ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ የታሪክ እና የምጣኔ ሀብት ይዘት ያላቸውን ሁለት ታሪካዊ መጻሕፍት ጽፈው በአፍላ ዕድሜያቸው የተቀጩ ሰው ናቸው። ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) “መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር” የሚለውን መጽሐፋቸውን በመቃኘት በተከታታይ በአዲስ ማለዳ ላይ ይተነትኑልናል። በዚህ ክፍል ጽሑፋቸው የነጋድራስ ገብረሕይወት ምጣኔ ሀብታዊ ናሙና ቀደምትነትን እንዲሁም የጀርመናዊው ሄነሪ ቻርለስ ኬሪን ሐሳቦች በእርሾነት የተጠቀሙ መሆኑን ያስነብቡናል።
ነጋድራስ ወንድሜ የምሁራን ቁንጮ
አስቦ አንብቦ አውጠንጥኖ አልሞ
ተውሮ ቀምሮ ከነጭ ሁሉ ቀድሞ
የወገኑ ስቃይ ባጭር እንዲያበቃ
መከረ ነገረ ለባለሥልጣናት
ሕዝቡን እንዲያወጡት ከድህነት ክፋት
ሰሙት፣ ሰሙትና ዳራው ቢገባቸው
ቀጠፉት ባጭሩ ምክሩ አሳስቧቸው።
(ሞምባሳ ታኅሣሥ 2002 ሕዳር 2002)
የነጋድራስ ገብረሕይወት ሥራዎች ላይ አንድ ሦስት የምርምር ሥራዎች ሰርቼ በምርምር መጽሔቶች ላይ አሳተሜ ነበር። በቅርቡ ለሁለተኛና የመጀመሪያ ድግሪ እንዲሆን ባዘጋጀሁት “የዓለምዐቀፍ ንግድ ትንታኔ” መጽሐፍ ላይም አንዱ ምዕራፍ የሚያተኩረው በነጋድረስ ገብረ ሕይወት ሥራዎች ላይ ነው። በዚህ አጭር ጽሑፍ፣ በእነዚህ የምርምር ጽሑፎች ያሰፈርኩትን የነጋድራስ ሐሳቦችን ጠቅለል አድርጌ ለማቀረብ እሞክራለሁ።
ምንም እንኳን የነጋድራስ የመጀመሪያው መጽሐፋቸው፤ “ዐፄ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ’’ በኢትዮጵያ በነበረው ስርዓት ላይ ጠንከር እና በሰል ያለ ትችት የሰጠ፣ ታሪክ ተመራመሪዎች ምን ዓይነት የምርምር አካሔድ መከተል እንዳለባቸው በውብ ቋንቋ ያስገነዘበ፣ እንዲሁም በዚያን ጊዜ የነበረችው ኢትዮጵያ መከተል የነበረባትን የፖሊሲ አቅጣጫ የነደፈ፣ እንዲያውም የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘወዴ ከብዙ በአንዱ መጣጥፋቸው እንዳስረዱን በኋላ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተግባራዊ ያደረጓቸውን ሐሳቦች ያፈለቀ ውብ መጽሐፍ ቢሆንም፥ እኔ ግን እንደምጣኔ ሀብት ባለሙያነቴ ለምጣኔ ሀብት ተንታኞች ይበልጥ በሚቀርበውን ሁለተኛው መጽሐፋቸው “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” ላይ አተኩሬያለሁ።
የገብረሕይወት ንድፈ ሐሳብ ግንባር ቀደምነት
