የብርሃኑ ድጋፌ “ለዛ”

0
1167

ብዙ የመዝናኛ ብዙኀን ዝግጅቶች በአማራጭነት ያልቀረቡበት ጊዜ ነበርና በልጅነቱ ጆሮዎቹም ሆኑ ዓይኖቹ በተለይ ቅዳሜ ምሽት ፊልም በማየትና ሙዚቃ በማዳመጥ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ። እርሱም አንዱን ብቻ አይመርጥም፤ ይልቁንም በእኩል ሰዓት ያስተናግዳቸዋል፤ ዓይኖቹ በየሳምንቱ ቅዳሜ ማምሻ የሚታየውን “ታላቅ ፊልም” ሲመለከቱ፤ ራድዮኑን ደግሞ ወደ ጆሮው አቅርቦ የቅዳሜ ምርጥ የሙዚቃ ምርጫ ፕሮግራምን ይከታተላል። መከታተል ብቻ አይደለም፤ ከፍ ሲል የሚወዳቸውን ሙዚቃዎች እየመረጠና እየቀዳ ለጋዜጠኛ ታምራት አሰፋ በመላክ የራሱን ሙዚቃ ምርጫ ይሰማል፤ ያሰማል።

ከልጅነት ዘመን በዚህ መልክ የጀመረው የራድዮንና የሙዚቃ ወዳጅነት አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ፤ “እኔም የሙዚቃ ግብዣ ባዘጋጅ” የሚል ምኞት ላይ ደረሰ፤ የዛሬው በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ የሬድዮ ፕሮግራም እንዲሁም የለዛ ሽልማት አዘጋጅ፤ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ።

ሆሊውድና ፕሮፋይል መጽሔትን የሚያስታውስ የብርሃኑን አሻራ ማየት ይችላል። የኅትመት ውጤቶቹ የቢልቦርድና የቦክስ ኦፊስ ሰንጠረዥን እንዲሁም የሙዚቃ ግጥሞችን ጋዜጣ ላይ በማቅረብ አንባቢን ከአዲስ ባሕል ያስተዋወቀም ነበሩ። በኢትዮጵያ ቴሌቨዥን መቶ ኻያ ፕሮግራም በመሳተፍ ብሎም ሾውቢዝ በማዘጋጀትም ሠርቷል። ታምራት አሰፋን መንገድ ላይ በአካል ካገናኘው አጋጣሚ በኋላ ነው ለራድዮን ፕሮግራም ሥራ ተመርጦ ራሱን ከጌታቸው ማንጉዳይ፣ መዓዛ ብሩ፣ ተፈሪ ዓለሙና አበበ ባልቻ መካከል ያገኘው።

“የመጀመሪያ ቀን ከመደንገጤ የተነሳ ‘ኦን ኤር’’ የሚለው ቀይ መብራት ሳይ አምቡላንስ ደረቴ ላይ የተገጠመ ይመስለኝ ነበር” ሲል የመጀመሪያ ቀን ፕሮግራም ቀረጻ ሁኔታውን የሚያስታውሰው ብርሃኑ፤ አሁን ላይ በመዝናኛው ዘርፍ ጋዜጠኝነት የበቃና ምሉዕ ሥራን ከሚያቀርቡ ጥቂት ባለሙያዎች ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።

የሚወደውን የሬድዮ መርሃ ግብር አዘጋጅነት ሲያነሳ ታምራት አሰፋን፤ ፊልም ላይ ስላለው ተሳትፎ ከተጠየቀ አብርሃም ገዛኸኝን እንዲሁም ስለ ለዛ ሽልማት የተባለ እንደሆነ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከአፉ የማይነጠሉ ናቸው።

