የወሲብ ንግድን በሕግ መከልከል ፤ የበሽታውን መንስዔ ትቶ ምልክቱን?

0
883

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሲብ ንግድን፣ ልመናንና ጎዳና ተዳዳሪነትን የሚከለክል አዲስ ሕግ ለማውጣት ረቂቅ ማዘጋጀቱን መነሻ በማድረግ፥ ቤተልሔም ነጋሽ የወሲብ ንግድን በተመለከተ ሕጉ መነሻውን ሳይሆን ምልክቱን ለማከም የሚሞክር እንዳይሆን ሲሉ ያላቸውን ሥጋት አንጸባርቀዋል።

 

 

“የወሲብ ንግድ ፣ አስቀያሚ ማኅበራዊ ክስተት ነው። ወጣት ሴቶች ዝሙት አዳሪ የሚሆኑት ለመኖር ሌላ ምርጫ ስላጡ ነው፤ ይህ ደግሞ የማኅበረሰቡ ችግር ነው።”
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጥር 18/2017 (እ.ኤ.አ) ለሲ ኤን ኤን በሰጡት ቃለምልልስ በሕክምናው መስክ “ምልክቱን ማከም በሽታውን ከማከም ጋር አንድ አይደለም” የሚባል አባባል አለ። ለምሳሌ አንድ ታካሚ ሆዴን አመመኝ ወይም ምቾት ነሳኝ ብሎ ሐኪም ዘንድ ቢቀርብ የመጀመሪያው ተግባር ሕመሙን የሚያስታግስ ክኒን መስጠት መሆን የለበትም። ይልቁንም ሐኪሞቹ የሚያደርጉት ሕመሙን ያስነሳውን ምክንያት ለማወቅ የተለያየ ምርመራ ማድረግ በዚያም ላይ ተመስርቶ ፈውስ የሚያመጣ እርምጃ መውሰድ ነው። የኩላሊት ጠጠር ይሆን የጨጓራ አልሰር ወይም የትርፍ አንጀት እንደ ምክንያቱም ሕክምናው ይለያያል። ምልክትን ማከም በሽታው እንዲስፋፋና እንዲባባስ ከማድረግ ውጪ በሽታውን አያጠፋውም።

የሴተኛ አዳሪነትና የወሲብ ንግድ ጉዳይ ሰሞኑን እንደ አዲስ በየመገናኛ ብዙኀኑና ማኅበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ይኸውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሲብ ንግድን፣ ልመናንና ጎዳና ተዳዳሪነትን የሚከለክል አዲስ ሕግ ለማውጣት ረቂቅ አዘጋጅቶ ውይይት ማካሔዱን ተከትሎ ነው። በበኩሌ የተለያዩ ጥረቶች ባደርግም ረቂቁን ማግኘት አልቻልኩም፤ ስለሆነም ጽሑፌ የሚያተኩረው የሕጉን ተገቢነትና ምናልባትም የክስተቱን መነሻ ሳይሆን ምልክቱን ለማከም የሚሞክር አዝማሚያ ያለበት መሆኑን በመጠቆም ላይ ነው። ለዝርዝሩና ጠለቅ ላለ ፍተሻ ረቂቁን ሳገኝ መመለስ እመርጣለሁ።

የእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት በወሲብ ንግድ መተዳደርን ወይም እኛ በልማድ ሴተኛ አዳሪ ብለን የምንጠራውን ሥያሜ ሲተነትን በገንዘብ ክፍያ ለሚፈፀም ወሲብ ራሷን የምታቀርብ ሰው ሲል ይተረጉመዋል። በዚህ ትርጉም መሠረት አንዲት ሴት ዝሙት አዳሪ እንድትባል ኹለት ነገሮች ሊፈፀሙ የግድ ይላል፤ በምትኩ ገንዘብ ሊሰጣት ለተስማማ ሰው የወሲብ አገልግሎት መስጠት አለባት።

