ትኩረት ያልተሰጠው አትራፊው የሩዝ ሰብል

0
1111

በኢትዮጵያ በሩዝ ምርት ምርታማነት ከሚታወቁ አካባቢዎች መካከል ከጣና ሐይቅ ደቡብ ምሥራቅ ላይ የምትገኘው ፎገራ አንዷ ናት። ከዛም ባሻገር እንደ ጉራ ፈርዳ፣ ማይጸብሪ፣ ፓዌ፣ አሶሳ፣ ጨዋቃና ጎዴ አካባቢዎችም በሩዝ ምርት ተጠቃሽ ናቸው። ይሁንና ግን የሩዝ ምርት ቢያንስ የአገር ውስጥ ፍላጎትን እንኳን ማርካት አልቻለም።

እንደማሳያ በአሁኑ ሰዓት በፎገራ የሩዝ ምርት በሔክታር በ20 ኩንታል ቀንሷል። ይህም ከ10 ዓመታት በፊት 40 እና 50 ኩንታል የነበረ ነው። በአንጻሩ በአገራችን የሩዝ ፍላጎት ከጊዜ ጊዜ ከፍ እያለ እንደመጣ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአንድ ጎን ራሱን ችሎ በምግብነት የሚቀርብ ሲሆን በተጓዳኝ ከጤፍ ጋር ተቀላቅሎ ለእንጀራ መዋሉ ፍላጎቱን ጨምሮታል። በቀጣይ ዓመት ብቻም ፍላጎቱ 6 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።

የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሠረት በ2012/13 በአገር ውስጥ የነበረው የ1.2 ሚሊዮን ኪንታል ምርት በ2013 ወደ 1.6 አድጓል። ከምርቱ የሚልቀው የሩዝ ፍላጎት እየተሟላ ያለው ታድያ ከውጪ በማስገባት ነው። በዚህ መሠረት በ2008/9 ከነበረው ከ2.3 ሚሊዮን ኩንታል የውጪ ገቢ ወደ 2018/19 ወደ 4 ሚሊዮን ኩንታል ከማደጉ ባሻገር ለሩዝ የወጣው የውጪ ምንዛሬ ከ12.1 ሚሊዮን ዶላር ወደ 170.7 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።

የ32 ዓመቱ አዲስ አሕመድ በፎገራ የሩዝ እርሻ ሥራ ላይ ከተሰማራ ጥቂት የማይባሉ ዓመታትን አስቆጥሯል። ቢሆንም ሥራው ብዙ ያገኘበት አይደለም። ከሦስት ዓመት በፊት ቻይና በማቅናት የሩዝ ምርት ለመጨመር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም ብዙ የተሳካ አልነበረም። “እስከአሁን ያመረትኩት ሩዝ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም” ሲል አስተያየቱን ይሰጣል።

የሩዝ ፍላጎት ከፍ ከማለቱ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ ለሩዝ ምርት አመቺ የሆነ የእርሻ መሬት አላት፤ በተለይም በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ላይ ከፍተኛ አቅም እንዳለ፤ ሞላ ተገኝ፤ በግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የምግብ ሰብሎች ጉዳይ ቡድን አስተባባሪ ተናግረዋል። ይሁንና የተፈለገውን ውጤት ለማምጣትም ሆነ አገሪቱ ራሷን እንድትችል ሊያደርግ እንዳልቻለ አያይዘው ጠቅሰዋል።

“ሩዝ በአሁኑ ሰዓት ከ150 ሺሕ እስከ 250 ሺሕ ሔክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ ይመረታል” የሚሉት ደግሞ ዳዊት ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው። በግብርና የምጣኔ ሀብት ባለሙያና በብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ልማት ኮሚቴ ምክትል ኀላፊ የሆኑት ዳዊት፤ ሩዝን ለውጪ ገበያ ለማዋል ወይም የገበያ ሰብል (cash crop) ለማድረግ መንግሥት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካም ያስታውሳሉ።

