በቅርቡ በተካሄደው የለዛ የአድማጮች ምርጫ የሽልማት መድረክ፤ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ አዲስ አርቲስት እና ምርጥ አልበም በሚሉ በሦስት ዘርፎች አርቲስት ሮፍናን ኑሪ ማሸነፉ ይታወቃል፡፡ ለአገራችን አዲስ ሊባል በሚችለው ኤሌክትሮኒክ ዳንስ ሚውዚክ ወይም (ኢዲኤም) የሙዚቃ ስልት ቀርቦ ይህንን ተቀባይንት ማግኘቱ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ የሙዚቃ ስልቱ ለአገራችን አድማጮች አዲስ ቢሆንም ‹ነፀብራቅ› በሚል መጠሪያ የቀረበው የሮፍናን አዲስ አልበም ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸውን ሙዚቃዎች ይዞ መቅረቡ ለተቀባይነቱ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡
ኤሌክትሮኒክ ዳንስ ሚውዚክ (ኢዲኤም) ወይም ‘ዳንስ ሚውዚክ’ በመባል የሚታወቀው የሙዚቃ ስልት መነሻው ከአውሮፓ እንደሆነ ቢነገርም ባለፈው ዐሥር ዓመት ግን ትልቁን የአሜሪካ የሙዚቃ እንዱስትሪ ከመቆጣጠር አልፎ በአለም ዙርያ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በአገራችንም በቅርቡ የተለቀቀው የሮፍናን ኑሪ ነፀብራቅ አልበምና በሌሎች ወጣት አርቲስቶች በተለያዩ ጊዜያት በኢዲኤም ስልት የተሰሩ ነጠላ ዜማዎች ከሚጠበቀው በላይ ተቀባይነት ማግኘታቸው ይታወቃል፡፡
ኢዲኤም እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1970ዎቹ የምት ማሽን (ሪትም ቦክስ/ማሽን) እና የስንቲሳይዘርን መፈጠርን ተከትሎ ከመጡት የደብ፣ ዲስኮ፣ ሲንዝ-ፖፕ፣ ቴክኖ፣ ኤሌክትሮ፣ ትራንስ እና ሀውስ ከሚባሉ የሙዚቃ ስልቶች እንደተፈጠረ ይነገራል፡፡ ይሁንና እንግሊዛዊው የሙዚቃ ጋዜጠኛ ሳይመን ሬኖልድስ ኢዲኤም አዲስ የሙዚቃ ስልት ከመሆን ይልቅ እነዚህን እና ሌሎች የሙዚቃ ስልቶችን በንዑስነት ያቀፈ ሰፊ የሙዚቃ ስልት እንደሆነ ያምናል፡፡ የአገራችን የሙዚቃ አድማጮች እና የምሽት ቤቶችም በውጪ አገር የተሰሩ የኢዲኤም ሙዚቃዎችን ማዘውተር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
ታዋቂው የሙዚቃ ባለሙያ ሰርፀ ፍሬ-ስብሀት እንደሚለው ‹‹አብዛኛውን ጊዜ ውጪው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚወሰዱ የሙዚቃ ስልቶች ለጊዜው ፋሽን ሲባል ብቻ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዛው የሚቀሩ ናቸው›› ያለው ሰርፀ ‹‹በዚህ መልኩ የሚታወቁ ሙዚቃዎች ‹ታስቦባቸው ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልቶችና ባሕል ጋር የሚቃኙም ሳይሆኑ በሌላው ዓለም የተሰራውን ሙዚቃ በማስመሰል ብቻ የሚሰሩ ናቸው›፡፡ ነገር ግን የሮፍናን ነፀብራቅ አልበም በምን መልኩ ከኢትዮጵያ ባህልና የሙዚቃ ቅኝት ጋር እንደተዋሃደ እና ምን አይነት ቅርፅ ይዞ እንደቀረበ በሚገባ ሳይጠና ይህን መደምደሚያ መስጠት እንደማይቻል ባለሙያው በአጽእኖት ተናግሯል፡፡
