ሥራ አስኪያጁ

0
651

የዛሬ 2 ዓመት ገደማ የጋዜጠኝነት ሞያ ስጀምር የምዘግበው ንግድና ቢዝነስ ተኮር ዜናዎችን ነበር ፡፡ አንድ ቀን የሆነ ትልቅ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅን ለማነጋገር ተላኩኝ፡፡ የሰውየው ዕድሜያቸውም ቦርጫቸውም ገፍቷል፤ ብቻ ድራማ ላይ የሚታዩትን ሽበታም የኩባንያ ኃላፊዎችን ይመስላሉ፡፡ እኔም ለትልቅ ሰው የሚገባውን ዓይነት ሠላምታ አቅርቤላቸው ወደ ጥያቄዬ ገባሁ፡፡ ይሁንና በመከካል አንድ ያልጠበቅኩት ነገር ተፈጠረ፡፡
እዚህ ጋር አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ አንዲት ሴት ከንግድ ጋር ተያያዥነት ያለው ሥራ በምትሠራበት ወቅት የሚጠበቁባት መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ማወቅ እንዳለባት አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በአጠቃለይ እንዲሁም በባንክና ኢንሹራንስ ዙሪያ በተለይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት መከታተል ይገባታል፡፡ መቼም ቁጥር የመደመርና የመቀነስ ጉዳይ ለቀባሪው ማርዳት ካልሆነብኝ በቀር የአስፈላጊነቱን ጉዳይ አሌ ማለት አይቻልም፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ነገሮች የጾታ እቀባ የለባቸውም፡፡ ማንኛውም ሰው የቢዝነስ ዜና እሠራለሁ ብሎ ሲነሳ የሚጠበቅበት አነስተኛ መመዘኛ መሆናቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እኔም በዚህ ሥራ ላይ ስሠማራ እንደማንኛውም ጋዜጠኛ ሒሳብም ኢኮኖሚም በከፍተኛ ደረጃ እንኳን ባይሆንም በበቂ መጠን አውቄ ነው፡፡
በዚህ ግንዛቤ ነበረ ለሥራ አስኪያጁ ጥያቄ አዘጃጅቼ የሔድኩት፡፡ ደብተርና እስክሮብቶ ይዘው ሲጠብቁኝ ምንም አልገባኝም ነበር፡፡ የኩባንያቸውን ትርፍና ገቢ እየጠቀስኩኝ የመጀመሪያውን ጥያቄ አቀረበኩላቸው፤ መልሱን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ በወረቀታቸው ላይ የነገኳቸውን የገንዘብ መጠን በማስፈር ገቢና ወጪን በመቀናነስ ትርፍ እንዴት እንደሚገኝ ያስተምሩኝ ጀመር፡፡ ነገሩ ግራ ቢገባኝም ድፍረት እንዳይመስልብን ብዬ በጥሞና ማዳመጥ ቀጠልኩኝ፡፡ ከሰውየው ጋር በነበረኝ ቆይታ ብናደድም ሥራዬን ፈጽሜ ወደቢሮዬ ተመልሻለሁ፡፡ ይሁንና ሰውየው እንዴት ቢያስቡኝ ነው እያልኩ በውስጤ ማብሰለሰሌን ለቀናት አላቋረኩም ነበር፡፡
ሥራውን እየለመድኩት ስመጣ ግን ብዙ ጊዜ ከባልደረቦቼ ስነጋገር ወንዶቹ እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደማያጋጥማቸው፤ ሴቶቹ ግን በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ተረዳሁ፡፡ አሁን ከምር በጣም ተናደድኩ!
በጊዜ ሒደት ብዙ ወንዶች ሳያስቡት በሥራቸው ላይ ሴት ስታጋጥማቸው የሚሳዩት ባህሪ እንደሆነ እየተገነዘብኩ መጣሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገርየው ከዚህም ከፍ ሲል እስከ ጾታዊ ትንኮሳ ሊደርስ ይችላል፡፡ እንደኔ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያላለፈች ሴት አለች ብዬ አላምንም፡፡ ይህ የሚያመለክተው ማኅበረሰቡ ለሴቶች የሚሠጠው ግምት የተዛባ መሆኑን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሴቶች ያለው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ብዙ በሥርዓተ ጾታ ሥራዎች ዙሪያ መሠራት እንዳለበት የኔ ገጠመኝ አንድ ማሳያ ይሆን እንደሆነ እንጂ በፍፁም ብቸኛው እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የቅርቡን የሚኒስትሮች ሹመት ብንወስድ እንኳን መወያያ የነበረው የብቃትና ልምድ ጉዳይ ሳይሆን ሴት ተሿሚዎች የተመለከተና ጾታን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ ለምን ይህ ሆነ የሚል ካለ ኅብረተሰባች ለሴቶች የሚሰጠው ግምት ወይም አመለካከት ውጤት ነው ባይ ነኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚቀረንን ሥራ ሳስበው ድክም ስለሚለኝ ጽሁፌን በዚሁ ባበቃ ይሻለኛል፡፡

menna.a@ethiopianbusinessreview.net

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here