መሬት ላይ የሌለው የዐቢይ አስተዳደር ለውጥ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የነበረው ቅቡልነት በፍጥነት እያሽቆለቆ ነው የሚሉት ዳንኤል ፀኀይ ሰዋሰው (ዶ/ር)፣ መንግሥት ችግሮችን ለመረዳት እየሔደበት ያለው መንገድ እና አረዳድ የተሳሳተ መሆን እንዲሁም የሚወስዳቸው እርምጃዎች መፍትሔው የሚያርቁ ናቸው ሲሉ በመሬት ላይ አሉ የሚሏቸውን ማሳያዎች በመከራከሪያነት አስቀምጠዋል፤ ሊወሰዱ ይገባል ያሏቸውንም እርምጃዎች ጠቁመዋል። አለበለዚያ ኢትዮጵያ ሌላ አብዮት እና የሕዝብ ሰቆቃ ልናስተናግድ እንችላለን ሲሉ ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል።

ብዙዎቻችን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ብዙ ተስፋዎች እና ለውጦዎች ጠብቀናል፣ በተለይም በመጀመሪያ ቀን ፓርላማ ላይ ቀርበው ባሰሙት ንግግር የብዙ ኢትዮጵያዊ ልቡ ርዷል፣ ብዙዎቹ ስለኢትዮጵያ የሰሙትንና ያዩትን ማመን ተስኗቸው ስሜታዊ የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ዐቢይ በወቅቱ ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ቀልብ የገዛ፣ ሳቢ እና ቢወራለት የማይሰለች ሰው ሆኑ። እንደዚህ ዓይነት ሕዝባዊ ቅቦልነት በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጡ ቢሆንም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፤ አንደኛ ሕዝቡ በቅርብ የሚያስታውሰው በጣም ጨቋኝ የሆነ የማወዳደሪያ ስርዓት መኖሩና የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰቡ፤ ኹለተኛ ዐቢይ የቀድሞ ገዥዎች ኢትዮጵያን ለመጥራትና ለማክበር በሚጠየፉበት አካሆድ በተቃራኒው ለኢትዮጵያ ያሳዩት ክብር፣ ትህትና መንሰፍሰፍ የሕዝቡን አንጀት መብላት፤ ሦስተኛ ሕዝቡ ለውጥ የፈለገበት ሰዓት እና ዐቢይ ወደ ሥልጣን የመጣበት ሁኔታና አካሆድ መገጣጠም በጣም ተወዳጅ መሪ አድርጓቸዋል።

ነገር ግን ሕዝባችን በዐቢይ አስተዳደር እና አመራር ዙሪያ የዘንጋቸው ምኞት እና መሬት ላይ ያለው እውነታ፣ የአመራር ብቃት እና አግባብነት እንዲሁም ኀላፊነትን መረዳት ላይ ጥያቄ ማንሳት ናቸው። እነዚህ ነጥቦች ላይ ራሳችንን ካልሞገትን፣ ለዐቢይ አስተዳደር የምንሰጠው ግምት እና ምላሽ የተሳሳተ፣ እንዲሁም ተስፋችን ምኞት ብቻ ያደርገዋል። ከላይ የተጠቀሱት ጥያቄዎች በተወሰነ መልኩ፣ የዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ሲመጣ ባሳየው አገራዊ ምልክት (Gesture)፣ ድስኩርና ትርክት የተዳፈኑ መስለዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የዐቢይ አስተዳደር “ለውጥ” አለ እና “እያደረኩ” ብሎ ቢገልጽም (ነፃ ሚዲያ፣ አፋኝ ሕጎች ማላላት፣ ተቃውሚዎችን ማሳተፍ፣ እስረኞችን መፍታት፣ ወዘተ)፣ አገሪቱ ካለችበት ፈርጀ ብዙ ችግር አንጻር ሚዛን የሚደፋና መሠረታዊ የሚባል ለውጥ አይደለም። በአንዳንድ የፖለቲካ ሀያሲያን አመለካከት ታዩ የሚባሉ ለውጦች በራሳቸው ለውጥ ያልሆኑ እና ሙሉ የለውጥን ትርጉምን የማያሟሉ ናቸው፣ ይልቁንም ነገሮችን ወደ ነበሩበት ቦታቸው የመመለስ የሚባለው ዓይነት ሲሆን፣ እንደ ሕዝብ ጥያቄነታቸው ድጋሜ ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው። በተለይም “ለውጡ” ከሕዝቡ ውስጥ ታች ወርዶ፣ ወረዳና ቀበሌ ላይ አለመታየቱ (በአመራርና አሠራር አገልግሎት ለውጥ አለመታገዙ)፣ ለውጥ ላለመኖሩ ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥብ አድርገው ያነሳሉ። እዚህ ላይ የለውጥ ጽንሰ ሐሳብና ውጤት አተያይ ላይ ስምምነት እንደሌለ ልብ ይሏል።

