ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) በ1943 በአርሲ ተወልደው፣ በአሰላ፣ አዳማ እና በአዲስ አበባ ትምህርታቸውን ተከታትለው የ12ኛ ክፍልብሔራዊ ፈተና በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ይገኝ በነበረው ልዑል በዕደ ማሪያም ት/ቤት ወስደዋል። ዓለማየሁ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ፣ እስከ ቅንጅት የደረሰ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበራቸው።
የኢሕአፓ እንቅስቃሴ ከተደናቀፈ፣ እርሳቸውም ከታሰሩ እና አገር ጥለው ከኮበለሉ በኋላ ዓለማየሁ በ1963 ጀምረው ያቋረጡትን ትምህርት ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በ1971 በመቀጠል በቀጣዩ ዓመት መባቻ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኬሚስትሪ ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ይዘዋል። እንዲሁም በ1979 በለንደን ዩኒቨርሲቲ በ‹ኒውትሪሽን ባዮ ኬሚስትሪ› የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል።
ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) በ2010 ‹ምሁሩ› የተሰኘ መጽሐፍ ደርሰዋል። ከአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ጋር ምሁራን በኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን እና የነበራቸውን ሚና እንዲሁም በአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሒደት ጉዳይ ዘለግ ያለ ውይይት አድርገዋል። እነሆ ንባብ!
አዲስ ማለዳ፡- አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ ሂደት እንዴት ያዩታል?
ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር)፡- እዚህ ሁኔታ ላይ የደረስነው ብዙ ነገሮች ሆነው ነው። ኢሕአዴግ በሰበስኩና ታደስኩ ያለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፤ ኅብረተሰቡ ውስጥም እንዲሁ ብዙ ነገሮች ተከስተዋል። ሥርዓቱ ያለምንም ጥርጥር አፋኝ ነበርና የፖለቲካ መድረኩን አጥብቦ በመያዝ ቀይ መስመር አስቀምጧል፤ ወይ መስመሯን ትዘላለህ ወይ ትራመዳታለህ። የመሰልቸቱ ሁኔታ ሁለት ነገሮችን ፈጥሯል።
የመጀመሪያው የኅብረተሰብ እንቅስቃሴ እንዲነሳ ሆኗል። በአዲስ አበባ ዙሪያ የተከሰቱ ትንንሽ የሚመስሉ እንቅስቀሴዎች ብለን የቆጠርናቸው እየጎሉ በመሄድ በጊዜ ሂደት ከቁጥጥር ውጪ ሆነዋል። ኢሕአዴግም በለመደው መንገድ ነበር ነገሮችን ለመፍታት የሚሞክረው። ‹ችግሬን ተረድቻለው› ብሎ ራሱን ከገመገመ በኋላ በለመደው የውሸት አካሄድ መሄድ አልቻለም። በለመደው መንገድ መግዛት እንደማይችል ሲያውቅ ነው ይሄ አዲስ ሁኔታ የተከሰተው።
ሰብዓዊነት የራቀው፣ ጠባብ የፖለቲካ ምሕዳር፣ ሁሉም ተቋማት በአንድ ወጥ [እዝ] ተቆጣጥሮ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲ እያለ መግዛት የትም እንደማያደርስ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግም ተረዳው። ጥልቅ ተሀድሶ ተብሎ መታደሱን ያወጀውና አሁን የለውጥ ኃይል ሆነው የወጡት እነዶ/ር ዓቢይ የመጡትም በዚህ ውስጥ ነው።
