እልባት ያልተገኘለት የኦሞ ፓርክ እና የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት ውዝግብ

0
1072

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ እንስሳትን እንቅስቃሴና ሥነ ምኅዳሩን እያወከ ነው ሲሉ የፓርኩ አመራሮች አስታውቀዋል። ከፓርኩ ህልውና አንጻር ማስተካከያ የሚሹ ጉዳዩችን የሚያመላክት ሪፖርት በባለሥልጣኑ ቢቀርብም፣ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት ጥናቱን ባለመቀበሉ ውዝግቡ እልባት እንዳልተበጀለት ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዝሆንን የመሳሰሉ የዱር እንስሳት ወደ ማጎ ፓርክ የሚሻገሩበት ኮሪደር በቁጥር 5 ፋብሪካው ምክንያት በመዘጋቱ የዱር እንስሳቱ ወቅትን ተከትሎ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚገድብ ነው ያሉት የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ኑሩ ይመር፣ በስኳር ፕሮጀክቱ የጎርፍ መከላከያ ተብሎ 50 ሜትር ርዝመትና 3 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ እንስሳቱ በመግባት ለሞታቸው ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል።

የፓርኩን ይዞታ 30 ከመቶውን ፕሮጀክት ሦስት እና ፕሮጀክት አምስት ወስደውታል የሚሉት ኀላፊው፣ ይህ አካሔድ የዱር እንስሳቱን እንቅስቃሴና ሥነ ምኅዳሩን እያወከው ነው ብለዋል። የመስኖ ውሃ ማስተላለፊያ ቱቦው ፓርኩን 24 ኪሎ ሜትር አቋርጦ እንደሚያልፍ የሚናገሩት ኀላፊው፣ ቱቦው የአራዊቱን ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ በማወክ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ይናገራሉ።

በቱቦው ላይ ለእንስሳቱ መሸጋገሪያ የሚሆን ድልድይ በየ5 ኪሎ ሜትሩ ይዘረጋል የሚል ስምምነት ቢኖርም፣ የተሠራው በየስምንት ኪሎ ሜትሩ ነው። በመሆኑም እንስሳቱ ለመሻገር 8 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንዲኖርባቸው ማድረጉን የፓርኩ የሥራ ኀላፊዎች የገለጹ ሲሆን፣ እንስሳቱ ያንን ያህል ኪሎ ሜትር የመጓዝ ትዕግስቱ ስለሌላቸው ቱቦው ውስጥ እየገቡ ለአደጋ እንደሚጋለጡ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ ቦታ ላይ እየገነባቸው ያሉ መሰረተ ልማቶች፣ ከፓርኩ ህልውና አንጻር ማስተካከያ የሚሹ ጉዳዮችን የሚያመላክት ሪፖርት በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቀርቦ ውይይት ተካሒዷል። ሆኖም የስኳር ፕሮጀክቱ እንዲያስተካክል የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበለው በመቅረቱ ችግሩ እልባት ሳያገኝ በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኝ ባለሥልጣኑ ገልጿል።

የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ የስኳር ፕሮጀክቱ በኦሞ ፓርክ ውስጥ በመዘርጋት ላይ ያለው የመስኖ ካናል የዱር እንስሳት መተላለፊያዎችን መዝጋቱ፣ የዱር እንስሳቱን ከኦሞ ወንዝ መለየቱ፣ የዱር እንስሳት ኮሪደሮች ከፕሮጀክቱ ዕቅድ ውጪ መሆናቸው፣ በዱር እንስሳቱ መኖሪያ አካባቢ የሆነው የፓርኩ አካል ለስኳር ልማት የሚውል መሆኑ የውዝግቡ ምክንያቶች ናቸው።

ይህንን ተከትሎ ኹለቱን አገራዊ ሀብቶች አመጋግቦና የኹለቱንም ህልውና ባረጋገጠ መልኩ የጋራ ውሳኔና መግባባት ላይ ለመድረስ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ታምኖበታል። ይህንም ተከትሎ ጉዳዩ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የማሻሻያ ሐሳቦች ተጠንቶ እንዲቀርብ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ናቃቸው ብርሌው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እንደናቃቸው ገለጻ፣ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ 11 አባላት ያሉት የቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም እና በቦታው በመገኘት እንዲጠና በመወሰኑ፤ ከኦሞ ስኳር ፕሮጀክት ተቋራጮችና አመራሮች፣ ከደቡብ ክልል የደን አካባቢ ጥበቃ እና አየር ንብረት ለውጥ፣ ከብዝኀ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ ከመስኖ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ እና ከባለሥልጣኑ የተውጣጡ አባላት ያለው ኮሚቴ በማቋቋም ጥናቱ ተካሒዶ ነበር።

በጥናቱ መሰረት የዱር እንስሳቱን ከማጎ፣ ከታማ እና ከኦሞ ጥብቅ ቦታዎች የሚያገናኝ መተላለፊያ ኮሪደሮች እንዳይታረሱ፣ የፓርኩን ስርዓት አያያዝ የሚያዛባ ተጨማሪ ካናል ግንባታ ሌላ አማራጭ እንዲፈለግለት፣ በሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት የተበላሹ የፓርኩ ገጽታዎችን እንዲስተካከሉ፣ ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኙ መተላለፊያ መንገዶች እንዳይዘጉ፣ የእንስሳት መተላለፊያ ድልድዮች ግንባታ እንዲካሔድ እንዲሁም ከፓርኩ ሠራተኞች ጋር የሚኖሩ የሥራ ግንኙነቶች፣ ጥሬ እቃ የማጓጓዝ፣ የትብብርና ቅንጅት ሥራዎች ስርዓቱን ተከትለው ሊተገበሩ እንደሚገባ ኮሚቴውን በማስረዳት መረዳዳት ላይ ተደርሷል።

