የራያ ሕዝብ ታሪክ፣ የመብት እና የአስተዳደር ጥያቄ ዳሰሳ (ክፍል አንድ)

0
1437

በራያ አካባቢ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ተቃውሞዎች እና ግጭቶች ደጋግመው ይነሳሉ፡፡ የጥያቄዎቹ ታሪካዊ መሠረት እና ወቅታዊ አጀንዳ ምንድን ነው? ብሩክ ሲሳይ ከሕዝቡ ጋር ባለው መስተጋብራዊ ዕውቀት ያፈራውን፣ በታሪክ ሰነዶች ላይ ከተከተበው ጋር እያመሳከረ በተከታታይ እንደሚከተለው ያስነብበናል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በልዩ ልዩ ጎሳ የመከፋፈላቸወን ያክል ለየብቻቸው ተፈናጥረውና ተሸሽገው አልኖሩም። በትንሹ ባለፉት ሁለት ሺሕዓመታት ውስጥ በግጦሽ ቦታ ፍለጋ፣ በንግድ፣ በጦርነት፣ በሃይማኖት ጉዳይ በመዘዋወር፣ በጋብቻና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በመለዋወጥ እርስ በርሳቸው ሲገናኙ ኖረዋል። ኢትዮጵያውያን በተናጠልም ሆነ በቡድን ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ መዘዋወር ከጥንት ጀምሮ ሲያደርጉት የኖሩ ልማዳቸው፡፡
ከእነዚህ ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴወች በታሪካችን ጎልቶ የሚታወቀው በገዳ ስርዓተ ማኅበር እየተመራ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከባሌ አካባቢ ተነስቶ ወደ ሰሜን ምሥራቅ እና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ያደረገው መስፋፋት ነው። ይህ ለበርካታ ዓመታት በተከታታይ የተካሔደ የሕዝብ እንቅስቃሴ በተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችና ቋንቋዎች ላይ የራሱን አሻራ ጥሎ አልፏል። ኦሮሞዎች ወደ ሰሜን ተጉዘው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ጋር ከተቀላቀሉና ተዋሕደው አዳዲስ ባሕላዊ ማኅበረሰቦች ከፈጠሩባቸው አካባቢዎች አንዱ ራያ ነው።
የራያ መገኛ
ራያ የምንለው አካባቢ በዛሬው ጊዜ በአማራ ክልል የሚገኘው ራያ ቆቦ ወረዳን፣ በትግራይ ክልል የሚገኙትን የራያ አላማጣ ወረዳ፣ የወፍላ ወረዳ፣ የራያ አዘቦ ወይም ጨርጨር ወረዳ እና እንዳ መሆኒ ወረዳን ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የአምባላጌ ወረዳን እና ዋጅራትንም ይጨምሩታል። ታዲያ በእነዚህ በተጠቀሱት አካባቢወች ከኦሮሞ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ በፊት ይኖሩ የነበሩ በታሪክ ከሚታወቁት ቀደምት ማኅበረሰቦች ዋናዎቹ ዶባዎች ናቸው። ዶባዎችበዛሬውጊዜአሸንጌ እየተባለ በሚጠራው ሐይቅእና የአፋር ተዋሳኝ በሆነው በዞብልመካከልባለው ረባዳቦታየነበሩቀደምትሕዝቦችነበሩ። ዶባዎች በመካከለኛው ዘመን ነገሥታት በእነ ዐጤ በዕደማርያም እና ዐጤ ልብነድንግል ዘመነ መንግሥት በተከታታይ እያመፁ የሚያስቸግሩ ማኅበረሰቦች ነበሩ።
