ግጭትን ለማስወገድ የመገናኛ ብዙኀን ሚና

0
763

መገናኛ ብዙኀን ግጭቶችን ከማስወገድ አሊያም ከመቀነስ አኳያ ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ ወሳኝ ሚናዎች የሚያነሱት አዶናይ ሰይፉ፥ በኢትዮጵያ በቅርቡ የታዩትን ከአገራት ተመክሮ ጋር በማሰናሰል መገናኛ ብዙኀን አሉታዊና ኀላፊነት የጎደለው ሚና በመጫወት የግጭቶች መነሾ ወይም አባባሽ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ መከራከሪያ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

በአንድ አገር ውስጥ በዜጎችና በመንግሥት እንዲሁም በራሳቸው በዜጎች መካከል ግጭቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገራት ውስጥ የሃይማኖት ልዩነቶችና የዘር መከፋፈሎች፣ የማንነት ጥያቄዎች፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀሞች፣ የእኩል ተጠቃሚነት ዕድልና የፍትሕ እጦት በተለያዩ ወቅቶች ለሚከሰቱ ግጭቶች በመነሻ ምክንያትነት ሲጠቀሱ ይታያል።

በአገራችን ኢትዮጵያም በተለይ ካለፉት ኻያ ስምንት ዓመታት ወዲህ ከጦርነት በመለስ እዚህም እዚያም መልከ ብዙ ግጭቶች መከሰታቸውና ለንብረት ውድመት፣ ለዜጎች አካል መጉደልና ሕይወት ማጣት ምክንያት መሆናቸው እየተበራከተ መጥቷል። በተለይ ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ወዲህ ከግጭቶቹ መብዛት የተነሳ ነው መሰል ነገሩን ተላምደነው እንደቀድሞ መሥጋቱንና ግራ መጋባቱን እየተውነው የመጣን ይመስላል።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በአገራችን በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን ግጭቶች መነሾ ምክንያቶች መመርመር ሳይሆን ይልቁንም ዛሬ ዛሬ ቁጥራቸው እየበረከተ የመጡትን የመገናኛ ብዙኀን ግጭቶችን ከማስወገድ አለያም ከመቀነስ አኳያ ሊኖሯቸውና ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ ወሳኝ ሚናዎች ጥቂት ሐሳቦችን መወርወር ነው።
ጠቅለል ባለአነጋገር መገናኛ ብዙሃን ስንል መደበኞቹን ማለትም ጋዜጣን፣ ቴሌቭዥንን እና ሬዲዮንን እንዲሁም በተለይ ካለፉት ዐሥርና ዐሥራ አምስት ዓመታት ወዲህ ተፈጥረው የዓለማችን የመገናኛ ምኅዳርን በፍጥነት እየቀየሩትና እየተቆጣጠሩት የሚገኙትን ማኅበራዊ መገናኛዎችን የሚያካካትት ነው። ዛሬ ዛሬ በመደበኞቹና በማኅበራዊው መገናኛ አውታሮች መካከል ያለው ቁርኝት እየጠበቀ ከመሔዱ የተነሳ በተለይ እንደ ቴሌቭዥን፣ ሬዲዮና የኅትመት ውጤቶች ያሉ መደበኛ መገናኛዎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወይም አውታሮች የምንላቸውን እንደ ኹነኛ የዜናና የመረጃ ምንጭነት መጠቀማቸው እንግዳ ነገር መሆኑ እየቀረ የመጣም ይመስላል።

ባለንበት ወቅት በአገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ በጠቅላላው የመገናኛው ዘዴ ባሕሪያትም ሆኑ ብዛታቸው በፍጥነት እየጨመረና እየተለወጠ ነው፤ የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ቀውሶች ባሉባቸው አገራት ውስጥ (እኛንም ጨምሮ ማለት ነው) በመገናኛ ብዙኀኑ ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ቁጥራቸው ግን ከወትሮ በተለየ ሁኔታ እየተበራከተ በመሔድ ላይ ይገኛል። የአዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት በተለይም የተንቀሳቃሽ ስልክ መፈጠር የመረጃ ልውውጥ ምኅዳሩን በጣሙን ያሰፉትና የጨመሩት ከመሆኑም ባሻገር በቦታ ርቀትና በድኅነት ውስጥ ለሚኖሩ ሕዝቦች ሳይቀር አዲስና ፈጣን የመገናኛ ወይም የግንኙነት ዕድሎችን ለማስገኘት በቅተዋል።

