የፖለቲከኞቻችን ንግግሮች መዘዝ ከመለስ ዜናዊ እስከ ዐቢይ አሕመድ

0
840

ፖለቲከኞቻችን በአደባባይ እና በብዙኃን መገናኛዎች ለሚያደርጉት ንግግር ምን ያህል ጥንቃቄ ያደርጋሉ? የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያዋ ቤተልሔም ነጋሽ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሯቸው እና ዘላቂ እና አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ ንግግሮችን በምሳሌ በማስረዳት ‹ጥንቃቄይደረግ› በማለት ይመክራሉ፡፡

የምንናገራቸውንም ሆነ የምንጽፋቸውን ቃላት ኃይል የሚጠራጠር ወይ ተፅዕኗቸውን የሚያቃልል ካለ ታሪክ ያገላብጥ።በጀርመን ናዚ ከዚያም በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያና ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በፊት ሩዋንዳ በተቃራኒ ጎራ የቆሙ ቡድኖች አናሳ ናቸው ባሏቸው ቡድኖች ላይበሚዲያ ሳይቀር ያደረጉት ጥላቻ የተሞላ ቅስቀሳ ግጭት ቀስቅሶ ወደ ጅምላ ግድያ የተቀየረው በዚሁ አኳኋን“እኛ” እና “እነሱ” ተብሎ በተዘራ ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ፣ የጠላትነት ፍረጃ ምክንያት ነው።
የዚች አጭር ጽሑፍ ዓላማ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊም ሆነ በአሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ንግግሮች ላይ ትንተና ማቅረብ አይደለም። ይልቁንም ጥቂት ምሳሌዎችን በመጥቀስ የፖለቲካ ንግግር በአግባቡ መያዝ እንዳለበት እና የፖለቲካ ተግባቦት በራሱሳይንስ እንደመሆኑ በዚያ የሚመራ አግባብ ያለው መልዕክት በንግግሮች መተላለፍ እንዳለበት ለማስታወስ ነው።
የፖለቲካ ተግባቦትን (Political Communication) ከዘርፉ ጎምቱ ምሁራን አንዱ ብሬይን ማክኔይር እንዳመለከተው በአብዛኛው የሚወክለው በመገናኛ ብዙኃን በኩል የሚተላለፍ የፖለቲካ መልዕክት የሚባለውን ነው።
ተግባቦት የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት በፖለቲከኞችና ፖለቲካው ውስጥ ባሉ ተዋናዮች የሚዘጋጅየፖለቲካ ማስታወቂያንጨምሮ በየመድረኩ የሚደረጉ ንግግሮችን ሲያካትት በመጀመሪያ በግለሰቦች፣ ቀጥሎም ተመሳሳይ ሐሳብ ባላቸው ሰዎች አስተሳሰብና ባሕርይ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ በስፋት የታየና የተጠናም ነው።
በዚህጽሑፍ አዘጋጅዋእምነት፣በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት የመንግሥትና የሕዝብ መራራቅና በመንግሥት ላይ መከፋትን ቀጥሎም አመፅን ያመጣው የተግባቦት እጥረት ነው።ሕዝቡ በአገሪቱ ውስጥ ምን ይካሔድ እንደነበር በግልጽ አይነገረውም። በመገናኛ ብዙኃን ከሚደገፍ እልም ያለ ቅጥፈትና ፕሮፓጋንዳ ባለፈየሕዝቡን አንገብጋቢ ችግሮችን ለመስማትምየሚፈቅድ አልነበረም። የሕዝብ ጥያቄና ሮሮ ችላ በመባሉምብሶቱ ወደ አመፅ እስኪሔድሕዝቡን አባከና ያለው አልነበረም።
የመለስ ዜናዊ አፍ ወለምታዎች
መለስ ዜናዊብዙ አወዛጋቢ ንግግሮችን በመናገር የሚታወቁ ነበሩ። ፓርላማውን ፈገግ እስከሚያሰኝ የኋላ ንግግራቸው ድረስ በተለያዩ ጊዜያት የሚያደርጓቸው ንግግሮች አንዳንዴ የሚያበሳጩና የሚያስቆጡም ነበሩ።“ባንዲራ ጨርቅ ነው” የሚለው ንግግራቸው መዘዙ ቀላል አልነበረም። አባቶቻችን ስንት የከፈሉለት የነፃነት ተምሳሌታችን የኩራታችን ምልክት የምንለውን ሰንደቅ ዓላማ እንዲያ ብለው ሲያዋድቁና ሲያቃልሉት ያላዘነ አልነበረም። በኋላም የባንዲራ ቀን በግድ ይከበር ቢባልም ከዚያ በኋላ በባንዲራ ጉዳይ የምናምናቸው አልሆኑም፤ ንግግሯ ያመጣችው መዘዝ።