የፖርቹጋል መንግሥት መልዕክተኛ ሆነው ወደ ዐጤ ልብነድንግል ዙፋን ችሎት የተላኩት ፖርቹጋላዊ መነኩሴ አባ አልቫሬፅ ከትግራይ ወደ መሐል አገር ሲጓዙ ስላጋጠማቸው የዶባ ሕዝብ እንዲህ በማለት ጽፈዋል “ወደ ሐይቁና[አሸንጌ ሐይቅ] ወደ ደቡብ በሚወስደው መንገድ የሚገኘው ሕዝብ ፈፅሞ ሙስሊም ነው። አገሩ ዶባ ስለሚባል ሰዎቹ ዶባዎች ይባላሉ። ዶባ አውራጃ ነው እንጂ ጠቅላይ ግዛት አይደለም። ሰዎቹ እንደነገሩን አውራጃው በ24 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 12 ወረዳዎች ሠላማዊ ሲሆኑ የቀሩት ዘወትር በጦርነት ላይ ይገኛሉ።” አባ አልቫሬዝ ብቻ ሳይሆን የነገሥታቱ ዜና መዋዕል እንደሚያሳየው ዶባዎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፣ ጦረኞች እና በተከታታይ አመፅ በማስነሳት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ሲጋጩ የነበሩ ማኅበረሰቦች ናቸው። ፀፄ ዘርያዓቆብ እና እሱን የተካው ልጁ ዐፄ በዕደማርያም ሁለቱም ንጉሠ ነገሥቶች አካባቢውን ለመቆጣጠር እና ዶባዎችን ለማስገበር ጨዋ የሚባለውን የሠራዊታቸውን ክፍል በዚህ ቦታ እንዳሰፈሩበት የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
ከተለያዩ ሐተታወች መረዳት የሚቻለው ነገር ራያ በሚባለው ከዛሬው አካባቢ ዶባዎች ሲኖሩበት የኖረው ቆላውን እና ከአፋር ጋር የሚዋሰነውን የሰሜን ምሥራቅ የራያ ክፍል ነው። ደቡባዊ እና ደቡብ ምዕራብ ራያ በአንጎት ጠቅላይ ግዛት ሥር ቄዳ በሚባል አውራጃ ሲጠራ፣ ሰሜን ምዕራቡ የራያ ክፍል በተለይ በዛሬው ዘመን ወፍላ እየተባለው የሚጠራው የራያ ክፍል ጃን አሞራ የሚባል እና ከዶባወች ጋር ለዘመናት ሲዋጋ የነበረ ማኅበረሰብ የሚኖርበት ግዛት ነበር[O.G.S. Crawford]። ከዚህ መረዳት የምንችለው የዛሬው ራያ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ የዶባዎች፣ የአንጎት ቄዳዎች እና የጃን አሞራ ማኅበረሰብ መኖሪያ ነበር። የንጉሠ ነገሥቱ የዐፄ ልብነድንግል መንግሥት ከምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የተነሳውን የኢማም አሕመድ አመፅ መቆጣጠር አቅቷቸው ኢማሙ አገሪቱን ከደቡብ ምሥራቅ ጫፍ እስከ ሰሜን ምዕራብ ጫፍ በመላ በቁጥጥሩ ሲያደርግ በዚህ በዛሬው የራያ ግዛት የሚኖረው ሕዝብም ተመሳሳይ ዕጣ ስለገጠመው ቀደም ባሉት ነገሥታትም ሆነ በዐፄ ልብነ ድንግል በአካባቢው የተሠሩ አብያተ ክርስትያናት ወድመዋል።
የራያ ጎሳ አመጣጥ እና ውሕደት
ይህ በክርስትያን እናሙስሊምወገኖች መካከል የሚደረገው ጦርነት ለኦሮሞ የተለያዩ ጎሳዎች መስፋፋት እና አዳዲስ መሬቶች ላይ የመሥፈር እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረ ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት ተከታታይ ዘመናት ዛሬ ራያ ተብሎ በሚጠራው ምድር የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች ሊሠፍሩ ችለዋል። በመሆኑም የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ባደረገው እንቅስቃሴና መስፋፋት በራያ የነበረውን ቀደምት የማኅበረሰብ ስብጥር በእጅጉ ቀይሮታል። በ1554 በዐጤ ሚናስ የሥልጣን ዘመን የሐንሩፋ ወይም የዱሉ ባለገዳዎች የወሎን ጎሳ በመምራት መጀመሪያ በቆላው አገር በማለፍ በኢፋት በእስከ ምሥራቅ አድርገው ከተጓዙ በኋላ በደጋውና በቆላው መካከል በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሚተዳደሩ አካባቢዎች እና በአዳሎች ድንበር አድርገው አዋሽን በማቋረጥ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተንቀሳቀሰዋል [ይልማ ደሬሳ]።
