በዝምታ ውስጥ ያለው አብላጫው ሕዝብ እና የምሁራን ሚና

0
819

ካሳዬ አማረ “የጎሳ” ፖለቲከኞች የሚሏቸው ሕዝብን ሳያማክሩና ውክልና ሳይኖራቸው ሥልጣንን ብቻ ግብ አድረገው በመነሳት ለኢትዮጵያ አንድነት መዳከም ብሎም መሰናከል እየሠሩ ነው ሲሉ ተጨባጭ ያሏቸውን ማስረጃዎች አቅርበዋል። ምሁራን የዳር ተመልካችነታቸውን ትተው ሕዝብን በማንቃት አገርን የሚያሻግር ሐሳብ በማቅረብ በኩል የዜግንት ድርሻቸውን ይወጡ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ስለ ዲሞክራሲ በሚቀርብ ሐሳብ ውስጥ የትንተና መነሻ ሕዝብ መሆኑ የቃሉ አመጣጥ ታሪክ ያስረዳናል። በዲሞክራሲ ሕዝብ የሚለው ቃል የሚያሳየው ዕድሜያቸው ለመምረጥ እና ለመመረጥ የደረሱ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ቦታ ያላቸው መሆኑን ያመለክታል። ስለሆነም ይህ ሕዝብ በአገሩ የሚካሔዱ ማናቸውንም ጉዳዮች የማወቅ መብት አለው፣ ለተገኙት ስኬቶች እና ፈተናዎች በቀጥታ እና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ (በወኪሎቹ አማካኝነት) ባለቤት ነው። ሕዝብን አያውቅም ከሚል ሐሳብ ከተነሳን የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በትምህርት ደረጃ፣ በአኗኗር ዘይቤ፣ በአመለካከት የተለያዩ ስብጥር ያለው በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ቁልፍ ከሆኑ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች በስተቀር የታቀዱ፣ ተግባራዊ የተደረጉ እና አዎንታዊ ሆነ አሉታዊ ውጤት ያስከተሉ ጉዳዮችን ያውቃል።

አሁን ባለችው ኢትዮጵያ አብላጫው ሕዝብ በጉዳዮች ላይ ሐሳቡን የሚያስረዳበት መድረክ የሌለ አልፎም የጠበበ እና ለሕዝቡ እናውቅለታለን በሚሉ ምሁራን የተያዘ እና መፍትሔው “ይህ ነው፣ ያ ነው” የሚል አስተያየት በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች፣ በስብሰባዎች እየቀረቡ ያሉበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ብዙኀኑ ሕዝብ ግን ድምፁ እየተሰማና እያሰማ አይደለም።

በብዙዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት ውስጥ የሚስተዋለው ዲሞክራሲ የማይጨበጥ እና ትክክለኛ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ የማይታይበት ነው። አልፎም ሕዝብን ያላማከለ የፖሊቲካ አመራር በማስፈን፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወይም የይስሙላ ምርጫ በማካሔድ ሥልጣን ላይ በመቆናጠጥ እና የሥልጣን ዕድሜ በማራዝም ሕዝብን አፍኖ የመግዛት አስተዳደር ተፈፃሚ እየሆነ ያለበት አሕጉር ነው፤ የኢትዮጵያም ከዚሁ የሚለይ አይደለም።

ተግባራዊ ዲሞክራሲ እውን የሚሆነው መነሻውና መድረሻው ሕዝብ ሆኖ ኅብረተሰቡ በአገሩ፣ በክልሉ፣ በዞኑ፣ በወረዳው ፣ በቀበሌው ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ሐሳቡን ለመግለፅ የሚያስችል መድረክ ሲፈጠርለት ነው። ዲሞክራሲ ፍሬ የሚያፈራውና ውጤት የሚያመጣው ሕዝቡ ሲሳተፍ ነው። በዚህ መልክ ይጀምርና በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ ማጭበርበር በሌለበት ዓመኔታ የሚጣልባቸውን ወኪሎች በመሰየም ወኪሎቹ በሕዝቡ ሥም ይመክራሉ፣ ችግሮችን ይለያሉ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ፣ ለአገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።