ሌላው የሚሾሟቸው ሚንስትሮች የብቃት ችግር አለባቸው በሚል ሲተቹ“አራተኛ ክፍልም ቢሆን ለፓርቲዬ ከታመነ ሚኒስትር ይሆናል” አሉ። ይህ ምን ታመጡ የምትል የንቀት አፍ ማዘጊያ ንግግር ዘላለም በባለሥልጣናት ላይ ጥላቻ እንዲፈጠርና መተማመን እንዲጠፋ አደረገ። ሁሉም ባለሥልጣን በዚህ ተፈርጆም የሚቀበለው አጣ።
የፍርሐት መንፈስ በመዝራት በማሸበር እኔ ብሔድ ጉድ ይፈላባችኋል፣ ሌሎች ቢመጡ አገሪቱ ትፈርሳለች፣ ይኼኛው ሕዝብ ወይም ብሔር ሁነኛ ጠላታችሁ ነው፣ ያለ ኢሕአዴግ ተስፋ የላችሁም እያሉ ከመለስ ዜናዊ ጀምሮ እስከ በረከት ስምዖን እና ሌሎች አንጋፋ የገዥው ፓርቲ ሰዎች አገዛዛቸውን ለማስቀጠል ያደርጉት የነበረ ፕሮፓጋንዳም ተጠቃሽ ነው።
የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲው ጄራርድ ሚጊየል “TheControlofPoliticiansinDividedSocieties:ThePoliticsofFear” በሚለው ጽሑፉ ሆን ብሎም ይሁን በተፈጥሮ በተለያየ ብሔሮች የተከፋፈሉ ሕዝቦች ባሉባቸውና የዴሞክራሲ ተቋማት ባልዳበሩባቸው አገራት፥ይህን ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳ በመሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ መሆኑን ጠቅሷል።
የመለስ ዜናዊ የሚያስከፉ ንግግሮችብዙ ቢሆኑም ሁሉም በዜሮ ይባዙ ማለት ግን አግባብ አይደለም። አሳማኝና አንደበተ ርቱዕነታቸውን የሚመሰክሩ ብዙ ማብራሪያዎችና ንግግሮች ነበሯቸው፡ ጊዜው ረዘም ቢልም የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሲከበር ያደረጉት ንግግርበጎ ምሳሌ ይሆናል።
የዐቢይ አሕመድ የአፍ ወለምታዎች
ዐቢይ አሕመድም ንግግሮቻቸው በአብዛኛው በመልካም የሚገለጡ ለውጡ በተግባር ከመጀመሩ በፊትም የተሻለ ነገን ለማለም የሚያነሳሱ፣ ብዙዎችን የፈወሱ፣ አንድነትን የሰበኩ፣ ትናንሽ ልዩነቶችን ያጠበቡ፣ መላውን ሕዝብ ከጎናቸው ለማሰለፍ ያስቻሉ ነበሩ። የሰኔ 16ቱን የድጋፍ ሰልፍ መንፈስ ያስታውሷል።
ሚሊኒየም አዳራሽ ድንገት ተገኝተው በምሕረት ደበበ (ዶ/ር) በተዘጋጀው መድረክ ላይ ያደረጉት የማነቃቃት መንፈስ ያለው ንግግራቸውም በበጎው የሚነሳ ነው።
በጀርመንፍራንክፈርት ከዛም በፊት በአሜረካ ሎስ አንጀለስ፣ አትላንታና ሜኒሶታ በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያደረጓቸው ተስፋ የተሞሉና አገራችን ያለችበትን ሁኔታ የሚያመላክቱ፣ ኢትዮጵያዊያኑ ስላሉባቸው አገራት ታሪካዊ ዳራና በታሪክ ስላለፉባቸው አስቸጋሪ ወቅቶች በመጥቀስ በዜጎቻቸው ልፋት ከመከራ የወጡበትን ጠቅሰው ያደረጓቸው ስሜት የሚነኩ ጥበብ የተሞላባቸው ንግግሮችም አሉበት።በዚህም ኢትዮጵያዊያኑ ራዕያቸውን እንዲጋሩና ከጎናቸውም እንዲሰለፉ ማድረግ ችለዋል።‹የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ› መመሥረትና ሥራ መጀመር ይህ ካስከተላቸው ስኬቶች መካከልም ይጠቀሳል።
ነገር ግን በእነዚህም ሆነ ሌሎች ጊዜያት በንግግሮቻቸው ጣልቃ በደፈናው “ጠላት” ብለው በሚፈርጇቸውና በግልጽ በማይነግሩን አካላት“ሌሎች” ላይ የሚያቀርቡት ውንጀላ ግን ምናልባትም በሁሉም ንግግሮቻቸው ውስጥ አሉ።