ሁለተኛ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀመር የተገነባው የፌደራሊዝም ሥርዓት ኢትዮጵያን እንደ አገር በባሕል፣ በሕግ፣ በታሪክ እንደተመሰረተች አገር አድርጎ ሳይቆጥር መራመድ እንደማይችል መገንዘቡን ነው ያየነው። ለምሳሌ መደመር የሚለው ልዕለ ሐሳብ በቶሎ ተቀባይነት ያገኘው የናፈቀንን ይዞ ስለመጣ ነው።ኢትዮጵያውያን በብዙ መከራ ውስጥ ያለፍን ስለሆነ አብሮ ከመኖር ውጪ ምርጫ እንደሌለን ሌላ ዕይታ ሊሰጠን አይችልም። ወደዚህ የመጣው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ቀስ እያለ ኢሕአዴግም ጭምር ነው። ይሄ ነገር ‹ትንሽ አሻሮ ይዞ ወደ ቆሎ መቅረብ› ማለት ይሆን ብለን የጠረጠርንበት ወቅት ነበር።
ኢትዮጵያውያን የተለያየ እውነት ይዘን፣ የተለያየ ባንዲራ ይዘን፣ በአንድ መርከብ ላይ ለመሳፈር ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም። ሁላችንም እዚች መርከብ ላይ ተሳፍረናል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ‹የዚህች መርከብ ማረፊያ ወደብ የትነው?› የሚል ጥያቄ እያነሳን ይመስለኛል። በአጭሩ ለውጡ የተስፋ ጭላንጭል አስጨብጦናል ነገር ግን ገና ብዙ ያልተፈቱ ነገሮች አሉ። ዴሞክራሲ ማለት በመጀመሪያ ነፃነትን ተቋማዊ ማድረግ ነው።
አንዳንዶች ሰው እየሞተና እየተፈናቀለ ነው ለሚሉት መልሴ ሰው ባይሞት ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ለብዙ ዘመን ተዘግቶ የነበረ ቤት ስትከፍተው ንፁህ አየር ብትጠብቅ ሞኝነት ነው የሚሆነው። አንዳንዱ የምናየው ነገር ያለፈው ፈሰስ ነው፤ አንዳንዱ የምናየው ደግሞ ከያዝናቸው ‹እውነቶች› ጥራት ጉድለት የመጣ ነው። አንዳንድ ጊዜ እኩልነትና ዴሞክራሲን በራሳችን መንገድ አጥረን የያዝን ሰዎች ካለን ችግሮቹ ገና ይቆያሉ። የተሻለ ሐሳብ ካለ የተሻለውን ሐሳብ ትጥቅ እየፈቱ ወደፊት የምንሄድበት መንገድ መገንባት ይኖርብናል። መቶ በመቶ ተግባባንም አልተግባባን ስለ ጋራ ሐሳብ ነው የምናወራው ይሄ አንድ ትልቅ ነገር ነው።
በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የምሁራንን ሚና ከማየታችን በፊት ለግንዛቤ እንዲረዳንና ለቃለምልልሳችን አመቺነት እንዲኖረው ምሁር ለሚለው ቃል ብያኔ ቢሰጡት?
ምሁርን በተመለከተ በርካታ ሰዎች ጽፈዋል፤ ሁል ጊዜ ትልቁ የመከራከሪያ ነጥብ ብያኔውን በተመለከተ በግልፅ ማስቀመጥ አለመቻል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አረዳድ ምሁር ማለት በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አልፎ ዲግሪ የያዘ ሰው ማለት ነው።
ምሁር ምን ማለት እንደሆነ ግን በምሳሌ በቀላሉ እንረዳለን። ሻማ ብንወስድና ሻማ በካርቶን ውስጥ እንዳለ በቤት ውስጥ ቢቀመጥ እንደማንኛውም በቤት ውስጥ እንዳለ ቁስ ነው። የበራ ሻማ ግን ክስተት ነው። ሻማውን ከብርሃኑ ለይተህ አታየውም። የበራው ሻማ ለራሱ ሲል አይበራም ላንተ ግን ዙሪያ ገባውን ያሳይሀል፤ ይከስትልሃል። ለእኔ ምሁር ማለት የበራ ሻማ ማለት ነው። የተማረ ማለት ደግሞ ያልበራ ሻማ ማለት ነው፤ የመብራት አቅም አለው ነገር ግን አልበራም።
ስለዚህ ምሁር ማለት በልምድ፣ በትምህርትና በልዩ ልዩ መንገድ ያገኛቸውን ማስተዋሎችና ዕውቀት በሐሳብ መልክ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ሰው ነው። ሥራው ሐሳብ ማመንጨት ነው። ሐሳብ ለማመንጨት ደግሞ በጎ ፈቃድ፣ ክህሎት፣ ዕውቀትና መስዕዋትነት ያስፈልገዋል። አውቆ ክህሎት ባይኖረው አያሻግርም፤ በጎ ፈቃድ ባይኖረው ዝም ይላል።
በአንዳንድ አገላለጾች ላይ እውነተኛ ምሁር፣ የአደባባይ ምሁር ሲባል ይሰማል። ምንን ለማመልከት ነው?
