ድሬ ቲቪ ሀገር አቀፍ ስርጭት ለመጀመር የበጀት እጥረት አለብኝ አለ

0
450

ቀደምት ከሚባሉ የክልል ሚዲያዎች ተርታ የሚመደበው ድሬ ቲቪ የስርጭት አድማሱን ወደ ሳተላይት በማሳደግ በአገር ውስጥ እንዲሁም በመላው ዓለም ለሚገኙ የከተማዋ ተወላጆች ለመድረስ እቅድ ቢኖረውም የበጀት እጥረት እንቅፋት እንደሆነበት ገለፀ።

ከተመሰረተ ከ10 ዓአመት በላይ ያስቆጠረው ድሬ ቲቪ በከተማዋ ውስጥ ብቻ ተወስኖ የ15 ሰዓት የአንቴና የቴሌቪዥን ስርጭት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ የድሬደዋ ነዋሪዎች ቴሌቪዥኑ የስርጭት አድማሱን እንዲያሰፋ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

ድሬ ቲቪ በተመሰረተበት ወቅት ከብሮድካስት ባለስልጣን የወሰደው ፈቃድ ፕሮግራሞቹን በአስተዳደሩ ውስጥ ብቻ ለማሰራጨት የሚያስችል ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በማሳደግ በአማርኛ፣ ሶማሊኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ስርጭቱን በማስፋት በምስራቅ ኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ (እንደ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ ባሉ ሀገራት) ተደራሽ መሆንን ዓላማው አድርጎ የተነሳ ቢሆንም፣ ከተማ አስተዳደሩ ባለበት የበጀት እጥረት ምክንያት ግቡን መምታት እንደተሳነው ድሬ ቲቪ የዘርፍ አስተባባሪ እና አርታኢ መላኩ ይፍሩ ይናገራሉ።

በህበረተሰቡ እና በአስተዳድር መዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች፣ ድሬ ቲቪ ስርጭት ሽፋንን ማሳደግ በድሬዳዋ ውስጥ ያለውን የመከባብር፣ አብሮ የመኖር፣ የመፈቃቀር የባህል ተሞክሮ ለሌሎች ለማካፍል ካለው ፋይዳ በዘለለ፣ ኢንቨስተሮችን ወደ ክልሉ ለመሳብ ያለው ሚና የሚታመን ቢሆንም፣ በከተማ አስተዳደሩ ያለው የበጀት እጥረት ለሌሎች መሰረተ ልማቶች ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ ለድሬዳዋ ቴሌቪዥን ዕድገት ውስን መሆን በምክንያትነት ያነሳሉ።

እንደ መላኩ ይፍሩ ገለጻ፣ በድሬ ቲቪ የሚገኙ የማሰራጫ መሳሪያዎች ሲመሰረት ጀምሮ የነበሩ እና ሀገር አቀፍ ስርጭት ለማስጀመር ከጊዜው ጋር የማይሄዱ ናቸው። ‹‹ለዕቃ ግዢ በጀት ስንጠይቅ የዛሬ 2 ዓመት ተገዝቶ የለም ወይ እንባላለን›› ያሉት መላኩ፣ ከደሞዝ እና ከጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ምላሽ ባለማግኘታቸው፣ ባለሙያዎች ወደ ሌሎች የክልል ሚዲያዎች እንደሚሄዱ እና ሚዲያው ለአስተዳደሩ ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ቆርጦ የተነሳ አመራር የለም ሲሉ ይናገራሉ።

የአስተዳደሩ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሕዝቅያስ ታፈሰ፣ ችግሮቹ መኖራቸውን አምነው የሚዲያውን አቅም ከመገንባት አንፃር በ2012 1.8 ሚሊዮን ብር በመመደብ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት፣ በአደረጃጀት ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ጥናቶቹ እንደተጠናቀቁ የድሬ ቲቪን ስርጭት ወደ ሳተላይት ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን በተመለከተ፣ የአስተዳደሩን በጀት እና የመክፈል አቅም ያገናዘበ የደሞዝ አከፋፈል ስርዓት መኖሩን ገልጸው፣ ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመውሰድ የሠራተኞችን ደሞዝ ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። ድሬ ቲቪ ከ100 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያስተዳድራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here