- በቀጣይ ዓመት 30 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ፕሮጀክት ተቀርጾላቸው ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሏል
የአዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ደረቅ ቆሻሻን ወደ እንስሳት መኖነት እና የተፈጥሮ ማዳበሪያነት ለመለወጥ የሚያስችል የፈጠራ ቴክኖሎጂ እውን ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። ቴክኖሎጂውን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ለማስተላለፍ የዲዛይንና የማምረት አቅም ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጿል።
ቴክኖሎጂው የፍራፍሬና የጓሮ አትክልት ተረፈ ምርት የሆነ ደረቅ ቆሻሻን በመፍጨት ወደ መኖነት የሚቀይር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የኮሌጁ ዲን ተሻለ ዱጉማ፣ ቴክኖሎጂው በከተሞች የሚታየውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና በአርሶ አደሩ በኩል ትልቅ ችግር የሆነውን የእንስሳት መኖ እጥረት የሚቀርፍ የፈጠራ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል። ቴክኖሎጂው በሰዓት እስከ ሦስት ኩንታል ደረቅ ቆሻሻ በመፍጨት ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያና የእንስሳት መኖ የመለወጥ አቅም ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።
ኮሌጁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን የሚረዱ 28 የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ባለፈው የበጀት ዓመት በምርምር በማቅረብ፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በማስተላለፍ ጥቅም ላይ መዋላቸውንና በዛም የምርቶቹን ጥራትና ጥቅም ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው አዲሱ የበጀት ዓመትም 30 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በምርምር ተለይተውና ፕሮጀክት ተቀርጾላቸው ተግባራዊ እንዲደረጉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ያስታወቁት ተሻለ፣ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማገዝና በገንዘብ በመደገፍ በቀጣይም በርካታ ሥራ የመሥራት እቅድ መያዛቸውን አውስተዋል።
የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ምርትና ገበያ ለመቀየር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከአይ.ቢ.ኤስ ኢትዮጵያ የፈጠራ ማዕከል ጋር የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጣራ ውጤቶች ወደ ምርት እንዲቀየሩ ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ሰኔ 26/2011 በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ስምምነቱ በኢትዮጵያውያን የተነደፉና ይፋ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ምርት ገብተው ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ ለማድረግ ባለቤቶቹን ከባለሃብቶች ጋር የማገናኘት ሥራን ያካትታል ተብሏል።
እስከ አሁን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች ወደ ምርት ተቀይረው ገቢ እንዲያስገኙ ማድረግ ላይ ያሉ መቀዛቀዞችን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም የኢፌዴሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሹመቴ ግዛው ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011