በመጀመሪያ እውነተኛ ምሁር እውነተኛ ያልሆነ የሚባል ነገር የለም። እንደአመለካከታችንና እንደጥበቃችን (expectation) ነው። ምሁር ሐሳብ ያመነጫል ስንል ሁል ጊዜ ጠቃሚ ሐሳብ ብቻ ያመነጫል ማለታችን አይደለም። እውነተኛ ምሁር እንደወቅቱና ሁኔታው መታየት ያለበት ይመስለኛል።
የአደባባይ ምሁር ማለት እንዲሁ አደባባይ ወጥቶ የሚለፈለፍ ማለት አይደለም። የአደባባይ ምሁር ደረጃዎች አሉት። በአጠቃላይ ስለሰው ልጅ ሞራላዊ ብቃቱን የተመለከተ፣ ራሱን የሚጠብቅበትን ቁመናን እያየ በጥልቀት የሚገመግም ሃያሲ ምሁር ይባላል። ኢትዮጵያ አለቃ ገብረሃናን የመሳሰሉ ብዙ ሃያሲ ምሁራን ነበሯት። ሃያሲ ምሁር የመጨረሻው የምሁርነት ደረጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በዋናነት ከእውነት ጋር የወገነ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
በተለይ የፖለቲካ ልሂቃን ዓላማቸውን ለማስፈፀም አንድ የታሪክ ኩነትን ከተገቢው በላይ በማጋነን፣ አሊያም በማኮሰስ አንዳንዴም በጥናት ያልተረጋገጡ ትርክቶችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ይህ ድርጊታቸው ታሪክ አረዳድ ላይ ወጥነት እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ ለግጭት መንስኤ እየሆነ መጥቷል። የኢትዮጵያ ምሁራን በዚህ ረገድ አገሪቱ ያለፈችበትን ታሪክ እና የታሪክ አረዳድ ሕዝቡ እንዲያውቅ በማድረግ ሚናቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
የፖለቲካ ልሂቃን ማለትህ ጥሩ ነው። ‹ቦለቲካህን ተው›፣ ‹ቦለቲካሽን ተይ› በሚባልበት ትርጉም ፖለቲካ ውሸት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህንን መሠረት አድርገው የሚነሱ ምሁራን ብዙ ጊዜ የሚመቻቸውን ነገር፣ ለስሜታቸው ቅርብ የሆነውን ወይም ከፊት ለፊታቸው ያስቀመጡትን ነገር ነው የሚወስዱት። ለምሳሌ አንድ ሰው ፖለቲካውን የሚፈልገው ለማስጠላት ከሆነ ከመልካም ነገርም ውስጥ ቆሻሻውን ነው የሚፈልገው ወይም መጀመሪያውኑ የሆነ ተረክ(myth) ትፈጥራለህ ከዛ በኋላ የምትፈልገው ታሪክ ሁሉ የእውነትን ሀቲት ተከትሎ አይሄድም።
እውነት በራሷ የራሷ ሀቲታዊ መንገድ አላት። ለምን? እንዴት? እያለች ነው የምትጠይቀው። ይህንን ተከትለው የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን አሉ ወይ? ካልከኝ÷ቁጥራቸው ጥቂት ነው እንጂ አሉ እልሃለው። ለምንድን ነው ቁጥራቸው ያነሰው? ለሚለው አንዱና መሠረታዊ ተልዕኮ ማንኛውም ኅብረተሰብ የራሱን ንቃተ ሕሊና ብቃት የሚመጥን ምሁር ነው የሚያገኘው። አሉባልታ፣ ወሬ፣ ሃሜት የሚፈልግ የዛን ዓይነት ምሁር ነው የሚፈልገው። በማይጠይቅ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ምሁር የእውነትን ሃቲት አይከተልም። ለምን? ካልከኝ ስለማይፈለግ። ስለዚህ ኅብረተሰቡ የሚያገኘው ምሁር የሚመጥነውን ዓይነት ምሁር ነው።
ከዚህ ውስጥ የመውጫ መንገዱ ምንድን ነው?
