በ2011 ቁጥሮች በሕይወት ዙሪያ ምን ይላሉ?

0
1122

በሰው ልጅ ሕይወት ልደት፣ ጋብቻና ሞት ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ኩነቶች ሲሆኑ ፍቺና ጉዲፈቻ ደግሞ በመካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ክስተቶች ናቸው። ታድያ እነዚህን ወሳኝ የሕይወት ክስተቶች ግለሰቦች በፎቶ ለማስቀረት፣ በመቅረጸ ምስል ለማቆየት ይጥራሉ፤ ትዝታን ለማቆየት። መንግሥት ደግሞ የኩነቶቹን ምዝገባ በእጅጉ ይፈልጋቸዋል፤ በአገሪቱ ውጤታማ የልማት ዕቅድ ለመቅረጽ እንደሚያስችለው ስለሚያምን።

መንግሥት በሕግ፣ በአስተዳደርና በማኅበራዊ አገልግሎት አቅርቦቶች ሕዝቡን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለው አስተማማኝ የሚባል የመረጃ ምንጭ ይኸው የእነዚህ ወሳኝ የሕይወት ኩነቶች ምዝገባ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በኢትዮጵያም ይህ ምዝገባ 2008 ማብቂያ ላይ የተጀመረ ሲሆን በአዲሱ ዓመት 2012 አምስተኛ ዓመቱን ይይዛል።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በ2011 ብቻ 1 ሚሊዮን 309 ሺሕ 153 ምዝገባዎችን በተለያዩ አምስት ኩነቶች (ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞት እና ጉዲፈቻ) ሊመዘግብ ያቀደ ሲሆን ሊያሳካ የቻለው 53 በመቶውን ወይም በቁጥር 693 ሺሕ 881 ምዝገባ ብቻ ነው። ይህም ካለፈው ዓመት ምዝገባ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደሳለኝ ተሬሳ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በምዝገባው መሰረት በ2011፤ 515 ሺሕ 964 ልጆች የተወለዱ ሲሆን 89 ሺሕ 818 ደግሞ ከዚህ ዓለም እስከወዲያኛው ያሸለቡ ሰዎች ብዛት ነው። የጋብቻ ቁጥር 79 ሺሕ 54 ሆኖ ሲመዘገብ፤ 8 ሺሕ 652 ትዳሮች ፈርሰዋል ወይም ፍቺ ተፈጽሟል። በሌላ በኩል ለጉዲፈቻ የተሰጡ ልጆች ብዛት 393 ነው። በድምሩ 693 ሺሕ 881 ምዝገባ ተከናውኗል።

በ2010 ከተመዘገበው አንጻር የ2011 ምዝገባ ቅናሽ ማሳየቱን የገለጹት ዳሳለኝ፤ ይህም በዋናነት ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳሉት አያይዘው ጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አገራዊ የጸጥታ ችግሮች መኖራቸው ነው።

እንደ ደሳለኝ ገለጻ፤ ሌላው የምዝገባው አፈጻጸም የቀነሰበት ምክንያት በቀበሌ ያሉ የክብር መዝገብ ሹም የሚባሉ መዝጋቢዎች በኤጀንሲው መዋቅር የተካተቱ ባለመሆናቸው የምዝገባ ሥራውን እንደ ኹለተኛ ሥራ መቁጠርና ትኩረት አለማድረግ ይስተዋላል። ሌላው ምክንያት በቀደሙት ዓመታት እንደሚነሳው ሁሉ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዙሪያ ያለው የኅብረተሰቡ የግንዛቤ ደረጃ ዝቅተኛ መሆንና ጥቅሙን አለመረዳት ነው ብለዋል።

“በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባና የመረጃ ልውውጥ ላይ የቅንጅት አሠራር ክፍተት በስፋት ይታያል” ያለው ደግሞ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ሲሆን ይህን ለማለት አከናውኛለሁ ያለውን ጥናት መሠረት አድርጓል። ዜና አገልግሎት ኤጀንሲው የወሳኝ ኩነትን አፈጻጸም አስመልክቶ ባደረገው ጥናትና እሱን ተከትሎ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ እንደተነሳው፤ በተቋማትና በኤጀንሲው መካከል የመረጃ ለውውጥ ክፍተት አለ ተብሏል።

በአንጻሩ የተሻለ የምዝገባ አፈጻጸም የነበራቸው የኢትዮጵያ ክፍሎችም ነበሩ። ከእነዚህም አዲስ አበባ ከተማ፣ አማራ እንዲሁም ትግራይ ጥሩ በሚባል አፈጸጻም ተጠቃሽ መሆናቸውን ደሳለኝ አስታውሰዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም በተቀሩት መካከለኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ የምዝገባ አፈጻጸም ያለ ሲሆን ዝቅተኛው ሱማሌ ክልል የተመዘገበ ነው።

ኤጀንሲው ዝቅተኛ ምዝገባ በተካሔደባቸው ክልሎችና አካባቢዎች ከአመራርና አስተዳደር ጋር በመነጋገር ለማሻሻል ጥረት እንደሚያደረግ ደሳለኝ ገልጸዋል። ከፍተኛ ምዝገባ የታየባቸው አካባቢዎችም በአንጻራዊነት የተሻለ የተባለውን ውጤት ያመጡት ሊያሰማሩ በቻሉትና ባላቸው የሰው ኀይል፣ እንዲሁም በነዋሪዎቻቸው የተሻለ ግንዛቤ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው ከቀናት በፊት ወሳኝ ኩነት ምዝገባ አተገባበርን በተመለከተ በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሚከናወን ጥናት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ውይይት፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሙጂብ ጀማል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ዘግይታ ወሳኝ ኩነት ምዝገባን እንደጀመረች ጠቅሰዋል። ባለፈት አምስት ዓመታት ውስጥም አራት ሚሊዮን ኩነቶችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስከአሁን ባለው አፈጻጸም ተግባራዊ የሆነው ከግማሽ በታች እንደሆነ ተናግረዋል።

ምዝገባው ከፍላጎት ጋር ባለመተሳሰሩ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት አልተቻለም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህን ፍላጎት ለመፍጠርም በ2012 የትምህርት ቤት ምዝገባንና የፓስፖርት አገልግሎትን ከልደት ካርድ ጋር ማያያዝ መጀመሩን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ካሉ 19 ሺሕ 20 ቀበሌዎች በ16 ሺሕ 900ዎቹ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እየተካሔደ መሆኑም በዕለቱ ተገልጿል።

በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ ኤጀንሲው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የመገምገሚያ ነጥቦች በመታገዝ አገር ዐቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሒደት ስርዓትን እገመግማለሁ ብሏል። ግምገማውም በአፍሪካና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመገምገሚያ ነጥቦች መሠረት የሚካሔድ ነው። ቀጥሎም ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገልግሎት የሚሰጥ ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማዘጋጀት መታቀዱ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here