የግል አልሚዎችን በቤቶች ግንባታ ላይ ለማሳተፍ መንግሥት ምክረ ሐሳብ አቀረበ

0
920

የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን በጋራ መኖሪያ ግንባታዎች ለማሳተፍ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ምክረ ሐሳብ ቀርበ። ከ20 የማይበልጡ የግል አልሚዎች በተሳተፉበት በሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ በተደረገ የምክክር መድረክ በቀረበው ሰነድ በቤት ግንባታው የሚሳተፉ ባለሀብቶች መነሻ ካፒታል 50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን ሐሳብ ቀርቧል።
ለሰነዱ መዘጋጀት አንደ ዋና ምክንያት የተገለፀው በመኖሪያ ልማት ዘርፍ ያለው አካሄድ በአገሪቷ እየጨመረ የመጣውን የከተማ ነዋሪ የቤት ፍላጎት ማርካት አለመቻሉ ነው። በአዲስ አበባ እና በክልል ትልልቅ ከተሞች የሚታየው የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ከ 25 እስከ 30 በመቶ ክፍተት እንዳለበት ያሳየው ሰነዱ የግሉ ዘርፍ በቤት አቅርቦት ላይ ማሳትፍ በትላልቅ ከተሞች ያለውን የመሬት አቅርቦት ውስንነት ጋር ተያይዞ ያለውን ተግዳርቶች ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን አስረድቷል።
በመንግሥት ፋይናንስ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የቤት ልማት ሥራዎች ከፍተኛ ግምት ሊሰጣቸው የሚገባ ቢሆንም ከከተማ ነዋሪው የቤት ፍላጎት አንፃር ሲታይ ሰፊ ጉድለት ይስተዋላል በማለት የተናገሩት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴሩ ዣንጥራር አባይ በበኩላችው የመንግሥትና የግል አጋርነት በባለሀብቶች ፋይናንስ አቅራቢነት ችግሩን ለመፍታት ጉልህ አስተዋዕፆ ይኖረዋል ብለዋል። የግል ባለሀብቶች በበኩላቸው የቀረበው ምክረ ሐሳብ የአገር ውስጥ አልሚዎችን አቅም ያላገነዘበ ነው በማለት ተችተዋል።
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በ2009 አድርጎት በነበረው ጥናት በኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤተሰብ ቤት ይፈልጋል፤ ሚኒስቴሩ እንደሚለው በየዓመቱ ተጨማሪ 100 ሺህ ቤት ፈላጊዎች እየተፈጠሩ ነው። ይህም ዓመት በጨመረ ቁጥር የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ ላይ ተጨማሪ መቶ ሺህ ፍላጎት ይጨመራል ማለት ነው። አብዛኛው ቤት ፈላጊ ያለው ደግሞ አዲስ አበባ ላይ መሆኑ ለከተማው አስተዳደር የራስ ምታት ሆኗል።
ነገሩ በአገሪቷ ትላልቅ ከተሞች ያለውን ፈጣን የምጣኔ ሀብት ልማት መስፋፋትን ተከትሎ የከተሞች መስፋፋትና የነዋሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ የቤት አቅርቦት ችግር እየሰፋ ከመጣ ቆይቷል። መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ነድፎ ያደረገው ጥረት ችግሩን ሊፈታው አልቻለም። ፍላጎቱ ከአቅርቦቱ ቀድሞ መጓዝ ችግሩን የበለጠ ከፍ እንዲል አድርጎታል። በቅርቡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሚል የተቋቋመው መስሪያ ቤትም ችግሩን በሚገባ ለመቅረፍ እስካሁን ሲኬድበት ከነበረው አካሄድ ሌሎች አማራጮችን መጤን እንዳለበት ተረድቻለው ብሏል።
ሚኒስቴሩ ማክሰኞ፣ ሕዳር 4 ቀን 2011 ከባለሃብቶች ጋር ባደረገው ስብሰባ የመንግሥት እና የግል አጋርነት ችግሩን ለመቅረፍ ወሳኝ መሆኑን አሳውቋል። በቀረበው የሐሳብ ሰነድ መሰረት በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚገነቡ ቤቶች በግል ባለሃብቶች ፋይናንስ ሲሆን የመንግሥት ዕዳን በመቀነስና የኅብረተሰቡን የቤት ፍላጎት ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ያስረዳል። ‹‹ባለሃብቱ ዕውቀቱንና ገንዘቡን፤ መንግሥት ደግሞ መሬት በማቅረብ በአጋርነት የቤት ልማቱን በማካሄድ ችግሩን ለማቃለል ትልቅ ሚና ይኖረዋል›› በማለት የሚኒስትሩ ባለሙያ የሆኑት አበበ ዘልዑል ሐሳቡን በመደገፍ ያስረዳሉ።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን አጋርነት ውጤታማ ለማድረግ ሚኒስትሩ ሰነዱን ለማዘጋጀት የቬትናም፣ ደቡብ ኮሪያ እና ህንድ ልምዶች ተወስዷል። በሰነዱ መሰረት ባለሃብቱ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ከመንግሥት ጋር በሚኖረው ስምምነት መሰረት የሚፈፀም ቢሆንም መንግስት ለባለሃብቱ የተወሰነ መቶኛ መሬት ለግሉ እንዲጠቀምበት የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት መሰረተ ልማቱን እንዲያለማ ማድረግን ያካትታል።
በተጨማሪም እንደ ሰነዱ ገለፃ አልሚ ባለሃብቶች ለቤት የሚሆን የፋይናንስ ፍላጎት ከመንግሥትም ይሁን ከግል ባንኮች ከሚገኝ ብድር እንዲሸፈን ይደረጋል፤ የሞርጌጅ ፋይናንስም ሰነድ ውስጥ ተካቷል። ሰነዱ አልሚው ቤት ከመገንባቱ በፈት ገንዘብ በመሰብሰብ ወደ ግንባታ መግባት እንዳለበት በማተት እንደ እቁብ ያሉ ባህላዊ የፋይናንስ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚቻልም ያስረዳል።
በሌላ በኩል የውጭ ባለሃብቱ ተሳትፎ ካለው አገራዊ የካፒታል እጥረት በተወሰነ በሚረዳ መልኩ ሃብት ይዞ የሚመጣና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ ወሳኝ መሆኑን ሰነዱ አስቀምጧል። ነገር ግን በቀዳሚነትና በወሳኝንት ደረጃ ግን በቤት ልማት በአጋርነት የሚሳተፈው የግል ዘርፉ መሆንን ሰነዱ ያስረዳል። የሃሳብ ሰነዱ ተጨማሪ ግብአት እስከ በጀቱ አመት መጨረሻ ከተሰበሰበ በኋለ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እስከ የካቲት 30 መሬቱን ለግል አልሚዎች በማስተላለፍ ግንባታ ይጀምራል ብሎ አቅጣጫ አስቀምጧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here