ወሲብ ንግድ ወንጀል ሳይሆን – አንድ መልኩን መከልከል ይቻላል?

0
1939

ቤተልሔም ነጋሽ ባለፈው ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 የአዲስ ማለዳ ዕትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴተኛ አዳሪነት፣ ልመናና ጎዳና ተዳዳሪነትን ለመከላለከል ያዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ መሰረት በማድረግ በተለይ ሴተኛ አዳሪነትን በተመለከተ አንድ መጣጥፍ ማስነበባቸው ይታወሳል። ጽሑፉን በሚያዘጋጁበት ወቅት ረቂቅ ሕጉን ማግኘት ባለመቻላቸው የመገናኛ ብዙኀንን ዘገባ መነሻ በማድረግ ያሰናዱት መሆኑን በመጥቀስ ረቂቅ ሕጉን ካገኙ በጉዳዩ ዙሪያ ተመልሰው እንደሚጽፉት ማስታወቃቸው ይታወሳል። እነሆ ረቂቅ ሕጉን በማግኘታቸው ከቀደመ ጽሑፋቸው የጎበጠውን በማቃናት በሴተኛ አዳሪነት ክልከላ ላይ ያላቸውን ምልከታ አጋርተዋል።

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት ሴተኛ አዳሪነትን፣ ልመናንና ጎዳና ተዳዳሪነትን ለመከልከል ስለወጣው ሕግ በዚሁ ዓምድ አንድ ጽሑፍ ማሳተሜ ይታወሳል። በዚህ መጣጥፍ በተለይ ሴተኛ አዳሪነትን በሚመለከት ሕጉ ሊኖረው ስለሚችለው አሉታዊ ጎን፣ አስተዳድሩ መሰል ሕጎችን በተለይም በወንጀል ሕግ ያልተከለከሉ ድርጊቶችን ወንጀል የማድረግ ሥልጣንና ባለቤትነት አለው ወይ ከሚለው አንስቶ በባለሙያ የቀረበውን የሚዲያ ዘገባ ዋቢ በማድረግ የተወሰኑ ነጥቦች ማንሳቴ የሚታወስ ነው። እንደምታስታውሱት በባለሙያዎች አካባቢ ሳይቀር ባደረኩት አሰሳ ለሕዝብ አስተያየት ቀርቦ ውይይት የተደረገበትን ረቂቅ ማግኘት ባለመቻሌ በአጠቃላይ ሴተኛ አዳሪነትን ወይም የወሲብ ንግድን መከልከል ምን ማለት ነው፣ በተለይ በእኛ አገር ካለው የአፈፃፀም አቅም ውሱንነት አንጻር እንዴት ይታያል የሚለውን ለማየት ሞክሬያለሁ።

ረቂቁን ዘግይቼ ማግኘቴን ስገልጽ በመጀመሪያ ማስረዳት የምፈልገው ሕጉ ቀደም ሲል በጽሑፌ እንደተገለፀው የወሲብ ንግድን ሙሉ በሙሉ የሚከለክል ሳይሆን በጎዳና ላይ የሚደረግን ወሲብ ብቻ የሚከለክል አለመሆኑን ጠቅሼ የባለፈው ሳምንሩ ጽሁፍ አጠቃላይ የወሲብ ንግድ እንደተከለከለ አድርጎ በማሳየቱ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ረቂቁን ሳገኝ በስፋት ወይንም ይዘቱን ተመርኩዤ ሐሳቤን ለማቅረብ እሞክራለሁ ባልኩት መሠረት ግን ይህ ረቂቅ የያዛቸውን ሐሳቦች ለማስፈር ተመልሻለሁ።
ረቂቁ ዘጠኝ ገጾችና ዐሥራ ዘጠኝ አንቀጾች የያዘ ሲሆን ሥያሜውም “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጎዳና ተዳዳሪነት፣ ልመናና ወሲብን ለመከልከል የወጣ አዋጅ” ይሰኛል። አዋጁ የወጣበትን ዓላማ ወይም ያፈለገበትን ምክንያት በሚመለከት እንዲህ ብሏል።

