በአዲስ አበባ ላይ ያተኮረ ታሪካዊ የፎቶግራፍ መጽሐፍ ይመረቃል

0
588

‹‹የአዲስ አበባ ትዝታ›› የተሰኘና የቀድሞ ማኅበራዊ ሁነቶች ላይ ያተኮረ ከሁለት ሺህ በላይ የቆዩ ፎቶግራፎችን ያሰባሰበ መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል፡፡

የአዲስ አበባ ትዝታ /Vintage Addis Ababa/ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከተፃፉ የተወሰኑ የመግለጫ እና ማስታወሻ ጽሑፎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፎቶግራዎችን ብቻ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ፎቶግራፎቹ የተለያዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 1941 ጀምሮ እስከ 1988 ድረስ ባሉ ዓመታት የተነሷቸው ናቸው፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጆች ለአዲሰ ማለዳ እንደተናገሩት ፎቶግራፎቹን ከባለቤቶቹ እጅ ለማሰባሰብ ሁለት ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡
የመጽሐፉ አዘጋጆች የሀያ ሦስት ዓመት ወጣት የሆነችው ወንጌል አበበ፣ ናፍቆት ገበየው እና ሲውዘርላንዳዊው የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ፊሊፕ ሹዝ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ‹‹ሂስትሪ ኢን ፕሮግረስ›› በተሰኘ ርዕስ ኡጋንዳ ውስጥ የታተመን የፎቶ መጽሐፍ ካዩ በኋላ አዲስ አበባውን መጽሐፍ ለማዘጋጀት እንደተነሳሱ አዘጋጆቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከአዘጋጆቹ አንዷ የሆነችው ወንጌል አበበ እንደምትለው ከሁለት ዓመት በፊት መጽሐፉን ለማዘጋጀት ሲነሱ እንደትርፍ ጊዜ ሥራ ከጓደኞቿና ከቤተሰብ አባላት በመጠየቅ የተወሰኑ ፎቶግራፎችን ማሰባሰብ ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን የፎቶ መጽሐፍ ለማዘጋጀት በርካታ ፎቶግራፎችን ማሰባሰብ በማስፈለጉ ከአንድ ዓመት በፊት በተለይም ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በእንደ አዲስ ፎቶዎችን ከተለያዩ ሰዎች ማሰባሰብ እንደጀመሩም አዘጋጆቹ ይገልፃሉ፡፡
ከማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አውታሮች ባለፈ በአካል በአዛውንቶች የሚዘወተሩ እንደ ፒያሳ ያሉ የአዲስ አበባ ክፍሎች በመሄድ ጭምር ፎቶግራፎችን ማሰባሰብ እንደቻሉ የምትናገረው ናፍቆት ብዙዎቹ ግለሰቦች ታሪካቸውን ለመስማት የሚፈልግ ትውልድ መኖሩን ማወቃቸው ብቻ ፎቶግራፎቻቸውን ለመስጠት እንዳነሳሳቸውም ትገልፃለች፡፡
አዘጋጆቹ እንደሚሉት የመጽሐፉ ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ከፖለቲካዊ ሁነቶች ባሻገር የዕለት ተዕለት የከተማ ኑሮ እና ማኅበራዊ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ማሳየት ነው፡፡ ይህም ታሪክን ከተለየ አቅጣጫ ለማሳየት እና መደበኛው የሰዎች የዘወትር እንቅስቃሴ ምን ዓይነት መልክ እንደነበረው ለመረዳት ይጠቅማል ብለው እንደሚያስቡም አስረድተዋል፡፡ ከመጽሐፉ የዝግጅት ሂደት በዋናነት ስላስተዋለችው ቁም ነገር ለአዲስ ማለዳ የገለፀችው የመጽሐፉ ዋና አዘጋጅ ወንጌል አበበ ‹‹ጎልቶ ከሚወራልት የአገራችን የፖለቲካ ውጥንቅጥ መሃል ማኅበረሰቡ የነበረውን የወዳጅነት፣ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ባሕል ለብዙዎች ተስፋ እንደነበርና በግለሰቦች ሕይወት ውስጥም ወሳኝ ሚና የነበረ እውነት መሆኑን ነው›› ብላለች፡፡
የፎቶግራፍ መጽሐፉ በጀርመን አገር የታተመ ሲሆን ቀዳሚ ተደራሲያኑ ቱሪስቶችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መሆናቸው ታውቋል፡፡ መጽሐፉ በ240 ገጾች ተዘጋጀ ሲሆን፤ በአንድ ሺህ ብር ለገበያ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡
በቀጣይ በአማርኛ ተተርጉሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኢትዮጵያዊያን የማቅረብ ሐሳብ እንዳላቸው የተናገሩት አዘጋጆቹ ከዚህም ባለፈ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዮችን የመካፈል፤ እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችን ትዝታዎች በዚህ መልክ እንዲሰንዱ የሚያነሳሱ ሥልጠናዎችን የመስጠት ሐሳብ እንዳላቸውም ለዝግጅት ክፍላችን ጠቁመዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here