በስህተት ተፈትተው የታሰሩት ባለሀብት ጉዳያቸው በድጋሚ ይታያል

0
741

በአራጣ ማበደር፣ በታክስ ማጭበርበር፣ በሀሰት ማስረጃና በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር 25 ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የነበሩት ከበደ ተሰራ የፌደራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ በመሻሻሉ እና የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 22(2) በሚደነግገው መሰረት በአዲሱ አዋጅ መሰረት የእስር ቅጣቴ ሊቀንስልኝ ይገባል በሚል ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ይሁንና የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተከሳሹ በቀረቡባቸው የተለያዩ ክሶች ላይ ከባድ በሚል ከመውሰዱ ባሻገር እያንዳንዱን ክስ መሠረት አድርጎ የቅጣት ጊዜን ስላልወሰነ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በአዲሱ አዋጅ መሠረት የቅጣት ውሳኔ እንደገና አስልቶ መስራት እንደማይችል ገልፆ መዝገቡን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡
በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ጉዳዩን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነበር ሰኔ ወር 2009 ከበደ ተሰራ ከሌሎች 91 ታራሚዎች ጋር በፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ይቅርታ ተደርጎላቸው ከእስር የተፈቱት፡፡ በዚህም ምክንያት የእስር ቅጣቴ ሊቀንስልኝ ይገባል በሚል ያቀረቡት አቤቱታ ሊዘጋ ቢችልም ይቅርታው የተሰጠው በስህተት ነው በሚል ምክንያት ከዐሥር ቀን በኋላ በድጋሜ ታስረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከበደ ተሰራ መጋቢት 10 ቀን 2010 የእስር ቅጣት ይቀነስልኝ የሚለውን አቤቱታ በድጋሜ ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ችሎት አቅርበዋል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ አቤቱታው የቀረበው ምሕረቱ ስህተት መሆኑ ታውቆ ወደ እስር ቤት ከተመለሱ በኋላ ያለ በቂ ምክንየት ከስምንት ወር በላይ ቆይተው መዝገቡን ማንቀሳቀስ አይችሉም ሲል ወስኗል፡፡
አቶ ከበደ ተሰራም ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ሲሉ ጉዳዩን ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበውታል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም ጉዳዩን መርምሮ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ስርዓት ለይግባኝ ማቅረቢያና ለተያያዥ ጉዳዮች የጊዜ ገደብ ቢያስቀምጥም የተዘጋ መዝገብ እንደገና ለመክፈት የሚቀርብ አቤቱታ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንዳለበት ገደብ እንዳላስቀመጠ አመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በተያዘው ጉዳይ መዝገቡ እንዲዘጋ ምክንያት የሆነው የከበደ ተሰራ ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ሳይሆን ይቅርታውን የሰጠው አካል ስህተት መሆኑን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ገልፆአል፡፡
በመሆኑም የተዘጋ መዝገብ በድጋሜ እንዲንቀሳቀስ አቤቱታ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ ባልተቀመጠበት እና ለመዝገቡ መዘጋት አመልካቹ ጥፋተኛ ባልሆኑበት ሁኔታ አመልካች ያለበቂ ምክንያት አቤቱታቸውን ሳያቀርቡ ቆይተዋል በማለት ጠቅላይ ፍ/ቤቱ የሰጠው ውሳኔ የአመልካችን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚያጣብብ እና መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊሻር ይገባ ሲል ሰበር ሰሚ ችሎቱ ወስኗል፡፡
በዚህም መሠረት ጉዳዩን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በድጋሜ ጉዳዩን እንዲያየው የተወሰነ ሲሆን ከበደ ተሰራ የፌደራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ መሻሻሉን ተከትሎ የእስር ቅጣት እንዲቀንስላቸው ያቀረቡት አቤቱታ በዚሁ ፍርድቤት ታይቶ የሚወሰንበት ይሆናል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here