ኃይሌ ሪዞርት ባሳለፍነው በጀት ዓመት 150 ሚሊዮን ብር ገቢ አገኘ

0
739
  • እ.አ.አ በ2025 የሆቴሎቹን ቁጥር ሃያ ለማድረስ አቅዷል
  • በጅቡቲ፣ ሶማሊያና ኤርትራ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ አቅዶ እየሠራ ነው

ኃይሌ ሪዞርት በአራት ሆቴሎች ለመሰብሰብ አቅዶ ከነበረው 167 ሚሊዮን ብር ገቢ 150 ሚሊዮን ብር ማግኘቱ ታወቀ።
ሆቴሎቹ በዕቅድ ከተቀመጠላቸው ገቢ አንጻር 89 በመቶውን ቢያሳኩም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ አለመረጋጋቶች የውጪ አገራት ቱሪስት ፍሰት መቀነሳቸውና ሌሎች ውስጣዊ ምክንያቶች ገቢው እንዲቀንሰ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ታውቋል።
በተያያዘ ዜና ኃይሌ ሪዞትር በአሁኑ ወቅት ጎንደር የሚገኘውን ‹‹ላንድ ማርክ›› ሆቴል ለ15 ዓመታት በሚዘልቅ እና በየአምስት ዓመቱ የሚታደስ ውል የተረከበው ሲሆን፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ታውቋል። ተጨማሪ የሆቴል ግንባታዎችን ለማከናወን በወላይታ ሶዶ መሬት የተረከበ ከመሆኑም ባሻገር በደብረ ብርሃንም ለሆቴል ግንባታ የሚውል መሬት ለመረከብ ዝግጅት ላይ እንዳለም ለአዲስ ማለዳ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገልጸዋል።
በኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ድርጅቶች ሥር የሚገኘው ኃይሌ ሪዞርት ከስምንት ዓመት በፊት በሐዋሳ የመጀመሪያውን ሪዞርት በመክፈት ሥራ መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን እ.አ.አ 2025 የሆቴሎቹን ጠቅላላ ብዛት ወደ 20 ለማድረስ እየሠራ መሆኑ ታውቋል። በሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ አርባ ምንጭና ሱሉልታ ካሉት ሆቴሎች በተጨማሪ በአዳማና አዲስ አበባ ግንባታዎችን እያካሔደ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ኤርትራን ጨምሮ በተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በተመሳሳይ መዋዕለ ነዋይ ለማፍስስ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የቀድሞው ኮረብታማ ሆቴል 10 ሺሕ ካሬ ሜትር ጊቢ ላይ ያረፈ አዲስ ሆቴል በመገንባት ላይ ነው።
ኃይሌ ሪዞርት ከ2008 ጀምሮ የሆቴል አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በሆቴልና መስተንግዶ ዘርፍ ሥልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን 400 ተማሪዎችን ማስመረቁንና ከእነዚህም 83 በመቶዎቹን በሥሩ ለሚገኙ ሆቴሎች እንዲቀጠሩ አድርጓል። በአጠቃላይ ሆቴሎቹ አማካኝነት ለአንድ ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here