በመቀጠል በንዑስ ጎሳ በመከፋፈል ወሎ የተባለው በአንጎት አውራጃ በእስከ ደቡብ ያለውን ደጋውን የቤተ አማራ ግዛት ያዘ፤ ሌሎቹ በርቱማዎች (መረዋ፣ ሁበና) ደግሞ ወደ ሰሜን ተንቀሳቅሰው እስከ ትግራይ ድረስ ተቆጣጥረው ያዙት[ዓጽመ ጊዮርጊስ]። በመረዋ ጎሳ ሥም የሚጠራ አካባቢ አሁን በራያ፣ ዋግ እና በላስታ ግዳን አዋሳኝ ድንበር ይገኛል። ከዚያም በመቀጠል በ17ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ደግሞ ራያ፣ ቦረን፣ ወረዋዩ፣ ወረቢቹ፣ አቡል፣ ሊበን፣ አራብሳ፣ ሬጌቻ የሚባሉ የሜጫ ንዑስ ጎሳወች በአካባቢው ደርሰው ተስፋፍተው ቀድሞ የነበረውን የአካባቢውን ዲሞግራፊ በእጅጉ ቀይረውታል። ዛሬ መሬት ላይ ከሚገኘው የማኅበረሰቡ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በዋናነት ነባሮቹ የዶባ፣ የአንጎት፣ የቀዳ እና የጃናሞራ ማኅበረሰቦች በአዲሶቹ ተስፋፊዎች በጉልበት ተሸንፈው አሊያም ደግሞ ያለ ጦርነት በሞጋሳ፣ በረኮ፣ በሚዲቻ እና በጉዲፈቻ አማካኝነት በፈቃዳቸው ከተቀላቀሉ በኋላ አዲስ ውህድ ማንነት ፈጥረዋል።
አዲሶቹ ተስፋፊወች የጉልበት የበላይነት ስለነበራቸው በቅልቅሉ ነባሩን ውጠው የራሳቸውን የአካባቢ ሥያሜ እና በሞጋሳ የተቀላቀላቸውን ሕዝብ ሥም እና ማንነት ቀይረዋል። ከዚህም ሌላ በኦሮሞ ትውፊት መሠረት አንድ የኦሮሞ ጎሳ ከራሱ ጎሳ ማግባት ስለማይፈቀድ አዲስ ተስፋፊዎቹ ከነባሩ ማኅበረሰብ ሴቶቹን በማግባት ወንዶችን ደግሞ በሞጋሳ ኦሮሞ ካደረጋቸው በኋላ ሥማቸውን በመቀየር በገዳው እርከን እንደ ደለደሏቸው መገንዘብ አይከብድም። በእርግጥ ወሎ ላይ የነበረው የኦሮሞ ሠፈራ ከነባሩ ማኅበረሰብ ጋር ብዙም ግጭት ባልነበረበት ሁኔታ በመደጋገፍ የተመሠረተ እና ከሚገባው በላይ ፍፁም ውህደት የነበረበት ነበር[Fekadu Begna]። በመሆኑም የነባሩ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ቁጥር በነበረባቸው አካባቢዎች የአማርኛ ቋንቋ ሳይጠፋ በጊዜ ሒደት እንደገና እየገነነ በመሔድ የአዲሶቹን የኦሮምኛ ቋንቋ እየዋጠ ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃደርሷል፤ ቅልቅሉ ሳሳ ባለበት እና የአዲሶቹ ቁጥር በበዛበት እንደ ራያ አዘቦ ወረዳ ባለው አካባቢ አሁንም ኦሮምኛው በተወሰነ ደረጃ አለ።
በዚህ ታሪካዊ የማኅበረሰብ መስተጋብር ባሕልን፣ ሃይማኖትን፣ ቋንቋን፣ ስልተ ምርትን፣ የአኗኗር ዘዬን ወዘተ አዲሶቹ ለነባሮቹ በኃይልም ሆነ በውዴታ የማስተላለፋቸውን ያክል በተቃራኒው ነባሮቹም ለአዲሶቹ የራሳቸውን አውርሰዋል። በዚህ መስተጋብር አሸናፊ የሆነ ጎሳና ነገድ ሳይሆን አሸናፊ የሆነ ባሕል፣ ስልተ ምርት፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ጎልቶ ወጥቷል። ምናልባት የአዲሶቹ ቋንቋ ቢገንን እና ቢጎላ የነባሩ ባሕል ደግሞ በሌላ በኩል ሊጎላ እና ሊገን ይችላል። በመሆኑም ይህ መስተጋብር አሁን በመሬት ላይ ያለውን ራሱን የቻለ የራያ ማኅበረሰብ መገለጫ ውበት፣ ጀግንነት፣ ባሕል፣ እሴት ፈጥሯል። ራያ ማለት ከዚህም ከዚያም የተውጣጣ የቅርስምስም ማንነት ሳይሆን በግዛቱ ውስጥ የተከናወኑት የዘመናት ታሪካዊ ሁነቶች በሒደት ፈጥረውት፣ ነጥሮ መውጣት ራሱን የቻለ ባሕላዊ የማኀብረሰብ ማንነት ነው።