ዛሬ የዓለማችንን የመገናኛ ምኅዳር ለመቆጣጠር የበቁት ማኅበራዊ መገናኛዎች ተከታዮቻቸውን የመረጃ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆን የመረጃ ወይም የይዘት ፈጣሪዎች ጭምርም እንዲሆኑ እያደረጓቸው ነው። ከዚህ አኳያም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቀድሞ ድምፃቸውን ለማሰማት፣ ችግሮቻቸውንና ብሶቶቻቸውን ለሌሎች ለመሳወቅ ዕድል ለተነፈጉ ሕዝቦች ድምፃቸውና ሐሳባቸው እንዲሰማ በማስቻላቸው “ጦር መሣሪያ ያላነገቡ ነፃ አውጭዎች” ተብለው እስከመወደስም ደርሰዋል።
ይሔ አዎንታዊ ሚናቸው እንደተጠበቀም ሆኖ ግን ለሁሉም ክፍት የሆኑት እነዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኀላፊነት ለጎደላቸው የዘለፋ፣ ያለመቻቻልና አብዛኛውንም ጊዜ ጎጂ ለሆኑ ሐቲቶችና አካሔዶች በራቸውን ወለል አድርገው ከፍተዋል። በዚህ የዲጂታል ዘመንም ቢሆን ሊከበርና ሊተገበር የሚገባው ሐሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ኀላፊነትንና ተጠያቂነትንም እንደሚያስከትል በብዙዎች ዘንድ እየተዘነጋ የመጣ ይመስላል። በአገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም ፌስ ቡክ በተባለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ ዜጎች የሚለጥፏቸው አፍራሽና ግጭት ቀስቃሽ ምስሎችና ጽሑፎች ለዚህ አባባላችን እንደማሳያ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ ከፍጥነታቸውና ከሚያዳርሷቸው አካባቢዎች ስፋት አኳያ ግጭቶችን ለማስነሳትና ለማቀጣጠል ኹነኛ መሣርያ እየሆኑ መጥተዋል። እነዚህን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የመሆኑ እውነታ በራሱ ሰዎች እውነተኛ ማንነታቸውን በመደበቅ አንዳንዴም እውነተኛ ማንነታቸውን ሳይደብቁ ተጠያቂ ልንሆን አንችልም በሚል ማን አለብኝነትና ትዕግስት ማጣት ስሜት የሚለጥፏቸው ሐሰተኛ ምስሎችና ጽሑፎች አስከፊ ውጤትን እያስከተሉ ስለመሆኑ ሩቅ ሳንሔድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እዚሁ አገራችን ውስጥ በዜጎች መካከል እየተነሱ ለንብረት መውደምና ለሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ተደጋጋሚ ግጭቶችን መታዘቡ በቂ ነው።

ይህ እውነታ ግን መገናኛ ብዙኀኑ ግጭቶችን ለማስወገድና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚጫወቱትን ወይም ሊጫወቱ የሚችሏቸውን በጎ ሚናዎች ሊጋርድብን አይገባም።
ቀደም ብለን በመግቢያችን ላይ የግጭት መነሻ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ከዘረዘርናቸው በተጨማሪ የዜጎች በገዛ አገራቸው ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍና የመወሰን ዕድል ማጣት፣ ራሳቸውን በነፃነት የመግለፅና ሐሳባቸውን የማሰማት መብት መነፈግ ከባድ የግጭት መንስዔዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ ግጭቶች እየተካሔዱ ባሉበት ወቅት የዜጎች መረጃ ማጣት ሰዎችን ተስፋ በማስቆረጥና እንዳይረጋጉ በማድረግ የግጭት አባባሽና ቀጥተኛ ተሳታፊም ሊያደርጋቸው ይችላል። እነዚህ አሉታዊ ሁኔታዎች ሰዎቸ ውሳኔያቸው በመረጃ ያልተደገፈ፣ ተግባራቸውም ከምክንያት ይልቅ በስሜትና በግብታዊነት የሚመራ እንዲሆን ያደርጋል።
ዜጎችን ከግጭት ለመታደግ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃዎች ሳይዘገዩ ሊደርሷቸው ይገባል፤ ይኽን ለመፈፀም ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት መገናኛ ብዙኀን ናቸው።

