የማስተማሪያ ቋንቋ ጉዳይ

0
1057

ቤተልሔም ነጋሽ የአፍ መፍቻ ቋንቋን ትምህርት ለማስተማር ተግባራዊ የተደረገውን ፖሊሲ በተመለከተ የሐረሪ ክልልን እንደማሳያ ተጠቅመው እንዲሁም በጉዳዩ ዙሪያ የተጠና ጥናትን ዋቢ አድርገው ፖሊሲው ከአተገባበሩ ጋር አልተጣጣመም ሲሉ መከራከሪያቸውን ተግዳሮት ካሏቸው ነጥቦች ጋር አቅርበዋል፤ ፖሊሲው ክለሳና ማሻሻያ ያስፈልገዋልም ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።

 

 

ከኹለት ዓመታት በፊት ይመስለኛል የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንስቶ የተወያየበት አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኀንን ትኩረት ስቦ ነበር። ፓርላማው ያለው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ተምረው፣ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን የጨረሱ ከክልሎች የመጡ ተመራቂዎች በፌደራል መሥሪያ ቤቶች የሥራ ዕድል ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱም የፌደራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ መናገር ስለማይችሉ።

ይህ ጉዳይ ቀደም ብሎ በአንድ ዓለም ዐቀፍ ድርጅት ስሠራ የነበረኝን ገጠመኝ የሚያስታውስ ነው። በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራ የነበረው የዚያን ጊዜ ቀጣሪዬ በጋምቤላ ሥራውን የሚያስተባብር የጤና ባለሙያ ቀጥሮ ነበር። በኋላ ብለምደውም በመጀመሪያ ያስገረመኝ የሥራ ባልደረባዬ አማርኛ ቋንቋ ስለማይችል በእንግሊዝኛ ለመነጋገር መገደዳችን ነበር።

አገራችን ልጆችን አንደኛ ደረጃ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር ከጀመረች ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። ይህ አሠራር የሚለወጥበት ሁኔታ መኖሩን ባላውቅም በአጠቃላይም የትምህርት ሥርዓቱ ችግሮች እንዳሉበት ታይቶ አዲስ ፍኖተ ካርታና ምናልባት ከቀደመው እኛ ከተማርንበት ጋር ተመሳሳይ ወደ ሆነ አሠራር የመመለስ ተግባር መጀመሩ ሁላችንም የምናውቀው ነው። በበኩሌ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የማስተማር ጉዳይም አብሮ ቢታይ እላለሁ።

ሐረሪ እየተባለ በሚጠራው ሐረር ከተማ ተወልጄ ባድግም በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ሳይሆን በቀደመው 12ኛ ክፍል ማትሪክ ተፈትኜ ያለፍኩ በመሆኑ እንደዛሬው ዘመን 10ኛ ክፍል ላይ በአስገዳጅነት የሐረሪ ቋንቋ ተምሬ ፈተና የምቀመጥበት አግባብ አልነበረም። ለነገሩ በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች 10ኛ ክፍል ላይ ሐረሪ (በቀድሞው አጠራር አደርኛ) የሚባለውን ቋንቋ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ተምረው ለብሔራዊ ፈተና እንደሚቀመጡ የሰማሁት በቅርቡ በከተማው በመምህርነት ሥራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ የቤተሰቤ አባላት ነው።

የወሬው መነሳት ምክንያት መምህራኑ ራሳቸው ትኩረት የማይሰጡት የመማር ማስተማር ሥራ ዓመቱ መጨረሻ ፈተና ሲመጣ ተማሪዎቹ ምንም ሳይማሩ እየተፈተኑ ውጤት እያጡ የመሆኑ ዜና ነው። “ራሳቸው ተናጋሪዎቹና ክልሉ ትኩረት ያልሰጡትን ቋንቋ ለምን ሌላው ተወላጅ እንዲማርና ፈተና ላይ እንዲቀመጥ ያደርጉታል?” የሚለው ጥያቄም አብሮ ተነስቶ ነበር። የሐረሪ ክልል ነገር መቼም ከዚህ በፊት በፃፍኩት ጽሑፍ ለማንሳት እንደሞከርኩት ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የተለየ ነው፤ ይኸውም ክልሉ የተሰየመበት ሐረሪ ብሔረሰብ በክልሉ ካሉ ነዋሪዎች አብዛኞቹን አይደለም አንድ አራተኛውን የማይሞላ መሆኑ ነው። ክልሉ በብሔረሰቡ ቋንቋ ማስተማሩ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ሌሎች መላው የክልሉ ነዋሪ ተማሪዎች ግን እንዲማሩ ማስገደዱ፣ ቋንቋ ምን ይጎዳል ብንል እንኳን በአግባቡ ትኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ ውጤታማ በሚሆኑበት መልኩ ማስተማር አለበት የሚለው ነው ጉዳዩ።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ ውሱን በኦሮምኛና ሐረሪ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ችግር በተደጋጋሚ የሚነሳባቸው ስለመሆናቸውና የብሔረሰቡን ቋንቋ የሚናገሩ ወላጆችና ከዚያ ብሔር ነን የሚሉ ቤተሰቦች ሳይቀር ልጆቻቸውን በሌሎች ትምህርት ቤቶች ማስተማር እንደሚመርጡም ነግረውኛል።
ሁኔታውን የተሻለ ለመረዳት እንዲያስችል ስለሐረሪ ክልል መረጃ ለመስጠት ያህል፤ በ19 ቀበሌዎች የተከፈለችውን ሐረር ከተማንና በዙሪያው ያሉ ኦሮምኛ ተናጋሪ 17 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራትን ይዞ የተመሠረተው የሐረሪ ክልል በኢትዮጵያ ትንሹ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሕዝቡ በከተማ የሚኖርበት ብቸኛ ክልል ነው። በመጀመሪያው የክልል አወቃቀር ክልል 13 ተብሎ የነበረና በነዋሪው ዘንድም የልዩ ልዩ ብሔረሰቦችን ስብጥር የያዘ እንደመሆኑ እንደ ድሬዳዋ የፌደራል ከተማ ይሆናል የሚል ተስፋ የነበረ ሲሆን፤ በኋላ ሐረሪ ክልል የሚለውን ሥያሜ አግኝቷል።