“በአዲስ አበባ የከተማ ጎዳና ተዳዳሪነት ፣ የጎዳና ልመና እና የጎዳና ላይ ወሲብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣቱ ለበርካታ ዜጎች የሰብኣዊ መብት ጥሰትና ለከፋ ማኅበራዊ ችግር መጋለጥ ምክንያት በመሆኑ፤ ለተለያዩ የትራፊክና ሌሎች አደጋዎች የመጋለጥና በአጠቃላይ ለአገራችንና ለከተማችን ገጽታ መበላሸት ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር የከተማው የፀጥታ ችግርና የወንጀል መስፋፊያ ምክንያት መሆኑ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ሥር እየሠደደና እየተባባሰ በመምጣቱ ነዋሪዎችን ለአስከፊ የሰብኣዊ መብት ጥሰት እና እንግልት እየዳረገ በመሆኑ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ተጎጂዎችን ወይም ተጋላጮችን ለመደገፍና ለማቋቋም ከሚደርገው የማቋቋምና የመደገፍ ጥረት በተጨማሪ ድርጊቱን በሕግ ማዕቀፍ መከልከል አስፈላጊ በመሆኑ፤ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ፣ በጎዳና ልመና ላይ የተሰማሩ እና በጎዳና ላይ ወሲብ ንግድ እየተዳደሩ ያሉ ዜጎችን ጥበቃ፣ እንክብካቤና መልሶ ማቋቋም ሊደረግላቸው እንደሚገባ በመገንዘብ እና ይበልጥ ለማኅበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸውን ጾታቸውንና ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ የተለየ ጥበቃ፣ ክብካቤና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም ተገቢው ድጋፍ ተደርጎ ወደ ቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ከተደረገ በኋላ በድጋሚ ወደ ጎዳና በመውጣት ወደ አስከፊ ኑሮ እንዳይመለሱና ለተለያየ ወንጀል ድርጊት መሣሪያ እንዳይሆኑ በሕግ ክልከላ ሊደረግበት እንደሚገባ በመታመኑ፤ ሕጉን ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ይላል።

በበኩሌ ይሔ በጎ ሐሳብ ምናልባት “በአጠቃላይ ለአገራችንና ለከተማችን ገጽታ መበላሸት ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር የከተማው የፀጥታ ችግርና የወንጀል መስፋፊያ ምክንያት መሆኑ” ከምትለው አገም ጠቀም ነክ ሐረግ በስተቀር የሕጉ መውጣት ምክንያት እንከን የለውም ባይ ነኝ። ባለፈው ጽሁፍ ያነሳሁት ሕጉ ምን ያህል በመረጃ በተደገፈ የጥናት ውጤት ላይ ያተኮረ ነው የሚለውና ምናልባት ከአስተዳድሩ በተለያዩ መድረኮች (ተጨማሪ የውይይት መድረክ ይዘጋጃል ብለን በማሰብ) ሊመልሰው የሚችለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

ከላይ እንደገለጽኩት ሕጉ የወሲብ ንግድን የሚከለክል አይደለም። በኢትዮጵያም ባለፈው ጽሁፍ በዝርዝር እንደሰፈረው በግል በወሲብ ንግድ መተዳደር ሕገወጥ ድርጊት ወይንም ወንጀል አይደለም። ለዚሁ ዓላማ ቤት ከፍቶ ሴቶችን ሰብስቦ የወሲብ ንግድ ማከናወን ግን ወንጀል ነው። በቤት ወይም በንግድ ደረጃ የተከለከለ በግል የተፈቀደ ነገር በግል ሊከናወንበት የሚችለው አንዱ አካሔድ ጎዳና ላይ በመቆም ደንበኛ ወይም ገበያ መፈለግ መከልከል ምን ያህል ያስኬዳል የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው።