ከላይ በቀረበው ሐሳብ መነሾ አሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገቢ ወኪሎች አይደሉም ወይ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህ ሐሳብ ተቀባይነት የማይኖረው መቶ በመቶ አግኝተው የተመረጡ ናቸው ብሎ ኢሕአዴግ በይፋ የነገረን የ2007ቱ ምርጫ ነፃ፣ ከማጭበርበር የፀዳ እና ገልለተኛ በሆነ የምርጫ ቦርድ የተመራ ምርጫ ስላልነበረ እውነተኛ የሕዝብ ወኪሎች ናቸው ለማለት አያስደፍርም። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሊነሳ የተፈለገው ሐሳብ የብሔረዊ ምርጫ ቦርድን ተሳትፎ በማይፈልግ እና የማንም ጣልቃ ገብነት በማይኖርበት መንገድ ከታችኛው የአስተዳደር ክፍል (ከወረዳ/ቀበሌ) ለክልል/ለከተማ አስተዳደር የሚሆኑ ወኪሎች (ተመጣጣኝነቱ ተጠብቆ) ከተሰየሙ በኋላ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች የተሰየሙ የሕዝብ ወኪሎች ከመካከላቸው ለአገር ዐቀፍ ጉባዔ የሚሆኑ ወኪሎችን (አሁንም ተመጣጣኝነቱ ተጠብቆ) መሰየምን ለማመልከት የቀረበ ነው ።

በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሥር አለመስደዱ ማሳያ እስከ አሁን ምሁራን ጎራ ለይተው የሚፋጩባቸው (ከሰላማዊ ፍጭት ይልቅ ወደ ነውጥ የሚያመዝኑ) አነታራኪ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ያለው ሐሳብ፣ ፍላጎት እና ሕዝቡን የሚያሳስቡት ጉዳዮች መድረክ አግኝተው ሊደመጡ አልቻሉም፣ እንዲደመጡም አይፈለግም። በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የአገራችን ውስን ምሁራን የሚሰጧቸው አስተያየቶች እና ማስጠንቀቂያዎች በሕዝብ ሥም የተሸፈነ ግን ከራሳቸው ተነስተው፣ ራሳቸውን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ የሚደክሙ ቡድኖች ናቸው። እናውቅለታለን የሚሉትን ሕዝብ ዕድል ተሰጥቶት ሕዝቡ አስተያየቱን፣ ፍላጎቱን፣ ሥጋቶቹን እና በአነታራኪ ጉዳዮች ላይ ያለው አቋም እንዲለይ አይሠሩም፤ እንዲሠራም አይፈልጉም።

እውን እነዚህ ኀይሎች የሕዝብ ሕጋዊ ውክልና አላቸው? ፈፅሞ፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሰየሙ ነገ ለሚያልሙት ሥልጣን እና ቁሳዊ ጥቅም የሚተጉ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንጂ ይህ በሥሙ የሚጮህለት ሕዝብ ድኅነትን ከመከፋፈል ውጭ የሚመጣለት ለውጥ እንደማይኖር የታወቀ ነው። አፍሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ንኖሊ ኦኮዲባ (1998) እና ሌሎች የመስኩ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የጎሣ ብሔርተኝነት በልኂቃን የሚዘወር እና ሕዝቡን መስዋዕት በማድረግ ለሥልጣን የሚሽቀዳደሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለው እንደሚያስረዱት በአገራዊ አንድነት ማዕቀፍ በአፍሪካ የጎሣ ብሔርተኝነት ለልማት እና ለሠላም መሠረት እና መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል።

ባለፉት የሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተዳደር ዘመን ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች ይተዳደሩ የነበረው በአካባቢው ተወላጅ እንደነበር እና አሁንም እንደሆነ እሙን ነው። ለለውጡ መምጣት ገፊ ምክንያት የሆነው በብሔራቸው፣ በብሔረሰባቸው ሰዎች እየደረሰባቸው ባለው መከራ መብዛት፣ እያደገ ባለው የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥ ቁጥር ማሻበቅ፣ በሌብነት መንገድ ሀብት አካብተው ሕይወታቸውን ሲለወጡ መታየት እና ከድኅነት ሊያላቅቁት ቀርቶ ወደ ባሰ ድኅነት ውስጥ ስለከተቱት እንደነበር በአደባባይ የሚታወቅ ነው።