ዘንድሮ ለዛ ሽልማት ለዘጠነኛ ጊዜ ይካሔዳል። አድማጭና ተመልካቾችም ድምጻቸውን በvote.lezashow.com ላይ እየሰጡ ይገኛሉ። መስከረም 2012 ላይ ሊካሔድ የሚጠበቀውን ይህንኑ የለዛ ሽልማት በተመለከተና ስለ ለዛ የራድዮን ፕሮግራም፤ እንዲሁም ብርሃኑ ድጋፌ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያሳየውን የፊልም ላይ ተሳትፎ በማንሳት ከአዲስ ማለዳዋ ሊዲያ ተስፍዬ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ ለዛ የሬድዮ ፕሮግራም እንዴት ተጀመረ? እንዴትስ ወደ ሽልማት ዝግጅት ውስጥ ሊገባ ቻለ?
ብርሃኑ ድጋፌ፡ ለዛ የሬድዮ ፕሮግራም በአዲሱ ዓመት 12 ዓመት ይሆነዋል። መጀመሪያ 97.1 ኤፍ ኤም አዲስ ላይ የጨዋታ ፕሮግራም መሥራቾችና አዘጋጆች አንዱ ነበርኩና በዛ ላይ ነበር የሚቀርበው። ከዛ ሸገር የሬድዮ ጣቢያ ሲከፈት የራሴ የአየር ሰዓት ኖረኝ። እንደ ማንኛውም ፕሮግራም የራሴን የፕሮግራም ምክረ ሐሳብ አቅርቤ ተቀባይነት አገኘና ወደ ሥራ ገባሁ።

ሽልማቱ ደግሞ የዛሬ 9 ዓመት ነው የተጀመረው። በወቅቱ የሚወጡ አልበሞች በጣም ትንሽ ነበሩ። አዳዲስ ሥራዎችም አይገኙም ነበር። የለዛ ፕሮግራም በሙዚቃ ግብዣው ከሳምንቱ ሐሙስ ቀንን ለኢትዮጵያዊ ሙዚቃ ሥራዎች የሰጠ ቢሆንም አዳዲስ ሥራዎች ግን ጠፉ። በወቅቱ የኮፒ ራይት፣ የገበያው ጉዳይና የመሳሰሉት ላይ መቀዛቀዝ ነበር። ቢያንስ እንዲህ ዓይነት ሽልማት ቢጀመር የሙዚቃ ባለሙያውን ሊያነሳሳው ይችላል በሚል፤ ከዕውቅናውም በዘለለ እዚህ ሽልማት ላይ መሸለምን እንደክብር ቆጥሮት አዳዲስ ሥራዎች ሊመጡ ይችላሉ፤ እኛም የምናስተላልፈው አዳዲስ ሥራ ይኖራል ተብሎ ነው የተጀመረው።

የለዛ ሽልማት ቅርጽ የኤሚ፤ ኦስካርና ግራሚ ሽልማቶች ድምር ነው። እንደሚታወቀው ኤሚ የቴሌቭዥን ፊልሞች፤ ኦስካር ለስክሪን የቀረቡ ፊልሞች እና ግራሚ የሙዚቃ ዘርፍ ሽልማቶች ናቸው። ስለዚህ ለዛ በሙዚቃ፣ በስክሪንና በቴሌቭዥን ፈልሞች ልቀዋል የሚባሉ ሰዎች የሚሸለሙበት ነው። በጊዜ ሒደት ደግሞ የአድማጭ ምርጫ የሚለው ዘርፍ ተካትቶ በዳኞችና ሙያተኞች እኩሌታው ከፍ እያለ ሽልማቱ እዚህ ደርሷል።

የመጀመሪያው ዝግጅት በብሔራዊ ቴአትር ሲካሔድ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ አልበም፤ ተዋናይና ተዋናይት በሚል አራት ዘርፎች ብቻ ነበሩ። አሁን በዘጠነኛው ዙር 12 ዘርፎች ላይ ደርሷል።

የለዛ ሽልማት የታሰበለትን አሳክቷል?
እርግጥ ነው የተሸለሙት አርቲስቶችና ባለሙያዎች በሙዚቃው እንዲሁም በፊልም ያገኙት ነገር አለ፤ ነገር ግን ምን ጨመረላችሁ የሚለውን ራሳቸው ተሸላሚ የሆኑት የሚመልሱት ነው። በእኛ በኩል ዘርፉ ከሦስትና አራት ወደ 12 አድጓል። ዋናው ትልቁ ነገር ዕውቅና መስጠት ነው። በዓመት ውስጥ ምን ዓይነት ሥራዎች ወጥተዋል? ምን ያህል አልበም ወጣ? ምን ያህል ፊልም ወጣ? የሚለው ጉዳይ ላይ ዕውቅና መስጠት ነው።