በዚህ በሁለተኛው የንድፈ ሐሳብ (theoretical) ሥራቸው ነጋድራስ በደቡብ አሜሪካ በ1950ዎቹ ተፈጠረ የተባለውን “በመዋቅራዊ ችግሮች ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ አተናተን” (Structural Economics)፣ በተለይ ደግሞ የፕሬብሽንና የፕሮፌሰር ሲንገርን ንድፈ ሐሳቦችን እርሳቸው ቀድመው ተረድተው በዚህ መጽሐፍ ጽፈውት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ በፈረንሳዩ የፖለቲካ ምጣኔ ሀብት ተንታኝ አርጌ ኢማኑኤልን እና ታዋቂው የግብፅ ፖለቲካል ኢኮኖሚስት ሳሚር አሚን እንደተነደፉ የሚነገርላቸው “ያደጉና እያደጉ ያሉ አገሮች ያልተመጣጠነ ንግድ ሁኔታ ትንተና” በዚህ መጽሐፋቸው ቀድመው ንድፈ ሐሳብ አድርገውት ነበር። በተመሳሳይም የታዋቂው እንግሊዝዊ የምጣኔ ሀብት ምሁር ፕሮፌሰር ፒጉና ኬንስን፣ እንዲሁም የፖላንዱ ዕውቅ የምጣኔ ሃብት ተንታኝ ፕሮፌሰር ሚካኤል ካልስኪን ንድፈ ሐሳቦችን እርሳቸው ቀድመዋቸው አመላክተው ነበር። ሆኖም በአማርኛ ቋንቋ ስለጻፉት ይሁን ከአፍሪካ ስለሆኑ እርሳቸው ቀድመው የፈለሰፉትን አስተሳሰብ ሌሎች 40 እና 50 ዓመታት ዘግይተው ሲያውቁት በምጣኔ ሀብቱ ዓለም ዕውቅናን ተቸሩበት።
ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገለጽ ነጋድራስ በሁለቱ መጻሕፍት በተጠቃለሉት ሥራዎቻቸው “Development Economics” ወይም “የልማት ምጣኔ ሀብታዊ አተናተን” የሚባለውን የምጣኔ ሀብት ሳይንስ አንዱን ክፍል ከማንም ቀድመው ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ፈጥረዋል ማለት ነው።
ይህ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ እና አሜሪካ የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደተፈጠረ ነው፤ ዛሬ ብዙ ተመራማሪዎች የሚያውቁት። እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ስለ ገብረሕይወት በጻፉት ጽሑፍ ገብረሕይወት ዘመናዊነትን ከአውሮፓ አንስቶ ኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ነበር የሞከረው የሚል ድምዳሜ ላይ የመጡ ስለመሰልኝ፤ በኔ ግምት ይህ ሐሳብ ልክ አለመሆኑን በመጽሐፉ ብዙ ቦታዎች የተመለከተ መሆኑን (ከአዲሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እትም ገጽ 28 እና 37ን ለናሙና መጥቀስ እንደሚቻል) ለመጠቆም እወዳለሁ።
በእነዚህ ቦታዎች ገብረሕይወት የአውሮፓን ዕውቀት በአያሌው አድንቀው ሲጨርሱ ወዲያው አውሮፓን እንከተል ይላሉ ብለን ስንጠብቅ “ስለዚህ ጃፓንን አጥንተን እንከተል” ነው እንጂ አውሮፓን እንከተል ካለማለታቸውም በላይ “ደንብ ሁሉ ምንም ቢጠቅም በተለየ ጊዜያት ውስጥ እና ለተለየ ሕዝብ ብቻ ነው”፤ እንዲሁም “ዕውቀት ላላቸው ሕዝቦች ደግ የሆነ ደንብ ዕውቀት ለሌላቸው ሕዝቦች ትልቅ ጉዳት ይሆንባቸዋል” ማለታቸውን ለማስታወስ እወዳለሁ።