የወረሴህስርወ መንግሥት
በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በየጁ የተነሱት የወረሴህ ስርወ መንግሥት ገዥዎች የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን ከተቆጠጠሩበት ጊዜ ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ ራያን ጨምሮ የጁን እንዲሁም ላስታ ለበርካታ ዘመናት በበላይነት አስተዳድረውታል። የወረሴህ ሥርወ መንግሥት መሥራች እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአባ ሴሩ ጓንጉል አባት ሼኹ አባጌትዬ ከሞፈር ውኃ እስከ ዋጅራት ቆላውን ክፍል በአምበል ቃዲነት፣ በአበጋርነት በሃይማኖታዊ ስርዓት ማስተዳደራቸውን ትውፊት ያስረዳል። ዛሬ ድረስ መውሊዳቸው ከሚከበርላቸው እና ከሚመጀንባቸው ከታላቁ ሼኹ አባ ጌትዬ 42 ልጆች መካከል ሥመ ገናናው አባ ሴሩ ጓንጉል ከራስ ፋሪስ ልጅ ከላስቴዋ ወ/ሮ ገለቡ የወለዱት ቀዳማይ ራስ ቢትወደድ ዓሊ የጎንደርን ቤተ መንግሥት በእጁ ካስገባ በኋላ ራያ ሲዘምት ዞብል ላይ የቀደምት ሥልጣኔ አሻራን የሚጠቁም የከተማ ፍርስራሾች አግኝቶ፥ በዚህ በፈረሰው ቦታ ላይ ዛሬ ዞብል ብለን የምንጠራትን የራያ ክፍል ዳግም እንደገና ማቆሙን የዘመነ መሣፍንት ዜና መዋዕል ያስረዳል። በትውፊቱ መሠረት ዐጤ ልብነድንግል ከብታቸውን ያረቡበት የነበረ ዐጤ በረት የሚባል ቦታ አሁን ድረስ በዚህ መጠሪያ ሥሙ በራያ ዞብል እና አፋር መዋሰኛ ድንበር አካባቢ ይገኛል።
እነዚህ የወረሴህ መሳፍንቶች ከራያ ማኅበረሰብ ጋር በጋብቻ የተሳሰሩ ስለነበሩ ተወላጆቹ እስከ ዐጤ ቴዎድሮስ መምጣት ድረስ ራያን እና አካባቢውን በበላይነት ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል። ሥመ ገናናው ወረሴህ አባሴሩ ጓንጉል ከራያ ባላባቶች ከምትወለደው ከወ/ሮ ራጅያ የወለዷቸው እነ ደጅ አዝማች ገልሞ ጓንጉል (አባ ቦና ገልሞ)፣ እነ ደጅ አዝማች ወሌ ጓንጉል፣ ከጉራ ወርቄዋ ሽመጥ ቦሩ የሚወለደው የራስ ቢትወደድ ዓሊጋዝ ጓንጉል ልጅ እነ ደጅ አዝማች ጎጂ ዓሊጋዝ (ዓይን አውጣው ጎጂ) እንዲሁም ሌሎች በርካታ የወረሴህ ተወላጆች ራያን በተለያየ ዘመናት በበላይነት አስተዳድረዋል። በደጋው የወፍላ ራያ ክፍል ደግሞ የዋግሹም ተወላጆች ተፅዕኖ የጎላ ነው። ፋሽስት ጣሊያን አንገቱን የቀላው አርበኛው ደጅ አዝማች ኃይሉ ከበደ በወፍላ ኮረም እንደተወለደ ታሪክ ያስረዳል፤ ይህ የሚያሳየው ዛሬ ወፍላ የሚባለውን የራያ ክፍል የዋግ ገዥወች ሲያስተዳድሩት እንደነበር ነው። በላስታ በኩል ባለው የራያ ክፍልየእነ ደጅ አዝማች አናፎ ትውልድ እና የወረሴሆቹ የራስ ቢትወደድ ዓሊጋዝ ጓንጉል ትውልድ የራሱ አሻራ ነበረው።

(ሳምንት ይቀጥላል)

ብሩክ ሲሣይ በአማካሪነት፣ ተመራማሪነት እና በኋላፊነት በማገልገል የሚገኙና በግላቸው የታሪክ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ተነስተው የተለያዩ ታሪካዊ ጦማሮችን ያዘጋጃሉ። በኢሜይል አድራሻቸው brooh77@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here