ከዛ በዘለለ የሰው ልጅ አይረካም፤ ሰው በሥራው ከረካና በቃኝ ካለ ምንም አዲስ ነገር የለም፤ መሻሻልም አይኖርም። እኛም ዘጠነኛው ላይ ሆነን አንደኛውን ስናስበው ለውጥ አለ፤ ከካቻምናው የአምናው ጥሩ ነበር። ነገር ግን አሁንም በጣም ጥሩ የሚሆንባቸውን መንገዶች ነው የምናሳበው።

የተፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ወይ ለሚለው ገና ነው ይቀራል። አሁን ልክ እንደ ተለኮሰ ሻማ የመጀመሪያው ብርሃን ነው፤ እየቆየ ሲሔድ ብዙ እንደሚሆን እናስባለን። አርቲስቱና ሙያተኛው ጋር የፈጠረው ስሜት በሒደት የሚታይና ጥሩ ነው። የተሻለ ሥራ ይዞ ለመምጣት እርስ በእርስ የሚታየው ፉክክርና በዓመት ይሔ ሽልማት እንዳለ ታውቆ በሽልማቱ መካሔድ ሰሞን የሚወጡ አልበሞች መኖራቸው ለውጥ ማምጣቱን ያሳያል።

በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሽልማት ክዋኔዎች ብቅ ይሉና ይጠፋሉ፤ ላለመቀጠላቸው ምክንያቱ ምን ይመስልሃል? ለዛ ሽልማት ጸንቶ ዓመታት እንዲሻገር ያስቻለውስ ምንድን ነው?
ሁሉም የየራሱ ምክንያት አለው። በሚመጡት ነገሮች ሁሉ መሸነፍን ተቀብሎ መሥራት ከሆነ መቀጠል አይኖርም። ይህን ነገር መንግሥትም ጀምሮት ያልቻለውና ኹለት ጊዜ ሽልማቶች ተካሒደው ተቋርጠዋል። ለዛ ሽልማት ዘጠኝ ዓመታትን ለምን ተጓዘ ለሚለው፤ አንደኛው ምክንያት ፍላጎት ነው። ዘጠኝ ዓመት ስንጓዝ ገንዘብ እንካችሁ ብሎ የሰጠን የለም። የእኛም ሐሳብና እቅድ እሱ አይደለም። [ኩባንያዎች/ድርጅቶች] በዓይነትና በጉልበትና በተለያዩ አገልግሎቶች ስፖንሰር ያደርጉናል።

እዚህ ለመድረስ ትልቁ ምክንያት በጎ ፈቃደኞች ናቸው። ሁሉም ሥራዎች የመረጃ ቴክኖሎጂ ባለሙያ፣ ግራፊክ ዲዛይነር፣ መድረክና መሰል ሥራዎች ሁሉ በበጎ ፈቃደኞች የሚሠሩ ናቸው። መጀመሪያ ማጽነት፣ ሙያተኛውን ዕውቅና መስጠትና ማበረታታት በሚል ነው የተነሳነው። እናም በልበ ቀናዎች በጎ ፈቃድ ነው እዚህ የደረሰው። እኔ ሐሰቡን ይዤ ተነስቼ ብዙ ዳክሬ ቆይቼ አብሮ ለመዳከር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ስላገኘሁ ነው እንጂ ማንም ተከፍሎት የሚሠራ የለም፤ ምንም የገቢ ምንጭም የለውም።

ገንዘብ ግን ያስፈልገዋል፤ ከኪሳችን ያወጣነው ገንዘብም አለ። ሙያተኛው ራሱ የሚሠራው ሥራ በገንዘብ ቢተመን እጅግ ብዙ ወጪዎች ይኖሩ ነበር። ይህ ታድያ ወደ ፊት የምናስብበት ጉዳይ ሆኖ አሁን ሐሳባችን እሱ ሳይሆን መጀመሪያ ሙያተኛውንና ሙያን ማክበር የሚለው ላይ ነው።