ይሄ ነው የምሁሩ ሥራ÷ ምሁር ሁሉንም ዓይነት ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ‹አይደለም› ማለት ይገባዋል። ይሄ ኅብረተሰብ እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ክብር ይገባዋል፣ የእውነትን፣ የእምነትን፣ የዕውቀትን ሀቲት በደንብ መረዳት አለበት ብለው ፊት ለፊት የሚጋፈጡ መሆን አለባቸው።
የፖለቲካ ልሂቃኑ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የኢትዮጵያ ሥር የሰደዱ ዋነኛ ችግሮች ማለትም ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ጥያቄዎችን አስረስተዋል ሲባሉ ይሰማል። እዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
ይህ በብዙ አገሮች ውስጥ ያለ ችግር ነው። ይሄ የሆነበት ዋናው ምክንያት ታሪካችን የተጻፈበት መንገድ ብዙ ተጽዕኖ አሳድሯል። የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የተጻፈው የነገስታቱ ታሪክ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሽሚያ ውስጥ የምትገባው ቤተክርስቲያን ብቻ ናት። የነገስታት ታሪክ በሚጻፍበት ጊዜ ሕዝብ ይረሳል። ሕዝብ ገባር ነው፡- ቀለብ ያቀርባል፣ ወይ ይቀድሳል፣ ወይ ያርሳል፣ ወታደር ሆኖ ቤተ መንግሥት ይጠብቃል። ይሄ እንደታሪክ አይቆጠርም። በእነዚህ [ዓይነት] ድርሳናት ነው አዕምሯችን ተኮትኮቶ ያደገው።
ፖለቲከኛ ማለት በቤተ መንግስት ዙሪያ ያለ ብቻ ይመስለናል። ለምሳሌ ‹ኃይለ ሥላሴ ተገለበጡ› ትልቅ ፖለቲካ ነው፤ ‹የጌዲዮ ሕዝብ በአስገባሪዎቹ ላይ ተነሳ› ይሄ ፖለቲካ አይደለም። ተማሪዎች ‹ንጉሱ ይውረዱ› እያሉ ያምጻሉ ፖለቲካ ነው፤ የጎጃም ገበሬ ‹ግብር በዛብኝ ይቀነስልኝ› ፖለቲካ አይደለም። እንደዛ ስናስብ ነው የኖርነው÷እውነኛፖለቲካ ግን እሱ ነው።
ስለዚህ የሕዝብ ታሪክ አይደለም ስንማር የነበረው። የሕዝብ ታሪክ አይደለም በብዛት እየተጻፈ የመጣው። የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን አሁን ነው ከአርኪዮሎጂው፣ ከተለያዩ ቅርሶችም የሚገኙ መረጃዎችን እየተደገፉ መጻፍ የተጀመረው። አሁን ሰው የማይረሳበት ታሪክ እየተጻፈ ነው። በዚህ ቅኝት ውስጥ ሆነን ነው የምንነሳው÷ የሕዝብ እንቅስቃሴ፣ እምነቶች፣ አስተሳሰቦች፣ ንግዱ፣ የኅብረተሰቡ ትርምስ፣ መደበላለቅ አብሮ የሚያካተትበት ማለት ነው።
ሌላው ብዙዎቹ ኢትዮጵያ ላይ የተጻፉት ሴክቶራል ናቸው። ለምሳሌ አብዛኞቹ የኦሮሞ ምሁራን ታሪክ ሁሉ የሚጀምር የሚመስላቸው በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን ነው። በ18ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ፍልሰት ተረጋግቶ ኢትዮጵያ ብሔራዊ መንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብታለች። የተወሰነውን አካባቢ ወስደው ነው የሚጽፉት። የሚጽፉት ነገር ልክ ነው አይደለም የሚለውን እንተወው። ሌሎቹም ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው።
የፖለቲካ ልሂቃን ግብ እውነት አይደለም። የምሁር ግብ ግን እውነት ነው። እባብ እንኳን ነድፎህ መርዙን ነቅሎ ማጥናት እውነትን ማግኘት ነው። አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ግብ ግን ፖለቲካ ነው። ይህ ማለት ወይ ተጨቁኛለሁ ከሚለው ወይም ቢችል መጨቆን ወይ ሥልጣን መያዝ ነው።
የአገራችን ፖለቲከኞች የፖለቲካ መፍትሔ ሐሳቦችን በማዋለድ እና ኩነቶችን በቅጡ በመተንተን ረገድ ለምን የተዋጣላቸው ሳይሆኑ ቀሩ?