በሌላ በኩል የዐቢይ አስተዳደር በአንጻሩ ለውጡን ለማግዘፍ ብዙ ቢጥርም፣ ለውጡ ግን እንደ አጭር ብርድ ልብስ ችግሮችን መሽፈን ተስኖት እዚህም እዚያም ግጭት እና አለመግባባት መመልከት የተለመደ ሆኗል። በጣም አሳሳቢው ነገር ችግር መፈጠሩና መኖሩ አይደለም፣ ነገር ግን መንግሥት ችግሮችን ለመረዳት የሚሔድበት መንገድ እና አረዳድ የተሳሳተ እና መፍትሔውን እያራቀው መሔዱ ነው። ለምሳሌ ጥቂት ማሳያዎችን እንመልት፡-

1. መሠረታዊ የዓመታት የሕዝብ ጥያቄዎች (የፍትሕ፣ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የመልማት፣ የማንነት)፣ በጊዜያዊ የፖለቲካ ኹነቶችና ፍላጎቶች የመተካት አዝማሚያ
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ዋና ዋና የሚባሉ የሕዝብ ጥይቄዎች ያልተመለሱ ወይም ለመመለስ ትኩረት ያላገኙ ሲሆን፣ በየደረጃው ከዓመት በፊት የተቋቋሙት ብዛት ያላችው የተለያዩ ችግር ፈቺ ሚኒስቴሮች፣ ኮሚሽኖች (ለምሳሌ፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የድንበር ወዘተ) እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠሩ አንድ ዓመት በላይ ተቆጥራል።
በተለይም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከመጀመርያው የድንበርና እርቅ ኮሚሽንን እንደማይቀበልና ወደ ክልል እንደማያስገባ የገለጸበት ሁኔታ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። በተጨማሪም ያለፈው አንድ ዓመት ተኩል በትርክት ደረጃ ዐቢይ ብዙ ያወሩለት የ “መደመር” ፍልስፍና ትርጉሙ በጊዜ ሒደት ዐቢይን ብቻ “መደገፍ” መሆኑ የተገለጸበት ነው።

በሌላ በኩል የዐቢይ አስተዳደር ለተለያዩ ለሚፈጠሩ ኹነቶች ዘገምተኛ እና ወጥ ያልሆነ አቋም ማሳየትና አንዳንዴም የተመቸው መምስል፣ በጣም አስጭናቂ ሁኔታ ሲፈጥር ደግሞ የሕዝብን አስተያየት በመመልከት ከመንግሥት በማይጠበቅ ሁኔታ ምላሽ መሰጠት የዐቢይ አስተዳደር ዋና መገለጫ ሁነው አልፈዋል (ለምሳሌ፣ በሕዝቦች መፈናቅል ላይ ያሳየው አቋምና ለዘብተኛ መላሽ፣ ሙሉ በሙሉ የአመራር ችግር መሆኑ እየታወቀ የጌዲዖን ጉዳይ የያዘበት መንገድ አሳዝኝ ነበር፣ የለገጣፎ መፈናቅል ምላሽም “አላወኩም ነበር” አስቂኝ ነው)።

2. የለውጥ አመራሩ የአቅም ውስንነት እና የችግር አረዳድ
በዘመናዊ ኢትዮጵያ እንደ ዐቢይ የተቃዊሚ መሪዎችን ያቀረበና ያቀፈ፣ እንዲሁም ቅቡል መሪ አይታውቅም። ነገር ግን በዛው ልክም በጣም ሕዝበኛ የሚባልና እና በብዙ ጉዳይ አስተዳደሩ በየጊዜው የሕዝብን ይሁንታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልግ፣ በራሱ ቆራጥ አመራር በጊዜ የማይወስድ፣ አቅመ ቢስ እና አቅጣጫ የጠፋበት አስተዳደር የለም።