ሌላው የለዛ ጥሩ ነገር ብለን የምናስበው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የሦስትና አራት ትውልድን ባለሙያ በአንድ አዳራሽ ማገናኘቱ ነው። በዛ ቀን የተጠፋፋ ይጠያየቃል፤ ተያይቶ የማያወቅ ይገናኛል። ለምሳሌ ዓለማየሁ እሸቴ እና ግርማ በየነ “ዓለም ግርማ” የሚባል ባንድ ነበራቸው፤ የዓለማየሁ እሸቴ ብዙ ሥራዎቹን ያቀናበረለት ያደረገለት ግርማ በየነ ነው፤ ግን በለዛ ሽልማት ሲገናኙ ከኹለትና ሦስት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ነው።

ሽልማቶች ላይ አንዱ ጥያቄ የሚያስነሳው የዳኝነት ነገር ነው። የለዛ ሽልማት ዳኝነት እንዴት ነው?
ፊልም ላይ 60 በመቶውን ድምጽ ከተለያየ የፊልም መስክ የተውጣጡ ዳኞች ናቸው የሚወስዱት። የሲኒማ ቤት ባለቤቶችን ጨምሮ ፊልም ሠሪዎችና አዘጋጆች ይሳተፋሉ። የሲኒማ ቤት ባለቤቶች ዓመቱን ሙሉ ፊልም ያያሉ፤ ይገመግማሉ። ከእነርሱ በላይ ብዙም ፊልም ያየም የለም። አድሎ እንዳይኖር ደግሞ አይተዋወቁም። ከዛም ባሻገር የፊልም ዳይሬክተሮችና ደራስያን እንዲሁም ተዋንያን አሉ፤ እነርሱም የየራሳቸው ድምጽ አላቸው።

ሙዚቃን በተመለከተ ቀጥታ ድምጽ መስጠትን በሦስተኛው የለዛ ሽልማት ላይ ሞክረነው ነበር። እንደውም በድረ ገጽ ላይ ቀጥታ ድምጽ መስጠትን በመጠቀም ለዛ ሽልማት የመጀመሪው ነው ማለት ይቻላል። መጀመሪያ ሥሙን የመገንባት፣ የሕዝቡ የኢንተርኔት አጠቃቀም፣ የድምጽ አሰጣጥና ሙያተኛን መደገፉ እስኪኖር ተብሎ እንጂ በዛን ጊዜም ዳኞች ነበሩ። ሦስተኛው ላይ ግን የዳኞችና የሕዝብ ድምጽ ተራራቀ። ስለዚህ ቀጥታ ድምጽ መስጠቱን አቆይተን ሰው ጋር መልዕክቱን ማድረስ ላይ ይሠራ ተባለ።

አሁን ዘጠነኛው ላይ ስንደርስ አገራችን አሉ የሚባሉ ከሁሉም ትውልድ የተውጣጡ ትልልቅ የሙዚቃ ሰዎች፤ እንዲሁም ብዙ አልበም ካቀናበሩት እስከ ጀማሪዎች ድረስ፤ ሙዚቃ ያላቀናበሩ ግን ሙዚቀኛ የሆኑ፣ የሙዚቃ እውቀታቸው ትልቅ የሆነ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትልቅ ሥራ የሠሩ ሰዎችን በማሰባሰብ አዋቅረን፤ መስፈርት ወጥቶ ነው ድምጻቸውን እንዲሰጡ ያደረግነው። የእነርሱ ድምጽ 40 በመቶ ነው። ይህን ያደረግነው የግድ የሙያተኛ ዕይታ ስለሚያስፈልግ ነው። አንዳንዴ ሕዝብ ጋር ያልደረሱ ነገር ግን ጥበባዊ ፋዳቸው ትልቅ የሆኑ ሥራዎች አሉ። ስለተጮኸላቸውና በቲፎዞ ሳይሆን የእውነት ፋይዳቸውን አይቶ ሊዳኝ የሚችል ባለሙያ ብቻ ነው።