በኢትዮጵያ ዝሙት አዳሪነት የተጀመረው ከውጪ አገር ዜጎች መምጣት በተለይም በኢጣሊያ ወረራ ወቅት እንደሆነና ከዚያ በፊት በወሲብ ንግድ መተዳደር የሚባለው ሐሳብ እንደማይታወቅ ቢነገርም አጥኝዎች ግን በነገሥታቱ ዘመን ጭምር ወሲብን ለቁሳዊ ጥቅም ማግኛ የመጠቀም ባሕል ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እንደነበር ይስማማሉ። በቅምጥነት፣ በጭን ገረድነት አገልግሎት በመስጠት ሕይወታቸውን ይመሩ የነበሩት ሴቶች በአብዛኛው በዝቅተኛ መደብ ላይ ይገኙ የነበሩ እንደሆኑም ጥናቶች ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባም ይሁን በክልል ከተሞች የወሲብ ንግድ ባለፉት ዓመታት በብዙ እጥፍ መስፋፋቱ ይታወቃል። በዚሁ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ላይ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ የተበራከቱት እርቃን ዳንስ ቤቶች በሚል ርዕስ በሳምሶን ብርሃኔ የተዘጋጀው ሐተታ ዘ ማለዳ የአዲስ አበባን ምሽት ሕይወት ያስቃኘ ዘገባም ይህንኑ ያመላከተ ነበር። በኢትዮጵያ በግለሰብ ደረጃ በወሲብ ንግድ መተዳደር በሕግ የተከለከለ ባይሆንም በድርጅት ደረጃ ሴቶችን ማቅረብ ወንጀል ነው።

በነገራችን ላይ በተለያዩ ሚዲያ አጋጥሟችሁ ሊሆን እንደሚችለው ረቂቁ (ከይዘቱ ይልቅ በአጠቃላይ ሐሳቡ) ተቃውሞና ውግዘት እንዲሁም ድጋፍና ጭብጨባ ተችሮታል። የሚበዛው ግን ከተፈፃሚነቱ ጥርጣሬ በተጨማሪ በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶችን ነባራዊ ሁኔታ (በአገራችን 98 በመቶ የሚሆኑት በዚህ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሴቶች በመጨረሻ አማራጭነትና በብቸኛ መተዳደሪያነት የያዙት ናቸው) ያላገናዘበ፣ የሕግ አስፈፃሚውን ክፍተት ያላየና ምናልባትም እነኝህን የኅብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ተጋላጭ የሚያደርግ ሊሆን እንደሚችል ግምት የተሰነዘረበት ነው።

ከተቃውሞ ጎልቶ የወጣው አንድ ሐሳብ ደግሞ በቢቢሲ አማርኛ ላይ የታየው ከተማ አስተዳደሩም ይሆን ምክር ቤቱ ይህን ዓይነቱን ሕግ የማውጣት ሥልጣን የለውም፤ ወንጀል የሚሆኑ ነገሮችን መደንገግ የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ነው የሚል ነው። ከዚህ ሌላ ሕገ ወጥነትን የመቆጣጠርንና ማስፈጸሙን ሥልጣንና ተግባር ለፖሊስ ብቻ የሚሰጥ መሆኑ ተግባሩን ሲያከናውኑ የሚገኙት አካላት ላይ የኀይል እርምጃ ላለመወሰዱ፣ መብት ጥሰትም ላለመፈፀሙ የሚከታተል አካል ከሌለ ሌላ በደል ተጋላጭነትን ያስከትላል።

አንዳንዶች በወሲብ ለመጠቀሚያነት ሴቶችን ማዘዋወርን ጨምሮ ታዳጊ ሴቶች ሳይቀሩ በግዳጅ የወሲብ ንግድ እንዲሠሩ በማድረግ ገቢ መሰብሰብን ብቸኛ ማስቆሚያ መንገድ የወሲብ ንግድን ሕጋዊ ማድረግ ነው ይላሉ። ሕጋዊነት ቁጥጥርን ያመጣል፣ ቁጥጥር ደግሞ ደኅንነታቸውን ያረጋግጣል። በተለይ እንደ ሕንድ ባሉ አገሮች “የወሲብ ንግድ ሥራ፥ ሥራ ነው” የሚል ዘመቻ በስፋት በመደረግ ላይ ይገኛል ሌሎች እንደ ኔዘርላንድና ታይላንድ ያሉ አገሮች ሕጋዊ አድርገው ቀረጥ ይሰበስቡበታል። በኔዘርላንድና ጀርመን እንዲሁም ግሪክና ኒውዚላንድ ከሴተኛ አዳሪነት በተጨማሪ ማገናኘትም ሆነ የሴተኛ አዳሪ ቤት ማዘጋጀት በሕግ የተፈቀደ ነው። እነኝህ አገራት ሕጋዊ ለማድረጋቸው የሚጠቀሰው ማሳመኛ ምክንያት ሕገወጥ መሆኑ ሴተኛ አዳሪነትን በፍጽም ያለማስቀረቱ በሌሎች አገራት ያለው ተሞክሮ ነው።

ከመፍቀድና ከመከልከል ለየት የሚለው በስካንዲኔቪያ አገሮች የሚተገበረው አካሔድ ሲሆን አገልግሎቱን ፈልገው የሚሔዱትን ወንዶቹን መቅጣት እና ከፍያ በመፈጸም ከሴተኛ አዳሪ ጋር ግንኙነት ማድረግን ወንጀል የማድረግ አሠራር ነው። በዚህ ሁኔታ የወንጀል ሸክሙን ከሴቷ ወደ ወንዱ አዙረውታል። ነገሩ “ገዥ ከሌለ ሻጭ አይኖርም” በሚል መርህ ላይ ተመሥርቶ ፈላጊን በመቅጣት አቅራቢን ማጥፋት እንደማለት ነው።

