“እርሱ የሌለበት?”

0
710

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

አንዳንዴ ተዝናኖትን ለመፍጠር፤ ብዙ ጊዜ ጨርሶ ባለማወቅ፤ ሌላ ጊዜ ባለማስተዋል አልፎ አልፎ ሆነ ተብሎ አግባብ ያልሆኑ አነጋሮች ሲቀርቡ እንሰማለን። ከሰሞኑ ቢቢሲ አማርኛ ላይ “ቴዲ አፍሮ ያልተሳተፈበት የአምለሰት ሙጬ አዲስ ፊልም” በሚል ርዕስ የወጣው ዘገባ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። “ምን ሴት ብታውቅ፣ በወንድ ያልቅ” የሚለው ተለምዷዊ አባባል ጡረታ አለመውጣቱን “አብሳሪ” መሆኑ ይመስላል፤ ያሳዝናል።

በኋላ ርዕሱ መነጋገሪያ ሲሆንና “ምነው!” ባዩ ሲበዛ ነው መሰለኝ ከይፋዊው ቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ላይ ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፤ የሥራ ባልደረቦቼም ልፋት መና ቀርቷል። እንዳልኩት መነሻ ምክንያቱን ባናውቅም አዘጋገቡ ግን ልክ አልነበረም። ምናልባትም ነገሩ ለፊልም ባለሙያዋ አምለሰት ሙጬም ሆነ ለቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከቅንጣት የማይቆጠር ወይም ከቶውንም ያልሰሙት ይሆናል።

በቅድሚያ ነገራችን ከተባሉት ግለሰቦች አይደለም፤ ከአባባሉ እንጂ። ደግሞም ተናጋሪው አድናቂ ነኝ ባይ አይደለም፤ ይልቁንም ዓለማቀፍ ዕውቅና ያለውና ተጽዕኖ አሳደሪ መገናኛ ብዙኀን ሲሆን በቀላሉ ሊታለፍ አይችልም።

እንድጠይቅ ያስገደደኝ “አምለሰት ያልተሳተፈችበት የቴዲ አፍሮ አልበም” ካለመባሉ ሊጀምር ይችላል። አንድ ሰው በምድር ቆይታው የትኛውንም ውጤት ብቻውን ሊያስመዘግብ አይችልም፤ ብዙዎች መሰላል ሆነው ያደርሱታል። ያም ሆነ ይህ ግን መሰላሉን ለመርገጥ መነሳትም ሆነ ረግጦ ወደ ላይ መውጣት የራስን ጥረት ስለሚጠይቅ ውጤቱ የግለሰቡ የራሱ ነው።

አንዲት ሴትም በራሷ መቆም ትችላለች። የቢቢሲ አማርኛን አዘጋገብ በውክልና ስንመለከተው፤ ሴትን ጥገኛ የሚያደርግ ነው። ለምን ጥገኛ? በምን ጥገኛ? በአስተሳሰብ? በአቅም? በችሎታ? በእውቀት? የት እንዳነበብኩት የማላውቀው አንድ ጨዋታ ትዝ አለኝ፤ ሂላሪ ክሊንተንና ባለቤቷ ቢል ክሊንተን ነዳጅ ሊቀዱ በገቡበት ማደያ የሂላሪ የመጀመሪያ ጓደኛ የነበረ ሰው ነዳጅ ቀጂ ሆኖ ተገናኙ። ክሊንተንም “እኔን ባታገቢ ኖሮ የነደጅ ቀጂ ሚስት ሆነሽ ነበር” ሲላት፤ “እርሱን ባገባ ኖሮ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ይሆን ነበር” አለችው ይባላል።

በትዳር፣ በጓደኝነት፣ በሥራ ቦታ፣ በቤተሰብና በመሳሰሉ ዝምድናዎች መረዳዳት ይኖራል፤ ጥገኝነት ግን አይደለም። ሴት ልጅ በራሷ መቆም ትችላለች፤ አልፎም ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም አላት። እናቶቻችንን እንደዛ ነው የምናውቃቸውም! አምለሰትም በራሷ የሠራቻቸው አፍ አውጥተው የሚናገሩ ሥራዎች ባለቤት ናት።

መገናኛ ብዙኀን ገጸ ባህሪ በመፍጠር ተጨባጭ እውነታውን ይናገራሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ ጥንቃቄ ሊደርጉ ይጠበቃል። ሲሆን እንደውም ማህበረሰቡ ሳያውቀው የታሰረበትን ልማድ ሰብረው አዲስ ነገር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። በአንጻሩ በባሰ ሁኔታ በተለይም ከሴቶች መብትና እኩልነት ጋር በተገናኘ የቆየውን ልምድ ከቀጠሉ፤ ‹‹ያው ጋዜጠኞችም የማህበረሰቡ ውጤት ናቸው!›› ብለን እንድናልፍ እንገደዳለን። ግን እንደዛ መሆን ነበረበት?

ሊድያ ተስፋዬ
liduabe21@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here