የኑሮ ውድነት ያጠላበት አዲስ ዓመት

0
823

የበዐል ሰሞን የገበያ ግርግር መቼም የተለመደ ነው። እንደዚህ ዓይነት ትዕይንት በአዲስ ዓመት ዋዜማም መመልከት እንግዳ ጉዳይ አይደለም። አዲስ ማለዳ በመዲናችን ያሉ የገበያ ማዕከላትን ጎብኝታና ሸማቾችን አነጋግራ እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን በማስተንተን የዕቃዎች ዋጋ ተመልክታ የኑሮን ሁኔታ በአጠቃለይ ለማሳየት ጥረት አድርጋለች።

ለአዲሱ ዓመት በዓል ቅቤና ዘይት፣ ዶሮ፣ በግ፣ እንቁላል፣ የጤፍና የስንዴ ዱቄት ሲሸምቱ አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ሸማቾች መካከል አንዳንዶቹ የበዓሉን ዝግጅትና የገበያውን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡን አስተያየት ገቢያቸውና ወጪያቸውን አመጣጥኖ መኖር ረጅም ዳገት የመውጣት ያክል እንደከበዳቸው ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ በተደረገው ጭማሪ መሰረታዊ ነገሮችን ለመሸፈን እንኳን መቸገራቸውን ነው ያስታወቁት። በዓልን ማሰብማ የማይታሰብ ነው ያሉን በርካቶች ናቸው።

ሾላ አካባቢ በሚገኘው በግ ተራ ያገኘናቸው በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት አዳሙ ይስማንጉስ፣ ከበግ ተራ ባዶ እጃቸውን ሲመለሱ አግኝተናቸዋል። “የበግ ዋጋ ከወራዊ ገቢዬ እኩል ሆኗል” ያሉን አዳሙ፣ ከዚህ በፊት በ1 ሺሕ 200 ብር የምገዛት ጠቦት ሦስት ሺሕ ብር ሆኗል። ደህና በግ ልግዛ ከተባለ 4 ሺሕ 500 ብር እየተጠራ ነው። “ምነው ባይበላስ?!” ሲሉ አማርረዋል። የበዓል ሽታው መጥፋቱን የሚያወሱት አባት፣ በዓል የደስታ ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የሰቀቀን ነው ሲሉ የኑሮ ውድነቱን አስከፊነት አመላክተዋል።

ካራና ሸጎሌ ከሚገኙት የቁም እንስሳት የገበያ ሥፍራዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ከሆነ ነጋዴዎች ለአንድ ትልቅ ሰንጋ የሚያቀርቡት የጥሪ ዋጋ እስከ 50 ሺሕ ብር ድረስ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። 30 ሺሕ፣ 25 ሺሕ ብር የሚጠሩባቸው መካከለኛና ዝቅተኛ ሰንጋዎችም አሉ። ጥጃ እስከ 15 ሺሕ ብር ይጠየቅበታል። ከዘራ፣ ምርኩዝና ገመድ ይዘው ሰንጋ ለመግዛት ከሚያማርጡት እና አዲስ ማለዳ ካነጋገረቸቸው አባወራዎች መካከል ብዙዎቹ ጥሪው ከአቅማቸው በላይ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

ዶሮ ለመግዛት ወደ ሾላ ገበያ ያቀኑትን እናት ወደ ዶሮ ተራ አቅንተን አግኝተናቸው ነበር። በዓሉ ከመድረሱ በፊት ዶሮ ለመግዛት ብመጣም ዋጋው አስደንግጦኛል ነው ያሉት። አንድ ዶሮ 250 ብር መባላቸውን የተናገሩት እናት፣ ትልቅ ዶሮ እስከ ሦስትና አራት መቶ ይጠራል ሲሉም አክለዋል። አዲስ ማለዳም በገበያው ተዘዋውራ የተመለከተችው ዋጋ ካነጋገረቸቸው ሴት ወይዘሮ ምላሽ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ታዝባለች።

እንቁላል የሐበሻ 5 ብር 50 ሳንቲም ሲሸጥ፣ የፈረንጁ ደግሞ 4 ነጥብ 50 ሳንቲም ተሸጧል። ለጋ ቂቤ 350፣ በሳል ቂቤ 280፣ ቀይ ሽንኩርት በሾላ ገበያና የተለያዩ ማከፋፈያዎች 25 ብር ሲሸጡ፣ በየመንደሩ 28 ብር በመሸጥ ላይ ነው። ነጭ ሽንኩርት 150፣ በርበሬ 120፣ ዘይት በሊትር ከ90 እስከ 100 ብር፣ ኮረሪማ 350፣ ብቅል 100 ብር፣ ጌሾ 60 ብር፣ ኮሰረት 120 ብር፣ ጥቁር አዝሙድ 100 ብር ሲቸረቸር ተመልክተናል።

ለዳቦ የሚሆን የስንዴ ዱቄት ነጋዴዎች ኪሎውን በ27 ብር ሒሳብ ሲሸጡ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች ደግሞ በ20 ብር ሒሳብ በመሸጥ ላይ ናቸው። በልደታ፣ በቂርቆስና በአራዳ ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር ያነጋገርናቸው እናቶች እንደተናገሩት ከነጋዴውም ሆነ ከማኅበራቱ የሚገዙት የስንዴ ዱቄት ጥራቱን የጠበቀ አይደለም።

ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከተደረገባቸው የምግብ ሸቀጦች መካከል የምግብ ዘይትና ቅቤ፣ የእህል ዱቄት፣ ሥጋ የመሳሰሉና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመው፣ ይህንን ማረጋጋት የሚችል መንግሥታዊ አካል መኖሩን እንጠራጠራለን ብለዋል። መንግሥት በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ ሲወስድ ሰምተው እንደማያውቁ የተናገሩም አሉ።

የኑሮ ውድነቱ የበዓሉን ድባብ እንዳደበዘዘው የሚናገሩት ወይዘሮ ስመኝ በልሁ“አሁን ስለበዓል ድምቀት የምናወራበት ጊዜ አይደለም። ያ ጊዜ ድሮ ቀረ። ከ10 ዓመት በፊት እኔና ባለቤቴ በሦስት መቶ ብር ኹለት ዶሮና ቂቤ ገዝተን ስንገባ እናማርር ነበር። አሁን ግን በዓሉ ቀርቶ ወር የሚያደርስ አስቤዛ ለማግኘት ጭንቅ ውስጥ ገብተናል” ሲሉ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በምሬት ይገልጹታል።

በቤት ኪራይ መወደድ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ጣሪያ መንካትና በትራንስፖርት ችግር ብቻዬን ማውራት ከጀመርኩ ሰነባብቻለሁ የሚለው የ43 ዓመቱ ጎልማሳ ፍሬው ተሾመ ፤የኑሮ ውድነቱ በወር ከማገኘው ገቢ የማይመጣጠን ሆኖብኛል፤ የምግብ እህሎችን ዋጋና የቤት ኪራይ ጭማሪ ተቋቁሞ መኖር ከብዶኛል ይላል። እንኳንስ አንድ ኩንታል ጤፍ ሦስት ሺሕ ብር ሸምቼ ቀድሞውንም መንገዳገድ ከጀመርኩ ሰነባብቻለሁ ይላል።

በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በቂ አቅርቦት ባለመኖሩ እንደሆነ የሚገልጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አጥላው አማረ (ዶ/ር)፣ በአቅርቦት ላይ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሠራቱ፣ የፍላጎት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ የሕዝብ ቁጥር እያደገ በመሔዱና የምግብ ሥርዓቱ መልክ የሌለው በመሆኑ የዋጋ ንረቱ እንዲታይ ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ።

ሌላው ምክንያት በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ከውጭ መግባታቸው እንደሆነ የሚያስረዱት አጥላው፣ በርካታ ሸቀጦች በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ ባለመደረጋቸው አገሪቷን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፤ የአገሪቱን 70 በመቶ ያህል ሕዝብ የወር ገቢው ከ2 ሺሕ ብር በታች በሆነበት ሁኔታና በግጭትና መፈናቀል ምክንያት ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ በተጋለጡበት ጊዜ በምግብ ዋጋ ላይ የሚታይ ማናቸውም ጭማሪ አገርና ሕዝብን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል የሚሉት አጥላው፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ንረት አምራች የሚባለው የገጠሩ ነዋሪ የከፋ ጉዳት አይደርስበትም ተብሎ ቢገመትም፣ የገቢ መጠኑ ባለበት ዳዴ እያለ ላስቸገረው ከተሜ ግን ፈታኝ መሆኑ አያጠያይቅም ይላሉ።

ለዚህም ነው ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጫናዎች ቅድሚያ ከተሜውን ገፈት ቀማሽ የሚያደርጉት የሚሉት አጥላው፥ በዚህ ከቀጠለና መንግሥት አፋጣኝ ማስተካከያ እርምጃዎችን ካልወሰደ ችግሩ የኅብረተሰቡን ኑሮ ከማቃወስ ባሻገር የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ክፉኛ ሊያንገራግጨው ይችላል ሲሉም አክለዋል። ይህን ለማለት የሚያስደፍረው ደግሞ በተከታታይ ዓመታት እንደታዘብነው የሸቀጦች ዋጋ አንዴ ጭማሪ ካሳየ ያንኑ መነሻ (baseline) አድርጎ በጭማሪው ሲቀጥል እንጅ በመኸር ወቅትም ቢሆን የዋጋ ቅናሽ አይስተዋልም። ትክክለኛ የምጣኔ ሀብት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ መንቀሳቀስ ካልተቻለ አሁን ካለው የባሰ ነገር ሊመጣ እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አጥላው “አገሪቷ ያለፈችባቸውን ሒደቶችና አፈጻጸሞች በመመርመርና ጉድለቶቹን በመንቀስ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ እንዲሁም ፖሊሲዎችን መፈተሽ ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ነን። በተለይ በመዋቅራዊ ለውጥ ሒደት ውስጥ ከነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ባሻገር የሰው ኀይል፣ የቁሳዊ ካፒታል እና የቴክኖሎጂ አጠቃላይ አገራዊ አቅሞቻችንን መፈተሽ አለበት” ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here