ለነገሩ በከተማ አስተዳድሩ የተዘጋጀው የሕግ ረቂቅ ኹለቱን ያጣመረ እንደሆነ የመገናኛ ብዙኀን ዜና ነግሮናል። ብዙ ጥሩ የሚባሉ ሕጎች የወጡባት ነገር ግን “የአፈጻጸም ችግር” የተለመደ ዜማ በሆነባት አገራችን በትክክል ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ ነው። ይህ እንግዲህ ምን ያህል በጥናት ላይ የተመሠረተ ነው? ችግሩን ከመሠረቱ ለማጥፋት (ማኅበራዊ ቀውስ ያመጣው እንደመሆኑ) ሕግ ብቸኛ ወይም ቀዳሚ መፍትሔ ነው ወይ ወይስ መንግሥት ተነስቶ የሥነ ምግባር አስተማሪ ሊሆን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።

ከቅብጠት ባትቆጥሩብኝ በመንግሥት ቋንቋ “የሚመለከታቸው አካላት” ሲሰበሰቡ ራሳቸው በወሲብ ንግድ የተሠማሩት ድምጻቸው ተጠይቋል? የሚለውም ሌላው ነው። ለምሳሌ የወሲብ ንግድ ሥራ ላይ መሠማራትን በሚፈቅዱ አገራት ያሉ በዚያ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶችም በማኅበራት በመታቀፍና በመመዝገብ መብታቸውን የሚያስከብሩበት መንገድ የተረጋገጠላቸው ናቸው። ዕውቅና ተሰጥቷቸው በየአገሮቻቸው በተለያዩ መስኮች እንደ አንድ ኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ እንዲያደርጉም ዕድል አላቸው።

ወደ አገራችን ስንመጣ ምናልባትም እንደምንገምተው ስለነሱ ከመወራት በቀር ድምጻቸው በተለይ በፖሊሲና በማኅበረሰብ አካልነት ዕውቅና ተሰጥቷቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ተደርጎላቸው የሚያውቅ አይመስለኝም።

ባለኝ መረጃ መሠረት በማኅበር የተደራጁ በተመሳሳይ ሥራ መስክ የተሠማሩ ሴቶች የማውቀው ሥራውን አቁመው ከኤች አይ ቪ መከላከል ጋር በተገናኘ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚንቀሳቀሱ ሌሎችን ከሥራው እንዲወጡ ለማስተማር የተቆራረጠ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን ነው። በአሁኑ ወቅት ስላሉበት ሁኔታም መረጃው የለኝም።

መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን ሴተኛ አዳሪነት የከፋ፣ በአገራችን ሁኔታ ሰፊ ሰብኣዊ መብት ጥሰት የሚካሔድበት፣ የሰውን ልጅ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መሆኑ ነው። በአገራችን ሥራው ተስፋፍቶ መረን እስኪወጣ የመቆጣጠርና የሚካሔድበትን አግባብ በመደንገግ ፈንታ መንግሥት እንደማይመለከተው ጉዳይ ሆኖ ማኅበረሰቡም መኖሩን የማይክደው፣ እጠየፈዋለሁ የሚለው ነገር ግን ራሱ የማኅበረሰብ ክፍሉ በአገልግሎት ተጠቃሚነት የሚሳተፍበት ሆኖ ቆይቷል።

በሥራው ከተሠማሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አለመሆንና በተለይ ታዳጊ ሕፃናት ሳይቀር ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ የሚገደዱበትና የሚገፋፉበት አግባብ እንደመኖሩ፣ የዜጎችን ሰብኣዊ መብት ጥሰት ለማስቆምም ሲባል ግልጽ ፖሊሲ ማውጣትና መተግበር የግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ደርሰናል ብቻ ሳይሆን እጅግ ዘግይተናል።
ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በአንድ ባለሙያ የተሰጠ ሁሉን ዐቀፍ አስተያየት ላስቀምጥና ሐሳቤን ልቋጭ።

የሕግ ባለሙያ፣ አማካሪና የስርዓተ ፆታ መብት ተሟጋቿ ሰብለ አሰፋ ለቢቢሲ አማርኛ እንደተናገረችው የወሲብ ንግድን የሚያግድ ሕግ ይውጣ ቢባል እንኳን በዘፈቀደ ሳይሆን በበርካታ ጥናቶች ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል።