በሌላ ጎን ደግሞ ሕገ መንግሥቱና ፌደራል ስርዓቱ አይነኬ ናቸው፣ ከተነኩ አገር ትፈርሳለች የሚል አስተሳሰብ በአገራችን የጎሣ ፖለቲከኞች በሰፊው እየተቀነቀነ መሆኑ የአደባባይ እውነታ ነው። እንደነዚህ ያሉ አስተሳሰቦች ለምን እንዲራገቡ ይፈልጋሉ? አንዱ ምክንያት አዲሱን የሪፎርም እንቅስቃሴ እና መሪዎችን ከሕዝብ ድጋፍ ማራቅ፣ በመቀጠል የለውጡን መስመር ማደናቀፍ ካልተቻለ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚለውን ሐሳብ ባለበት በማቆም እና የጎሣ ፌደሬሽኑን መሠረት በማድረግ የማያባራ የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ ማድረግ፣ አስከትሎም ብሔራዊ ቀውስ እንዲጋጋል በማድረግ እና መንግሥትን በማዳከም ሲያልሙት የነበረውን መገንጠል እውን በማድረግ አገር ምሥረታን ማወጅ ናቸው። ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ትምህርት ሳይሆናቸው ሕዝቡን ለሌላ መከራ እና እንግልት በማዘጋጀት ግባቸው ግን ተወናዮቹ የሥልጣን ባለቤት መሆን ነው። የጎሣ ፖለቲከኞች ግብ ሥልጣን መሆኑን ለማሳየት የሚከተለውን እንይ።

በሲዳማ ዞን ውስጥ ከሐምሌ 11/2011 ጀምሮ በተከሰተው ቀውስ መነሻ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ከፍተኛ አመራር የቀረበው ማስረጃ በ11/11/11 ሊመሠረት በነበረው ክልል አስቀድሞ የተማርን ነን ባይ ፖለቲከኞች ሕዝብ ባልመከረበትና ባልተሳተፈበት መንገድ የሥልጣን ድልድል አድርገው ጨርሰው እንደነበር በቴሌቪዥን መስኮት ተከታትለናል። ሲጠቃለል በመብት ሥም ግዴታን በማሽቀንጠር የራስን ጠባብ ፍላጎት ለማሳካት እየተሞከረ እንደነበር በግልፅ ያስረዳናል። የዚህ ድምር ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት የሚደረገውን ትግል በማዳከም እና በማሰናከል ሁሉም በጎሣው ውስጥ እንዲደበቅ፣ ለጋራ ጉዳይ እንዳይነሳ የማደረግ ዓላማ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል አርቆ አሳቢ መሆኑን ያስተዋልነው በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 ማክስ 8 ቢሾፍቱ አቅራቢያ በደረሰበት የመከስከስ አደጋ መነሾ ሕይወታቸውን ላጡት የብዙ አገር ዜጎች ያሳዩት ከልብ የመነጨ ሐዘንና በአገራችን የለቅሶ ስርዓት መሠረት እስከ አርባ ቀን ድረስ የአካባቢው ኗሪዎች በማስተዛዘን ውስጥ መክረማቸው ኢትዮጵያዊነት የማይሞት መሆኑን ጥሩ ማስረጃ እና ኢትዮጵያዊነትን ቢገዘግዙት እንኳ አሁንም ባለበት ያለ መሆኑን ያረጋግጣል። ከከተሜው ይልቅ ያልተበረዘ ኢትዮጵያዊነት አሁንም በገጠሪቱ ኢትየጵያ ባለበት አለ፣ ሁላችንም በየሔድንበት የገጠር አካባቢ ማንም እንግዳ ሲስተናገድ እና አገርን የሚያዩበት መንገድ ዘር ቆጥረው፣ ነገድ ለይተው አለመሆኑ ሁላችንም የሚያጋጥሙን ሁነቶች ናቸው። ነገር ግን የተወሰኑ ተማርን ባዮች ከሥልጣን ከተገለለው ሕወሓት ጋር በመቀናጀት ሆን ተብሎ ታስቦበት ለአገር ህልውና እንቅፋት የሆኑ ድርጊቶች እንዲፈፀሙ በማድረግ በሰላም የሚኖረውን ሕዝብ በጎሳ በመለያየት እርስ በርሱ እያጣሉት ይገኛሉ። በየጊዜው አጀንዳ ፍለጋ ላይ የሆኑት ግለሰቦች እና ቡድኖች አገር አጣብቂኝ ውስጥ ባለችበት ወቅት ክልል እንሁን ጥያቄዎች የሚቀነቀኑት በጥቂት ምሁራን መሆኑን በደቡብ ክልል ውስጥ የተካሔደ ጥናት ማመላከቱን ከመገናኛ ብዙኀን አዳምጠናል። ሌላው በቅርቡ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረታዊ ነጥቦች ለሕዝብ ሲቀርብ ስለ አማርኛ ቋንቋ ቁንፅል እና ያልተባለ መረጃ ያናፈሱበት መንገድ አቧራ ለማስነሳት እንዴት እየጣሩ እንደሆነ ያሳየናል።

