“ሁሉም ከዘመዱ ሲባል፥ አክንባሎ ጋጣ ገባ”

0
1022

“የአክንባሎ ጋጣ” ብዬ የምጠራው አምድ ላይ ብዕሬን የማሾለው ለትችት ሲሆን ነው፤ መወድሰ መንግሥት፣ መወድሰ እምነት፣ መወድሰ ባሕል፣ መወድሰ ወግ እና ወዘተ. መሥማት የሚፈልጉ ሰዎች ላይመርጡት ይችላሉ። ለፍትሐዊ እና ርትዓዊ የእርስ በርስ ግንኙትነት የራስን ምቾት አሳልፎ እስከ መስጠት ለቆረጡት ግን እንደሚመቻቸው አልጠራጠርም።

 

የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የቤተ ዘመድ ፖለቲካ ነው ቢባል ቅጥፈት አይሆንም። ምን አመላክቷቸው እንደሁ አላውቅም እመው ሲተርቱ “ዘመድ ከዘመዱ ሲባል፥ አክንባሎ ጋጣ ገባ” ይሉ ነበር፤ ይህን ተረታቸውን በቅርቡ የሚጠቀምበት ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። ነገሩን በቅጡ ለማይረዱት ለኔ ቢጤ ከተሜዎች አክንባሎ የሚባለው የእንጀራ ምጣድ መክደኛ ሲሆን፥ የሚሠራው ከሸንበቆ ሳጣራ ጉንጉን እና በጭድ በተቦካ እበት (የከብት እዳሪ) ተለቅልቆ ነው፤ ጋጣ ደግሞ የከብቶች ማደሪያ ነው። ታዲያ ሁሉም ከየቤተ ዘመዱ ይግባ ሲባል፥ አክንባሎም ወጉ አይቅርብኝ ብሎ የገባበት ጋጣ ከብቶች እዳሪያቸውን የሚጥሉበት መሆኑ ነው፤ የዝምድና ሐረጉም የሚመዘዘው እዚያ ካሉት ከብቶች መሆኑ ነው። እመው በተረታቸው ሊያመሠጥሩ የፈለጉት አክንባሎ ወጥሮ ካቆመው ሸንበቆ ይልቅ የተሻለ “ዋጋ” ያላቸውን ከብቶችን ለዝምድና መምረጡን ይመስለኛል።

የቤተ ዘመድ ፖለቲካ በዓለማችን እያገረሸ ያለ የፖለቲካ ክስተት ነው። ይሁንና የተለያዩ የዳቦ ሥሞች አሉት። ብዙ ጊዜ ብሔርተኝነት ነው የሚባለው። ብሔርተኝነት ደግሞ ዞሮ ዞሮ በመወለድ የሚገኝ ነው፤ ወይ በአንድ አካባቢ በመወለድ አሊያም ከአንድ የዘር ግንድ በመወለድ የሚገኝ እንጂ በሥራ ብዛት የሚገኝ ነገር አይደለም።
በርግጥ “የማንነት” ፖለቲካም በውስጡ አለ፤ እንደኔ የተለያዩ ማንነቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ የማንነት ጭቆና የለም ብሎ መካድ ነውር ነው። ሆኖም የማንነት ጭቆናን ለመዋጋት ሁነኛው መንገድ ብሔርተኝነት ነው ማለት ከነውሩ ተለይቶ አይታይም። ማንነት ማኅበረ-ፖለቲካዊ ሥሪት ነው። አንዳንዶች የማንነት ጥያቄዎችን ከብሔርተኝነት ጋር ቀይጠው ቢያደናግሩበትም፥ ነገሩን ዘልቀው ለሚመለከቱት ግንብሔርተኝነት የቤተ ዘመድ ፖለቲካ መሆኑን ለመረዳት አይቸግራቸውም።

የቤተ ዘመድ ፖለቲካ በእንግሊዝኛ ‘nepotism’ የሚባለው ነው። በኢትዮጵያ ብሔር ላይ የተሰቀለው ማንነትን መሠረት ያደረገው የብሔርተኝነት ፖለቲካ በዘር ግንድ ቆጠራ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ አንክንባሎን ጋጣ ካስገባው የቤተ ዘመድ ፖለቲካ የተለየ አይደለም የሚል እምነት አለኝ።

“ያስተሳሰረን ውሸት”
የማንነት አረዳዳችን ብዙውን ጊዜ በውሸት ላይ የተመሠረተ ነው። ክዋሜ አንቶኒ አፒያህ ጋና ውስጥ ከሚገኘው የአሳንቴ ማኅበረሰብ ከወጡ ቤተሰቦቻቸው በለንደን ከተማ የተወለዱ “ጋና-እንግሊዛዊ” ናቸው። እ.ኤ.አ. በ2018 “The Lies That Bind” (“አስተሳሳሪ ውሸቶች”) የሚል መጽሐፍ በማንነት ፖለቲካ ዙሪያ አሳትመዋል። ርዕሱ እንደሚነግረን ማንነት፣ አገር፣ እምነት የመሳሰሉትን በሙሉ እንድናምናቸው በተደረጉ ውሸቶች የተገነቡ ናቸው። በተለይ ብሔራዊ ማንነቶች ያለ ውሸት መቆም የማይችሉ ናቸው። እነዚህን ውሸቶች በእንግሊዝኛ “Myth” ይሏቸዋል። ውሸቶቹ በርግጥም አስተሳስረውን እና ዘላቂ ወዳጅነት አፍርተውልን ቢሆን፥ በወደድናቸው። ችግሩ ሊያጫርሱን የሚችሉ፣ ካላጫረሱን ደግሞ በውስጣችን ቀን ቆጥሮ የሚፈነዳ የልዩነት ፈንጂ አዝለን እንድንኖር የሚያደርጉን ናቸው።