የታጠቁ ወታደሮች ቤተመንግሥቱን ከበው አገር በመሰለኝና ደሳለኝ ሲታመስ አራት ኪሎና አካባቢው መንገድ ተዘግቶ ሌላውም የከተማው ክፍል ሲሸበር በዋለበት ከሰዓት በኋላ የተፈጠረውን ሁናቴ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በሳቸው አባባል“ማዕበሉ” ካለፈ በኋላ ለፓርላማው ያደረጉትና ብዙ ሰዎች ደስ አይልም ብለው ከወሰዷቸው ንግግራቸው ብንወስድ “አምስትና ዐሥር ሰዎች ለክፉ ዓላማ ቀስቅሰው የታጠቀ ወታደር፣ ቤተመንግሥት ድረስ መምጣት የሚችልበት አገር ነው።… ባልተለመደ ሁኔታ እየተዝናናሁ፣ እየሳቅሁ ነበር ኢንተርቪ የሰጠሁት፣ ውስጤ እርር እያለ፣‹ለምንድን ነው ይህን ያደረከው?› ያላችሁ እንደሆነ ከቡራዩ፣ ከሰበታ ከለገጣፎ አርሶ አደር ወጣት ተደራጅቶ እየመጣ ነው ሊዋጋ፣ መንግሥታችን ተነክቷል ብሎ እየመጣ ነው። እኔ የተዝናና ነገር ካላሳየሁ በስተቀር ሕዝቡ ሊረጋጋ አይችልም። የተዝናናሁ መስዬ ሕዝብ አረጋግቼ የሰው ሕይወት መታደግ ደግሞ የሰጣችሁኝ ኃላፊነት ነው። በነገራችን ላይ በዛ ሁኔታ ከታለፈ በኋላ ‹ወይኔ አመለጠን ሳንገድለው› የሚሉ ኃይሎች ነበሩ። አቃለን አንመልከተው” የሚለው ይገኝበታል።
በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ አካባቢ ሕዝቦችን የለውጡ ጠባቂዎች አድርጎ መጥቀስ ምን አስፈለገ? በግልጽ በመረጃ ሊነግሩን የማይችሉ ከሆነ በደፈናው የሆኑ የማይታወቁ “ጠላቶች” ሊገድሏቸው አስበው እንደተንቀሳቀሱ ለሕዝቡ መንገር ለማሸበር ካልሆነ ምን ይጠቅማል? ይኼ ፕሮፓጋንዳ እንጂ ምን ሊባል ይችላል?
ፖለቲከኞቻችን የሕዝብን ትኩረት ለማግኘት ቃላት ማሰማመር ሲወዱ ተከታዮቻቸው ደግሞ የእነሱን ቃላትና ስያሜዎች ተቀብለው ማስተጋባትን እንደ ድጋፍ መግለጫ ይወስዱታል። በፖለቲከኞቻችን ንግግሮች የምንሰማቸውን አዲስ ቃላት ወይም በአገባብ ምክንያት አዲስ ትርጉም ያገኙ ነባር ቃላትን በቶሎ ቀልበን የምንይዛቸው፣ ለራሳችን በሚመች መልኩ ጥቅም ላይ የምናውላቸውና የንግግራችን አካል የምናደርጋቸውም ለዚያ ነው። ቃላት አመለካከትና አስተሳሰብን፣ ልማድና ባሕልን ለመቀየር፣ የሚደረግና የማይደረግን ለመለየት የምንጠቀማቸው የመጀመሪያዎቹ መሣሪያዎች ናቸው።
“የቀን ጅብ” የሚለው ቃል ለዚህ ምሳሌ ነው። ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት የሕዝብ ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ የዘረፉ ያሏቸውን የመንግሥት አካልናየገዛ ፓርቲያቸውን አባላት እገሌ ከእገሌ ሳይሉ በጥቅል“የቀን ጅቦች”አሉ። አገርም ሆ! ብሎ በየማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ የራሱን ግምት እያነሳ “እነ እገሌን ነው” ብሎ ደመደመ። ጥያቄ የሚያነሳና ‹አልተደመረም› የተባለ ሁሉ ስያሜና ስድቡ ይኸው ሆነ። የሰሞኑን እስር ተከትሎ ደግሞ መግለጫቸው ላይ “ካንሰር” የሚል አሻሚ ቃል ተጠቅመዋል።
በፍራንክፈርት ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር ባካሔዱት ጥያቄና መልስም እንዲሁ ጠቅላይ ሚንስትሩ “እኛ መደመር የምንለው በተለይ አማራና ኦሮሞ በስተቀኝና በስተግራ ያላችሁ፣ በብዙ መልኩ የተደመራችሁና ለዛ አገር ምሰሶ ሆናችሁ የተፈጠራችሁ ሕዝቦች፣ በማይረባ ፖለቲካ ከመገፋፋት ተቆጥባችሁ፣ ተደምራችሁ፣ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም ፈርጥ እንድትሆኑ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።‹መፈናቀል መቼ ይቆማል?