የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የልደት የምስክር ወረቀት ለማገኘት ለሳምንታት እንሰለፋለን አሉ

0
879

በያዝነው ዓመት በመላው አገሪቱ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት በሚሄዱበት ወቅት የልደት የምስክር ወረቀት መያዝ ግዴታ መሆኑን ተከትሎ በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ እና ወረዳዎች ውስጥ ባሉ የምዝገባ ቦታዎች መጉላላታቸውን ነዋሪዎች ገለፁ። የምስክር ወረቀቱን ለማግኘትም ወላጆች ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ እንደሚይዙ እና እስከ 20 ቀን ድረስም እንደሚጠብቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ልጃቸውን ወደ መዋእለ ህፃናት ለማስገባት የምስክር ወረቀቱን ለማግኘት የኹለት ሳምንት ወረፋ መያዛቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት ጋሻዬ ጌታሁን፣ እንግልቱም በሥራቸውም ላይ ተጽእኖ እየፈጠረባቸው መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

የክልሉ የወሳኝ ኩነቶች የምዝገባ ኤጄንሲ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ማስተዋል አለባቸው፣ ከልደት የምስክር ወረቀት ጋር ተያይዞ በተማሪዎች ምዝገባ ላይ መጉላላት እንዳይፈጠር ጊዜውን የሚያራዝም አሠራር ማስቀመጡን ገልጸዋል።

ከትምህርት ቤቶች እየቀረበ ባለው ጥያቄ መሠረት፣ ከመስከረም 6 እስከ 11/2012 በሚጠናቀቀው የተማሪዎች ምዝገባ ወላጆች ለልጆቻቸው የወሳኝ ኩነት የልደት የምስክር ወረቀት መያዝ ስላለባቸው፣ ትምህርት ቤቶች የሚጠይቁትን የወሳኝ ኩነት የልደት ወረቀት ለማውጣት በቀበሌዎች ያለው አግልግሎት አሰጣጥ ምቹ አለመሆኑን ነው ተገልጋዮቹ የሚናገሩት።

እንደማስተዋል ገለጻ፣ ኤጀንሲው የልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞት ያሉ ሰርተፍኬቶችን እንዲወስዱ በክልሉ ሚዲያዎች መቀስቀስ የጀመረው ሐምሌ 4/2011 ጀምሮ ነው።
‹‹ኤጀንሲው ከ2008 ጀምሮ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ያሉ ክስተቶች በአግባቡ እንዲካሄዱ ቅስቀሳ የጀመረ ቢሆንም፣ ህዝቡ ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር አያይዞ ይመለከተው ስለነበር፣ ለመመዝገብ ፈቃደኛ አልነበረም። የምስክር ወረቀቱን ገንዘብ መሰብሰቢያ አድርጎ የሚመለከተውም ህዝብ ቀላል አይደለም›› ሲሉ ተናግረዋል። ዳይሬክተሯ ጨምረውም ‹‹በብዙ ሺ የሚቆጠር ህዝብ በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ አቅሙ ስለሌለንና ጊዜም የሚያስፈልገው በመሆኑ የመመዝገቢያውን ጊዜ እስከ መስከረም 11/2012 እንዲራዘም አድርገነዋል ብለዋል።

በወረዳ አራት፣ በቀበሌ ደግሞ አንድ የምዝገባ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች መኖራቸውን አውስተው፣ በዚህ የሰው ኃይል በጥቂት ቀናት ውስጥ ከአስር ሺ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ ከባድ መሆኑንም አመላክተዋል። ህብረተሰቡ የተሰጠውን ጊዜ በአግባቡ ባለመጠቀሙ የተፈጠረ ችግር እንጂ እኛ ያመጣነው አይደለም ሲሉም አክለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here