ራሳቸውን ወክለው የሚቀርቡ ባለሙያዎች/ምሁራን፣ የፓርቲ ወኪሎች፣ የፓርቲ መሪዎች፣ አክቲቪስቶች በአገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲመክሩ ቢፈለግም ሙሉ በሙሉ ሕዝቡን ተክተው ብቸኛ ተዋናይ ይሁኑ ማለት አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ የሕዝቦቿ ንቁ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ነን። በምን መልክ ሕዝብ ይሳተፍ ለሚለው መንግሥት አሳታፊ የሆነ ስርዓት በመዘርጋት በኩል መሥራት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም በተጨባጭ የምንታዘበው ብዙኀኑ ሕዝብ የዳር ተመልካች ነው። ሕዝቡ በራሱ ሥም የሚቀርብለትን አወዛጋቢ ሐሳቦች ከማዳመጥ በቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለቤት ሆኖ የመከረበት ሁኔታ አልተመቻቸም።

ሌላው ትኩረት የሚሻው ነገር የተጠናከረች ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉት የውጭ ኀይሎች (ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ሌት ተቀን የሚታትሩ መንግሥታት፣ እንደ አልሸባብ እና አይ ሲስ ያሉ ፅንፈኛ ቡድኖችም ጭምር) አንዱ የሚጠቀሙበት ዘዴ አገር ውስጥ ካሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ኀይሎች ጋር በማበር የፖለቲካ ትኩሳት የሚያስነሱ ጉዳዮችን አጀንዳ ማድረግ፣ የሽብር ተግባራት በመፈፀም ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስን መፍጠር፣ የሕዝቡን ሥነ ልቦና መጉዳት ናቸው። እንደዚህ ያሉ ተግባራት አገርን ደረጃ በደረጃ ዋጋ በማስከፈል አጠቃላይ ውድቀት እንዲከሰት ያደርጋል።

አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው እውነታ እና እያራመዱና እየፈፀሟቸው ባሉት ተግባራት መሠረት ምሁራን በ3 ክፍሎች ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ። የመጀመሪያዎቹ ለአገር ልማትና አንድነት የሚተጉ፣ በአገራቸው ለውጡ ፍሬ እንዲያፈራ የሚደክሙ ገንቢ ምሁራን ሲሆኑ በተቃራኒው አገር የማደፍረስ፣ አጀንዳ በመፈብረክ፣ በመንግሥት የሚቀርቡ መረጃዎችን ለራሳቸው በሚመች መልክ ትርጓሜ በመስጠት ጉዳዮችን በሚያነታርክ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች አማራጮች በማራገብ ላይ የተሰለፉት አፍራሽ ምሁራን ተብለው ሊመደቡ ይችላሉ። ሦስተኛው ምድብ ከነገሩ ጦም እደሩ በማለት በታዛቢነት የሚገኘው፣ ከካፌ እና ከኮሪደር ፖለቲከኝነት ያልዘለለ ሚና ያላቸው የዳር ተመልካች ምሁራን (‘ፓሲቭ ግሩፕ’) ተብለው ሊመደቡ ይችላሉ።

ዋናው ዓላማ የምሁራን ምድብ ለማሳወቅ ሳይሆን ወሳኙ እና ባለቤት የሆነው ሕዝብ እንዲሳተፍ የሚያስችል መደላድል በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት አስተማማኝ መፍትሔ ለማግኘት የሕዝብ ድምፅ የሚሰማበት ሁኔታ እንዲመቻች መጠቆም ነው። በተጨማሪ በዳር ተመልካችነት የሚገኙት እና ገንቢ ምሁራን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሕዝባዊ ጉባዔ ወቅት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አገርን የሚያሻግር ሐሳብ በማቅረብ በኩል የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ማሳሰብ ነው። ሕዝብ የተሳተፈበት (ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ) የለውጥ እንቅስቃሴ በተማሩ ቅን እና አስተዋይ ዜጎች ሲታገዝ ስኬት ላይ መድረስ ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here