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ወቅታዊ ግምት 246 ሺሕ ነዋሪዎች ያሉት ሐረሪ ክልል በኤጀንሲው ይፋዊ ግምት መሠረት 56.41 በመቶ የኦሮሞ፣ 22.77 በመቶ የአማራ፣ 8.65 በመቶ ደግሞ በድሮው አጠራር አደሬ ለክልሉ መጠሪያ በሆነው በአሁኑ አጠራር የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ሲኖሩበት የጉራጌ 4.34፣ የሶማሌ 3.87 የትግራይ 1.53 የአርጎባ 1.26 እንዲሁም ሌሎች ተብለው የተጠቀሱ 1.1 በመቶ ሕዝቦች መኖሪያም ጭምር ነው።

በ1987 ወጥቶ የነበረው የመጀመሪያው የክልሉ ሕገ መንግሥት ከነበረው ታሪካዊ ሁኔታና በወቅቱ ከሚነገርበት ስፋት አንጻር አማርኛ የክልሉ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሲወስን በ1997 መስከረም ተሻሽሎ የወጣውና አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች ሐረሪና ኦሮምኛ መሆናቸውን ይደነግጋል። ሆኖም ከተናጋሪ ብዛት አንጻርና የአስተዳደሩ መቀመጫ፣ አብዛኛው የክልሉ አካል ሐረር ከተማ በመሆኑ አሁንም የሥራ ቋንቋው አማርኛ ነው። በክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶችም ከጥቂት በኦሮምኛና አንድ በሐረሪ ቋንቋ ከሚሠራ ትምህርት ቤት ውጪ 95 በመቶ ትምህርት ቤቶች በአማርኛ የሚያስተምሩ ናቸው።

በሐረሪ ክልል አብዛኛውን ክፍል በሚይዘው ሐረር ከተማ ከ40 በላይ አንደኛና መለስተኛ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ከትምህርት ቤቱ አራቱ ብቻ በከፊልና ሙሉ በሙሉ ኦሮምኛ (የተማርኩበት አንደኛ ሞዴል አንደኛና መለስተኛ ኹለተኛ ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ኦሮምኛ እና ቁንድዶና አቦከር በአማርኛና ኦሮምኛ) እንዲሁም ኹለቱ ሙሉ በሙሉና በከፊል (አማርኛና ሐረሪ በራስ መኮንን፣ ጀጎል የሚገኘው መድረሳ ሙሉ በሙሉ በሐረሪ) ከማስተማራቸው በቀር ሌሎቹ ትምህርት ቤቶች የማስተማሪያ ቋንቋቸው አማርኛ ነው።

በሚገባ የማውቀውን የሐረሪ ክልልን ጉዳይ እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ በሌሎችም የአገራችን ክልሎች የማስተማሪያ ቋንቋ ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሳ ከሆነ ሰንብቷል። የተለያዩ ጥናቶች የአፍ መፍቻ ቋንቋን እንደማስተማሪያ መጠቀም በጎ ጎን ያለውን ያህል በትግበራ ችግር ምክንያት አማራጭ የሌላቸው ተማሪዎች ካልሆኑ ሌሎች እንደማይደግፉት ያሳያሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት በ2016 (እ.ኤ.አ) የቋንቋ ፖሊሲና ትግበራ በሕፃናት የመማር ሁኔታ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ በሚል ያወጣው ሪፖርት ጥናቶችን ጠቅሶ እንደሚለው፥ በኢትዮጵያ በጥንታዊ መልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የትምህርት ሁኔታ ትምህርት የሚሰጥበት ቋንቋ ግዕዝና አማርኛ የነበረ ሲሆን 1908 (እ.ኤ.አ) ዘመናዊ ትምህርት ሲተዋወቅ አረብኛና ፈረንሳይኛ በተጨማሪ የማስተማሪያ ቋንቋ ሆነዋል። በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ሕዝቡን ለመከፋፈል ቋንቋ ለትምህርት ሲውል ከቆየ በኋላ በ1940ዎቹ ከስደት የተመለሱት አፄ ኀይለሥላሴ አንድነትን ለማጠናከር በሚል የማስተማሪያ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን አድርገዋል። በ1966 ወደ ሥልጣን የመጣው ሶሻሊስታዊው የደርግ ሥርዓት ማይምነትን ለማጥፋት ዘመቻ የተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ሲያበረታታ ቢቆይም ለመደበኛ ትምህርት ሥራ ላይ ግን አማርኛና እንግሊዝኛ ብቻ ጥቅም ላይ ሲውሉ ቆይቷል። ከደርግ መውደቅ በኋላ እንዲሁ በ1986 በወጣው ሕገ መንግሥት አማርኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል ሲደነግግ የፌደራሉ አካላት የሆኑ ክልሎች የየራሳቸውን ክልል የሥራ ቋንቋ የመወሰን ሥልጣን እንደተሰጣቸው ይገልፃል።