የኢኮኖሚና የሰላም ተቋም ተብሎ የሚጠራው ታዋቂ የምርምርና የጥናት አካል ስምንቱ “የሰላም ምሰሶዎች” በማለት አንድ ሁሉን አካታች የሆነ ማዕቀፍ አውጥቶ ነበር። ከእነዚህ ስምንት የሰላም ምሰሶዎች ደግሞ አንደኛው የመረጃ ፍሰት በነፃነት መኖር ነው። ይህ ደግሞ የዜጎች ለመረጃ ተዳራሽ ለመሆን መቻልንና ዜጎች በሚያገኟቸው መረጃዎች ላይ በመመርኮዝም በአገራቸው ፖለቲካና ፖለቲካዊ ሒደቶች ውስጥ ለመሳተፍ መቻላቸውን ያካትታል።

በአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የመናገር ነፃነትንና መብትን ለማስፈን የተለያዩ ብዝኀ ሐሳቦች መንሸራሸር መቻል ወሳኝነት አለው። ከዚህ አኳያ በተለይ በዜጎቿ መካከል የጠፋውን ሰላም መልሶ ለማስፈን በምትተጋ አገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙኀን አሳታፊ መድረክ በመፍጠር ልዩ ልዩ ሐሳቦችና ክርክሮች በሰለጠነ መንገድ እንዲደረጉ ዕድሉን ሊያመቻቹ ይችላሉ። ይህን በማድረጋቸውም የዜጎች ብሶቶች እንዲሰሙ ከማስቻላቸውም ባሻገር አንዱ የሌላውን ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶች እንዲገነዘብና እንዲያከብር ስለሚያደርጉ በዜጎች መካከል ዕርቅ ለማውረድ ብሎም የተረጋጋና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ሊያግዙ ይችላሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በክልሎች መካከል በወሰንና በቦታ ይገባኛል ምክንያት (ሌሎች ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆኖ) እንዲሁም በየክልሎቹ በራሳቸውም ውስጥ በማንነት ጥያቄ ዙሪያ እዚህም እዚያም ንብረት ያወደሙና ሕይወት የቀጠፉ በርካታ ግጭቶች ከመቼውም ጊዜ በከፋ መልኩ እየተከሰቱ ነው። መገናኛ ብዙኀኑ ታድያ ለእነዚህ አስከፊ ግጭቶች መፍትሔ ከመፈለግ አኳያ ምን እየሠሩ ነው? ብለን ብንጠይቅ ምላሹ ከተራ ዘገባ ያለፈ እንዳልሆነ እነሱም እኛም እናውቃለን፤ እንደውም መገናኛ ብዙኀኖቻችን አንዳንድ አካላት ከአለፍ ገደም በሚያዘጋጇቸው የግጭት አያያዝና የሰላም ጋዜጠኝነት (Peace Journalism) ሴሚናሮች ላይ ጥቂት ጋዜጠኞቻቸውን ለይስሙላ ልከው ከማሳተፍ ውጭ በእርግጥ ምን ዓይነት ወሳኝና ግዙፍ ሚና እንዳላቸው በቅጡም የተገነዘቡት አይመስልም።

