የአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለ10 ቀናት ሥራ ማቆሙ ተገለጸ

0
432

የአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ባጋጠመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያት አስር ቀናት ያህል ሥራ የተቋረጠ ሲሆን አንድ ድርጅት የጄነሬተር ኃይል በመጠቀም ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል።

የፓርኩ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ መሐመድ ሃጂ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ፓርኩ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ከአዋሽ መልካሳ የኃይል ማመንጫ ሲሆን፣ ለፓርኩ ኃይል የሚያቀብለው ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ምክንያት ሥራቸው መስተጓጎሉን ተናግረዋል። ባሳለፍነው ሰኞ ነሐሴ 20/2011 አዲስ ትራንስፎርመር ተገዝቶ ወደ አዋሽ መልካሳ መላኩን የነገሩን መሐመድ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ጥገናው ተጠናቆ የኃይሉ ችግር እንደሚቀረፍ ተናግረዋል።

በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ለችግር የተጋለጠው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ አለመሆኑን በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መኮንን ኃይሉ ገልጸዋል። ብዙዎቹ ፓርኮች ሥራቸውን ባቀዱት መጠን እንዳይሠሩ የኃይል መቆራረጡ እቅፋት እንደሆነባቸውም ኃላፊው ተናግረዋል።

ሰኞ፣ ነሐሴ 20/2011 ወደ ስፍራው አቅንታ የነበረችው አዲስ ማለዳ የፓርኩ ሠራተኞች ያለሥራ ተቀምጠው የተመለከተች ሲሆን፣ ሠራተኞቹም በኃይል መቆራረጡ ምክንያት ለስድስት ቀናት ያለሥራ መቀመጣቸውን ተናግረዋል። በፓርኩ ከሚገኙት 19 ሼዶች ውስጥ አንቴክስ የተባለ የጨርቃጨርቅ አምራች ኩባንያ ብቻ ጄነሬተር በመጠቀም ሥራውን ሲያከናውን እንደነበር ለመታዘብ ችላለች።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ  በቻይና ሲቪል ምሕንድስና ግንባታ ኩባንያ (ሲሲኢሲሲ) በተባለ ድርጅት ተገንብቶ መስከረም 27/2011 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል። የኢንዱስትሪ ፓርኩ በ102 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በ2009 የተጀመረው ግንባታው ከ147 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈጅቷል። 11 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ ማጣራት የሚችል የፍሳሽ ማስወገጃ መሣሪያ ያለው ሲሆን ፓርኩ 19 የመሥሪያ ሼዶችንም የያዘ ነው።

ከአንድ ዓመት በፊት የተመረቀው አዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በአሥር ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው በጨርቃ ጨርቅ አምራቹ አንቴክስ የተባለው የቻይና ኩባንያ፤ በኃይል እጦት ምክንያት በቀን ለኃይል ከሚያወጣው ወጪ አስር እጥፍ ያህል እያወጣ አንደሚገኝ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ቂያን አሁኢ ተናግረዋል።

‹‹ሥራ ከማቆም በሚል እንጂ አዋጪ ሆኖ አይደለም›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ ‹‹ችግሩ በቅርቡ መፍትሄ እንደሚያገኝ ተነግሮናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ምርቶቹን ወደ ውጭ መላክ የጀመረው ድርጅቱ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባት የተለያዩ አልባሳትን አምርቶ 100 ሺሕ ዶላር ግምት ያላቸውን የመጀመሪያ ዙር አልባሳት ለዓለም ገበያ ማቅረቡንም ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here