“በበጎዎች ለበጎዎች” የበጎ ሰው ሽልማት

0
1626

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሔዱ የሽልማት መርሃ ግብራት ጥቂት ናቸው። እነዚህም በሙዚቃ፣ በፊልም እንዲሁም በመጻሕፍት ሕትመት ሥራዎች ላይ ያተኩራሉ። ሁለገብ የሆኑ የመመሰጋገኛና የማመስገኛ መድረኮች ግን ብዙም አልተፈጠሩም። በዚህ መካከል ነው ከሰባት ዓመታት በፊት የበጎ ሰው ሽልማት በሚል ሥያሜ የተጠራ ዓመታዊ የሽልማት መርሃ ግብር የተጀመረው። ሽልማቱ በአክሱም ሆቴል በአምስት የሽልማት ዘርፎች በማካሔድ የጀመረው ጉዞ ዛሬ ላይ ዐሥር የሚጠጉ ዘርፎችን አካትቶና በቅርቡም በበጎ አድረጎት ድርጅትነት ተመዝግቦ ሰባተኛውን መርሃ ግብር ለማካሔድ ዋዜማው ላይ ይገኛል።

የበጎ ሰው ሽልማት የየዓመቱን ተሸላሚዎች በሚያወሳበት ዓመታዊ መጽሔት መግቢያ ተከታዩ ሐሳብ ተከትቦ በየዓመቱ ይነበባል፥ “…አገራዊ ኀላፊነት ወስደው ትውልድን የሚጠቅም፣ የአገርን ዕድገት የሚያስመነድግ፣ ለሌሎች አርዓያ የሚሆን፣ የታሪክን ማርሽ የሚለውጥ ሥራ የሠሩትን… የማበረታታት፣ የማድነቅ፣ የመሸለምና ዕውቅና የመስጠት ባሕል እምብዛም የለንም። ከዚህ ይልቅ የመተቻቸትና የመናናቅ፣ የመመቀኛኘትና የመጓተት ልማዶች ጎልተው ይታያሉ። ይህንን ልማድ ለመቅረፍና አገራዊ ጀግኖችን ለማውጣት፣ ለመሸለምና ትውልዱ እንዲያውቃቸው ለማድረግ መሥራት የመንግሥት ብቻ ኀላፊነት አይደለም። ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ሊፈጽመው የሚገባ የዜግነት ግዴታው ነው።”

በዚሁ መሰረት የ2011 የበጎ ሰው ሽልማት በሥነ ጥበብና ኪነጥበብ ሥር ዘንድሮ በያዘው የፎቶግራፍ ዘርፍ እጩ ከሆኑት መካከል፤ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ፎቶ አንሺ በመሆን ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው ፎቶግራፈር ዳኜ አበራ አንዱ ነው። ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ ለሽልማቱ እጩ ከመሆኑ በፊት ስለሽልማቱ የሚያውቃቸው ጥቂት ነገሮች እንደነበሩ ገልጾ፤ ይልቁንም በሙያቸው ውለታ የዋሉ፣ ጥሩ ነገር ያበረከቱ ነገር ግን የተዘነጉ ሰዎችን የሚያስታውስ ነው ሲል ጠቅሷል።

ዳኜ ከራሱ መታጨት ባሻገር ዘርፉ ትኩረት ማግኘቱ እጅግ አስደስቶታል። “ሙያውን በሽልማት ዘርፍ ማካተቱ ቀላል የሆነላቸው አይመስለኝም፤ ብዙ ትግልን እንደጠየቃቸው አምናለሁ። ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ሙያውን በስፋት አያውቁትምና ጥቆማ ለማግኘትም ያስቸግራል” ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። በጎ ሰው ሽልማት ዘርፉን ማካተቱ ከሱም አልፎ ሙያው ላይ ላሉ በቅርበት ለሚያውቃቸው ባለሙዎችም ጭምር መነቃቃትን የፈጠረ እንደሆነ አስታውሷል።

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰው በተንቀሳቃሽ ስልክ ካሜራ ይዞ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የፎቶግራፍ ባለሙያ መታወሱም ቀላል እንዳይደለ ዳኜ በአጽንዖት ለአዲስ ማለዳ ያነሳው ነጥብ ነው። ዳኜም መታጨትን በራሱ እንደ ሽልማት ቆጥሮት፤ ከወዲሁ መታሰቢያነቱንም በባድመ ጦርነት ሕይወቱን ላጣውና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባልደረባው ለነበረ ፎቶግራፈር ዘውዱ ጥላሁን ይሁንልኝ ብሏል።