እነዚህ ሥራዎቸ ለምን በሕዝብ አልተደመጡም ስንል፤ ራስን በመሸጥ ጉዳይ የእኛ አርቲስቶች ደከም ስለሚሉ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ዘፋኝ አልበም ሲያወጣ ብዙውን ነገር ራሱ ይሠራል፤ ፕሮድዮስ ከማድረግ ጀምሮ ለግጥምና ዜማ ደራሲ ከፍሎ፣ አሳትሞና ቪድዮ ክሊፕ ሠርቶ ሲያበቃና ልክ አልበሙ ሲወጣ ትንፋሽ ያጥረዋል፤ ገንዘቡን ይጨርሳል። ያኔ ማስታወቂያ በበቂ ሁኔታ ስለማይሠራ በስፋት ሳይታወቅና ሳይደመጥ ይቀራል። እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ጎልጉሎ የሚያወጣው ሙያተኛው ነው በሚል ነው ድምጻቸው መታከል እንዳለበት የታመነው።

ከቀጣይ ዓመት በኋላ ደግሞ ልክ እንደ ፊልሙ በሙዚቃውም የዳኞችን ድምጽ 60 በመቶ የማድረስ እቅድ አለ። በተመሳሳይም የቴሌቭዥን ፊልሞች ላይ ያለውን የምርጥ ተዋናይና ተዋናይት ምድቦች ላይ በዳኝነት ሙያተኞች የሚሳተፉበት ይሆናል።

በጥቅሉ በእኛ ሐሳብ የሠራ ሰው ሁሉ አሸናፊ ነው፤ ደፍሮ መሥራት በራሱ አሸናፊነትን ያበስራል። በዓመት ውስጥ የመጡ ሥራዎች በሙሉ አሸናፊዎች ናቸው። በዳኞች ምርጫ አንድ አሸናፊ ልቆ ይወጣል እንጂ፤ ለእኛ ሁሉም አሸናፊ ናቸው።

ዘንድሮ ለዛ ሽልማት ምን አዲስ ነገር ይዞልናል?
ዘንድሮ ሦስት አዳዲስ ምድቦች ተጨምረዋል። አንዱ ተከታታይ የቴሌቭዥን ፊልሞችን የሚመለከት ነው። እዚህ ላይ ተከታታይ የቴሌቭዥን ፊልሞች በአገራችን እየበዙ ነው። አብዛኞቹ ግን ዘውጋቸው ይሔ ነው ተብሎ የተለየ አይደለም። ሲርያል ድራማ፣ ሳታየር ኮሜዲ፣ ፖለቲካል ሳታየር ተብሎ በዘውግ የሚሠራ ስንት ፊልሞች በዓመት ውስጥ ይወጣሉ? በፊልም ብቻ ሳይሆን በሙዚቃውም እንደዛው ነው። በአንድ አልበም ውስጥ ሬጌ፣ ፖፕ፣ ሮክ፣ ትዝታ፣ ባቲ፣ ባሕላዊና መሰል ሙዚቃዎች ይካተታሉ። ወደፊት በዓመት ዐሥር የሬጌ አልበም ከወጣ ማወዳደር አይከብድም። አሁን ላይ ግን ራሱ ሙያተኛውም ዘውግ ሰጥቶ ሊመድበው የሚችል አይደለም።
ከኹለት ዓመት በፊት ምርጥ ተከታታይ የቴሌቨዥን ፊልም ብለን ጀምረን ነበር፤ አሁን ከኹለት ዓመት በኋላ በዛው ዘርፍ ውስጥ ተዋናይና ተዋናይት የሚሉ ዘርፎች ተጨምረዋል።

ሦስተኛው በአገራችን አልተለመደም እንጂ የዓመቱ ምርጥ ዘፈን የሚል አዲስ ዘርፍ ተካትቷል። ይህም ከአልበም ውስጥ ነው። የነጠላ ዜማ ችግር የለብንም፤ አሁን ላይ በቀን አምስት ነጠላ ዜማ ሊለቀቅ ይችላል። የእኛ ችግር ደግሞ አልበም ነው። የአልበም ሥራ ነው የሚያለፋው። እኛ አልበም ሠርቶ፤ ደክሞ ላወጣ ሰው ነው እውቅና መስጠት የምንፈልገው። ነጠላ ዜማ አያለፋም ማለት አይለደም፤ ግን የአልበም ይበልጣል።