የስልሳ ስድስቱ አብዮት ሲፈነዳ ምሁሩ ከእጁ ላይ ሁኔታዎች መነጠቁ ይታወቃል÷ ምክንያቱም በግብታዊ ሁኔታ ይንቀሳቀስ የነበረው ወጣቱ፣ አስተማሪው፣ የተማረ የሚባለው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያና የዓለም አቀፍ ሁኔታ ገንፍሎ በአንድ ጊዜ ከእጁ ላይ ነጠቀው። ሳይደራጅ ለንጉሳዊ መንግሥት ሥነ ስርዓት አስከባሪ ለነበረው ወታደራዊ ኃይል ነው ተደራጅቶ የነበረው። የተደራጀ ነው ሁል ጊዜ የሚያሸንፈው።
በዘጠና ሰባት የሕዝብ ዕውቀት ወይም መረዳት፣ የሕዝብ መከፋት፣ የሕዝብ መጥላት ጣሪያ ደርሶ ያንን በሥነ ስርዓት ተደራጅቶ ልክ ወቅቱን የሚመጥን የፖለቲካ ጥናት (thesis) አዘጋጅቶ በሁኔታ ውስጥ የሚመጣውን ጉዳት ተምኖ ወደፊት ምን ያክል ልራመድ እችላለሁ የሚለውን አይቶ የሚንቃሰቀስ እውነተኛ የፖለቲካ ኃይል አልተፈጠረም። ቅንጅትም ቢሆን መሀል ሜዳ ላይ ነው የቀረው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይን ጨምሮ በርካቶች የኢትዮጵያ ትልቁ ተግዳሮት የዘውግ ብሔርተኝነት እንደሆነ በስፋት ሲናገሩ ይሰማል። መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ዓቢይ አህመድ ማለት የኦዴፓና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ናቸው። እሳቸው ራሳቸው ዛሬ ትልቁ ተግዳሮታችን ብሔርተኛነት ነው ብለው ነው የሚያስተምሩን። ልብ አድርግ! ራሳቸው የአንድ ብሔርተኛ ፓርቲ ሊቀ መንበር መሆናቸውን።
በመጀመሪያ እርምጃ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ወይም በአጠቃላይ ብሔርተኝነት ከታሪክ የተፈጠረ ክስተት እንጂ እንደው ከሰማይ ዱብ ያለ መጥፎ ነገር አይደለም። የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያየ እምነት የሚያራምዱ፣ የተለያየ ሐሳብ፣ የተለያየ ማኅበረ ሥነ ልቦና ያላቸው ሕዝቦች ከመኖራቸው ጋር ተያያዘ ነው።
ነገድ በጣም ለስላሳ አስተሳሰብ ነው። ያንን ለስላሳ ሐሳብ ወስደው ተበድያለሁ ማለት ሲጀመርና የፖለቲካ ልሂቁ ሲገባበት ወደ ርዕዮት ይቀየራል። ስለዚህ የመጀመሪያ ነገር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትልቁ ተግዳሮት ብሔርተኝነት መሆኑን መቀበል ነው። በትምክህተኝነትም በጠባብነት በሚሉት ማለት ነው።
ችግሩ መፈታት አለበት÷ ለመፍታት ደግሞ ምን መደረግ አለበት የሚለው ቀጣይ ጥያቄ ነው የሚሆነው። መልሱ ደግሞ ከዓለም ታሪክ መማር ነው። በመጽሐፌ ውስጥ ኢትዮጵያ ልትማር የምትችልባቸውን ስምንት አገራት ጠቅሻለሁ። ብሔርተኝነትን በመፍታት ረገድ ሊብራል ዴሞክራሲ ነው የሚያዋጣው። ሶሻሊዝም ብሔርተኝነትን አልፈታም፤ እንዲያውም የበለጠ ወደ ከረረ ሁኔታ ውስጥ ነው የከተተው። መሰመር ያለበት ብሔርተኝነት የሕዝቡ ርዕዮት አይደለም፤ የልሂቁ እንጂ።
አሁን እየታየ ያለው ለውጥ በኢሕአዴግ ውስጥ ነው። ይሁንና ለውጡን ተከትሎ ይሄነው የሚባል የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቀሴ እየተመለከትን አይደለም። ይህ የሆነው ለምን ይመስሎታል?