የአገሪቱ ችግር ውስብስብና ዘመናት ያስቆጥረ ሲሆን፣ የሚያስፈልገውም ውስብስብ እና የተጠና መፍትሔ ነው። ነገር ግን የዐቢይ አስተዳደር ውስብስቡን የኢትዮጵያን ችግር በቀላል መፍትሔ ለመፍታት የሚሞክር ነው፣ ያ ማለት የዐቢይ አስተዳደር ያለውን ችግር የተረዳበት መንገድ ወይ የተሳሳት ነው፤ ወይም ደግሞ የራሱ ችግርን የሚረዳበት መንገድ አለ ማለት ነው። እንደማሳያ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል አይደለም የተቀመጡ ችግሮች ሊስተናገዱ ይቅርና፣ ወቅታዊ የሆኑ ግጭቶችን እንኳን መቆጣጠር አልተቻለም፣ ከሁሉም በላይ በአገሪቱ ያሉ የገዥ ኀይሎች በውይይት ችግርን ለመፍታት ፍላጎት ማጣትና አለማሳየት፣ የዐቢይ አስተዳደርን ከፍተኛ አመራር የመናበብ ችሎታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኗል። የፖለቲካ አመራር ክህሎት በባሕሪው ከፍተኛ ልምድ፣ ትምህርት እና ዕድሜ የሚፈልግ ቢሆንም ኢትዮጵያ እንዳለመታደል ሆኖ መሪዎቻችን ባልዳበር ተሞክሮ ወደ ትልቁ የሥልጣን ቦታ በመምጣቸው አገር መምራት አልቻሉም።

3. ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ የተጠና የማሻሻያ እርምጃ አለመውሰድ
በአሁኗ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚው በሚገርም ፍጥነት እያሽቆለቆለ ይገኛል። ለምሳሌ፣ በወርሀ ነሐሴ 2011 የዋጋ ግሽበቱ 19 በመቶ የደረስ ሲሆን፣ አስገራሚ ነገር የዋጋ ጭማሪው በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ በጣም መታየቱ ነው። ይህም የሚያሳየው የዐቢይ አስተዳደር የአገር ውስጥ ምርቶችን ለመቆጣጠር እንኳን ምንም ዓይነት ዘዴ እንደሌለው የሚያሳይ ነው። ስንዴ ከውጭ ማስገባትም አሁን ላለው ችግር የማይገጥም መፍትሔ ያደርገዋል፤ ይልቁንም ተምሮ መንገድ ላይ ለሚንከራተትው ምሩቅ፣ በኑሮ ውድነት ስለሚስቃየው ምስኪን ሕዝብ፣ ለፍቶ አዳሪው ገበሬና የደቀቀው የኢኮኖሚ አቅም፣ መፍትሔው ከፖለቲካው በዘለለ ኢኮኖሚውን ማነቃቃትና ማሻሻል ብቻ ነው።

4. በኢትዮጵያ የሚካሔድው ለውጥ ሁሉን ዐቀፍ እንዲሆን ፖለቲከኞች እና ልኂቃን መግባባት ላይ መድረስ አለመቻል
ብዙ የአገሪቱ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን እንደሚያነሱት፣ ግልጽ አገራዊ የለውጥ ፍኖተ ካርታ አለመኖር ብዙ ግርታዎች፣ አለመግባባቶች እንዲሁም የማያባራ ሁኑቶች ውስጥ አገሪቷን ከቷታል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች ብዛት፣ ያልተገደበ ፍላጎት፣ የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ አገራዊነት ማኮሰስ፣ ሕዝበኝነት እና ቡድናዊነት መስፋፋት ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብን አብሮ የከፋፈለው ሲሆን፣ የለውጡ አቅጣጫ እንደ አገር ወደ የት እንደሚያደርሰን እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።

5. በቀላል ለውጥ መሠረታዊ የሕዝብን ጥያቄን ማምታታት
ለምሳሌ፣ በግላጭና በስውር የ‘ዲሞግራፊክ’ ለውጥ ለማምጣት መሥራት፣ የአዲስ አበባን ሕዝብ በጽዳት፣ ማስ ስፖርት’፣ በችግኝ ተከላ፣ እና በመሳሰሉት መልካም የሚመስሉ ነገር ግን ውስጣቸው በሌላ ዓላማ በተሞሉ ተግባራት ወጥሮ መያዝና “የማይታመነውን” የአዲስ አበባን ሕዝብ ከምርጫ በፊት ያለውን ድጋፍ ለዐቢይ እንዲያድርግ ማረጋገጥ ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

