በመጠለያ ያሉ ተፈናቃዮች ከአንድ መቶ ሺህ በታች መሆናቸው ተገለፀ

0
627

በተለያዩ ጊዜያት በመላው ሃገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች፣ ከቀያቸዉ ተፈናቅለዉ ከነበሩ 2.3 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 2.2 ሚሊዮኑ ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን እና ከአንድ መቶ ሺህ በታች የሚሆኑት በኦሮሚያ እና በድሬደዋ እንደሚገኙ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘዉዴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በነሃሴ ወር በተደረገው ቅኝት በመላው ሃገሪቱ ያሉ ተፈናቃዮች ከመጠለያ መውጣታቸውን እና በሁለት መንገድ እንዲቋቋሙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ወደ ተፈናቀሉበት አካባቢ መመለስ አንዱ ሲሆን ችግሩ ባስከተለባቸዉ የስነ ልቦና ጫና ምክንያት የመመለስ ፍላጎት ለሌላቸው ደግሞ ባሉበት መኖሪያ ቤቶች እንዲገነቡላቸው መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደሄዱበት ክልል ጋር በመነጋገር ቦታ እንዲያገኙ መደረጉን እና ኮሚሽኑም መኖሪያ ቤት ከመገንባት ባሻገር የተለያዩ ቁሳቁሶች እንደሚያሟላ ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃቹ ከመጠለያ ካምፕ ከወጡ በኋላ ለስድስት ወራት ድጋፍ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ኮሚሽኑ አብዛኛው ተፈናቃይም አርሶ አደር በመሆኑ በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያመርቱ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ በራሳቸዉ ተነሳሽነት አደጋዉ የደረሰበት ቦታ ድረስ በመገኘት ድጋፍ ያደረጉ ወገኖች እንደነበሩ ገልጸው አለማቀፍ ተቋማት ደግሞ የኮሚሽኑን ፈቃድ አግኝተዉ ድጋፍ ማበርከታቸውን ደበበ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በድርቅ የተጎዱ ዜጎችንም ጎን ለጎን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም፣ በመተከል ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በፓዊ ወረዳ (አልሙ) በድንኳን ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች፣ በጎርፍና በዝናብ ምክንያት ለወባ መጋለጣቸውን እና በርካቶችም አካባቢውን ለቀው መሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው መናገራቸውንም ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ ታረቀኝ ተሲሳ በበኩላቸው፣ የቧንቧ ውሃ አልፎ አልፎ ስለሚቆራረጥ የውሃ ችግር ነው የነበረባቸው እንጂ ሌላ ችግር የለባቸውም ብለዋል። ሃምሌ 4/2011 በስፍራው ተገኝተው ማረጋገጣቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ በአካባቢው ያለውን ሰው ሰብስቤ ባነጋገርኩበት ወቅት ይህ ችግር እንዳለባቸው አልነገሩኝም ሲሉ አስታውቀዋል። በስፍራው የእህል ችግር አለመኖሩን የሚያወሱት ታረቀኝ፣ ከእነሱ ተርፎ ዳንጉር ወደሚባል ቦታ መወሰዱንም ገልጸዋል።

እንደ ታረቀኝ ገለፃ፣ የሕጻናት አልሚ ምግብና ዱቄት፣ በቆሎ 15 ኪሎ፣ ዘይት ከመንግስት በኩል በመደበኛ በወር እየቀረበላቸው ሲሆን፣ ከህብረተሰቡ በኩልም እገዛ ተደርጎላቸዋል። ብዛታቸውም በጣም ትንሽ ስለሆኑ እነሱን ለመንከባከብ አልተቸገርንም ብለዋል። ባለፈው ወር ከመድኃኒት ጋር ተያይዞ ችግሮች ገጥሟቸው እንደ ነበር አስታውሰው አሁን ላይ ተፈትቶላቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here