የወሲብ ንግድን መከልከል ጉዳይ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የምትናገረው ሰብለ በተለይም የወንጀል ሕጉ በ1997 ሲሻሻል የወሲብ ንግድና ፅንስ ማቋረጥን የመከልከል ጉዳይ በጣም አነጋጋሪ ሁኔታም እንደነበር ትጠቅሳለች።

በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ፈቅደው የሚገቡበት ባለመሆኑ ወደዛ የሚመራቸው ማኅበራዊ ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ ድርጊቱን ሕገወጥ ማድረጉ “ከሕመሙ ይልቅ የሕመሙ ምልክት ላይ ማተኮር”፤ ከዚህም በተጨማሪ ሰፋ ያለውን የፖሊሲ ጉዳይ እልባት ሳያገኝና ሴቶቹን ወደዛ የሚገፋፋቸውን ውስብስብ ነገሮች መፍትሔ ሳይሰጥና ተገቢውን የማብቃት ሥራ ሳይሰራ ዝም ብሎ ማገድ ትክክል አለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዶበት በቂ ጥናት ተሰርቶ ሕጋዊ እንዲሆን መደረጉንም ትናገራለች።

በወቅቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ነገር በአግባቡ እንደተመለከተውና ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የሴቶች መብት ተሟጋቾች ጥናት የተሳተፉበት ጥናት መቅረቡን ታስረዳለች። ከዚህም በተጨማሪ በየከተማው ውይይት ተደርጎ ባለው የአገሪቷ ሁኔታ የሚሻለው ሕጋዊ አድርጎ መቀጠል ነው በሚል ተወስኗል ትላለች።

“የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ይህንን እከላከላለሁ ሲል ወንጀል እያደረገው ነው፤ ያንን ለማድረግ ሥልጣኑ የለውም። ሥልጣኑ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው” ትላለች።

በወሲብ ንግድ ላይ መሰማራት ሴቶቹ መርጠው ይገቡበታል ተብሎ የሚታሰብ ባለመሆኑ ለጎዳና ልጆች እንደታሰበው ለሴቶቹም የገቢ ማግኚያ መንገድ መቀየስ ሲገባው ይህ አለመሆኑ “በጣም አደገኛ አካሔድ ነው፤ የሴቶቹን መብት እየተጋፋ ነው” በማለት ታስረዳለች።

በተጨማሪም ባለሙያዋ ክልከላው ሲደረግ አፈፃፀሙ እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች። በረቂቅ ሕጉ መሰረት የጎዳና ወሲብ ንግድን ለመከላከከል ቅጣቱ ተፈፃሚ የሚሆነው በንግዱ ላይ የተሰማሩት ሴቶች ናቸው።

“የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሶችን እየላከ ጎዳና ላይ ያሉ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችን ከሆነ ዒላማ የሚያደርገው ይሔ ክልከላ ሳይሆን ዓላማው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህ ከሆነም አፈፃፀሙም ከባድ ነው፤ ለከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰት፣ የፆታዊ ጥቃት ለመሳሰሉት የሚዳርግ ነው፤ እንደ ወንጀለኛም እንዲቆጠሩ ይዳርጋል” ትላለች።

ሰብለ እንደምትለው የወሲብን ንግድ ሕገ መንግሥቱ ስለማይከለክለው በዚያ መሰረት ወንጀል ተደርጎ አልተቆጠረም ማለት ይህ አንድ የሥራ መስክ ሊሰማሩበት የሚገባ ጉዳይ ሲሆን መከልከል ደግሞ የሴቶቹን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጣረስ ነው ትላለች።

“ይህ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው። ሕገ መንግሥቱም ስለማይከለክለው እንደ አንድ የገቢ ማግኛ የኢኮኖሚ መስክ የመምረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። የከተማ አስተዳደሩም የመከልከል መብት የለውም” የምትለው ሰብለ የከተማ አስተዳደሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንደገና ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስተያየቷን ሰጥታለች።

በእርግጥ በሚዲያ እንደተዘገበውና ከላይ በጠቀስኩት የቢቢሲ ዘገባ ላይም እንደተመለከተው ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪ ፌቨን ተሾመ አስተዳደሩ ትረስት ፈንድ አቋቁሞ በሕጉ የሚዳሰሱት የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው ። የተነሳውን ተቃውሞ በመመልከት ረቂቅ ሕጉ በድጋሚ ይቃኛል፣ ጊዜ ተወስዶበት ይዳብራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በግሌ ረቂቁን የማየት ዕድል ገጥሞኝ የበለጠ ይዘቱን በማስረዳት ለመመለስ የሚደረገውን ውይይትም አካቶ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here