ታላቋ ሕንድ ‘ካስት’ በሚሏቸው ሕዝባዊ መደቦች የተከፋፈለች አገር ነች። ማኅበረሰቡ ዛሬም ድረስ የላይኛው ካስት፣ የታችኛው ካስት በሚል ተከፋፍሎ ለጋብቻ እንኳን የላይኛው የታችኛውን እየተጠየፈ የሚኖርባት አገር ነች። ይህ የካስት ምድብ ግን የተፈጠረው በጥንታዊ የግዛተ ዐፄ ግንባታዎች ወቅት ነው። የምሥራቅ አፍሪካ አጎራባቾቻችን ሩዋንዳዎች የዛሬ 20 ዓመት ግድም ለዘር ፍጅት የተዳረጉት ለአገዛዝ ስልት ቅኝ ገዢያቸው ቤልጂየም በፈጠረችው የውሸት ማንነት ነው። ሁቱ እና ቱትሲ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ጥቁር ሕዝቦች ናቸው። ልዩነታቸው የአፍንጫ ቅርፅ ነው ቢባል የተሳሳተ አይደለም። በዚህ ምድብ አንዱ ሌላውን ሲንቅ፣ ሌላኛው አንዱን ሲጠላ መጨረሻቸው የዘር ፍጅት ሆነ። በሌላ በኩል ዩጎዝላቪያን ያፈረሳትም የውሸት ማንነት የወለደው ብሔርተኝነት ጦስ ነው። የጠቡ አጫሪዎች ሰርቦች እና ክሮአቶች አንድ ቋንቋ የሚናገሩ የሁለት ዓይነት እምነት ተከታይ እና የሁለት ዓይነት ፊደል ተጠቃሚ ነበሩ። በቃ በነዚህ ልዩነቶች ላይ የተገነቡ ልዩነቶች ወደ ጦርነት፣ ከዚያም ወደ መበተን ዘለቀ።

በአንድ ወቅት አገራትን ለመመሥረት አገልግሎት ላይ ውለው የነበሩ የብሔርተኝነት ዘመቻዎች በሌላ ወቅት እርስበርስ መተላለቂያ መንስኤዎች መሆናቸውን ለመማር ዓለማችን ከበቂ በላይ ትምህርት ሰጪ ምሣሌዎች አሏት።

የሚያዛልቀን እውነት
ብዙዎች ብሔርተኝነት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች አንድ የዘውግ ቡድን ወይም ብሔር ላይ የተሰነዘረ ትችት አድርገው ይመለከቱታል። እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። ብሔርተኝነት አንድ የዘውግ ቡድን ውስጥ ያሉ ሰዎች አንድ ናቸው፤ ከሌሎች ደግሞ ይለያሉ የሚል ግንዛቤ ይዞ ከሌሎች ጥቃት ራሱን ለመከላከል ወይም በሌሎች ላይ ያለውን የበላይነት ለማስጠበቅ የሚደረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው። ይህ የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕሪይ የሚጋፋ ጊዜያዊ የስሜት አገዛዝ ስልት በመሆኑ ነቀፌታ የሚገባው እንቅስቃሴ ነው። ይሁንና የብሔርተኝነት ንቅናቄ መሪዎች ይህ እንዲታወቅ እና ያለምንም አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያሰልፉትን ተከታይ ማጣት ስለማይፈልጉ፣ ብሔርተኝነት ሲነካ ብሔራችን ተነካ ብለው ያስወራሉ። ይህ ዓምድ ዓላማው የማይደፈረውን እየደፈሩ፣ የማይነቀነቀውን እየነቀነቁ የአክንባሎ እና ጋጣ ዝምድናን ማፍረስ ነው።

እንደ አንድ ጸሐፊ፣ እንደ አንድ ለሰብኣዊ መብቶች ተቆርቋሪ፣ እንደ አንድ አፈንጋጭ ተራማጅ፣ የኔ ሚና ብዬ የማስበው ሁሌም በውሸት (‘ሚት’) ላይ የተመሠረተ፣ ለሰዎች አርነት እና ክብር እንቅፋት የሆነ ትርክት፣ እምነት፣ ወግና ልማድ ለማሻሻል ወይም ለመቀየር መነቅነቅ ነው። ይህንን የአዲስ ማለዳ አምዴን “የአክንባሎ ጋጣ” ብዬ ለመሠየም የፈለግኩት “የሚያስተሳስሩንን ውሸቶች” ለመግለጽ ከዚህ የተሻለ ሐረግ ባለማግኘቴ ነው። “የአክንባሎ ጋጣ” ብዬ የምጠራው አምድ ላይ ብዕሬን የማሾለው ለትችት ሲሆን ነው፤ መወድሰ መንግሥት፣ መወድሰ እምነት፣ መወድሰ ባሕል፣ መወድሰ ወግ እና ወዘተ. መሥማት የሚፈልጉ ሰዎች ላይመርጡት ይችላሉ። ለፍትሐዊ እና ርትዓዊ የእርስ በርስ ግንኙትነት የራስን ምቾት አሳልፎ እስከ መስጠት ለቆረጡት ግን እንደሚመቻቸው አልጠራጠርም።
በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here