6. ባለፈው አንድ ዓመት፣ የዐቢይ አስተዳደር በፍትሕ ዘርፍ ከቀድሞው አሠራር የጎላና ተሻለ ውጤት አለማስመዝገቡ
የዐቢይ አስተዳደር እስረኞችን በመፍታት፣ ኢ-ሰባኣዊ የሆኑ የተከስሽ ምርመራን በማስቀረት እንዲሁም አንዳንድ ሕጋዊ የፍትሕ ስርዓት አካሔድም መከተል በጎ የሚባል ጅምሮዎች ቢያሳይም፣ በግርድፉ ፍትሕን የማቀላጠፍ ሥራ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳየም። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተቋማዊ የአሠራር ለውጥ ካላመጡ (ለምሳሌ ፈጣን የፍትሕ ስርዓት፣ የዐቃቢ ሕግ ሹመት ከመንግሥት ነፃ ማድረግ)፣ እንዲሁም በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሕጋዊ አካሔድን ለማስተካከል የሚደረጉ የመንግሥት ተጽዕኖ መቋቋም ካልቻለች የፍትሕ ስርዓቱ ሕመሙ እንደሚቀጥል ልብ ይሏል።

7. ማቆሚያው የማይታውቀው የሕዝቦች መፈናቅል፣ ግጭትና ስጋት
በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ እንደአሁኑ የዜጎች መፈናቅል የታየበት ዘመን የለም፣ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ኅብረ ብሔራዊ፣ የተዋለደ እና የተጋመደ ሕዝብ ያልተለመደ፣ አስደንጋጭና መቆም ያለበት አስነዋሪ ድርጊት ነው። ግጭቶችን ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች በአጠቃላይ ቅደመ መከላከል ያልተደረገባቸው ነገር ግን መንግሥት ግጭት ሲከሰት ብቻ የማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምዶ ታይቷል፣ በሌላ በኩል ቅደመ መረጃ ደርሶ ብዙ ግጭቶችን ማስቀረት አልተቻልም። በመሆኑም በአገሪቱ በአሁን ሰዓት በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ግጭት እንደማይከሰት የደኅንነት ማረጋግጫ ማንም መስጠት አይቻልም።

8. የማዕከላዊ መንግሥት የሥልጣን አመራር መዳከም እና የክልል መንግሥታት ሥልጣንን ባልተግባ መንገድ ማዋል
ለዐቢይ አስተዳደር ትልቁ የራስ ምታት የክልል መንግሥታት መፈርጠም እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መብዛት ናቸው። ለምሳሌ፣ የትግራይ ክልል መንግሥት በፌዴራል ዐቃቢ ሕግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን ለማቅረብ ፍቃደኛ ሳይሆን እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት በዐቢይ አስተዳደር ከባድ ማስጠንቀቂያ ወይም ቆራጥ እርምጃ አልወሰደም። እነዚህ እና መሰል ተግዳሮቶች የማዕከላዊ መንግሥትን የሥልጣን አቅም የተፈታተኑ ሲሆን የፌዴራል መንግሥቱ መሬት ላይ ያለው ቁጥጥር በተግባር ምን ያህል እንደሆን ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል።

9. የገዥ ፓርቲው ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እርስ በርስ ግጭት አለማቆም
ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢሕአዴግ ውስጥ በተካሔዱ ውስጣዊና ውጫዊ ፍትጊያና ትግሎች፣ እንደ ግንባር የነበረው ፖርታዊና ድርጅታዊ አንድነት አሽቆልቁሎታል፤ እንዲያውም ድርጅቱ በከፋና አደባባይ በወጣ ልዩነት ውስጥ ይገኛል። ኢሕአዴግ አገር የሚመራ በመሆኑ የውስጥ ችግሩን መፍታት ካልቻለ የግጭት ምንጭ መሆኑ አይቀርም፣ ያም መንግሥት የችግር መፍትሔ ሳይሆን ራሱ ችግር ይሆናል።