ለመሆኑ የጎዳና ላይ ወሲብ የተባለው የቱን ዓይነት ነው ለሚለው የጎዳና ወሲብ የተባለውን ረቂቅ አዋጁ ሲተረጉመው ፡ “የጎዳና ወሲብ ማለት ወሲብን እንደገቢ ምንጭ በመቁጠር በጊዜ ወሰንና በገንዘብ ወሲብን (ግብረ ሥጋ ግንኙነትን) በመፈጸም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በጎዳና ላይ በዚህ ገቢ የሚተዳደር ሆኖ በመንገድ ወይም በተሽከርካሪ ወይም በመኪና ማቆሚያ ስፍራ ውስጥ የሚፈፀም የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ያካትታል” ይላል።

ይህንኑ የጎዳና ወሲብን የሚከለክለው የረቂቅ ሕጉ ክፍል 7 ደግሞ በዝርዝር ከጎዳና ጋር ተያይዟል ባለው (ምንም እንኳን ከታች እንደምትመለከቱት በቁጥር አራት ላይ ጎዳና ከሚለው ወሰን የወጣ ቢመስልም) ወንጀል ላይ ዝርዝር አስቀምጧል። በዚህ ም መሠረት
7. በመንገድ፣ በተሸከርካሪ ውስጥ እና በመኪና ማቆሚያ ላይ የሚፈፀም ወሲብን ስለመከልከል
ማንኛውም ሰው ከዚህ በታች በተጠቀሱት መንገዶች፣ ጎዳናዎች ወይም ቦታዎች ላይ ወሲብ መፈፀም የተከለከለ ነው፤
(1) በዋና ዋና መንገዶችና የመንገድ ዳርቻዎች፤
(2) በዋና መንገድ ላይ በመቆም የወሲብ ንግድ ላይ መሠማራት፤
(3) በማንኛውም የመኪና ፓርኪንግ ቦታዎችና በተሸከርካሪ ውስጥ በመሆን ወሲብ መፈፀም፤
(4) በቴአትርና ሲኒማ ቤቶች፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾችና የመናፈሻ ቦታዎች ላይ ወሲብ መፈፀም

የተከለከሉ መሆናቸው ተደንግጓል። አፈፃፀሙን በሚመለከት ደንብ አስከባሪዎችና የፀጥታ አካላት በቅንጅት የቁጥጥር ሥራውን በሚመለከት እንደሚሠሩ፣ የመጀመሪያው ሥራ የልመና የጎዳና ተዳዳሪነትና የጎዳና ላይ ወሲብ ንግድ የሚከናውኑትን ሰዎች “ተግባሩን እንዳይፈጽሙ መንገር” ሲሆን ተነግሯቸው ከጥፋታቸው ካልተመለሱ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት በደንብ መተላለፍ ወንጀል እንዲጠየቁ እንደሚደረግ ተመላክቷል። ከአስፈፃሚ አካላቱ ወይም እነኝህ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ የቁጥጥር ሥራውን ይሠራሉ ተብለው ከተቀመጡ አካላት በተጨማሪ ሌሎች አስፈፃሚ አካላት ተብለው በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ተቋማት ለማኅበራዊ ችግር የተጋለጡ አካላትን በማቋቋም “የወሲብ ንግድ አስከፊ ገጽታን በማስተማር” ትምህርት በመስጠት አፈፃፀሙን ማገዝ እንዳለባቸው ተቀምጧል። አስተዳደሩ ይህን ረቂቅ አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስችሉ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል የሚል በመሆኑ ሦስቱም ዓይነት ጎዳናን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች በሚገባ ተዘርዝረው አፈፃፀሙ አዋጁ መግቢያ ከተቀመጠው የዜጎችን መብት የመጠበቅ በጎ እሳቤ ርቆ ሌላ ሰብኣዊ መብት ጥሰት የሚፈፀምበትና ተጋላጭ የሆኑትን እነኝህን የኅብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ተጋላጭ የሚያደርግ ክፍተት እንዳይኖር የሚረዳ ሊሆን ይገባል።