› ለሚለው አፈናቃዮች መፈናቀል ነውር መሆኑ ሲገባቸው ነው።… ተፈንዮችና አፈናቃዮች ካሉ ሚስቶቻቸውንም ፈንግለው ከቤት ማስወጣታቸው ስለማይቀር ማቀፍ እንጂ መገፍተር ተገቢ አለመሆኑን በተከታታይ በማስተማር ሲቀየር ይቆማል። ኢትዮጵያን ማኮሰስ የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን ኢትዮጵያን ማኮሰስ አይቻልም።… አሁን ያለው ሁኔታ አምባገነን መንግሥት አያስፈልገንም፣ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል፣ ሠላም ያስፈልገናል፣ ልማት ያስፈልገናል ብለው አምርረው የታገሉ ሕዝቦች መንግሥት ዴሞክራሲ ያስፈልገናል ሲል የመንጋ አምባገነኖች ግን ተበራክተዋል። አምባገነንነት የማያስፈልገው ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለመንጋ ቡድንተኞች ጭምር ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከላይ የተቀመጡት ዓረፍተ ነገሮች በብዙ መልኩ ሊተረጎሙ የሚችሉ የእኛ እና እነሱ ክፍፍልን የሚያጠናክሩ የተወሰነን ክፍል ለማስደሰት ተብሎ ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ የተባሉ የሚመስል ነገር አላቸው።
በአይስላንድ የሰብኣዊ መብቶች ማዕከል የጥላቻ ንግግሮችን ሁኔታ በቃኘበትና እንዴት መዋጋት ይቻላል ለሚለው የመፍትሔሐሳብ ባቀረበበት ሪፖርት የጠቀሰውም ይህ አካሔድ አደገኛ መሆኑን ነው።
ትንተናው እንደሚለው በአንድ ሰው አዕምሮ የሚመላለስ አመለካከት እስስካልተገለጸና እስካላወጣው የሚጎዳው ራሱኑ ነው። ይህ ሰው ታዋቂ ቢሆን አልያም ፖለቲከኛና የአገር መሪ ነው ብንል ሐሳቡ ወጥቶ ሲነገር የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚነኩ ድርጊቶችን ማስከተሉ አይቀሬ ነው።በተለይ ሐሳቦቹ አዎንታዊ ካልሆኑና ውጤታቸው አሉታዊ ሲሆን ባስ ሲልም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን አልያም ቡድኖችን የሚያጠቁ፣ ክብሩን የሚያዋርዱ ከሆነ ምላሽ ሊሰጣቸው የግድ ነው። ንግግሮችን በአንክሮና በጥንቃቄ መስማት የሚገባውም ለዚሁ ነው።ምላሽ ካልተሰጣቸውና ዝም ተብለው ከታለፉ እንደ መደበኛ ነገር ሊታዩ ከዛም ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ።በፈጠራ ወሬ፣ በሰዎች ጥርጣሬ ላይ ተመሥርቶ በተዘራ መርዝ እና በፌስ ቡክ ፖስትና በአሉባልታ ምክንያት ተደብድበው የተገደሉ ንፁኃን ዜጎች መኖራቸው ይታወቃል።
አንድ ቡድን ላይ ያነጣጠረ ንግግር በዚያ ቡድን ላይ ትክክል ያልሆነ አስተሳሰብ ብሎም ጥላቻ እንዲኖር ያደርጋል። ጥላቻው አድጎ ወደ መንጋ ፍርድም ይቀየራል፤ ተቀይሯልም። በተለይ ጠቅላይ ሚንስትራችን የቡድኑን ማንነት በግልጽ ያላመለከተና ለትርጉም ክፍት የሆነ ውንጀላ ቀድሞ ለተመሠረተ የግለሰቦች የራስ እሳቤ ተጋልጧል፤ ለሕልፈት የዳረጋቸው ሰዎችም አሉ።
በእኛ አገር ጥንቃቄ የጎደለው የፖለቲከኞች ንግግር የዘር ፍጅት ላይ ይደርሳል ብለን ክፉ መመኘት ባንወድም፣ ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እንዲሉ መጠንቀቅ ግድ ነው። መጭው ምርጫ መሆኑንተከትሎም አሻሚናለትርጉም የተጋለጡ የፍረጃ ንግግሮችን አውቆም ይሁን ሳያውቁም ከመጠቀም መታቀብ ያስፈልጋል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ እና ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here