መገናኛ ብዙኀን እንደማንነት ጥያቄ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኢ-ፍትሐዊነት፣ መገለል፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዕድል ማጣት ባሉ ውስብስብ ግን መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች ግንዛቤን እንዲያገኙና ወደ ተግባርም እንዲቀይሩት የማነሳሳትና የማስቻል ሚናም ሆነ ሙያዊና ማኅበራዊ ኀላፊነት አለባቸው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዋነኛ መላው መገናኛ ብዙኀኑ መደበኛ የአየር ጊዜ መያዝና ልዩ ልዩ ሐሳቦችን በነፃነትና በገለልተኝነት እንዲንሸራሸሩ ማድረግ ነው። ታዋቂ የብሪታኒያ መገናኛ ብዙኀን የሆነው ቢቢሲ በቅርቡ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው በመገናኛ ብዙኀን ላይ የሚደረጉ ውይይቶችንና ክርክሮችን የሚከታተሉ ሰዎች ከማይከታተሉት ይልቅ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እውቀት እንዳገኙ፣ ለተለያዩ ሐሳቦች ራሳቸውን ክፍት እንዳደረጉ፣ በፖለቲካ ውስጥና በሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም ይበልጥ ንቁ ተሳታፊዎች እንደሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በወሳኝነት የመገናኛ ብዙኀኑን አዎንታዊ ሚና ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

ቀደም ብሎ ለመግለፅ እንደተሞከረው የታፈኑ ስሜቶችና ብሶቶች ለግጭት መከሰት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ አኳያም መገናኛ ብዙኀን እነዚህ የታፈኑ ስሜቶችና ብሶቶች ከመፈንዳታቸውና ግጭቶችም ከመከሰታቸው በፊት ጉዳዮቹን ይፋ በማውጣት መፍትሔ እንዲሰጥ ጫና በመፍጠር ለመንግሥትም ሆነ ለሚመለከተው ወገን የማንቂያ ደውል ለመደወል ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች ሥጋቶቻቸውንና ብሶቶቻቸውን ለሌሎች በማካፈል ልምዶችን እንዲቀያየሩና ምክክሮችን እንዲያደርጉ መድረኩን ሊያመቻቹ ይችላሉ።

በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት በራሱ ስህተት ወይም ደግሞ የግድ ሊወገድ የሚችል ክስተት ነው ብሎ ማሰቡ ወይም መገመቱ የሚያስኬድ አለመሆኑን ነው። በየትኛውም አገርና ማኅበረሰብ በተለይም የሀብት እጥረት ባለበት ዓውድ ውስጥ በጥቅሞችና ፍላጎቶች አለመጣጣምና አለመመጣጠን ግጭቶች ይነሳሉ፤ እንደውም ፈረንጆቹ እንደሚሉት ግጭት ፅንፍ የያዘ የግንኙነት መልክ (ወይም ‘ፎርም’) ነው። በዚህ ጊዜም የመገናኛ ብዙኀኑ ሚና እጅግ ወሳኝ ሊሆን የሚችለው ከኹከትና ከብጥብጥ ውጭ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ፍጭቶችንና ግጭቶችን ይፋ ማውጣትና ውይይትና ክርክርም በሰለጠነ መንገድ እንዲካሔድባቸው መድረኩን ለሁሉም ወገኖች ማመቻቸት ነው። ይኽም ለግጭቶች መፍትሔ ከማፈላለግ ባሻገርም መገናኛ ብዙኀን በዜጎች ውስጥ የመወያየትና የመከራከር ባሕል እንዲፈጠር ብሎም እንዲጎለብት የማድረግ ሚናን ሊጫወቱ ያስችላቸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ግን ዜጎችን ወይም ማኅበረሰቦችን የጋራ ከሚያደርጓቸውና ከሚያስተሳስሯቸው ይልቅ በሚከፋፍሏቸው ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፣ የተሳሳተ፣ ወገንተኛ፣ ኢ-ተዓማኒ መረጃዎችን የሚያቀርብ እንዲሁም ወቅታዊና አገራዊ የፖለቲካና ማኅበረሰባዊ ዓውድን ከግምት የማያስገባ መገናኛ ብዙኀን ለግጭት መፍትሔ አፈላላጊና አምጪ ከመሆን ይልቅ የግጭት አቀጣጣይና አባባሽ ሆኖት ያርፋል። ለዚህ ደግሞ ቀደም ብሎ በሩዋንዳ በቅርቡም በማይናማር (ወይም በርማ) ለደረሰው የዘር ፍጅት የመገናኛ ብዙኀኑ አፍራሽ ሚና እንደ አብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ አስረጂዎች ናቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም እዚሁ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ የክልል መገናኛ ብዙኀን በዚህ አፍራሽና አሉታዊ ወጥመድ ውስጥ መግባታቸው ሁላችንንም ሊያሳስበንና ድምፃችንንም ልናሰማበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ቀደም ብሎ እንደተገለፀው ማንኛውም ነፃነትና መብት አብሮ ኀላፊነትና ግዴታንም ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንደሚያስከትል ሁሌም ቢሆን ሊታወቅና ሊታወስ ይገባል።
መገናኛ ብዙኀን ሙያዊና ማኅበረሰባዊ ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት የጥላቻና የኹከት መፈልፈያ ብሎም የግጭት መሣርያ ከመሆን መቆጠብ ይገባቸዋል። ከከፋፋይና ከማንነት ፖለቲካ ይልቅ ትኩረታቸውን ማኅበረሰባዊ ትስስሮሽን ወደ ማጠናከሩና የዜጎችን ንቃተ ሕሊና ወደ ማጎልበቱ ቢያዞሩ ለሁላችንም ይበጃል። ማኅበራዊ ሜዲያዎች ብለን የምንጠራቸው የግንኙነት ዘዴዎች አዎንታዊ አበርክቷቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በተቃራኒውም ግጭት አቀጣጣይና አባባሽ ሆነው የመገኘታቸው እውነታ እንደ ጀርመን ባሉ አገራት እንደወጡት ሕጎች ሁሉ በእኛም አገር ጠበቅ ያለ ሕግን የማውጣትና ሥራ ላይ የማዋልን አስፈላጊነት እየጠቆመ ነው።
ለማጠቃለል በአገራችን የመገናኛ ብዙኀኑ ቁጥር እጅጉን እየተበራከተ መጥቷል፤ ሕግን ጠብቀውና ከሙያም ሆነ ከማኅበረሰባዊ ኀላፊነቶቻቸው አኳያ ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣት እስከቻሉ ድረስ መበራከታቸው እሰየው የሚያስብለን ነው። ከምንም በላይ ደግሞ መገናኛ ብዙኀኑ ከንግድ ሥራቸው አኳያ አትራፊና ዘላቂ ሊሆኑ የሚችሉት አገር ሰላማዊ ስትሆንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነባ ሲችል ብቻ እንደሆነም ልብ ሊሉት ይገባል።

ወገንተኝነትን ያስወገደ፣ ለሙያዊና ለማኅበረሰባዊ ኀላፊነቶቹ በተግባር ተገዢ የሆነ መገናኛ ብዙሃን የተገፉና የተበደሉ ዜጎች ድምፅ በመሆን፣ ዋልጌነት የተጠናወታቸውን ባለሥልጣኖችንና መንግሥታዊ አሰራሮችን በማጋለጥ፣ ለተቃራኒ ሐሳቦችና ትርክቶች ይፋ የመወያያና የመከራከርያ መድረኮችን በማመቻቸት ግጭቶችና ኹከቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ የማይተካና ግዙፍ ሚናን ሊጫወት ይችላል። በተለይም እንደ እኛ መልከ ብዙ ግጭቶችና ማኅበረሰባዊ ንቃቶች ባሉበት አገር መገናኛ ብዙኀኑ ሚናቸውንና ኀላፊነቶቻቸውን በአግባቡ የመወጣታቸው ግዴታ ከምንም ጊዜ በላይ ጎልቶ ይወጣል። በመሆኑም የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎችም ሆኑ ባለቤቶች ይኽን ከፍተኛ ሚና እና ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ ጊዜው አሁን መሆኑን ተገንዝበው ሊተጉ ይገባል።
አዶናይ ሰይፉ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው adoseifu@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here