ለመጪው የገና ዓውደ ርዕይ ኮሜርሻል ኖሚኒስ በታሪክ ከፍተኛውን ዋጋ አቀረበ

0
803

በመጪው የገና በዓል በኤግዚቢሽን ማእከል የሚካሄደውን ዓውደ ርዕይ አዘጋጅ ለመለየት ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 21 በተደረገው የጨረታ ውድድር ኮሜርሻል ኖሚኒስ 38 ሚሊዮን 395 ሺህ ብር በማቅረብ እና ካለፈው ዓመትም የ12 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት በኤግዚቢሽን ማእከሉ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን ዋጋ ሰጠ።

ሁለተኛውን ደረጃ የያዘው ኢዮሀ አዲስ ኢንተርቴመንት 38 ሚሊየን ብር ያቀረበ ሲሆን ሴንቸሪ ፕሮሞሽን 37 ሚሊዮን 355 ሺህ ብር እንዲሁም ሀበሻ ዊክሊ 34 ሚሊዮን 177 ሺህ ብር በማቅረብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ስድስት ድርጅቶች የተሳተፉበት ጨረታው ብስራት ኢንተርቴመንት 27 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በማቅረብ በአምስተኛ ደረጃ ሲቀመጥ ለበዓል ዓውደ ርዕይ አዲስ የሆነው ሄኖክ በቀለ ኤቨንትስ 27 ሚሊዮን ብር በማቅረብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል።

ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በሚደረግ የአገልግሎት እና የንብረት ማስተዳደር ሥራው የሚታወቀው ኮሜርሺያል ኖሚኒስ የበዓል ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት ሲወዳደር የመጀመሪያው ነው። ድርጅቱ ከፍተኛውን ዋጋ ያቅርብ እንጂ ለጨረታው ከዋጋ ማቅረቢያ የተዘጋጀውን ቅፅ በመተው ዋጋውን በደብዳቤ በማስገባቱ በሌሎች ተጫራቾች ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ ሲሆን ጨረታው እንዲሰረዝም ጥያቄ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማይስ ቢሮ ዳይሬክተር ቁምነገር ተከተል ገለጻ፣ የበዓል ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት የኤግዚብሽን ማእከል ኪራይ ዋጋ መጨመሩ የመጀመርያው ምክንያት እንደዚህ ዓይነት ነገር ለማዘጋጀት ያለው አማራጭ ኤግዚብሽን ማእከል ብቻ መሆኑ ነው፡፡ የኪራዩ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ተጫራቾች ከፍተኛ ዋጋ ያስገቡና ጫናውን ደንበኞች ላይ ይጥሉታል፡፡ በዚህ ጊዜ በዋናነት ተጎጂ የሚሆኑት ደንበኞች ናቸው፡፡

ከማእከሉ ጋር አብሮ እየሰራ የዋጋ ጭማሪውን የሚያጣራ አካል ቢኖር ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አይኖርም ነበር የሚሉት ቁምነገር፣ አማራጭ አለመኖሩ ይህን ችግር የሚፈጥር ሲሆን የባዛሩን መንፈስም እያዳከመው ይመጣል ብለዋል፡፡በተጨማሪም ሸማቾች ማህበር በስፋት ሊሰራበት የሚገባ ይመስለኛል ሲሉም ያክላሉ፡፡ ዋጋውን ተቆጣጠሮ ማስተካከል ደግሞ የመንግስት ሀላፊነት ነው ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የበዓል ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት የሚያገለግለውን የኤግዚቢሽን ማእከልን ለመከራየት የሚቀርበው የኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ እንደሆነ ይታወቃል። በተገባደደው የ2011 የገና ዓውደ ርዕይ ላይ ሀበሻ ዊክሊ 26.2 ሚሊዮን ብር በማቅረብ ከሌሎች ተጫራቾች ከፍተኛውን ዋጋ በመስጠቱ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።

በተመሳሳይ ቀን የተካሄደው የፋሲካ በዓል ዓውደ ርዕይ ሴንቸሪ ፕሮሞሽን 28 ሚሊዮን 855 ሺህ ብር በመስጠት ከፍተኛውን ዋጋ ያቀረበ ሲሆን ኮሜርሺያል ኖሚኒስ 27 ሚሊዮን 114 ሺህ ብር በማቅረብ ሁለተኛ ደረጃውን ይዟል። ኢዮሀ አዲስ ኢንተርቴመንት 27 ሚሊዮን ብር በማቅረብ ሦስተኛውን ደረጃ ይዟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here