እንደሚሉት ፕሮጀክቱ ግዙፍና አገራዊ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ተጠቃሎ መረከብ ስለምንፈልግ አቅም ያላቸውን ድርጅቶች ብቻ ነው የጋበዝነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። አያይዘውም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን የሚነዛው እና የከተማ አስተዳደሩ በልብስ ስፌት የተሰማሩትን ለማዳከም እየሠራ እንደሆነ ተደርጎ የሚወራው ከእውነት የራቀ እንደሆንም አስረግጠው ተናግረዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ግልፅ ጨረታ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አውጥቶ እንደነበረና ኹሉም መስፈርቱን የሚያሟሉ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ክፍት እንደነበር ተገልጿል። ይሁን እንጂ ጽሕፈት ቤቱ ጨረታውን በሙሉ እና በከፊል የመሰረዝ መብቱ የተጠበቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተመረጡትን ድርጅቶች ብቻ በማካተት ዝግ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here