በጥቁር አሜሪካውያን እንደተፈጠረ የሚነገርለት የጃዝ የሙዚቃ ስልት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በፊት በአንጋፋው የሙዚቃ ሊቅ ሙላቱ አስታጥቄ አማካኝነት ከኢትዮጰያዊ ቅኝቶች ጋር ተሰናናሎ ‹ኢትዮ ጃዝ› መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ የሙዚቃ ስልቱ በሌሎች ኢትዮጰያዊና የውጩ አገር ሙዚቀኞች መጎልበቱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ ጨምሮታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ኢዲኤም በኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ቅርፅ ይዞ ‹ኢትዮጵያዊ ኢዲኤም› እየተፈጠረ ነው ወይስ ምዕራባዊው ኢዲኤም ‹እንደወረደ› በሚሉት አኳኋን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተፅዕኖ ማሳደር ጀምሯል የሚለው ጥያቄ ግን መልስ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህር የሆኑት አቶ ሳሙኤል አድማሱ እንደሚሉት አንድ የሙዚቃ ስልት ለመፈጠር ብዙ ሂደቶችን ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ የብዙ አርቲስቶች ተሳትፎና ፈጠራዊ አስተዋፅዖ፤ እንዲሁም የሙዚቃ ባለሙያዎች ጥናትና ምርምሮች አንድ የሙዚቃ ስልት ከሌሎች በተለየ መልኩ ራሱን ችሎ እንዲመሰረት ሊያደርገው ይችላል፡፡ አቶ ሳሙኤል እንደሚሉት የሮፍናን ‹ነፀብራቅ› አልበም፤ አምባሰልና ባቲን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ቅኝቶችን ከማካተቱም በላይ የተጠቀመባቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች እና የግጥም ሐሳቦች በስፋት ኢትዮጵያዊ ቃና (ቀለም) የተላበሱ ናቸው፡፡ ይሁንና ሌሎች አርቲስቶች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን የሙዚቃ ዓይነቶች እየሠሩ የሙዚቃ ስልቱ እንዲጎለብት ባላደረጉበት ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ኢዲኤም የሚባል ራሱን የቻለ የሙዚቃ ስልት ተጀምሯል ለማለት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡
አርቲስት ሮፍናን ኑሪ ከዚህ ቀደም ለለዛ የራዲዮ ፕሮግራም በሰጠው አስተያየት የኢትዮጵያን የብሔረሰብ ሙዚቃዎች ላይ ሰፊ ጥናት በማድረግ ከራሱ የሙዚቃ ዘይቤ ጋር ማዋሃዱን ተናሯል፡፡ አልበሙ ብዙ ኢትዮጵያዊ ቀለማትን ቢይዝም ኢትዮጵያዊ ኤልክትሮኒክ ሙዚቃ ተፈጥሯል ለማለት እንደማይደፍርና ጊዜው እንዳልሆነ አስረድታቷል፡፡
በዚህ ጥያቄ ላይ አቶ ሳሙኤል አድማሱ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት ‹አሁን ባለው ደረጃ ኢትዮጵያዊ ኢዲኤም ይህ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ቀለሞችና አካሄዶች አሉት፤ ከዓለም አቀፉ ኢዲኤም በዚህ መልኩ ይለያል ብሎ ትርጉም መስጠት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን የሮፍናን ነፀብራቅ አልበም ግሩም የሆነ ኢትዮጵያዊ ቀለም ይዞ መውጣቱ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ሌሎች አርቲስቶች መሰል ሙዚቃዎችን ሲሰሩና በጊዜ ሂደት የራሱን መልክ እየያዘ ሲሄድ፤ እንዲሁም የራሱ የሆነ አድማጭ የማኅበረሰብ ክፍል እያገኘ ሲመጣ ኢትዮጵያዊ ኢዲኤም ብለን ልንጠራው የምንችል የሙዚቃ ስልት ሊፈጠር ይችላል፡፡
በተመሳሳይም አርቲስት ሮፍናን ኑሪ ሌሎች ሙዚቀኞች በዚህ የሙዚቃ ስልት ላይ መስራት ሲጀምሩ እና እንደ አንድ ኢንዱስትሪ ሲስፋፋ ኢትዮጵያዊ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ለመባል ይበቃል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ይህን ተፅዕኖ መፍጠር ዋና አለማው እንደሆነ ተናገሯል፡፡ ተስፋው ሰምሮለት አርቲስት ሮፍናን ኑሪ ከሃምሳ ዓመት በኋላ የኢትዮ ኢዲኤም አባት ለመባል ይበቃ ይሆን?