10. የለውጥ ኀይሉ በሒደት ወደ ቀድሞው የኢሕአዴግ አሠራር የመመልስ አዝማሚያ
የዐቢይ አስተዳደር፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ፣ በሰኔ 15ቱ የባሕር ዳር ጉዳይ ዙሪያ እንዲሁም በሐምሌ 11 የሐዋሳ ጉዳይ፣ እንደ ቀድሞ ገዥዎች ያለበቂ ምክንያት በጅምላ ወጣቶች ማፈኑና ማሰሩ፣ የማሰቃየት ድርጊት ውስጥ መግባቱ፣ የፍርድ ቤት ሒደቱን ያለበቂ ምክንያት ተጨማሪ ቀን በመጠየቅ ማጓተቱ፣ የታሰሩትን በመፈንቅለ መንግሥትና ፌዴራል ስርዓት መናድ መክሰስ መጀመሩ፣ ቃል የገባውን ተቋማዊና መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ አለመዘጋጀትና አለመፈለጉ ያሳያል። በተለይም በተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ክልሎች በተናጠል አገራዊ ጉዳዬችን አፍራሽ በሆነ መልኩ በየጊዜ መገዳድርና መቃውም፣ የዐቢይ አስተዳደር የደረሰበትን የመንግሥትና አመራር ምስቅልቅል መገለጫ ናቸው።

11. በኦሮሞ ጽንፈኞችና በሕወሓት የተከፈተው አዲሱ የፖለቲካ ዓውደ ውጊያ እና የዐቢይ አያያዝ
በቅርቡ የተካሔደው የመቀሌ ስብሰባ በዋናነት ዐቢይ የፌዴራል መንግሥት ኀላፊነቱን አልተወጣም የሚል ክስ ያቀርባል። ከኹለት ቀናት ጉባኤ በኋላ መግለጫ በማውጣት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የፌዴራል ስርዓቱን ለመታደግ ዓለማቀፍ ጥሪ አቅርቧል። በአጠቃላይ አዲሱ የመቀሌ ስብስብ ከዐቢይ መንግሥት በላይ ሌላ የመንግሥት ተቆርቋሪና ተቆጣጣሪ ሆኖ ቀርቧል። የዐቢይ አስተዳደር ብዙ ስህተቶችን እየሠራ አሳዛኝ ውሳኔዎችንም እያሳለፈ እየተመለከትን ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ ለጃዋር አንጃ እና ሕወሓት ጥሩ የመጫወቻ አጀንዳ ለምሳሌ፣ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ያለው ብዥታ፣ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ እንዳያገኙ አድርጓል።

ማጠቃላይ
የዐቢይ አስተዳደር የለውጥ እንቅስቃሴ ፍጥነትና ግለት በጊዜ ሒደት እየቀዘቀዘ እና እየነፈሰበት የሚገኝ ሲሆን፤ በዋናነት የተጋነነ የለውጥ ቃል፣ የቅቡልነት መቀነስ፣ የግጭቶች መበራከትና የሥልጣን ቁጥጥር ማነስ፣ የዜጎች ደኅንነት ማሽቆልቅል፣ በፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ኢኮኖሚው አደጋ ላይ መውደቅ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ኀይሎችና የሕወሓት ጠንካራ መገዳደርና ማሳጣት፣ የዐቢይን አስተዳደር ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ከመመለስና የለውጡ መሪ ከመሆን፣ ወደ መከላከል (ፓርቲውን ወደ ማዳን) እንዲሁም ወደ ቀድሞ የድርጅት አጋሮች ለዕርዳታ እንዲያማትር ያስገደደው ሆኗል። በዋናነት የለውጡን መገታትና መንሸራተት፣ የዘመናት የሕዝብ ጥያቄዎች እንደተጨናገፉ ጉልህ ማሳያ ነው። በተለይም ወቅታዊ እና መሠረታዊ የፖለቲካ ችግሮች ላይ የዐቢይ አስተዳደር የሚያሳያቸው ምላሽዎች እና አያያዞዎች በፍጥነት ካልተሻሻሉ፣ አሁን እየታየ እንዳለው የፖለቲካ ተግዳሮቶች የበለጠ ወደ ኢኮኖሚ ችግሮች እየተቀየሩ ከሔዱ ምናልባትም በኢኮኖሚ ችግር የሚመጣ በቅርቡ ሌላ አብዮት እና የሕዝብ ሰቆቃ ልናስተናግድ እንችላለን።