ለዚህ መልሴ እንደአተያይህ ነው የሚል ነው። ኅብረተሰቡ ምን ይጠብቅ ነበር፣በግለሰብስ ደረጃ ምን እንጠብቅ ነበር የሚለው መፈተሽ አለበት። የኢሕአዴግ አስተሳሰብ ርዕዮት ውስጥ አጥፎ የሚሄደውን anti-thesis አማራጭ ሆኖ ነበር ወይ ብለህ ብጠይቀኝ መልሴ አይታየኝም ይሆናል። የኢትዮጵያን ውድቀት ብቻ ስናስብና ሙሾ ስናወርድ ከከረምን÷ ስለ ትንሣኤዋ ለማውራት የሚበቃ እውቀት የለንም ማለት ነው።
በገዢው ግንባር ወይም መንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች ይታዩ ከነበሩ ኢዴሞክራሲያዊነት/ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ባልተናነሰ በተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችም ውስጥ ፍፁም ተመሳሳይነት ይታያል ይባላል። የዚህ ተመሳስሎ አንድምታ ምንድን ነው?
ብዙዎቻችን የተቀዳንበት የፖለቲካ ባህል አንድ ነው። ኢሕአፓ ትልቁ ችግሩ በውስጡ ያለው ፀረ ዴሞክረሰራሲያዊነት ነው። በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ታግሎ የሚያውቅ ድርጅት ኖሮ አያውቅም። በውስጡ ዴሞክራሲ የሌለው ድርጅት ለዴሞክራሲ ሊታገል አይችልም። ማርክሲዝም ሌሊኒዝም ደግሞ የዴሞክራሲ ርዕዮት አይደለም።
ሌላው በነፃነት መወያየት ነበረ ወይ? እንተማመን ነበር ወይ? ጭቃ መወራወሩስ አልነበረም ወይ? ሰላይ ተብሎ ያልተፈረጀ ሰው ማነው? ትርጉም የሌለው የስም ማጥቆር ነበር የሚካሄደው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ መጥላት በቂ ነው፤ ጎበዝም ያስብላል። ይህ አሁንም አልቆመም።
አገር ችግር ላይ በወደቀችበት ጊዜ፣ ሕዝብ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ ወይም ነፃነት በታፈነበት ጊዜ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት?
የምሁራን ሚና ይሄን ያለውን ሁኔታ በዕውቀት ላይ ተመስርቶ እውነቱን ፈልቅቆ በማውጣት ፊት ለፊት መሄድ ነው። ቀደም ብለን ሻማ ብለናል። ሻማውን ፊት ለፊት አድርገን ነው መሄድ ያለብን። ይሄ ኅብረተሰብ ፊት ለፊት እየሄደ ብርሃን የሚያሳየው ያስፈልገዋል። የበራውንም ሻማ ጨፍልቆ አጥፍቶ ለመሄድ የሚችል የኅብረተሰብ ኃይልም አለ፤ ‹በቃ አበዛኸው ዝም በል› የሚል።
በመጀመሪያ ግን የኢትዮጵያ ምሁራን ራሳቸውን ማግኘት አለባቸው። በዚህ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ እነሱ ምን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ይሄ ሁኔታ የተከሰተው ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። በመጀመሪያ በሐሳብ ልዕልና ማመን አለባቸው። የሰው ልጅ በሐሳቡ በሚያመነጨው ምናብ አማካኝነት ነው የሚንቀሳቀሰው÷ሕይወታችን ምናባዊ ነው።
ምሁራን ራሳቸውን ካገኙ በኋላ መቀራረብ፣ መሰባበሰብና መደማመጥ አለባቸው። ዕውቀቷ እንደሰንሰለት እየተቀጣጠለች ትሄዳለች። አሁን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መኖሩን እየሰማን ነው÷እየተወያዩ እንዳሉ እየሰማን ነው። ይህ ጥሩ ነው መወያት ያበረያልና።