በ1986 የወጣው የቋንቋና ሥልጠና ፖሊሲ እንዲሁ በሁሉም ክልሎች ሕፃናት በክልሉ በሚነገረው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ይደነግጋል። ሆኖም መንግሥት ፖሊሲው ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ የየአካባቢው ቋንቋዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ በመፍቀዱ ሁሉም ቋንቋ ሊባል በሚችል መልኩ የየአካባቢው የትምህርት ሥራ ላይ ውሏል።

ይህ አሠራር የትምህርት ሥርዓቱን የሚያግዝ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን በብዙ ቋንቋዎች በማስተማር የባሕልና የቋንቋ ብዝኀነትን በማክበር ልዩ አድርጎ ሲያስቆጥራት፤ አፈፃፀሙ ፖሊሲው ላይ ከተቀመጠው ጋር አብሮ የማይሔድ መሆኑ ሌላ የሚጠቀስ ደካማ ጎን ነው። ጥናቶች እንደሚያስረዱት 30 ያህል ቋንቋዎች በትምህርት ማስተማሪያ ቋንቋነት ሥራ ላይ ውለዋል። ይኸው ተራማጅ ነው የተባለለት ፖሊሲ አፈፃፀም ጥያቄ የሚስነሱ ጉዳዮች እንዳሉበት ባለሙያዎች ሲገልጹ መቆየታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ክፍተት የሚታየው የፖለቲካ ሥልጣን ላይ ያሉት ሳይቀር የተማሩ የሚባሉት በአፍ መፍቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ትምህርት ወደሚሰጥባቸው በአብዛኛው በግል ወደ ተያዙ ትምህርት ቤቶች እንደሚልኩ ሲታይ ነው። ከላይ በጠቀስኩት የሐረሪ ክልል ምሳሌ ሳይቀር ከኦሮምኛ ተናጋሪው የሐረሪ ክፍል (ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት) ሳይቀር ልጆቻቸውን ወደ ሐረር ከተማ ልከው በአማርኛ ቋንቋ ወደሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መላክን ይመርጣሉ።

ከላይ የጠቀስኩት የዩኒሴፍ ሪፖርት እንደሚለው በፖሊሲውና በአተገባበሩ መካከል አለመጣጣም ሊኖር የቻለበት አንዱ ምክንያት ሁሉም የአካባቢ ቋንቋዎች ለማስተማሪያ ቋንቋነት ለመዋል ብቁ አለመሆናቸው መሆኑን ሲጠቅስ ይህም በየአካባቢው ባሉ ተማሪዎች መካከል ትምህርት በእኩልነት መካሔድ እንዳይችል ማድረጉን አንዳንድ አካባቢዎች እንዲበደሉ ጭምር ሆኗል። የመምህራን በእነዚህ ቋንቋዎች በበቂ ሁኔታ ሠልጥኖ በብቃት ለማስተማር አለመቻል ሌላው ተግዳሮት ሲሆን ይኸው ሪፖርት በዚህ ምክንያት ክልል ትምህርት ቤቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሳይሆን በእንግሊዝኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዲሰጡ ግፊት እንዲደረግባቸው ሆኗል። ክልሎቹ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚፈለገው መልኩ የሰለጠነ ብቁ መምህራን የሏቸውም። በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተማሩ ሕፃናት ማንበብና መፃፍ በሚፈለገው መልኩ አለመቻላቸው ሌላው ፖሊሲው ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ከሚታሰበው የተሻለ የትምህርት አቀባበልና ተሳትፎ ጋር አብሮ አይሔድም።

የአፍ መፍቻ ቋንቋን ለማስተማሪነት የመጠቀም ጉዳይ ክለሳና ማሻሻያ የሚገባው አስፈላጊነቱም ጭምር ሊፈተሽ የሚገባና ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎች በማፍራት ረገድ ሌሎች የውጪ ቋንቋዎች ጭምር ተካተው ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ ሊታይ ይገባል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here