ለዚህ ማሳያው እስከ አሁን በሥራ ላይ ያለው ብቸኛ ሩዝ አምራች ሳውዲ ስታር መሆኑ ነው። ሳውዲ ስታር በጋምቤላ 6 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሩዝ እያመረተ ይገኛል። ኩባንያው ወደ ሥራ ሲገባ የመጀመሪያ ግቡ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሩዝ ምርት መላክ የነበረ ቢሆንም ይህም በደንብ የተሳካ አልነበረም። በዚህም ምክንያት አዳዲስ ባለሀብቶችም ሩዝ ማምረትን ሲመርጡ አይታይም።

የኢትዮጵያ ሩዝ ፕሮጀክት ዋና አማካሪ ኪዮሺ ሺራቶሪ ከታሪክ አጣቅሰው፤ ፎገር ያለው የሩዝ እርሻ የተስፋፋው ያለ መንግሥት ተሳትፎና ጣልቃ ገብነት መሆኑን ልብ እንዲባል ያመላክታሉ። በዚህ መሰረት ሩዝን የማምረት ነገር አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አርሶ አደሩ ራሱ አዋጭ መሆኑን አውቆ የሚሰማራበት ነው።

ዳዊት በበኩላቸው ሩዝን ማምረት ለኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ከየትኛውም ሰብል የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ነው ብለው ያምናሉ። ከሌሎች የሰብል ወጤቶች ጋር ሲነጻጸር ዋጋውም ሆነ የሚገኘው ምርት የሚበልጥ፤ በዛም ላይ ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። አያይዘውም “በአንድ ሔክታር መሬት ላይ እስከ 60 ኩንታል ሩዝ ምርት ሊሰበሰብ ይችላል። ይህ ከጤፍ ጋር ሲነጻጸር ኹለት እጥፍ ነው” ብለዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የሩዝ ምርት በሔክታር በአማካይ 30 ኩንታል ሲሆን፤ ይህም በአፍሪካ በአማካይ በሔክታር ከሚሰበሰበው 18 ኩንታል የሚልቅ ነው።

ዮኮ ያማዛኪ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለማቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ፕሮጀክት አማካሪ ናቸው። ከዳዊት ሐሳብ ጋር ቢስማሙም፤ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ሩዝ እንደ ዋና የምግብ ሰብል የሚቆጠር ባይሆንም፤ ፍላጎቱ ግን በጣም ከፍ ማለቱን አስታውሰዋል። ይህም በመሆኑ የሩዝን የገበያ ትስስር እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርትን ከፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል። መንግሥት ባቀደው መሠረት ሩዝን ለገበያ ማውጣት ከቻለም፤ አሁን ላይ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለው የሩዝ ፍላጎት ለኢትዮጵያ እንደ መልካም አጋጣሚ ይቆጠራል ባይ ናቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ቻይና 1.6 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ሩዝን ታስገባ ነበር፤ ይህን የዓለም የሩዝ ገበያ ላይ ወጪ ከሚደረገው 24.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 6.5 በመቶው ነው።

በአሕጉር ደረጃ ሩዝን ከወጪ ንግድ በመግዛት እስያ መሪነቱን የያዘች ሲሆን፤ በሌላ በኩል በከፍተኛ ደረጃ ሩዝን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ሕንድ በ2018 ቀዳሚ ነበረች። በዚህም 7.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች።

ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት ለኢትዮጵያ ምርትን ውጪ ከመላክና ዓለም ዐቀፍ ገበያውን ከመቀላቀል በፊት በአገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአንጻሩ ዳዊት እንደሚናገሩት ደግሞ ከውጪ የሚገባውን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት መተካት ከባድ ነው። ደግሞም የተለያየ የሩዝ ምርት ዓይነት በመኖሩ አንዲት አገር ሁሉንም ለራሷ አምርታ አትዘልቀውም።

