በኢትዮጵያ ኻያ አዳዲስ የእንስሳት ክትባቶችን ለማምረት ጥናት እየተደረገ ነው

0
897

ብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከ20 በላይ የበሽታ አምጪ ባክቴሪያዎችን እና የቫይረስ ዘሮችን በዘረመል ባንኩ ውስጥ በማደራጀት ክትባት ላልተመረተላቸው የእንስሳት በሽታዎች የክትባት ማዘጋጀት ሥራ እንደጀመረ አስታወቀ።

የኢንስቲትቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አደይ አበባ ታምሩ፣ በላቦራቶሪው ውስጥ ያሉትን እና አዲስ የተሰበሰቡ እንዲሁም ክትባቶቹን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉትን የባክቴሪል ተሕዋስያን ዘሮችን ጨምሮ እስካሁን 22 ዘሮች (Genus) እና ከ108 በላይ ዘረመሎች (Species) መደራጀታቸውን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የእንስሳት ሀብት ቁጥር እንዳላት ቢታወቅም፣ ከዚህ ክፍለ ምጣኔ ሀብት የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ ላለመሆኗ እንደ ምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የተለያዩ ተላላፊ የእንስሳት በሽታዎች በብዛት እንስሶቹን ማጥቃታቸው እና አስፈላጊውን ሕክምና ማድረግ አለመቻሉ ነው ሲሉ አደይ አበባ ያስረዳሉ።

ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆነ እንስሳት ዘር በበቂ ሁኔታ ለአርብቶ አደሩ ማራጨት ያለመቻሉ እና ኋላ ቀር የአረባብና የአያያዝ ዘዴ መከተል ሌሎች ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮች መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል።

እነዚህ በሽታዎች የአርብቶ አደሩን ኑሮ ከልፋቱ በታች ከእጅ ወደ አፍ ከማድረጋቸው ባሻገር በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል ያሉት ባለሞያው ለሰው ጤና ጠንቅ መሆናቸው ችግሩን የበለጠ ውስብስብ እንዳደረገውም ያክላሉ።

“ተላላፊ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል የተለያዩ ስትራቴጂዎች አሉ። የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅ ዝቅተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ እና ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ለመከላከልም የባክቴሪያ ተሕዋስያን ዝርያዎች ላይ ምርምር በማካሔድ በአገር ውስጥ ክትባት በማዘጋጀት በሽታዎቹን መከላከል ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።

ኢንስቲትዩቱ የመድኀኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና ማሽን ተከላ ሥራ አጠናቅቆ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምርት ማምረት ሳይችል መቅረቱንና አዲሱ የቫይራል ክትባቶች ማምረቻ በይፋ ሥራ ሳይጀምር መቅረቱን አደይ አበባ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። “ኢንስቲትዩቱ በራሱ በኩል ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የኤሌትሪክ ኀይል እጥረት በመኖሩ ላቦራቶሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት አልተቻለም” ሲሉም አክለዋል። ይህ ብቸኛ አገራዊ ተቋም በሚጠበቀው መልኩ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲችልም ባፋጣኝ ችግሩ እንዲፈታ አሳስበዋል።

በዚህ በጀት ዓመት 5 የተለያዩ የአዳዲስ ክትባቶችን ጥናት ለማካሔድ የታቀደ ሲሆን፣ ክትባቶቹም የዶሮ፣ የበግ፣ የዳልጋ ከብት፣ የአባ ሰንጋና ክትባቶችን ለማዘጋጀት መታሰቡን፣ የአባ ሰንጋና ጎሮርሳ ክትባቶችን ለግመል እንዲሆን ሆኖ የሚዘጋጁ ክትባቶች መሆናቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here