የመሠረተ ልማት ግንባታ በዕውቀት ላልታነፀ ሕዝብ መዘረፊያው፤ በዕውቀት ለታነፀ ሕዝብ መበልፀጊያው መሆኑን አበክረው መግለጻቸው ሌላው አመላካች ነው። ይህ ትንተናቸው መንገድና ባቡር ለመዘርጋት ለሚተጋው የዛሬ መንግሥታችን ሳይቀር የማስጠንቀቂያ ደውል ነው። በዚያን ጊዜ ምናልባትም ስለ ባሕልና ተመሳሳይ ጉዳዮች ከአትዮጵያ ሥልጣኔ ሁኔታ ለመነሳት ቢቻልም ስለምጣኔ ሀብት ዕድገት ግን (ክስመት ካልሆነ!) ከኢትዮጵያ ለመነሳት የሚከብድ ይመስለኛል። ክስመቱን ግን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ተነስቶ፣ ቀጥዬ እንደማትተው ገብረ ሕይወት በጥልቀት አብራርተውታል።
እንግዲህ ከዚህ ሁኔታ በመነሣት ነው በዚህ ጽሑፌ የነጋድራስን ምጣኔ ሀብት ነክ ሥራዎችን አጠር አድርጌ በማቅረብ “የልማት ምጣኔ ሀብታዊ ትንተና” የሚባለው ትምህርት መሠረቱ አፍሪካ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ መሆኑን መጠቆም የምፈልገው። በተጨማሪም የነጋድራስ ሥራዎች አሁንም ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ የሚጠቁሙ ቁልፍ ሥራዎች መሆናቸውን አስረግጬ ለመግለጽ እሞክራለሁ።
“የነጋድራስ ገብረሕይወት ናሙና”
በሚከተሉት አንቀፆች ውስጥ የነጋድራስ ገብረሕይወትን አስተሳሰብ “የነጋድራስ ገብረሕይወት ናሙና” ወይም “የገብረሕይወት ምስለ ኢኮኖሚ” ብዬ እጠራለሁ። በደምሳሳው ናሙና (‹ሞዴል›) ወይም ምስለ ኢኮኖሚ ማለት ወጥ እና አጠር ባለ መልኩ የምጣኔ ሀብት አስተሳሰብ የሚገለጥበት የአስተሳሰብ መሣሪያ ልንለው እንችላለን። ብዙ ጊዜ ናሙና የሒሳብ ቀመር መልክ ሊይዝ ይችላል። ወደ “ምስለ ኢኮኖሚው” ከመሔዴ በፊት ግን ስለ ነጋድራስ ገብረሕይወት የሥነ ምርምር አካሔድ ጥቂት ልበል።
ነጋድራስ ገብረሕይወት ጀርመን አገር መማራቸው ይታወቃል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የገብረሕይወት ሞዴል በዘመኑ የጀርመን የምጣኔ ሀብት አስተሳሰብ የተቃኘ ይመስላል። ይህንንም እንድንል የሚያደርገን በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ የምጣኔ ሀብት ምሁር ሲሆን እሱም ኬሪ የሚባል ነው። ይህ ሰው በዘመኑ ዝነኛ የነበረው ማቲዎስ ኬሪ ወይም ደግሞ ከሱ በላይ ዝነኛ የነበረው ልጁ ሄነሪ ቻርለስ ኬሪ ይሆናል ብዬ ከዚህ በፊት ገምቼ ነበር። የሄነሪ ቻርለስ ኬሪን ዝነኛነት ማርክስና ኤንግልስ ሳይቀሩ መስክረውለታል (ለዚህም የቻንግን መጽሐፍ Kicking Away The Ladder: Development Strategy in Historical Perspective ይመልከቱ)። ሄነሪ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሊንከን አማካሪ ብቻ ሳይሆን ከእነአባቱ ታዋቂው የዘመኑ የጀርመን ምጣኔ ሀብት ተንታኙ ፍሬድሪክ ሊስት ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳድሯል። ሊስት ጀርመን ማደግ ከፈለገች ለእንግሊዝ የነጻ ገበያ መርሕ ሳትንበረከክ ጨቅላ ኢንዱስትሪዎችን በመንግሥት ድጋፍና ከለላ ማሳደግ አለባት የሚለውን አስተሳሰብ ያመጣው በእነዚህ አሜርካኖች ተፅዕኖ ይመስላል። ለምሳሌም ሄነሪ የዛሬ 150 ዓመት ገደማ ሲጽፍ፤ የእንግሊዝ የምጣኔ ሀብት ምሁራን (በተለይ የሪካርዶና ስሚዝን) የነጻ ገበያ ንድፈ ሐሳቦች አሜሪካን ዘላለም የጥሬ ዕቃ አቅራቢ ለማድረግ የተወጠነ የእንግሊዝ ኢምፒሪያሊዝም ዘዴ ነው ይል ነበር።
