ዴሞክራሲ ስለታሪክ ይገደዋል?

0
717

የአዲስ አበባ ጥያቄ የነዋሪዎቿ የአስተዳደር ጥያቄ ከመሆን አልፎ፣ አንድ ቀን እንኳን ጎብኝተዋት የማያውቁ ሰዎች ታሪክ እየጠቀሱ “የኛ ነች”፣ “የናንተ አይደለችም” እያሉ የሚሻሙበት ሆኗል። ይህ አተያይ ግን ከዴሞክራሲ አኳያ አንድ እርምጃ አያስኬድም።
በዴሞክራሲያዊ መርሕ በአዲስ አበባ ጉዳይ መወሰን የሚችሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው። አዲስ አበባ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት ተሰጥቷታል። በዚህም መሠረት ምክር ቤት አላት። የምክር ቤቱን አባላት የመምረጥ ይሁን ለምክር ቤቱ አባልነት የመወዳደር መብቱ የነዋሪዎቿ ብቻ ነው።
በታሪክ እና ትርክቶች ላይ የተመሠረቱ የባለቤትነት ጥያቄዎች ደጋግመው የሚደመጡ ቢሆንም ዴሞክራሲ ስለ ታሪክ እምብዛም አይገደውም።በዴሞክራሲ መርሕ በታሪክ የነበሩ ሰዎች፣ የተፈፀሙ በደሎች፣ ወይም ፈሰስ የተደረጉ መዋዕለ ሀብቶች በነባራዊው ሁኔታ ላይ እንዲወስኑ የሚፈቀድበት አሠራር የለም። ይልቁንም በአንድ የአስተዳደር ክልል ውስጥ ዛሬ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች በተሳትፏቸው እና በፈቃዳቸው የሚወስኑት ብቻ ተፈፃሚ ይሆናል።
ዴሞክራሲ የብዙኃን አመራርን (ወይም በአሪስጣጣሊስ ቋንቋ የብዙኃንን ይሁንታ) ሕግ አውጪ ወኪሎቻቸውን በነጻነት እንዲመርጡ በማድረግ የሚያረጋግጥ ስርዓት ነው።በመሆኑም፣ ነዋሪዎች በአስተዳደር ክልሎቻቸው ውስጥ የሚያሳስባቸውን ጥያቄ የሚያነሳላቸውን እና የሚፈልጉትን ፖሊሲ የሚቀርፅላቸውን ወኪል ይመርጣሉ።ለዚህም ነው ከኮሎምበስ ምድረ-አሜሪካን ማግኘት በኋላ በፍልሰት ሰሜን አሜሪካን የወረሩት አውሮጳውያን (እና ሌሎችም) አሜሪካን በመረጡት መሪ እና ወኪል መምራት የቻሉት። ከ2 በመቶ የማይበልጡት ቀደምት የምድረ አሜሪካ ነዋሪዎች (“ቀይ ሕንዶች”) የምድረ-አሜሪካ ባለቤትነት ጥያቄ አላነሱም። ቢያነሱም፣ በዴሞክራሲያዊ አሠራራቸው መሠረት መልስ የሚያገኘው ብዙኃን በመረጧቸው ወኪሎች አማካይነት ነው። የአሜሪካ ሕዝብ ቀደምት ነዋሪዎች የደረሰባቸውን ታሪካዊ በደል ከግምት ውስጥ በማስገባት የባሕል ማሳደጊያ ማበረታቻዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ድጋፎችን በብዙኃኑ ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ አድርጓል። ይሁን እንጂ የባለቤትነት ጥያቄ በጥያቄነት ደረጃም ሲቀርብ አይታይም። የዴሞክራሲ ሞዴል የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here