ሌላው ትልቁ መሳሪያ በእንግሊዝኛ appreciative inquiry የሚባለው እያንዳንዱ ነገር ውስጡ መልካም ነገር አለ፤ መጥፎም ሊኖር ይችላል እንደማለት ነው። እነዚህን ነገሮች ተንትኖ መረዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ስርዓቱን በተመለከተ ይሄ ስርዓት ምን ሰጠን፣ ለምን ሰጠን፣ እንዴት ሰጠን የሚለውን በማጠየቅ የሰጠውን እያደነቁ መገንባት መቻል አለባቸው። ፊት ለፊት መሄድ ይኖርባቸዋል። ከሁሉም ይበልጥ ግን ራሳቸውን ማግኘት አለባቸው ብዬ ነው የማስበው።
‹‹ምሁሩ›› በተሰኘው መጽሐፍዎ ላይ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተሳካላት አይመስልም ብለው ገልጸዋል። ለዚህ ድምዳሜዎት ተጠቃሽ የሚሆኑት ገፊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዴሞክራሲን ራሱ ከመርህ አንጻር ሳይሆን ከተልዕኮው አንጻር ካየነው ዛሬ በዓለም ላይ ዴሞክራሲ ማለት ከተቋማት መገንባት ጋር የተሳሰረ ነው። እንደጥንቱ የግሪክ ዴሞክራሲ በአንድ ቦታ ተሰብስበህ የምታካሂደው እሰጣ ገባ አይደለም። ቀጥተኛ ዴሞክራሲ ቀርቷል፤ አሁን ያለነው የውክልና ዴሞክራሲ ላይ ነው። የውክልና ዴሞክራሲ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ነው።
ኢትዮጵያ እነዚህን የዴሞክራሲ ተቋማት በመገንባት ረገድ አልተሳካለትም። ገና አሁንም በልምምድ ላይ ነን። ትንሹ(ቀላሉ) የዴሞክራሲ ትግበራ የሚጀምረው አንድ ሰው የራሱ ነፃ ሰው መሆኑ እውቅና ከመስጠት ይጀምራል። አንዱ የሚያመነጨውን ሐሳብ ራስህ ካመነጨኸው ሐሳብ እኩል መመልከትም ያስፈልጋል። ይሄ ሐሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ በባህል፣ በአኗኗር እንዲሁም በእምነታችን ውስጥ አለ ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልገዋል። የእምነት ተቋሞቻችን እንኳን ጨዋታውን የሚጫወቱት ዘግተው ነው። ዴሞክራሲ ደግሞ በነፃ አስተሳሰብ (በሊብራሊዝም) ላይ ነው የሚገነባው። እነዚህ የሌሉበት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ገና ሩቅ አይመስልህም?
የምሁራን የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መሳተፍ ይሻላቸዋል ወይስ በገለልተኝነት ማማከር?
በአጠቃላይ የዓለም ታሪክን ስንመለከት በተለይ የፖለቲካ ሃያሲያን የሆኑ ምሁራን በአብዛኛው በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አይደሉም፤ ከኮሚኒስት ምሁራን ውጪ። ሌኒን፣ ማኦ ሴቱንግ፣ ስታሊን የፓርቲያቸው ምሁርም ፖለቲከኞችም ነበሩ። በሌላ በኩል አንቶኒዎ ግራሚሽ፣ ሉዊስ አልታስን የፖለቲካ ዝንባሌ ቢኖራቸውም ዕውነትን ግን ለፖለቲካቸው ብለው መስዋት አላደረጉም። እንደኔ ዕይታ ፖለቲከኛም ይሁን ከፖለቲካ ውጪ እውነትን ግን በምንም ነገር መስዕዋት ማድረግ የለበትም እላለሁ። ከእውነት ጋር መወገን ይገባዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 100 መስከረም አዲስ ማለዳ መስከረም 23 ቀን 2013