የሄነሪ ተፅዕኖ በገብረሕይወት ሥራ ላይም አሻራውን በደንብ አስቀምጧል። ጠቅለል ባለ መልኩም ሲታይ የገብረሕይወት የአስተሳሰብ ወይም የምርምር ዘዴ የአውሮፓን የዕድገት ጥበብ ከእኛ ሁኔታና ታሪክ ጋር አጣጥሞ ማቅረብ ነው። ይህ የምጣኔ ሀብት ማሳደጊያ ጥበብን ከታሪክ ጋር አቆራኝቶ የማጥናት ዘዴ ደግሞ አንድምታ /hermeneutic/ የሚባለው የዘመኑ የጀርመን ሊቃውንት፣ በተለይ ደግሞ ታዋቂዎቹ የጀርመን ሊቆች ዲቲና ዊበር የሚጠቀሙበትና ከእንግሊዝ ሊቆች ይለየናል የሚሉት የጥናት ዘዴያቸው ነው። (የዊበርን የፕሮሰታንት ኤቲክስ መጽሐፍ ይመልከቱ።) የገብረሕይወት የአስተሳሰብ ወይም የሥነ ምርምር ዘዴ ከዚህ ጋር በጅጉ ይመሳሰላል።
ይህንን መግቢያ ከማጠቃለሌ በፊት በገብረሕይወት ሥራ ላይ የአሜሪካዊው ሊቅ ቻርለስ ካሬ ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሆነ ጠቁሜ ልለፍ:: በቅርቡ አንድ ጥሩ አጋጣሚ ነበረኝ። ይህ ደስ የሚል አጋጣሚዬ ሐሰን መሐመድ የተባለ አንባቢዬ በላከልኝ የኢሜል ደብዳቤ የካሬን መጽሐፍ አግኝቶ የሚገኝበትን አድራሻ በጠቆመኝ መሠረት መጻሕፍቱን አግኝቻቸዋለሁ። በነቀምት የገጠር መንገድ ሥራ ላይ የተሠማራው ኢንጂነሩ ሐሰን ታሪካዊ ዳራ ያላቸውን የኢትዮጵያ ምጠኔ ሀብታዊ ጽሑፎችን መውደዱና ምርምሩ በጣም አስደስቶኛል፤ ምስጋናዬም የላቀ ነው። እናም አሁን መጻሕፍቱን ሳያቸው፣ ገብረሕይወት የጠቀሱት እና የተጠቀሙበት ልጅየው ሄነሪ ቻርለስ ኬሪ ከአውሮፓዊያኑ 1858 ጀምሮ በሦስት ቅጽ የጻፋቸው መጻሕፍት በተለይም ቅጽ አንድ እና ሁለት ናቸው።
ገብረሕይወት “በመንግሥትና አስተዳደር” መጽሐፋቸው ምዕራፍ ሦስትና አራት ላይ ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ የልማትና የዕድገት ጉዞ እንቅፋቶች እና የገዢ መደብ አፈጣጠርን የተረኩባቸውን መሠረታዊ ሐሳቦች የመሠረቱበት፣ እንዲሁም አንዳንድ አባባሎችና ምሳሌዎች በቀጥታ የወሰዱት ከካሬ መጽሐፍ ቅጽ አንድ ከገጽ 45 እስከ 147 ነው። ለነገሩ ገብረሕይወት ይህን ሲያደርጉ መጽሐፋቸው ላይ በግልጽ ካሬን ጠቅሰው ነው። በተጨማሪም ስለሥራ ሚዛንና የዋጋን ትርጉም የተመለከቱ ሐሳቦችን እና ምሳሌዎችን ከዚሁ መጽሐፍ ወስደዋል፤ ለምሳሌ ስለሮቢንሰን ኩሩሶ፣ ስለሀብት ማስረጃ፣ የማናቸውም ነገር አጠቃቀሙን ካላወቁበት ዋጋ እንደሌለው፣ ስለብልጫ እና እርግጠኛ ሀብት ከካሬ ተወስደው በኢትዮጵያ ቀለምና እውነት ላይ ተመሥርተው የተጻፉ ናቸው። ኢንዱስቱሪ በመንግሥት ከለላ ሥር መደረግ እንዳለበት፣ ስለገንዘብና ልማት የተነሱ ሐሳቦች፣ የወለድ መጠን የአንድ አገር ዕድገት ደረጃ ከፍ ሲል እንደሚቀንስ፣ ጥሬ ዕቃ መሸጥ አፈሩን እንደመሸጥ መሆኑን እና በዛው ከቀጠለ ለስደተኝነት እንደሚዳርግ በካሬ መጻሕፍት የተገለጹትን ሐሳቦችን ገብረሕይወት በእርሾነት እንደተጠቀሙባቸው ከእነዚህ መጻሕፍት መረዳት ይቻላል።