የበጎ ሰው ሽልማት አዘጋጆች “እኛ የምችለውን እንሥራ፤ በዐቅማችን እንወጥነው” ብለው የጠነሰሱት የበጎ ሰው ሽልማት በአሁኑ ሰዓት መምህርነት፣ ቅርስና ባሕል፣ ሳይንስ፣ መንግሥትና የሥራ ኀላፊነት፣ ንግድና ሥራ ፈጠራ፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ ኪነጥበብ /ፎቶግራፍ/፣ ሚድያና ጋዜጠኝነት እንዲሁም ልዩ ተሸላሚ ዘርፎችን ይዟል። ማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ በተለያዩ ምክንያቶች ዘንድሮም ሳይካተት የቀረ ሲሆን ለኢትዮጵያ መልካም የሠሩ የውጪ አገር ዜጎች የተሰኘው ዘርፍም ለአገራቸው መልካም የሠሩ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚል ዘርፍ ተተክቷል።

የበጎ ሰው ሽልማት ዘንድሮ የያዘው አዲስ ዜና አለ፤ ይህም ለዓመታትና በተደጋጋሚ ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ መልስ አግኝቶ፤ በበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ መመዝገቡ ነው።

የበጎ ሰው ሽልማት በበጎ አድራጎት ድርጅትነት መመዝገቡ በአንድ ወገን አስተዳደራዊ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ የቦርድ አባልና ገጣሚ አንዷለም አባተ (የአጸደ ልጅ) ይጠቅሳል። ይህም የተደራጀ ቢሮና ቋሚ አድራሻ እንዲኖረው፣ የሰው ኀይል ቀጥሮ ለማሟላትና መሰል ተያያዥ ሁኔታዎችን ለማካተት ያስችላል። ያም ብቻ አይደለም የስብሰባ ቦታንና የአባላቱን መገናኛ ቋሚ በማድረግ በኩል በብዙ ያግዛል።

ከዛ ባሻገር ወደፊት ከሽልማት ውጪ ያሉ በጎ አድራጎቶችን በማንቀሳቀስና ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር ተባብሮ ለመሥራት ይህ የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ነው አንዷለም ለአዲስ ማለዳ የገለጸው። በየዓመቱ በሚያዙ ዕቅዶች መሠረትም ሥራዎችን ለማከናወን ያግዛል ብሏል። በእርግጥ የበጎ ሰው ሽልማት የበጎ አድራጎት ድርጅትነት ሳይሰጡት በፊትም ምክንያት ሆኖ ያስገኛቸው መልካም ውጤቶች ነበሩ። አንዱም የተሸላሚዎች እውቅና ማግኘት ነው። ይህም ተሸላሚዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ መልካም ሥራዎቻቸውና ምሳሌ የሚሆኑ ጥረቶቻቸው እንዲታወቁና ክብርም እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው።

ሽልማቱ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሔዱንም አንዷለም አስታውሷል። ለዚህም የሰዉ ተሳትፎ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱና ጥቆማዎች ከአገር ዳር እስከዳር እንዲሁም ከባሕር ማዶ ጭምር መቅረባቸው ማሳያ ነው። “ዘንድሮ ድርጅቶችም ከሠራተኞቻቸው መካከል መጠቆም ጀምረዋል” ሲል አንዷለም አክሏል። ዘንድሮ በድምሩ 291 ሰዎች በእጩነት የተጠቆሙ ሲሆን በወራት የመለየት ሥራም አሁን ላይ በድምሩ 27 እጩዎች ቀርበዋል።

የማኅበራዊ ዘርፍ ባሳለፍነው ዓመት የበጎ ሰው ሽልማት እንዲሁም በዘንድሮው ሳይካተት የቀረበትን ምክንያትም አንዷለም አስረድቷል። ይህም የሆነው ጠቋሚዎች ለዘርፉ ብለው የሚልኳቸው ሰዎች በአብዛኛው በሌሎች ዘርፎች ይልቁንም በመምህርነት ሊካተቱ የሚችሉ እየሆኑ በመገኘታቸው ነው። ጠቋሚዎች እጩዎችን ሲያቀርቡ አያይዘው ስለማንነታቸው አጠር ያለ መግለጫ ማኖራቸው ሥራውን ያገዘ ቢሆንም በጎ ሰውን ሽልማት እንደወትሮ አሁንም ያጋጠመው ችግር አለ። ይህም ሰዎች ታሪካቸውን ሰንደው የማስቀምጡ ልመድ የሌላቸው መሆኑ ነው።

