የወረዳ አስተዳዳሪው ላውንቸር እና ሌሎች ከባድ የጦር መሣሪዎችን በማዘዋወር ተጠረጠሩ

0
755
  • የአፋር ክልል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ይዞ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ደርሶታል

በአፋር ክልል ዳሊሳጊ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት መሐመድ የጊሊስ ላውንቸር እና ከባድ መትረየስን ጨምሮ ሌሎች 11 ዓይነት ከባድ እና ቀላል መሣሪያዎችን ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል በሚል ክስ ተመሰረተባቸው።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በመሰረተው ክስ የወረዳ አስተዳዳሪው ከኹለተኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን በመንግሥት መኪና የጦር መሣሪያዎቹን ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል ሲል አብራርቷል። በአፋር ክልል ባቲ ተብሎ በሚታወቀው ኬላ ላይ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እና መኪናውን ሲያሽከረክሩ የነበሩት ጀማል ሁሴን ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የዋስትና መብታቸውን ነፍጓቸዋል።

መሐመድ ጊሊስን ግን የክልሉ ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ ቢታዘዝም ይዞ ለማቅረብ እንዳልቻለ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገለጿል። የክልሉ መንግሥትም የተያዙት ጦር መሣሪዎች የክልሉ ንብረት ከሆኑ እንዲያሳውቅ እንዲሁም የሚዘዋወሩትም ለሥራ ዓላማ ከሆነ እንዲገለጽ ከፍርድ ቤቱ ጥያቄ ቀርቧል።

እስካሁን በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትን አንደኛ ተከሻሽን የፌደራል ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ ችሎቱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን በተመሳሳይም የክልሉ ፖሊስም ተከሻሹን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቶች እስከ ጥቅምት መጀመሪያ በእረፍት ምክንያት በሥራ ላይ ያለመሆናቸውን ተከትሎም ለኅዳር አንድ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ በዕለቱ ፍርድ ቤቱ ክስ እንደሚሰማ ይጠበቃል።

ከመንግሥት አካላት ውጪ በጦር መሣሪያ ንግድ ወይም ያለፈቃድ መሣሪያዎቹን ይዞ መገኘት መከልከሉን ተከትሎ በኮንትሮባንድ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል።

በተፋጠነ የችሎት ሥነ ስርዓት ከተመሰረቱት ክሶች ባሻገር ሌሎች በርካታ መዝገቦች ላይ በዳይሬክቶሬቱ በምርመራ ላይ ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለውም በጊዜ ቀጠሮ ላይ ሌሎች መዝገቦች የሚገኙ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች የጦር መሣሪያዎች ዝውውር በሰፊው እየተካሔደ እንዳለ የተለያዩ ፀጥታ አካላት ሲገልፁ ቆይተዋል። ከዚህ ጋር በተያየዘም መንግሥት የተለያዩ የቁጥጥር እርምጃዎችን እየወሰደ እንዳለ እና ልል የሚበለውን የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አንቀፆች የሚያጠናክር አዲስ አዋጅ ማርቀቁም ይታወቃል።

የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪዎችን አስተዳደር የሚደነግገው የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ ረቅቆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን በተደጋጋሚም ለውይይት መቅረቡ ይታወሳል። ነገር ግን አዋጁ ከባድ ጦር መሣሪዎችን የማያስተዳድር ሲሆን ላውንቸርን ጨምሮ ከግማሽ አውቶማቲክ በላይ የሆኑ ማንኛውንም የጦር መሣሪያዎችን በግለሰብ ደረጃ ለመጠቀም የሚሆን ፈቃድም እንደማይሰጥ ረቂቁ ደንግጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here