እንደምሳሌም ሲጠቅሱ ቻይናን ያነሳሉ። ቻይና አንዳንድ የሩዝ ዓይነቶችን ለውጪ ገበያ ስታቀርብ የተወሰኑ ዓይነት የሩዝ ምርቶችን ከጃፓን ትገዛለች። ኢትዮጵያም በተመሳሳይ የተወሰኑ የሩዝ ዓይነቶችን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ልትተካ አልፎም ውጪ ድረስ ልትልክ ትችላለች። በአገር ውስጥ የማይመረቱትን የሩዝ ዓይነቶች ደግሞ ከሌሎች አገራት ማስገባት አለባት ሲሉ ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም ዐቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ፕሮጀክት አማካሪ ያማዛኪ እንደሚሉት ለሩዝ ምርት መነቀስ ምክንያት የሆኑት የሚሰበሰብ የሩዝ ምርት ማነስና ከውጪ ገበያ ከሚገባው ምርት ጋር መወዳደር አለመቻል ነው። ሌሎች ፈተናዎች ናቸው ያሉትን አያይዘው ሲጠቅሱ፤ የገበያ ትስስር ጠንካራ አለመሆንና ብቁ የሆነ የሰው ኀይል አለመኖሩ ነው ብለዋል።

ዳዊትም ከሩዝ ልማት ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ጥናት ተኮር ተቋማት መደራጀታቸው ወሳኝ ነው ሲሉ በአገሪቱ ከስልሳ በላይ የግብርና ምርምር ላይ የሚሠሩ ተቋማት ቢኖሩም አንዳቸውም በሩዝ ላይ እንደማይሠሩ አስታውሰዋል። ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል የነበረውን የተለመደ ሁኔታ ለመቀየር በዓይነቱ የመጀመሪያ ማዕከል መሆኑን አውስተውም ማዕከሉ እንቅስቃሴው እንዲሳካ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከአርሶ አደሩ ጋር ቀርቦ ጥናትና ምርምሮችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

በሩዝ እርሻ ሥራ ላይ የተሰማራው አዲስ እንደሚለው ከምርት ሒደትና ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚያማክር የለም። እንደውም በፎገራ ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የታየው የሩዝ ምርት መቀነስ ላይ ትኩረት ያደረገም የለም። “አርሶ አደሩ የሚጠቀምባቸው የሩዝ ዘሮች የደከሙ ሆነዋል፤ መቀየር አለባቸው። መሬቱም በተደጋጋሚ የታረሰበት በመሆኑ ምርቱ እንዲቀንስ አድርጓል” ብሏል።

ሞላ በዘርፉ ባለሙያ የሆነ ሰው አለመኖሩ አንዱ ችግር ነው ይላሉ። ይህም መንግሥት አርሶ አደሩን በሚገባ እንዳያግዝ አድርጎታል። ሩዝ በግብርና ማስፋፊያ ፕሮግራም ላይ የተካተተ ቢሆንም፤ የሩዝ አምራች ገበሬዎችን ግን የረዳ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ በተልዕኮ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሩዝ ላይ በቂ እውቀት የሌላቸው በመሆኑ ነው።

ሚኒስቴሩ ከቀጣይ በጀት ዓመት ጀምሮ የሩዝ ምርት ማሳደግ የሚቻልበትን ዳሰሳ አድርጊያለሁ ብሏል። መንግሥት የሰጠውን ትኩረት በተመለከተም ሞላ ሲናገር፤ መሬት፣ ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ማሽነሪዎች እንዲገቡ በማድረግ፣ እስከ አምስት ዓመት የግብር እፎይታ መስጠትና መሰል ማበረታቻዎች ይደረጋሉ። የአርሶ አደሩን አቅም ከመገንባት ባሻገር ሩዝን በስፋት ማስተዋወቅ ላይም ይሠራል ብለዋል።

ዳዊት ግን በዚህ የመፍትሔ ሐሳብም ላይ ጥርጣሬ አላቸው። በምክንያትነት ከዚህ በፊትም ጥቅም ላይ ውሎ አዋጭ ሳይሆን መቅረቱን ያነሳሉ። “ባለሀብትን ከመከተል ይልቅ መንግሥት አገር በቀል እውቀት ይዞ የሚሠራውን አርሶ አደር መደገፍ አለበት። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጠቃሚ የሆነውን ልመድ መቅሰምና የየአባወራውን የግብርና አቅም ማሳደግ ነው” ሲሉ ዳዊት ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።
ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ከሆነችው ‘ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው’ በሊድያ ተስፋዬ ተተርጉሞ የቀረበ

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here