ዘንድሮ ከሐምሌ 1/2010 እስከ ግንቦት 30/2011 ድረስ 13 አልበሞች ወጥተዋል። እነዚህን ከእነዚህ አልበሞች ውስጥ የበለጠ ጥሩ ነው ብሎ ሙያተኛው ይመርጣል፤ እሱን ለሕዝብን እንሰጣለን። ይህኛው ዘርፍ በመቶ በመቶ በዳኞች የሚመረጥ ነው፤ ለሕዝብ የሚመረጠው ኹለተኛ ዙር ላይ ነው።

ምርጥ የሙዚቃ ቪድዮ ላይም አልበም ሠርተው የሙዚቃ ቪድዮ የሠሩ ናቸው። ይህም የሆነው እነርሱን ለማበርታት ነው። እጥረትም ያለው እዚህ ላይ ስለሆነ ነው።

አሁን በአገራችን ያለውን የሙዚቃ ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ?
ለእኔ ሁሉም በጊዜው ውብ ነው፤ እኛ ደግሞ ለሁሉም ነገር ገና ነን ብዬ እስባለሁ። በበኩሌ ትችት አልጠላም ግን ስንተች ምክንያታዊ መሆን አለብን። ገና እየበቀለ ባለ ነገር ላይ ብዙ ድብደባ ማካሔድ አያጸድቀውም። ሸፈፍ ያለውን እያስተካከሉ ካልሆነ አይሆንም።

በዚህ ዘመን የሚሠሩ ጥሩ ሙዚቃዎች አሉ። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ወርቃማ ዘመን የሚባለው 1960ዎቹ ነው። በዛ ዘመን እንዴት ተሠሩ የሚባሉ ቀሽም ሥራዎች አሉ። በዚህም ዘመን የሚሠሩ እንዴት በዚህ ዘመን ይሔ ይታሰባል የሚባሉ ዓይነትም አሉ። ግን ለምን ጥሩ ጥሩውን አንወስድም ነው።

ደግሞም ድሮ አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ አንድ ራድዮ ጣቢያና አንድ ጋዜጣ ነበር፤ አሁን ግን ብዙ የራድዮ ጣቢያ አለ፤ የሚሰሙበት ዕድል አለ። ሕዝቡ ጆሮው ስል ሆኗል። በእኔ የ9 ዓመት የለዛ ሽልማት ጉዞ የሕዝብና የሙያተኛው ድምጽ እንዴት እየተቀራረበ እንዳለ እያየን ነው፤ ሰዉን መናቅ የለብንም። ሰውም ሲሰማ ይመርጣል። ሁሉም ግን በጊዜው አሪፍ ነው።

ወደ ፊልሙ እንምጣ፤ “የነገን አልወለድም” ከሚለው ፊልም በኋላ በቅርቡ ደግሞ በኢቢኤስ ይተላለፋል ተብሎ በሚጠበቀ “የእግር እሳት” በተሰኘ የቴሌቨዥን ተከታታይ ፊልም ላይ በትወና ተሳታፊ ሆነሃል። ይህ እንዴት እንደሆነ አጫውተን?
ከልጅነቴ ጀምሮ ፊልሞች አያለሁ፤ ክላሲክ የሚባሉ ፊልሞች ስብስብ አለኝ። የአማርኛ ፊልሞች የቀረኝ የለም። አሪፍ ሆነ አልሆነ አያለሁ። አይቼ ደስ ይለኛል፣ ይከፋኛል ወይም እናደዳለሁ። ጥያቄው እሱ አይደለም፤ መሠራት አለበት። እኔ ገብቼ ካላየሁ ደግሞ መኮነንም ሆነ ማመስገን አልችልም። ጥሩውን ከመጥፎ ለመለየት መጀመሪያ መታየት አለበት ብዬ አምናለሁ።