መውጫ፣ የዐቢይ አስተዳደር
1. የአገሪቱን ተጨባጭ የችግር መጠን፣ ዓይነት እና ክብደት መረዳት (መንግሥት በዚህ ረገድ ችግሮችን እንደተረዳ ወዲያውኑ እርምጃ ቢወስድ፤ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን አሁንም ችግርን የመለየት፣ መተንትን እና መረዳት ትልቅ ክፍተት እንዳለ ነው)፣ እንዲሁም መፍትሔ ተኮር እርምጃዎች ላይ ማተኮር አማራጭ የሌለው አካሔድ ነው።

2. ለችግሮች ቅድሚያ ማውጣት እንዲሁም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት፣ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ቁጥር አንድ ችግር የዜጎች ደኅንነት መሆኑን መቀበል ግድ ይላል።

3. ሕግ እና ስርዓት በአገሪቱ መከበር ለብዙ ዘርፎዎች (ለኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች) መርጋጋት ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት፣ እንዲሁም የመንግሥትን ፖለቲካዊ ሥልጣን እና አቅም የሚጨምርና የሚያጠናክር በመሆኑ፣ የዐቢይ አስተዳደር ሕግ እና ስርዓትን ለዜጎች ደኅንነት ሲል የማይደራደር አቅም ማሳየትና ማስከበር አለበት።

4. አሁን አገሪቱ ባላት የደኅንነት እና የሰላም ደረጃ አገራዊ ምርጫ ማካሔድ አደገኛ ቁማር ሲሆን፣ አገሪቱም ሊደርስ የሚችለውን ምስቅልቅል ለመሽከም የሚያስችል አቅም ወይም ዝግጅት የላትም። መንግሥት ከምርጫ ዝግጅት ጎን ለጎን ከሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ጋር ሰፊ የሆነ ብሔራዊ ውይይትና ድርድር እስካላደረገ ድረስ መጪው ምርጫ አደጋ አርግዞ እንደሚመጣ መገመት አያዳግትም።

5. መቆሚያ ለሌለው የዋጋ ግሽበት መንግሥት፣ የአቅርቦትና ፍላጎት መመጣጠን ላይ ማተኮር፣ በሸማችና ሻጭ መካከል ቀጥተኛ የግብይት ግንኙነት መፍጠር (የደላላን ተጽዕኖ ለመቆጣጠር)፣ ሕገ ወጥ አሠራሮች መቆጣጠር፣ የትራንስፖርት ችግርን መቅረፍ፣ የማክሮ ፖሊስ ማሻሻያ እርምጃ መውሰድ፣ አምራቾች የተሻለ ቴክኖሎጅ እንዲጠቀሙ ማድረግና ምርታምነት ማሳደግ፣ እንዲሁም አማራጭ የኢኮኖሚ ዘርፎችና የውጭ ምንዛሬ ምንጮዎች ላይ ማተኮር፣ ዓይነተኛ መፍትሔዎች ናቸው።

6. ዐቢይ እንደ ግለስብ ይሁን እንደራሱ አስተዳደር እየተገበረ ያለው መሰረታዊ አመራር የሚባል ዓይነት ሲሆን፣ የተሻለ ሕግ፣ ዲሞክራሲ እና ሕዝባዊ አሠራርና ስርዓት ባላቸው አገሮች የሚተገበር የአመራር ስልት ነው። ነገር ግን አሁን አገሪቱ ካለችበት ችግር መጠንና ዓይነት አንጻር ሲታይ የማይዛድ እና የማይመጥን ነው፤ ይህ ሁኔታ የዐቢይ አስተዳደርን ችግርን የመረዳት አቅም ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

አገሪቱ በአሁኑ ስዓት የሚያስፈልጋት ጠንካራ፣ አሳታፊ፣ ወጥ እና ቆራጥነት ያለው አመራር ነው። እስካሁን ያየናቸው ቅድሚያ የማንስጣቸው ጉዳይ ላይ ማተኮር፣ በአማላይ ንግግሮች፣ እርካሽ ገለፃዎች እንዲሁም ሃይማኖታዊ አመራር (Pastoral Leadership) አገር ማስተዳደር ውጤት አልባ እና አዋጭ አለመሆናቸውን መረዳት ግድ ይላል፣ ምክንቱም አደገኛ የሆኑ አገራዊ ችግሮች በተለሳለሱ መፍትሔዎችና አካሔዶች ለመፍታት መሞከር ችግሮችኑ የበለጠ እንደሚያወሳሰብ ልብ ይሏል።

በዳንኤል ፀኀይ ሰዋሰው (ዶ/ር) የሥነ ልቦና መምህርና ተመራማሪ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው sewsewdaniel@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here