እነዚህን ሐሳቦች እና ምሳሌዎችን እንዲሁም ገብረሕይወት በመጽሐፋቸው በገጽ 123 ላይ የተሳለውን ስዕል ከካሬ መጽሐፍ እንደገለበጡት፣ በዚሁ ገጽ ላይ በግልጽ ጽፈውታል። በመጽሐፉ በገጽ 44 ጀምሮ የጻፉትን ከዛው ከካሬ መጽሐፍ እንደወሰዱ ከመናገራቸውም በላይ በጣም የተንዛዛውንና ከዘመኑ የእንግሊዙ የምጣኔ ሀብት ሊቅ ሪካርዶ ንድፈ ሐሳብ ጋር ካሬ ለመጋፈጥ ብዙ ገጾች ያጠፋበትን፤ ብዙ ታሪካዊ ምሳሌዎችን የተነተነበትን ከ50 የማያንሱ ገጾች ገበረሕይወት ለራሳቸው ሥራ ተገቢ የመሰላቸውን መሠረታዊ ሐሳብ በድንቅና ቀላል ቋንቋ በሦስትና አራት ገጾች መጻፋቸው ድንቅ የሚያሰኝ ነው።
በተጨማሪም የካሬን የብዙ አገሮች ታሪክ ትተው የኢትዮጵያን ታሪክ በሚገርም ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ ቅርፅ አስይዘው፤ በካሬ ሐሳብ ላይ ተመሥርተው ከተነተኗቸው አስተሳሰቦች ጋር አዋሕደው ለተደራሲዎቻቸው ያቀረቡበት አካሔድ አስደናቂ ነው። እዚህ ላይ የሥራና ዋጋን ትወራ ባለቤት የእንግሊዙን የምጣኔ ሀብት ሊቅ የሪካርዶን ንድፈ ሐሳብ መውሰድ ትተው የሞጋቹ ካሬ ጽሑፍ ላይ መመርኮዛቸው ግርምት የሚጭርና ከላይ ከጠቀስኩት የሥነ ምርምራቸው ፈለግ የተመዘዘ ይመስለኛል።
በአጠቃላይ በገብረሕይወት ሥራ ላይ በተለይ የካሬ አስተሳሰብ ተፅዕኖ የጎላ ነው። ሆኖም ግን እነዚህን ሐሳቦች ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር አስማምተው፤ የራሳቸውንም አዳዲስ ሐሳቦች ጨምረው በቀላልና ለኅብረተሰቡ በሚገባ መልኩ የኢትዮጵያን ችግር የፈተሹበት አካሔድ የራሳቸውና ልዩ አቀራረብ ነው። ለማጠቃለል፣ ራሳቸው ገብረሕይወት በዋቢነት የሰጡንን መጻሕፍት ስንዳስስ የካሬን የጎላ ተፅዕኖ ማወቃችን ጥሩ ሲሆን ይህ ግን የገብረሕይወት ሥራ ልዩ፣ ድንቅና ቀዳሚ ሥራዎች የመሆናቸውን ሁኔታ አይለወጥብንም። ቢያንስ ለኔ አለወጥብኝም። ይህን ካልኩ ወደ ምስለ ምጣኔ ሀብት ናሙናቸው ልመለስ።
በነጋድራስ ገብረሕይወት “ምስለ-ኢኮኖሚ” ሞዴል ማንኛውም አገር የመልማት ተስፋ አለው። ዳሩ ግን ሁለት መሰናክሎች (ተግዳሮቶች) ሊጋረጡበት ይችላሉ። እነርሱም ግጭት ወይም ጦርነትና የውጪ የንግድ ሚዛን መዛባት ናቸው። እንግዲህ ለነጋድራስ የአንድ አገር ክስመት ወይም ዕድገት ደረጃ በእነዚህ ተግዳሮቶች ግዝፈትና ደካማነት ይወሰናል። የነጋድራስን ሐሳብ ከስሩ ለመረዳት እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች (ውስጣዊ እና ውጫዊ አንበላቸው) በጥልቀት መመልከት ያሻል። በዚህ ምስለ ምጣኔ ሀብታዊ ሐሳባቸው መመለስ የሚፈልጉት ጥያቄ ‹የኢትዮጵያዊያን የዕድገት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ ችግሮችስ እንዴት ወጥተን ወደ ልማትና ብልፅግና መሔድ አንችላለን?› የሚሉት ናቸው። በዚህ መልኩ ችግሮቹን በሁለት ከፍለው ‹ውስጣዊ› እና ‹ወጪያዊ› ይሏቸዋል።
(ክፍል 2 ይቀጥላል)