“እጩዎች ከተለዩ በኋላ ለምዘና በሚያበቃ መልኩ ለማውጣት የሚደረገው ትግል ሁሌም ፈታኝ ነው። ሥራዎቻውንና አስፈላጊ ሰነዶችን ማግኘት ያስቸግራል” ሲል አንዷለም ለአዲስ ማለዳ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሷል። የመገናኛ ብዙኀንን ሚና ደግሞ በበጎ ጎን አንስቷል። ይህም የበጎ ሰው ሽልማት አዳዲስ መረጃዎችን ለሕዝቡ ከማድረስ ጀምሮ ጥቆማ እስከ ማድረግ ድረስ በመገናኛ ብዙኀን በኩል ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ መታየቱ ነው። ይህም ሽልማቱ የሁሉም እንዲሁም የጋራ መሆኑ እየታወቀ መምጣቱን ያሳያል።

“አሁንም ግን በተለይ ጥቆማን በተመለከተ ከሕዝብ ብዙ የሚጠበቅ አለ። ዋናው ጠቋሚ ሕዝብ ነው፤ አሁንም በየዘርፉ ያልደረስንባቸው በርካቶች ስለሚሆኑ የሕዝቡ ጥቆማ የበለጠ ሊሻሻል ይገባዋል ብለን ነው የምናስበው” ሲልም አንዷለም ተናግሯል።

ዘንድሮ ሰባተኛው የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት ከሳምንት በኋላ እሁድ፣ ነሐሴ 26 በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ይካሔዳል። በዚህም ለዓመቱ የቀረቡት 27 እጩዎች ሁሉ ለበጎ ሰው አሸናፊ መሆናቸውን እንደወትሮው አዘጋጆቹ ይገልጻሉ። አንዷለም “ከጣት ጣት ይልቃል እንዲሉ እንጂ 27ቱም ለእኛ በጎ ሰዎችም አሸናፊዎችም ናቸው” ብሏል።

የበጎ ሰው ሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት፤ “በሥራ ክፍተት ይኖራልና ይህን ተጋግዞ መሙላት ያስፈልጋል። በጎ ሰው ሽልማት በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ ወይም በመደብ የተመሠረተ አይደለም፤ ከእነዚህ በላይ ሆኖ ነው የሚሠራው” ሲል በአንዷለም በኩል ለአዲስ ማለዳ አንባብያን መልዕክቱን ልኳል።

አዲስ ማለዳም ለዘንድሮ የበጎ ሰው ሽልማት እጩዎችም መልካም ዕድልና ምኞቷን ታስተላልፋለች። በዘንድሮ የበጎ ሰው ሽልማት በትሩ አድማሴ፣ ዶ/ር አሚር አማን እና ግርማ ወንዳፍራሽ በመንግሥታዊ የሥራ ኀላፊነት ዘርፍ፤ ኦባንግ ሜቶ፣ ታማኝ በየነ እና ጸጋዬ ታደሰ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ዕድገት አስተዋጽዖ ያበረከቱ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘርፍ፤ ዳንኤል መብራቱ፣ ክቡር ገና እና ነጋ ቦንገር በንግድን ሥራ ፈጠራ፤ በልሁ ተረፈ፣ አማረ አረጋዊ እና አንድነት አማረ በሚድያ እና ጋዜጠኝነት፤ ሽታዬ ዓለሙ (ፕሮፌሰር)፣ ሕይወት ወልደመስቀል እና መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) በመምህርነት፤ ለገሠ ነጋሽ (ፕሮፌሰር)፣ሰብስቤ ደምሴ (ፕሮፌሰር) እና ታደለች አቶምሳ (ዶ/ር) በሳይንስ፤ ሚካኤል ጸጋዬ፣ በዛብህ አብተው እና ዳኜ አበራ በኪነጥበብ (ፎቶግራፍ) ዘርፍ፤ ጀንበር ተረፈ (ዶ/ር) ፣ አብዱላዚዝ መሐመድ (ዶ/ር) እና ላሌ ለቡኮ በበጎ አድራጎት፣ አበዱልፈታ አብደላ፣ አድማሴ መላኩ እና ሳሙአል መኮንን በቅርስና ባሕል ዘርፍ የታጩ በጎ ሰዎች ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here