ይሁን እንጂ በስኳር ፕሮጀክት በኩል፣ የመተላለፊያ ኮሪደሩ ካልታረሰ ፋብሪካው ከአቅም በታች እንዲያመርት የሚያደርገው በመሆኑ፣ በዚሁ ቦታ የሚገነባው ድልድይ ፋብሪካ ኹለትን እና ሦስትን ለማገናኘት የሚያገለግል መሆኑን በመግለጽ ተጨማሪ ለመገንባት ለታቀደው 10 ቱቦዎች ሌላ አማራጭ መፈለግ ከፍተኛ ወጭን የሚያስከትል መሆኑንና፤ አገሪቷ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሳጣት በመግለጽ አቋም በመያዛቸው የጋራ መተማመን ላይ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የሰላማጎና እና የኛንጋቶም ወረዳዎችን፣ በቤንች ማጂ ዞን የሱርማና የሚኤኒት ሻሻ ወረዳዎችን እንዲሁም በከፋ ዞን የዴቻ ወረዳ አንዳንድ የተመረጡ ቦታዎችን ያካተተ ነው።

በተከለሰው የስኳር ልማት ዘርፍ ዕቅድ መሰረት፣ በቀን እያንዳንዳቸው 12 ሺሕ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች እና በቀን 24 ሺሕ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችል አንድ ስኳር ፋብሪካ እየተገነባበት የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ ለአራቱም ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚውል የሸንኮራ አገዳ በ100 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ እየለማ እንደሚገኝ ከስኳር ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እንደኮርፖሪሽኑ ገለጻ፣ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት በጣም በጥቂት አካባቢዎችና ወንዞችን ተከትሎ ከሚካሔድ የሰብል ልማት በስተቀር፣ ፕሮጀክቱ በሚገኝባቸው አብዛኛዎቹ ወረዳዎች ይህ ነው የሚባል ምርት አይመረትም ነበር። በመሆኑም የፕሮጀክቱ ሥራ በተጀመረበት ወቅት በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የአካባቢው ተወላጆች ቁጥር ግምት ውስጥ የሚገባ አልነበረም።

የአካባቢው ተወላጆች ዋንኛ ምግብ ከገበያ የሚገኙ ሰብሎችና የእንስሳት ተዋጽዖዎች (ወተት፣ ሥጋና የመሳሰሉት) ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ግን ይህ ታሪክ ተለውጦ በራሳቸው ማሳ ላይ በቆሎ አምርተው ለመጠቀም ችለዋል። ይህ የሆነውም በፕሮጀክቱ አማካኝነት በርካታ የአካባቢው ተወላጆች በመስኖ የሚለማ መሬት እንዲያገኙ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ኤክስቴንሽን አገልግሎት ድጋፍ ጭምር እየተደረገላቸው፣ ከእርሻ ሥራ ጋር በመተዋወቃቸው ምክንያት ነው። በዚህም ብቻ ሳያበቁ የሸንኮራ አገዳ አብቅለው በአሁኑ ወቅት ስኳር ማምረት ለጀመሩት ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎች የሚያቀርቡበት ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል ሲል የኮርፖሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት በይፋዊ ድረ ገጹ አስፍሯል።

በሌላ በኩል የፕሮጀክቱና የአካባቢው ተወላጆች በትራክተርና በማሽን ኦፕሬተርነት እንዲሁም ከስኳር ልማት ዘርፉ ጋር ተያያዥ በሆኑ ሌሎች የቴክኒክ ክህሎቶች ሰልጥነው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግም ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ይጠቅሳል። በመሆኑም በፕሮጀክቱ የተፈጠሩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድሎች የአካባቢው ተወላጆችን በእጅጉ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል። በዚህም እስከ ሰኔ 2009 በፕሮጀክቱ አማካኝነት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የሥራ ዕድል ያገኙት 50 ሺሕ 692 ያህል ዜጎች ሲሆኑ በፕሮጀክቱ የቋሚ፣ ጊዜያዊና የኮንትራት የሥራ ዕድል ያገኙት ደግሞ 81 ሺሕ 661 ናቸው።

በዚህ መሰረት በኦሞ ፓርክና በኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በኩል በሚነሱት እነዚህ ነጥቦች መካከል ሚዛን ፈጥሮ ማስተካከልና እልባት ማግኘት ባለመቻሉ፣ እንደገና አዲስ ኮሚቴ መዋቀሩን አዲስ ማለዳ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

የኦሞ ብሔራዊ ፓርክን ተግዳሮት ከመሰረቱ ለመፍታት የስኳር ፕሮጀክት ከፍተኛ አመራሮች፣ የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት አመራሮች፣ የኦሞ ፓርክ አመራሮች፣ በባለሥልጣኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ከፌዴራል ተቋማት (ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከአካባቢ ጥበቃ እና ደን ኮሚሽን፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት)፣ ከደቡብ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አመራሮች እንዲሁም የሐሳብ አመንጪ ቡድን አባላት በድምሩ 40 አካላት የተሳተፉበት ኮሚቴ ተዋቅሮና ጥናት ተጠንቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መቅረቡን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ናቃቸው ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here