የልማት ባንክን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ጥናት ተጠናቀቀ

0
410

የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ልማት ባንክ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያጋጠመውን ከፍተኛ ቀውስ ለመፍታት በዓለም ባንክ እና በጀርመን መንግሥት ድጋፍ ለአምስት ወራት በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሲጠና የነበረው ጥናት ተገባዶ ለውሳኔ ተላከ።

ይህ ጥናት ባንኩ ያጋጠመውን ችግር ከመለየት ባሻገር የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚለይ ሲሆን በጥናቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሞያዎች ያቀረቡት የፖሊስ ለውጥ አማራጮችም ባንኩ እንዴት መቀጠል ይችላል ለሚለው መነሻ ሐሳብ የቀረበበት ነው። የብሔራዊ ባንክ እና የልማት ባንክ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የሚገኙበት ኮሚቴም የመፍትሔ አማራጮች ላይ በመወያየት የአቅም፣ የሰው ኀይል እንዲሁም የመዋቅር ለውጥ አማራጮች መቅረባቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በስምንት ቡድኖች እና በሥራቸው ባሉ ንዑስ ቡድኖች በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ በአማራ እና ትግራይ ክልል በተደረገው ጥናት የኮንትራት እርሻዎቹ ትንንሽ ገበሬዎች ከሚያመርቱት ያነሰ ውጤታማነት እንደነበራቸው ለይቷል። አዲስ ማለዳ የተመለከተችው የጥናት ሰነድ እንደሚያሳየው ብድሮቹን የመመለስ አቅም ማጣት ለተበላሸው ብድር ምክንያት ከመሆን ይልቅ የማምረት ፍላጎት ያለመኖር እና የብድሩ አሰጣጥ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በፖለቲካ ላይ የተመሰረተ ነበር ሲል ያትታል።

የጥናት ቡድኑ አባል ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት በጥናቱ ወቅት በነበሩ ውይይቶች በጫማ መጥረግ ሥራ ላይ የተሰማራ ግለሰብ ከባንኩ በሚሊዮኖች ብድር ያገኘበት ሁኔታ እንዲሁም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በአራት የተለያዩ ግለሰቦች ሥም ብድር እንደቀረበ መረዳታቸውን ተናግረዋል። አክለውም አንዳንድ ብድሮች ባንኩ መስጠት ያልነበረበት በመሆናቸው የተሰጡበት አግባብ እንዲብራራ በሚደረግበት ወቅትም ‹‹በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥጣናት ቀጭን ትዕዛዝ የተሰጠ ነው›› የሚል መልስ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

እነዚህን እርሻዎች በሚመሰረቱበት ወቅትም ጥቅጥቅ ደኖች ተመንጥረው የተሰጡ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ የዝናብ እጥረት እና በደኑ ላይ የተመሰረተው የገቢ ምንጩ በመጥፋቱ ችግር ላይ መውደቁን መመልከታቸውን እና በሕዝብ ውይይቶች ወቅትም ተደጋግሞ መነሳቱን ይናገራሉ። በተለይ በማር ምርት እና በትንንሽ እርሻዎቻቸው ላይ የሚያገኙት ገቢ በመቅረቱ እንዲሁም እርሻዎቹም እንደተገመተው የስራ እድል ባለመፍጠራቸው ሕዝቡ ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ መግባቱንም ለማወቅ ተችሏል። ባለሃብቶቹን የመግደል እና ምንም አይነት ስራ እንዳይሰሩም የማድረግ አዝማሚያ መኖሩን እንደዳሰሱ ተናግረዋል።

ነገር ግን የኮንትራት ሰብል ከሆኑት( እንደ ሰሊጥና ጥጥ) ይልቅ የኮንትራት ያልሁኑት (እንደ በቆሎ ማሽላ እና ያሉ ሰብሎች) ላይ የተሰጡ ብድሮች የተሸለ አፈጻጸም መታየቱን ጠቅሰዋል።

ለብድሩ መያዣነት የህዝብ እና የመንግስት ንብረት እንደሆነ በሕገ መንግስቱ የተደነገገው መሬት መሆኑ ባንኩ ካበደራቸው ብድሮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እንዲበላሹ እና ማስመለስም እንዳይቻል ያደረገ አሰራር እንደ ነበርም ተገልጿል።በሺዎች የሚቆጠር ሔክታር መሬት የሸፈኑት እርሻዎቹ ባለሀብቱ ለረጅም ዓመታት ሳይሠሩበት ኅብረተሰቡም ሳያለማው ጦም እያደሩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። ለኢንዱስትሪዎችም ሆነ ለእርሻዎቹ የተወሰዱት ቦታዎች እንዲሁም ፋብሪካዎች ባለሀብቶቹ ትተዋቸው አንድም ከስራ ቦታው አንዳዶችም ከአገር መውጣታቸውን ጥናቱ ያትታል።

በጥናቱ ከተገኙ ክፍተቶችም የእርሻ ማሽነሪ አስመጪዎችም ምንአልባትም በአግባቡ እየሠሩ ላይሆን ይቻላል የሚል ግምት እንዳለ እና ልማት ባንክ ከውጪ በቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ክፍያ ቢፈፀምላቸውም ግዢውን ማካሔዳቸው ላይ ግን የሚያጠራጥሩ ምልክቶች መታየታቸውንም የጥናት ውጤቱ በማሳዎች ላይ የተመለከቷቸው መሳሪያዎች የማይሠሩ እና የተበላሹ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የጥናት ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር) እንዲሁም የባንኩ ፕሬዝዳንት ሃይለየሱስ በቀለ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ከሆነ በባንኩ ላይ ስለሚወሰን ውጤቱን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናገግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here