የቻይናው ኩባንያ የቤተ መንግሥቱን የመኪና ማቆሚያ 1.5 ቢሊዮን ብር ሊገነባ ነው

0
660

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሻሽነት ወደ ሙዝየም በመቀየር ላይ ላለው ብሔራዊ ቤተመንግሥት የመኪና ማቆሚያ ለመገንባት ከተወዳዳሩት ኹለት የቻይና ግንባታ ኩባንያዎች መካከል ቻይና ጂያንግ ሱ ኮንስትራክሽን በ1.5 ቢሊዮን ብር ውል ፈፀመ።

የአዲስ ኣበባ ኮንሰትራክሽን ቢሮ በቤተ መንግሥቱ ግቢ ውሰጥ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ሙዚየም ለመጎብኘት ለሚመጡ ጎብኚዎች ከቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት የሚገነባው ይህ የመኪና ማቆሚያ ግንባታ ወጪ የሚሸፍን ይሆናል።

በጨረታው ላይ የአገር ውስጥ እና ዓለም ዐቀፍ የግንባታ ተቋራጮች እንዲሳተፉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ላይ የሚገኘው ቻይና ጂያንግ ሱ ኮንስትራክሽን የወጣውን ዓለም ጨረታ አሸንፋል። በጨረታው እንዲሳተፉ ጥሪ ከቀረበላቸው ሌሎች ሰባት ዓለማቀፍ የግንባታ ድርጅቶች መካከል ሦስቱ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ሰነዶችን ያስገቡ ሲሆን አንድ ድርጅትም ዘግይቶ ባስገባው የጨረታ ሰነድ ምክንያት እንዲወጣ ተደረጓል።
ቻይና ጂያንግ ሱ ባለው ልምድ እና ባቀረበው ግንባታ ዋጋ ማሸነፉን የአዲስ ኣበባ ኮንሰትራክሽን ቢሮ ኀላፊ ደምመላሽ ከበደ ተናግረዋል። ግንባታው ከአንድ ሺሕ 600 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የዲዛይን ጥናት ሥራውን ጨምሮ በአንድ ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በውስጡ ከአንድ ሺሕ በላይ መኪኖችን ማቆም ይችላል። በተጨማሪም ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ የመፃሕፍት፣ የጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾች የሚሸጡባቸው ሱቆች እና ባሕለዊ ምግቦችን ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡ ምግብ ቤቶች ቴአትር ቤቶች የትራፊክ እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ማዕከላትን የሚይዝ ነው። እነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት የሚመጡ ተጠቃሚዎች የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአካባቢው የመኪና ማቆሚያ እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚረዳ ታምኖበታል። ሕንፃው ከመሬት በታች አራት ወለሎች እና ወደላይ ሦስት ሕንፃዎችን እንደሚይዝም ለማወቅ ተችሏል።

የግንባታ ሥራው በአዲስ ኣበባ ኮንሰትራክሽን ቢሮ ተቆጣጣሪነት የሚሠራ ሲሆን የአዲስ ኣበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በማማከር ሥራ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ግንባታውን የሚያከናውነው ጂያንግ ሱ ኮንስትራክሽን በተመሳሳይ በ4.6 ቢሊዮን ብር የአድዋን ድል የሚዘክር ሙዝየም፣ የስብሰባ አዳራሾችን እና የመዝናኛ እንዲሁም ስፖርታዊ እንቀስቃሴዎች የሚዘወተሩባቸው ስፍራዎችን በመሀል ፒያሳ ከሚኒሊክ አደባበይ ፊት ለፊት በሚገኘው ስፍራ ላይ ለመገንባት ጨረታ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአራት ወራት በፊት ግንባታውን ያፀደቀው ሲሆን በአዲስ ኣበባ ኮንሰትራክሽን ቢሮ ባቀረበው የግንባታ ዲዛይን ሐሳብ መሰረት ቻይና ጂያንግ ሱ ኮንስትራክሽን በ45 ቀናት ውስጥ ዝርዝር የግንባታ ዲዛይን እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ቻይና ጂያንግ ሱ ኮንስትራክሽን በቻይና እንዲሁም በበርካታ የዓለም አገራት በግንባታ ሥራ እና በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን በከተማዋ የሚገኙ የንብ ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here