የሎሚ ሽታ የተሰኘው ፊልም እንደወጣ ነበር ያየሁት። ባየሁት ነገር በጣም ስለተደሰትኩ ዳይሬክተሩን ለማግኘት ጠየቅኩ። የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ ወይም ስኮር የሠራው አብርሃም ተስፋዬ “የጣዕም ልኬት” የራድዮ ዝግጅትን ከሰርጸ ፍሬስብሐት ጋር የሚያዘጋጅና በቅርበት የማውቀው ሰው ነበርና ዳይሬክተሩን አገናኘኝ አልኩት። እርሱም ከፊልሙ ዳይሬክተር አብርሃም ገዛኸኝን ጋር አገናኘኝ። ስቱድዮ እንግዳ አድርጌው ስለፊልሙ አወራን፤ ተግባባን፤ አልፎም ወዳጅ ሆንን።

ልጁ በጣም አቅም ያለው ነው፤ በጨዋታችን መካከልም ከአንተ ጋር አንድ ፊልም እሠራለሁ እለዋለሁ። በእርግጥ ከዛ በፊት የቀረቡልኝ የፊልም ሥራዎች ነበሩ፤ ግን ለመሥራት አልፈቀድኩም ነበር።

አብርሃም አንድ ቀን ደውሎልኝ “ኢሕአፓና ስፖርት”ን አንብቤ ከሆነ ጠየቀኝና ብርሃኑ ፑዛን ታውቀዋለህ ወይ? አለኝ፤ ማንበቤን ነገርኩት። ደግሜ እንዳነበው እንዲሁም ከጸጋዬ ገብረመድህን “እሳት ወይ አበባ” መጽሐፍ ላይ በአንዱ እንድዘጋጅ ነገረኝ። ስንገናኝ አቀረብኩለት፤ እሱም ለፊልሙ በትወና እንደመረጠኝ ነገረኝ። መጀመሪያ አልቀበልም ብዬዋለሁ፤ በጣም ከባድ ገጸ ባሕሪ ነው። በኋላ ግን ተስማምቼ ተሠራ፤ አለቀ።

ፊልሙ እስኪወጣ ድረስ ግን አላየሁትም። ብዙ ወጪ ስለወጣበትም እንዳላበላሽ ሰግቼ ነበር። አብርሃም ደጋግሞ እየው ቢለኝም አላየሁትም። በቅርበት የሚያውቀው ማንያዘዋል እንደሻው ቀድሞ ፊልሙን አይቶት ነበርና አንድ አስተያየት ጻፈ፤ በዛም ላይ ገጸ ባሕሪው ከባድ እንደነበር፤ እንኳን ለአዲስ ሰው በሙያው ለቆየም ከባድ ነው ሲል ለእኔ ያለውን አድናቆት ጻፈ።

ያንን መልዕክት ሳይ ደነገጥኩ፤ በማንያዘዋል አንደበት እንደዛ መባል ትልቅ ነገር ነው። እናም ጥሩ ሠርቻለሁ ማለት ነው ብዬ አሰብኩ። ይሔኔ አብርሃም ፊልሙን እንዲያሳየኝ ስጠይቀው በተራው አላሳይም አለኝ። እናም ፊልሙ ሲመረቅ እንደታዳሚ ነው ያየሁት።

ይህ ከሆነ ዓመታት በኋላ ከአብርሃም በቀጠለ ወዳጅነታችን አንድ ቀን አንድ አጽመ ታሪክ ሰጠኝ፤ ስመለከትም ራሴን ነው ያየሁት። እርሱም እኔ እንድሠራው እንደሚፈልግ ነገረኝ። ፊልሙ አንድ ዓመት የሚሔድ ተከታታይ የቴሌቭዥን ፊልም ነው፤ ብዙ ተነጋገርን ሠራነው።

ኃይሌ ገሪማ (ፕሮፌሰር) በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ “ጥሩ ዳይሬክተር ጥሩ ተዋናይ መፍጠር ይችላል ወይ?” ብዬ ስጠይቀው፤ “አይ! ያለውን ተሰጥኦ ያወጣዋል እንጂ እንዴት ተዋናይ ይፈጠራል?” ብሎኝ ነበር። እኔ ግን እውነት ለመናገር አብርሃም ነው የፈጠረኝ። ወዳጅትም አለን፤ በደንብ እሰማዋለሁ፤ ይመራኛል። ሰው ባለው ላይ የሚጨምር እና የሌለንም የሚሰጥ ሰው ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here