ሌላው ምናልባት ጽሑፌን ከማብቃቴ በፊት ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ብዬ የማስበው ነጥን አዋጁ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ሁኔታዎች ከሚለው የመጨረሻው አንቀጽ 18 ያስቀመጠው ነጥብ ነው። አንቀጹ “በዚህ አዋጅ የተደነገጉ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በማንኛውም ባሕላዊና የእምነት ሥነ ስርዓቶች ወይም ፌስቲቫሎች የበዓል አከባበር ላይ የሚደረጉ ኩነቶች በተመለከተ የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት አይኖራቸውም” ይላል።

እንዴት ነው ነገሩ? የተባሉት በዓሎች ጎዳና ላይ የሚከወኑ ሆነው ሳለና ምናልባትም በንግድ መልኩም ባይሆን በተለይ የወሲብ ጥቃት ሊፈፀምባቸው የሚችልባቸው ሆኖ ሳለ በእነኝህ ቦታዎች የሚፈፀሙ ድርጊቶች ወንጀል የማይሆኑት ለምንድን ነው? ንግዱስ ቢሆን በዚህ ዓይነት ቦታዎች ይፈቀዳል? የሚለው አጠያያቂ ነው።

በተረፈ አሁንም በተለይ ወጣት ሴቶች ሴተኛ አዳሪነትና የጎዳና ላይ የወሲብ ንግድ ፈቅደው የሚገቡበት አለመሆኑ እውነት ሆኖ ሳለ መቅጣት የመጀመሪያ መፍትሔ ነው ወይ የሚለው መነሳት የሚገባው ጥያቄ ነው። ከዚህ ሌላ አሁንም በግል “ገላን ሸጦ መኖር” የሚለው የመጨረሻ አማራጭ በወንጀል ሕግ ያልተከለከለ ሆኖ ሳለ፣ በአብዛኛው በተለይ በቡና ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የማይሠሩ ዜጎች (በጭራሽ መበረታታት ያለበት የሥራ ዘርፍ ነው ብዬ በፍጹም አላምንም) ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን የወዲው መፍትሔስ ታስቧል ወይ የሚለውን ጉዳይ አስተዳድሩ ያጤናቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በተረፈ እንደማጠቃለያ ማለት የምፈልገው ባለፈው ጽሁፌ የጠቀስኩት ደግሜ ማሳሰብ የምፈልገው ግን ሴተኛ አዳሪነት የከፋ ፣ በአገራችን ሁኔታ ሰፊ ሰብኣዊ መብት ጥሰት የሚካሔድበት፣ የሰውን ልጅ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መሆኑን ነው። ሥራው ተስፋፍቶ መረን እስኪወጣ የመቆጣጠርና የሚካሔድበትን አግባብ በመደንገግ ፈንታ መንግሥት እንደማይመለከተው ጉዳይ ሆኖ ማኀበረሰቡም መኖሩን የማይክደው፣ እጠየፈዋለሁ የሚለው ነገር ግን በአገልግሎት ተጠቃሚነት የሚሳተፍበት ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ሴተኛ አዳሪነት ወይንም የወሲብ ንግድ ጎዳናም ላይ ይሁን ቤት ውስጥ የሚከናወነው የተሻለ የሞራል ልዕልና ያለው ማኅበረሰብ መገንባት ስንችል፣ ይሔም ቢቀር በዚህ ሥራ ላይ አማራጭ አጥተው የተሠማሩትን ዜጎች ገጽታን ለማሻሻል ብቻ ሳይሆን እንደ ሰውና እንደ ጠቃሚ፣ ለአገር አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ዜጎች አይቶ ለማቋቋምና ከሥራው እንዲወጡ ለማድረግ የሚጠይቀውን ከባድ ሥራ የማከናወን ቁርጠኝነት ከመንግሥትም ከሕዝብም ሲኖር ነው።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here